No edit permissions for Amharic

ማንትራ አንድ

ኢሻቫስያም ኢዳም ሳርቫም
ያት ኪንቻ ጃጋትያም ጃጋት
ቴና ትያክቴና ብሁንጂትሀ
ማ ግርድሀህ ካስያ ስቪድ ድሀናም

ኢሻ — በዓብዩ ጌታ፣ አቫስያም — በቁጥጥር ሥር ያለ፣ ኢዳም — ይህ፣ ሳርቫም — ሁሉም፣ ያት ኪንቻ — ማናቸውም፣ ጃጋትያም — በጠፈር ውስጥ፣ ጃጋት — የሚንቀሳቀሱም ሆነ የማይንቀሳቀሱ ሁሉ፣ ቴና — በእርሱ፣ ትያክቴና — ተለይቶ የተመደበ ድርሻ፣ ብሁንጂትሀ — መቀበል ይኖርብሃል፣ — አታድርግ፣ ግርድሀህ — ለማትረፍ መጣር፣ ካስያ ስቪድ — የሌሎችን፣ ድሀናም — ሀብት

በዚህ ቁሳዊ ጠፈር ውስጥ የሚገኙ የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ፍጥረታት ሁሉ የዓብዩ ጌታ ሀብት የሆኑ እና በእርሱ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው ቢሆን በዚህ ዓለም ውስጥ የሚገኙትን ፍጥረታት ሁሉ የዓብዩ ጌታ ሀብት እንደመሆናቸው በመገንዘብ፣ የሚያስፈልገውን ብቻ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ እነዚህም ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሁሉ፣ በተፈጥሮ ለእያንዳንዱ ፍጥረታት የተመደቡ ናቸው። ከዚህ ድርሻ በላይ የተረፈውን ሀብት የማን እንደሆነ በመገንዘብ፣ ከሚገባን በላይ ለመውሰድ ጥረት ማድረግ አይገባንም።፡

የቬዲክ ዕውቀት ለዘለዓለም የሚጸና እና ከቶም ወዳቂ ሊሆን የማይችል ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ዕውቀት የመነጨው ከዓብዩ ጌታ ሲሆን፤ ለዘመናት ሲተላለፍ የቆየውም በዲቁና ሥርዓት አማካኝነት ሲወርድ ሲዋረድ ነው፡፡ ይህንንም ዕውቀት ዓብዩ ጌታ ከመጀመሪያው የቬዲክ ቃል መነሻ ቃል ጀምሮ በጥልቅ የገለጸው ስለሆነ፣ መላ የቬዲክ ዕውቀት ሁሉን የተፈጥሮ ዕውቀት ያካተተና፣ ንጹሕ መንፈሳዊ ዕውቀት ሆኖ ቀርቦልናል፡፡ በዓብዩ ጌታ የተነገረው ዕውቀት ሁሉ “አፖሩሼያ” ይባላል፡፡ ይህም ቃል የሚገልጽልን ይህ ዕውቀት ተራ በሆነ ፍጥረት ወይም የሰው ልጅ የተገለጸ አለመሆኑን ነው፡፡ በዚህ ምድር ላይ የሚገኝ ተራ የሆነ ሰው፣ አራት ዓይነት እንከን ወይም ጉድለት ይኖሩታል፡፡ (1) ስሕተት ለማድረግ የተጋለጠ ነው፡፡ (2) በሐሰታዊ ራእይ ውስጥ በቀላሉ የሚዋልል ነው፡፡ (3) ሌሎችን ለማታለል የሚያደላ ነው፡፡ (4) ስሜቶቹ ሁሉ ፍጹም ትክክል የሆነ ዕውቀትን ሁልጊዜ ሊሰጡት አይችሉም፡፡ በእነዚህ አራት ዓይነት እንከኖች የሚጠቃ ማንም ተራ ሰው፣ ፍጹም የሆነ ዘለዓለማዊ ዕውቀትን ሊፈጥር አይችልም፡፡ የቬዳ ዕውቀቶች ይህንን በመሰለ ጉድለት በተሞላበት የሰው ልጅ፣ የተፈጠሩ ዕውቀቶች አይደሉም፡፡ የቬዳ ዕውቀት ለመጀመሪያ ጊዜ የተላለፈው ከዓብዩ ጌታ ወደ ጌታ ብራህማ ልብ ውስጥ ነው። ጌታ ብራህማ በመጀመሪያ ደረጃ በዓብዩ ጌታ የተፈጠረ የቁሳዊው ዓለም ፍጡር ነው፡፡ ጌታ ብራህማ ይህንን የቬዲክ ዕውቀት ከዓብዩ ጌታ ከቀሰመ በኋላ፣ ለልጆቹ እና ለዲያቆኖቹ አስተማረ፡፡ እነዚህም ልጆቹ እና ዲያቆናት ይህንኑ ዕውቀት ለመጪዎቹ ትውልዶች ሲያስተላልፉ እንደ ነበር በታሪክ ተገልጿል፡፡

ዓብዩ ጌታ “ፑርናም” ወይም ሁለመናው ፍጹም የተሟላ እና በሁለመናውም ጉድለት የሌለው ኅያል ጌታ ስለሆነ፣ በቁሳዊው ዓለም ሕግጋት ሊወሰን የሚችል አይደለም። ምክንያቱም ይህንንም የቁሳዊ ዓለም ሕግጋት የፈጠረው ወይም የሚቆጣጠረው እርሱ ራሱ በመሆኑ ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ በእነዚህ ቁሳዊ ዓለማት ውስጥ የሚገኙት ሕያው እና ቁሳዊ ፍጥረታት ሁሉ፤ በእነዚህ የቁሳዊ ዓለም ሕግጋት ቁጥጥር ሥር የሆኑ እና ከእነዚህም ሕግጋት በላይ በዓብዩ ጌታ ቁጥጥር ሥር የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ይህ የኢሾፓኒሻድ መጽሐፍ “ያጁር ቬዳ” ተብሎ ከሚታወቀው ትምህርት በከፊል ተነጥሎ እና ተጽፎ የቀረበ ነው፡፡ የያዘውም ዕውቀት የመላው የቁሳዊው ዓለም ጠፈር ጌታ እና ባለቤት ማን እንደሆነ የሚያስተምር ነው፡፡

ዓብዩ ጌታ የመላው ቁሳዊ ጠፈር ባለቤት እንደሆነም፣ በብሀገቨድ ጊታ በሰባተኛው ምዕራፍ (7.4-5) ውስጥ ተገልጾልናል፡፡ በዚህም ምዕራፍ “ፓራ” እና “አፓራ ፕራክርቲ” ምን እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ የተፈጥሮ ንጥረ ነገሮች ማለትም አፈር፣ ውሀ፣ እሳት፣ አየር፣ ኢተር (ቦታ ወይም ክፍተት)፣ ሐሳብ፣ አእምሮ እና ኢጎ (ቀልብ) ሁሉ የዓብዩ ጌታ ዝቅተኛ ኃይላት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ቁሳዊ ኃይላት ወይም “አፓራ ፕራክርቲ” ተብለው የሚታወቁ ናቸው። ሕያው ፍጥረታት ሁሉ ደግሞ የዓብዩ ጌታ ከፍተኛው ኃይላት ወይም “ፓራ ፕራክርቲ” ተብለው ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ዓይነት ኃይላት የሚመነጩት ከዓብዩ ጌታ ነው፡፡ በመላ ቁሳዊ ዓለማት ውስጥ ለሚገኙት ፍጥረታት ሁሉ የበላይ ተቆጣጣሪው እርሱው ዓብዩ ጌታ ነው፡፡ በእነዚህ ቁሳዊ ዓለማት ውስጥ ከእነዚህ ከሁለቱ ዓይነት ኃይላት ውጪ ምንም ነገር የለም፡፡ እነዚህ ኃይላት ወይ “የፓራ ፕራክርቲ” ኅይል ናቸው ወይም ደግሞ “የአፓራ ፕራክርቲ” ኅይል ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ነገር የዓብዩ ጌታ ውርስ ወይም ሀብት ነው፡፡

ዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ፣ ሁለመናው ፍጹም የተሟላ በመሆኑም፣ ፍጹም የተሟላ አእምሮ ያለው ነው፡፡ ስለዚህም ሁሉንም አስተዳደር ፍጹም እና ትክክል በሆነ መንገድ የማስተዳደር ኅይል አለው፡፡ ዓብዩ ጌታ ብዙውን ጊዜ እንደ እሳት ይመሰላል፡፡ በምድር ላይ ግዑዝ እና ግዑዝ ያልሆኑ ነገሮች ሁሉ ልክ እንደ እሳት ብርሃን እና ሙቀት ይመሰላሉ፡፡ ምክንያቱም እሳት ኃይሉን በሙቀት እና በብርሃን አስፋፍቶ ሰፋ ባለ ቦታ ላይ ይገኛል። ልክ እንደዚህም ሁሉ የዓብዩ ጌታ ኅይል ግዑዝ እና ግዑዝ ባለሆኑ ነገሮች ተመስሎ በመላ ዓለም ውስጥ ተስፋፍቶ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ለሁሉም ነገር የበላይ ተቆጣጣሪ፣ ተንከባካቢ፣ መሪ ሆኖ ይገኛል፡፡ የኃይላት ሁሉ ባለቤት፣ የሁሉም ነገር ዐዋቂ፣ የሁሉም ዕድል አቅራቢ እና ጠቃሚ እርሱው ራሱ ብቻ ነው፡፡ ለመተመን የማይቻል ሀብት፣ ኅይል፣ ዝና፣ ቁንጅና፣ ዕውቀት ያለው እና እንዳሻው በቀላሉ ማናቸውንም ነገር እርግፍ አድርጎ ለመተው የሚችልም ዓብይ ጌታ ነው፡፡ ስለዚህ ከዓብዩ ጌታ በቀር፣ ማንም ሰው የዚህ ዓለም ሀብት ባለቤት ለመሆን እንደማይችል ዕውቀቱ ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡

መውሰድ የሚገባንም ነገር ሁሉ፣ በዓብዩ ጌታ እንደ ድርሻችን ሆኖ የቀረበልንን ነገር ብቻ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ ላም ወተትን ትሰጣለች፡፡ ቢሆንም ግን ወተቷን አትጠጣውም፡፡ የምትመገበው እርጥብ እና የደረቀ ሣር ብቻ ነው፡፡ ወተትም በተፈጥሮ ለጥጃዋ እና ለሰው ልጅ ኅብረተሰብ እንደ ምግብ የምታቀርብለት ሀብት ነው፡፡ ከዓብዩ ጌታ በፈቃዱ እና በቸርነቱ አማካኝነት የቀረበልንም የላሚቷ በረከት ይህንን የመሰለ ነው፡፡ ስለዚህ በቸርነቱ ላቀረበልን ነገሮች ሁሉ ምስጋናን በማቅረብ፣ ደስተኞች በመሆን በአክብሮት መቀበል ይገባናል፡፡ እንደሀብት የምናያቸው እነዚህም የተፈጥሮ ስጦታዎችን ሁሉ፣ የማን ሀብት እንደሆኑ ሁልጊዜ በማስታወስ እና ዓብዩ ጌታን በማመስገን መቀበል ይገባናል፡፡ እንደ ምሳሌ በማድረግ አንድ የመኖሪያ ቤታችንን እንመልከት፡፡ ቤቱ የተሠራው ከአፈር፣ ከእንጨት፣ ከድንጋይ፣ ከብረት፣ ከሲሚንቶ እና ከሌላም የተለያዩ ነገሮች ሊሆን ይችላል፡፡ ከሽሪ ኢሾፓኒሻድ ትምህርትም አንጻር ብናየው እና እንደምናውቀውም፤ እነዚህን የሕንፃ መሥሪያ ነገሮች ራሳችን ልንፈጥራቸው አንችልም፡፡ ማድረግ የምንችለው ግን ቁሳቁሶቹን በማሰባሰብ እና ጉልበታችንን በማቀነባበር የተለያዩ ቅርጾች እንዲይዙ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳን ማናቸውም የጉልበት ሠራተኛ ለሕንጻ መሥሪያ የሚሆኑ መሣሪያዎችን የሚያመርት ቢሆንም፣ እኔ ፈጠርኳቸው ለማለት ግን አይችልም፡፡ በአሁኑ ዘመን ይህንን የመሰለ ዕውቀት በጎደለባቸው ፖለቲከኞች፣ ሠራተኞች እና በታላላቅ ነጋዴዎች መሀከል ብዙ ቅራኔ እና ብጥብጥ ይታያል፡፡ ይህንንም ቅራኔ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመስርቶ እናየዋለን፡፡ በዚህም ምክንያት ዓለም ውጥረት በተሞላበት ሁኔታ ላይ ሰፍራ ትገኛለች፡፡ የሰው ልጆች በጥላቻ ምክንያት እንደ እንስሳት ሲተናኮሉ ይታያሉ፡፡

ለዚሁም እንደ መፍትሔ ይህ የሽሪ ኢሾፓኒሻድ መልእክት፣ ልቦና ላላቸው ሰዎች እና እውቅና ባላቸው አቻርያዎች (መምህራን) ለሚመሩት ሁሉ፣ የዓብዩ ጌታን መልእክት ይዞ ቀርቧል፡፡ የሰው ልጅም የቁሳዊ ሀብት ባለቤት ለመሆን፣ እንደ እንስሳት በጥላቻ መበጣበጥን አቁሞ፣ ይህንን የቬዲክ ብልኃትን እና ዕውቀት ከዚሁ ከሽሪ ኢሾፓኒሻድ መቅሰም ይገባዋል፡፡ አንድ ሰው፣ በዓብዩ ጌታ ቸርነት አማካኝነት በተፈጥሮ ተመድቦ በቀረበለት ነገር ሁሉ የረካ መሆን ይገባዋል፡፡ ኮሚኒስቶች፣ ካፒታሊስቶች ወይም ታላላቅ ነጋዴዎች፣ የተፈጥሮን ሀብትን ከሚገባው በላይ እንደ ግል ባላቤትነት የሚይዙ ከሆነ፣ በምድር ላይ ሰላም ሊገኝ አይችልም፡፡ ምክንያቱም የመላው የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ ብቻ ነው፡፡ ካፒታሊስቶች በፖለቲካዊ ቅንብር ብቻ፣ ኮሚኒስቶችን ለማሸነፍ አይችሉም፡፡ እንዲሁም ኮሚኒስቶች ለተሰረቀ ሀብት በመጣላት ብቻ ካፒታሊስቶችን ለማሸነፍ አይችሉም፡፡ ዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ፣ የሁሉም የተፈጥሮ ሀብት ቀዳማዊ ባለቤት መሆኑን እስካልተረዱ ድረስ፣ የኔ ነው ብለው የሚጣሉበት ሀብት ሁሉ፣ የተሰረቀ ሀብት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በተፈጥሮ ሕግጋት መሠረት፣ ለተሰረቀው ሀብት የሚገባቸውን ምላሽ እንደተግባራቸው ለማግኘት ይበቃሉ፡፡ የተፈጠረውም የኒውክሊየር ቦምብ፣ በኮሚኒስቶችም ሆነ በካፒታሊስቶች እጅ ይገኛል፡፡ እነዚህም ሁለቱ የኅብረተሰብ አካሎች፣ የዓብዩ ጌታን ባለቤትነት በትክክል የማይረዱ ከሆነ፣ ይህንን የመሰለው አጥፊ ቦምብ ሁለቱንም አካሎች ሊደመስስ የሚመጣበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ እራሳቸውንም ለማዳንም ሆነ ለምድር ሕዝብ ሰላም ለመስጠት፣ ሁለቱም አካሎች የሽሪ ኡፓኒሻድን ትእዛዝ እና መልእክት በትክክል መረዳት እና መከተል ይገባቸዋል፡፡

የሰው ልጆች ሕይወት በጣም አስፈላጊ እንደመሆኑ፣ ዓላማው ምን እንደሆነ በትክክል ለመረዳት አእምሯችን የላቀ መሆን ይገባዋል፡፡ ይህም የቬዲክ ዕውቀት የቀረበው ለሰው ልጆች እንጂ ለውሾች እና ለድመቶች አይደለም፡፡ እንስሳት ለምግባቸው ሲሉ ሌላውን እንስሳ ሲገድሉ በኅጢአት የሚተሳሰሩ አይደሉም። የሰው ልጅ ግን ሊቆጣጠረው ባልቻለው በምላስ የማጣጣም የስሜት እርካታ ምክንያት ሌሎች እንስሳትን ለምግቡ ሲል ለመግደል ቢበቃ የተፈጥሮን ሕግጋት እንደጣሰ ይቆጠራል፡፡ ለዚህም ጥፋት ኃላፊነቱን በመውሰድ በተፈጥሮ የሚጠበቅበትን ምላሽ ለማግኘት ይበቃል።

የሰው ልጆች የኑሮ አስተዳደር ልክ በእንስሳት እንደሚታየው የተፈጥሮን ፈለግ መከተል ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ ነብር ሩዛችንን እና ስንዴያችንን ሲበላ አይታይም፡፡ የላም ወተታችንንም ሲጠጣ አይታይም፡፡ ምክንያቱም ለነብር በተፈጥሮ የተሰጠው ምግብ የእንስሳትን ሥጋ መብላት ነው፡፡ በእንስሳት እና በወፎች መሀከል አትክልታዊ የሆኑ እንስሳት ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ሌሎች እንስሳት ደግሞ ሥጋ የሚበሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ቢሆንም ግን እንስሳት በተፈጥሮ ከተመደበላቸው ምግብ ውጪ ሲመገቡ አይታዩም፡፡ ይህም የተፈጥሮ ሕግጋት የተደነገገው በዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ ነው፡፡ እንስሳት፣ አእዋፋት፣ በደረት የሚሳቡ ፍጡራን ወይም ሌሎች በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ፍጡራን ሁሉ የተፈጥሮን ሕግጋት በመከተል ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ እንስሳት ሁሉ ኅጢአት የሚባል ነገር የለም፡፡ በቬዲክ ሥነጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት ትእዛዛት ሁሉ ለእነሱ ተብሎ የተደነገገ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ሕይወት ግን ኃላፊነት የተሞላበት ነው፡፡

ቢሆንም ግን፣ አትክልታዊ በመሆን ብቻ የተፈጥሮን ሕግጋት ከመስበር እንርቃለን ብለን ለማሰብም አንችልም፡፡ አትክልቶችም እንደ እንስሳት ሕይወት አላቸው፡፡ ምንም እንኳን በተፈጥሮ ቅንብር፣ የአንድ ፍጡር ገላ ለሌላ ፍጡር ምግብ እንዲሆን የተዘጋጀ ቢሆንም፣ የሰው ልጅ የዓብዩ ጌታን ባለቤትነት በትክክል መረዳት ይገባዋል፡፡ ይህንንም በመረዳት በቬዳዎች እንደተደነገገው አትክክልቶችን በፍቅር በመሥራት ለምግብ አዘጋጅቶ ለባለቤቱ ለዓብዩ ጌታ ደስታ ማቅረብ ይኖርብናል። በዚህም መንፈሳዊ ሥርአት የተባረከ እና ከኅጢአት ነጻ የሆነ ምግብ ለማግኘት እንችላለን። ስለዚህ አንድ ሰው አትክልታዊ በመሆን ብቻ ትዕቢት ሊኖረው አይገባም። እንስሳት ዓብዩ ጌታን ለመረዳት የበለጸገ አእምሮ ወይም ንቃት የላቸውም፡፡ የሰው ልጅ ግን የቬዲክ ዕውቀትን በትክክል ለመረዳት በቂ አእምሮ ስለተሰጠው፣ ይህንን የቬዲክ ዕውቀት በመቅሰም፣ እንዴት የተፈጥሮ ሕግጋት እንደተደነገጉ እና በዚህ ዕውቀት እንዴት በጎ ነገሮችን በሕይወቱ ላይ ማድረግ እንደሚገባው ማወቅ አለበት፡፡ የሰው ልጅ የቬዲክ ትእዛዛትን የማይከተል ከሆነ ግን፣ ሕይወቱ ለኅጢአት እና ለስቃይ የተጋለጠ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ የዓብዩ ጌታን ሥልጣን በትክክል መረዳት ያስፈልገዋል። ከዚህም አልፎ ተርፎ የዓብዩ ጌታ ትሑት አገልጋይ መሆን ይገባዋል፡፡ የሚያገኘውን ነገር በሙሉ፣ ለዓብዩ ጌታ ደስታ እና አገልግሎት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ በዓብዩ ጌታ በተፈጥሮ ቀርቦ ከተረፈውም የምግብ ምርቶች ለራስ ብቻ ከማከማቸት መቆጠብ፣ ሁሌ የሚያስፈልገውን ያህል ብቻ በመውሰድ መኖር ይገባዋል፡፡ ይህንንም አስተሳሰብ በመያዝ የሚጠበቅበትን ትሑት አገልግሎት በትክክል ለማቅረብ ይችላል። በብሀገቨድ ጊታም እንደተገለጸው (9፡26) ዓብዩ ጌታ በትሑት እና በንጹሕ አገልጋዮቹ በፍቅር ተዘጋጅቶ የቀረበለትን አትክልታዊ ምግብ በደስታ ተቀብሎ በመመገብ ይባርከዋል፡፡ እንደዚህም ሁሉ የሰው ልጅ አትክልታዊ ብቻ ሳይሆን፣ የዓብዩ ጌታ ትሑት አገልጋይ በመሆን፣ በፍቅር መንፈሳዊ አገልግሎትን ማቅረብ ይችላል፡፡ የሚያዘጋጀውንም ምግብ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ለዓብዩ ጌታ ደስታ አዘጋጅቶ ማቅረብ ይገባዋል፡፡ ከዚያም የተባረከውን መንፈሳዊ ምግብ ወይም “ፕራሳድ” የዓብዩ ጌታ የበረከት ምግብ እንደመሆኑ፣ በአክብሮት ተቀብሎ መመገብ ይገባዋል፡፡ የሰውን ልጅ ሕይወት በትክክል ሊመሩ የሚችሉትም፣ በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ የተመሰጡ ሰዎች ወይም ትሁት መንፈሳዊ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ምግባቸውን በፍቅር ለዓብዩ ጌታ ሠርተው የማያቀርቡ ግን የሚወስዱት ምግብ ኃጢአታዊ በመሆን የሚታይ ሲሆን፣ እራሳቸውንም ለተለያዩ ጭንቀት የሚያጋልጡ ናቸው፡፡ የተለያዩ ዓለማዊ ስቃይ የሚከሰቱብንም ከፈጸምናቸው ኅጢአት አንጻር ነው፡፡ (ብጊ፡ 3፡13)

የኅጢአት ሁሉ መነሻ የተፈጥሮን ሕግጋት እያወቁ አልታዘዝም ማለት ነው፡፡ ይህም ኅጢአት የዓብዩን ጌታ ቀዳማዊ ባለቤትነትን ባለመቀበል የሚደረግ ድርጊት ሁሉ ነው፡፡ የተፈጥሮን ሕግጋት አለመከተል እና፣ የዓብዩ ጌታን ትእዛዝ አለመቀበል፣ የሰውን ልጅ ሰላም ሊነሳ እና ጥፋትን የሚያመጣበት ነው፡፡ ከዚህም በተቃረነ መንገድ፣ አንድ ሰው አንደበቱ ያልተረበሸ እና፣ የተፈጥሮን ሕግጋት በትክክል የተረዳ ከሆነ፣ በሚያብረቀርቁ ዓለማዊ ነገሮች በቀላሉ የማይታለል እና የማይጓጓ ከሆነ፣ በዓብዩ ጌታ ታዋቂ እና ተወዳጅ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ወደ መንግሥተ-ሰማያት ለመግባት ዕድል የሚኖረው ሲሆን፣ ተመርጦም ወደዚሁ የዘለዓለም መንፈሳዊ መኖሪያው ለመመለስ ብቁ ይሆናል፡፡

« Previous Next »