No edit permissions for Amharic

ማንትራ አስራ ሁለት

አንድሀም ታማህ ፕራቪሻንቲ
ዬ ሳምብሁቲም ኡፓሳቴ
ታቶ ብሁያ ኢቫ ቴ ታሞ
ያ ኡ ሳምብሁትያም ራታሀ

አንድሀም — ድንቁርና፣ ታማሀ — በጨለማ ውስጥ፣ ፕርቪሻንቲ — በመግባት፣ ዬ — እነዚያ ሁሉ፣ አሳምብሁቲም — መላእክት፣ ኡፓሳቴ — የሚያመልኩ፣ ታታሀ — ከዚያም አልፎ፣ ብሁያህ — በተጨማሪ፣ ኢቫ — እንደዚያ፣ ቴ — እነዚያ፣ ታማሀ — በጨለማ ውስጥ፣ ዬ — ማን፣ ኡ — በተጨማሪ፣ ሳምብሁትያም — ፍጹም በሆነው፣ ራታሀ — የተሰማሩ

ከዓብዩ ጌታ በስተቀር መላእክትን ልክ እንደ ዓብዩ ጌታ በመቁጠር የሚያመልኩ ሁሉ ወደ ጨለማው እና ድንቁርና ወደተሞላበት ፈለግ ያመራሉ፡፡ በዓብዩ ጌታ ዓብይ ሰብአዊነት የማያምኑት እና ሰብአዊ ያልሆነውን የዓብዩ አምላክ ኅይልን የሚያመልኩትም ሁሉ፣ ወደእዚሁ ስፍራ ያመራሉ።

“አሳምብሁቲ” ተብሎ የሚታወቀው የሳንስክሪት ቋንቋ ቃል፤ ከሌሎች ተለይቶ ለመኖር የማይችል የሚለውን አባባል ይገልጻል። “ሳምብሁቲ” የሚለው ቃል ደግሞ፣ በማናቸውም ነገር መደገፍ የማያስፈልገውን የዓብዩ ጌታን መንፈስ የሚገልጽ ቃል ነው፡፡ ይህንን ጥቅስ በተመለከተ፣ በብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ (ሽብ 10-02) ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና እንዲህ በማለት ገልጾልናል፡፡

ናሜ ቪዱህ ሱራ ጋና
ፕራብሀቫም ና ማሃርሳያህ
አሀም አዲር ሂ ዴቫናም
ማሀርሲናም ቻ ሳርቫሳህ

“ደሚጎዶች” ወይም መላእክትን የሚያመልኩና የሚያገለግሉትም ሆኑ፣ ታላላቅ ባሕታውያን፣ የእኔን ችሎት እና ሀብት መነሻ ሊያውቁት አይችሉም፡፡ በሁሉም ረገድ እኔ የደሚጎዶች ወይም የመላእክት እና የባሕታውያን ሁሉ ምንጭ ነኝ፡፡” ሽሪ ክርሽና ለመላእክት፣ ለታላላቅ ባሕታውያን እና የምስጢራዊ ስልት ላላቸው ሁሉ፣ የኃይላቸው ምንጭ ነው፡፡ ምንም እንኳን እነዚህም ሁሉ በታላላቅ ምስጢራዊ ኅይል የታደሉ ቢሆኑም፣ ያላቸው ኅይል የተወሰነ ነው፡፡ ሽሪ ክርሽና በውስጣዊ ኃይሉ እንዴት እንደ ሰው በመመሰል በፈቃዱ ወደ ምድር እንደሚመጣ ለመረዳት ያዳግታቸዋል፡፡

ብዙኃኑ ፈላስፎች፣ ታላላቅ ባሕታውያን እና በምስጢራዊ ኅይል የታደሉ ሁሉ፣ ይህንኑ የፍጹም እውነት ክስተት ከተነጻጻሪ ዓለማዊ እውነት ጋር በማመዛዘን፣ በተወሰነው አእምሮዋቸው፣ የዓብዩ ጌታን አፈጣጠር ለመረዳት ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ በዚህ ውስን በሆነው ምርምራቸው ከፍጹም እውነት የተቃረነውን ዓለማዊ ክስተት ሊረዱ ይችላሉ እንጂ፣ ፍጹም እውነት የሆነውን መንፈሳዊ ክስተት በትክክል ሊረዱት አይችሉም፡፡ የተዛመደውን ዓለማዊ እውነታ በመረዳት፣ ፍጹም እውነት የሆነውን መንፈሳዊ ክስተት፣ በትክክል መረዳት አይቻልም፡፡ አንድ ሰው ፍጹም መንፈሳዊ እውነታን ከተቃረነው ዓለማዊ ክስተት ጋር በማነጻጸር ወደ ተሳሳተ ግምታዊ ድምዳሜ ሊያመራ ይችላል፡፡ ስለዚህ ከመንፈሳዊ ክስተት የተቃረነውን ቁሳዊ ክስተት በመመርኮዝ ብቻ፣ ፍጹም እውነትን ለመረዳት መሞከር፣ የተሟላ ዕውቀትን ሊሰጠን አይችልም፡፡ በዚህ በተቃራኒው ቁሳዊ ክስተት የተመረኮዘ ድምደማ ሁሉ የመነጨው፣ ከግል ምርምር እና ድምደማ ሲሆን፣ ይህንን ፈለግ የተከተሉ ሁሉ፣ ዓብዩ ጌታ ምስል እና ባሕርይ የሌለው አድረገው ሊገምቱት ይችላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱም ድምዳሜዎች ሁሉ፣ ከመንፈሳዊው ፍጹም እውነታ የተቃረኑ ናቸው፡፡ በዓብዩ ጌታ እምነት ያላቸው ሆኖ፣ የግል ምስል እና ባሕርይ እንዳለው የማይረዱ ሁሉ፣ ወደ መንፈሳዊ ዓለም ሲመለሱ “ብራህማን” ወደተባለው የዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ የብርሃን ጮራ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይህ ስፍራ ከዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ገላው የሚመነጨው የብርሃን ጮራ የሚገኝበት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን፣ ወደ “ብሃገቫን” ወይም የግል ዓብይ ሰብአዊ ምስሉን ይዞ ዓብዩ የመላእክት ጌታ ወደሚገኝበት የመንፈሳዊ ዓለም ሊሸጋገሩ አይችሉም፡፡

እነዚህ በግምት የሚፈላሰፉ ሰዎች፣ ዓብዩ የመላእክት ጌታ ሽሪ ክርሽና መሆኑን አልተረዱም፡፡ ሰብአዊ ባሕርይ የሌለው የዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ጮራ፣ ከመንፈሳዊ ገላው የሚመነጭ እንደሆነም የተረዱ አይደሉም፡፡ “ፓራም አትማ” በልባችን ውስጥ የሚገኘውንም የዓብዩ ጌታ አካል፣ በሁሉም ቦታ የተሰራጨ የዓብዩ ጌታ ቅንጣፊ አካል መሆኑንም አልተረዱም፡፡ ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና ዘለዓለማዊ ዕውቀት እና ደስታ የተሞላበት መንፈሳዊ ገላ እንዳለውም አይረዱም። ዓብዩ ሽሪ ክርሽናን፣ ልክ በእርሱ ሥር እንደሚተዳደሩትም መላእክት፣ ከፍተኛ ኅይል እንዳለው ሌላ መልአክ አድርገው ይቆጥሩታል። ከሽሪ ክርሽና መንፈሳዊ ገላ የሚመነጨውንም መንፈሳዊ ጮራ፣ ልክ እንደ ዋነኛው ዓብይ ጌታ በማድረግ ይቆጥሩታል። ቢሆንም ግን የሽሪ ክርሽና ትሑት አገልጋዮች የዓብዩ ጌታን የበላይነት እና ሁሉም ነገር ከእርሱ የሚመነጭ መሆኑን በትክክል የተረዱ ስለሆኑ፣ ሙሉ ልቦናቸውን በመስጠት በፍቅር ሲያገለግሉት ይገኛሉ።

በብሀገቨድ ጊታ (ብጊ 7:20/23) እንደተጠቀሰው፣ በመንፈሳዊ ዕውቀት ያልዳበሩ እና ዓለማዊ ስሜታቸውን ለማርካት የሚጓጉ ሰዎች ሁሉ፣ ይህንን ጊዜያዊ የደስታ ፍላጎታቸውን ለማርካት ለመላእክት ሲሰግዱ እና ሲጸልዮ ይታያሉ። በዚህ ዓለም ውስጥ እንደምናየው፣ ነፍስ በዓለማዊ ሕይወት ውስጥ ተጠምዳ ትገኛለች። ቢሆንም ግን፣ ከዚህ ቁሳዊ ዓለም በመውጣት ወደ ዘለዓለማዊው ዕውቀት እና ደስታ ወደሞላበት መንፈሳዊ ዓለም መመለስ ይገባታል። ስለዚህም ሽሪ ኢሾፓኒሻድ የሚያስተምረን ጊዜያዊ ደስታ ለማግኘት መላእክትን ከማምለክ ይልቅ፤ ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽናን ጠለላ በማድረግ፣ ከቁሳዊው ዓለም ትስስር ነጻ እንድንሆን እና ወደ ዘለዓለማዊው መንፈሳዊ ዓለም እንድንመለስ ማገልገልን ነው።

በብሀገቨድ ጊታ እንደተገለጸው (ብጊ 7:13) ለመላእክት የሚሰግዱ ሁሉ፣ ከሞት በኋላ ወደ ሚሰግዱላቸው መላእክት እንደሚሄዱ ተገልጿል። ለጨረቃዎች መልአክ የሚያመልኩ ሁሉ፣ ወደ ጨረቃዎቹ ይሄዳሉ። እንዲሁም ለፀሐይ መልአክ የሚሰግዱ ሁሉ፣ ከሞት በኋላ ወደ ፀሐይ ይጓዛሉ። ሳይንቲስቶች ሮኬትን በመሥራት ወደ ጨረቃ ጉዞ ለማድረግ በመጣጣር ላይ ይገኙ ነበር። ይህ ግን ለቬዲክ ተከታዮች አዲስ ነገር አይደለም። የሰው ልጅ በተፈጥሮ የታደለ አእምሮ ስላለው፣ ወደ ህዋ የመጓዝ እና ሌሎች ፕላኔቶችን የመጎብኘት ችሎታ አለው። ይህም ሊሆን የሚችለው፣ እንደዘመኑ የሳይንሳዊ ምርምር ውጤት መንኮራኩሮችን በመሥራት ሳይሆን፣ በመንፈሳዊ ዮጋ ልምድ ከሚገኙት ምስጢራዊ ኃይሎች ወይም ፕላኔቶቹን የሚወክሉትን መላእክት በትሑት መንፈስ በማምለክ እና በማገልገል ነው።
በቬዲክ ስነጽሑፎች ውስጥ እንደተገለጸው አንድ ሰው ከእነዚህ ከሦስቱ በአንዱ ፈለግ፣ ወደ ሌሎች ፕላኔቶች መጓዝ ይችላል። ከሁሉም በላይ ግን በጣም የተለመደው ጥረት፣ ፕላኔቶቹን የሚወክሉትን መላእክት በትሑት መንፈስ በማምለክ እና በማገልገል ነው። በዚህም መንገድ ነፍስ ወደ ጨረቃ፣ ወደ ፀሐይ ወይም ወደተፈለገው ፕላኔት መጓዝ ትችላለች። “ብራህማ ሎካ” ተብሎ ወደሚታወቀውም የቁሳዊው ዓለም የገነት ታላቁ ፕላኔት እንኳን ለመጓዝ ይቻላል። ይሁን እንጂ በቁሳዊው ዓለም የሚገኙት እያንዳንዳቸው ፕላኔቶች ጊዜያዊ እንጂ ዘለዓለማዊ አይደሉም። ዘለዓለማዊ ፕላኔቶች ግን፣ በመንፈሳዊው ዓለም የሚገኙት ቫይኩንታ ፕላኔቶች ተብለው የሚታወቁት ናቸው። በእነዚህ ፕላኔቶች ውስጥ ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና በእውን የመንፈሳዊው ዓለም ዓብይ ጌታ ሆኖ ይገኝበታል። ይህንንም ዓብዩ ሽሪ ክርሽና እራሱ በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ገልጾታል። (ብጊ 8:16)

አብራህማ ብሁቫና ሎካህ
ፑናር አቫርቲኖርጁና
ማም ኡፔትያ ቱ ኩንቴያ
ፑናር ጃንማ ና ቪድያቴ

“በቁሳዊው ዓለም ውስጥ ከሚገኙት ከከፍተኛዎቹ ፕላኔቶች ጀምሮ እስከ ዝቅተኛው ፕላኔት ድረስ፣ እያንዳንዳቸው ስቃይ የሰፈነባቸው እና ተደጋጋሚ ትውልድ እና ሞት የተሞላባቸው ናቸው። ቢሆንም ግን የኩንቲ ልጅ ሆይ፣ ወደ እኔ መንፈሳዊ ዓለም የተመለሰ ሁሉ፣ እንደገና ወደ እዚህ ቁሳዊው ዓለም በመወለድ ለስቃይ አይፈጠርም።”

ሽሪ ኢሾፓኒሻድ እንደሚያስተምረንም፣ መላእክትን በማምለክ ወደ ሌሎች ፕላኔቶች የሚጓዙ ሁሉ፣ ከጨለማው የቁሳዊው ዓለም እንዳልወጡ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። መላው የቁሳዊው ዓለም፣ በቁሳዊ ንጥረ ነገሮች የተሞላ ነው። ይህም የሚመሰለው፣ ልክ እንደ ኮኮናት ፍሬ በጠንካራ ሽፋን የተከደነ እና፣ ውስጡ በግማሽ ውሀ እንደተሞላው ዓይነት መሆኑ ነው። ይህ የቁሳዊው ዓለም በአየር እና በጨለማ የተሞላ ስለሆነ፣ ብርሃንን ለማግኘት የግዴታ ፀሐይ እና ጨረቃ ያስፈልጉናል። ከዚህ የቁሳዊ ዓለም ባሻገር ደግሞ “ብራህማ ጆይቲ” ተብሎ የሚታወቀው የዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ጮራ ይገኛል። በእዚህም መንፈሳዊ ጮራ ውስጥ፣ “ቫይኩንታ ሎካ” ተብለው የሚታወቁት መንፈሳዊ ፕላኔቶች ይገኛሉ። ከእነዚህ ሁሉ መንፈሳዊ ፕላኔቶች ታላቁ መንፈሳዊ ፕላኔት፣ “ክርሽና ሎካ” ወይም “ጎሎካ ቭርንዳቨና” ተብሎ ይታወቃል። በዚህ መንፈሳዊ ፕላኔት ውስጥ፣ ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና ይኖርበታል። ዓብዩ ሽሪ ክርሽና “የክርሽና ሎካን” ፕላኔት ፈጽሞ ለቆ አይሄድም። ምንም እንኳን ከዘለዓለማዊ አገልጋዮቹ ጋር በዚህ መንፈሳዊ ፕላኔት ውስጥ የሚኖር ቢሆንም፣ በመንፈሳዊ ኃይሉ በመላው ቁሳዊው እና መንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ተሰራጭቶ ይገኛል። ይህ እውነታም በማንትራ አራት ውስጥ ተገልጾ ይገኛል። ይህም ልክ እንደ ፀሐይ ይመሰላል። ምክንያቱም ፀሐይ ምሕዋሯን ሳትለቅ በአንድ ቦታ ብቻ በመገኘት በመላው ህዋ ውሰጥ ኃይሏን በማሰራጨት ላይ ስለምትገኝ ነው።

የቁሳዊ ዓለም ስቃይ እና መከራ ወደ ጨረቃ በመሄድ፣ ወይም ወደላይ እና ወደታች ወደሚገኙት ፕላኔቶች በመሄድ አይፈታም። ሰለዚህ ሽሪ ኢሾፓኒሻድ የሚመክረን፣ ወደ እነዚህ ጨለማ ቁሳዊ ዓለማት ለመሄድ ጥረት ከማድረግ ይልቅ፣ ወደ ብርሃናማው የዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ዓለም ለመጓዝ ጥረት ማድረግ የሚገባን ነው። በዚህ ዓለም ውስጥ ብዙ አስመሳይ መንፈሳውያን ይገኛሉ። እነዚህም ሰዎች በመንፈሳዊ አገልግሎት ስም፣ ዝናን ለማትረፍ የሚሹ ሰዎች ናቸው። እነዚህም ሰዎች ከዚህ ቁሳዊ ዓለም ለመውጣት የሚሹ እና ወደ መንፈሳዊ ዓለም ለመመለስ የሚጥሩ አይደሉም። በመንፈሳዊ አገልግሎት ስም ግን፣ ዝናቸውን በቁሳዊ ዓለም ውስጥ ለማስፋፋት የሚጥሩ ናቸው። እንዲህ ዓይነቶቹም ከሃዲያን እና በዓብዩ ጌታ ሰብዓዊነት የማያምኑ ሰዎች ሁሉ፣ የሚያስተምሯቸውን ሰዎች ወደ ጨለማ እና የድንቁርና መንገድ ሲመሯቸው ይገኛሉ። ከሃዲያን የዓብዩ ጌታን በእውን መኖር የሚክዱ ሲሆን፣ “ማያቫዲ” ተብለው የሚታወቁት፣ በዓብዩ ጌታ ሰብአዊነት የማያምኑ ደግሞ፣ ከሀዲያንን በከፊሉ የሚደግፉ በመሆን በዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ጮራ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ናቸው። በዚህ በሽሪ ኡፓኒሻድ ማንትራዎች ውስጥ እንደተገለጸው፣ የከሃዲያን እና የማያቫዲዎች ፍልስፍና ፈጽሞ የሚደገፍ አይደለም። ዓብዩ ጌታ እንደሰብአዊነቱ ከሁሉም በላይ በፍጥነት እንዳሻው እና ወደፈለገበት በፍቃዱ መጓዝ ይችላል። ወደ ሌሎች ፕላኔቶች ለመጓዝ የሚታገሉት ግን፣ የሰው ፍጥረታት ናቸው። ዓብዩ ጌታ ዓብይ ሰብአዊ ፍጥረት የለውም የሚለው ፍልስፍና፣ ድንቁርና የተሞላበት ነው። ይህም ፍልስፍና የሚመነጨው፣ ትክክለኛ የመንፈሳዊ ዕውቀት ከጎደለባቸው ፈላስፎች ነው።

ድንቁርና የተሞላባቸው አስመሳይ መንፈሳውያን እና የቬዲክ መመሪያዎችን የማይከተሉ ሰዎች ሁሉ፣ ተከታዮቻቸውን ወደ ተሳሳተ መንገድ ስለሚመሩ፣ ድንቁርና ወደተሞላበት ፕላኔት እንዲጓዙ ያበቋቸዋል። አንዳንዶቹም አስመሳይ መንፈሳውያን፣ የዓብዩ ጌታ ተወካይ ነኝ በማለት፣ ስለመንፈሳዊ ሕይወትና ስለ ቬዳዎች ትምህርት ዕውቀት የሌላቸውን ሰዎች ሲያታልሉ ይገኛሉ። እነዚህ ይህን የሚያዳምጡ ሰዎች፣ ስለ ቬዳዎች ትንሽ ዕውቀት ቢኖራቸውም እንኳን፣ ያላቸው ዕውቀት በቂ መንፈሳዊ ዕውቀት ባለመሆኑ፣ በቀላሉ ለመታለል ይበቃሉ። በቬዲክ ሥነጽሑፎች ውስጥ መላእክት እንዴት መመለክ እንደሚገባቸው በዝርዝር ተገልጿል። ቢሆንም ግን በዓብዩ ጌታ ሰብአዊነት የሚያምኑ ሰዎች የቬዳዎችን ዋነኛ ዓላማ በመከተል፣ መላእክትን ሲያመልኩ አይገኙም። በቬዳዎች ውስጥ እነዚህ መላእክት ለዓለማዊ ነገሮች መመለክ እንደሌለባቸውም ተገልጿል። በብሀገቨዲ ጊታ (ብጊ 7:23) ውስጥ እንደተገለጸው መላእክትን በማምለክ የሚገኘው ነገር ሁሉ ጊዜያዊ ነው። መላው ጨለማ የቁሳዊው ዓለም ጊዜያዊ እንደመሆኑ ሁሉ፣ በውስጡ የሚገኙት ቁሳዊ ነገሮች ሁሉ፣ ጊዜያዊ ናቸው። መገንዘብ የሚገባን ነገር ግን፣ እንዴት አድርገን ዘለዓለማዊ ሕይወትን ለማግኘት እንደምንችል ነው።

ዓብዩ ጌታ እንደገለጸውም በትሑት መንፈሳዊ አገልግሎት ለሚቀርቡት ሁሉ፣ ከዚህ የጨለማ ቁሳዊ ዓለም ትውልድ እና ሞት ነጻ ሊያወጣቸው ይችላል። ከዚህ ውጪ ሌላ ምንም ዓይነት አማራጭ የለም። ከዚህ ቁሳዊ ዓለም መውጣት የሚቻለው፣ ዓብዩ ጌታን በትሑት መንፈስ በማገልገል እና፣ መንፈሳዊ ዕውቀትን በማዳበር፣ ከቁሳዊው ዓለም ጉጉት በመራቅ ነው። አስመሳይ መንፈሳውያን ግን፣ ዕውቀቱን በትክክል የተረዱ ሳይሆኑ የሚያስተምሩ እና፣ ከዓለማዊ ኑሮም ለመራቅ ጥረት የሚያደርጉ አይደሉም። በመንፈሳዊነት ስም ግን የበጎ አድራጎት ሥራ በመሥራት በዚህ ዓለም ውስጥ የተመቸ ኑሮአቸውን ሲያደራጁ ይታያሉ። መንፈሳዊ ስሜቶችን እንደያዘ ሰው በማስመሰል፣ የዓብዩ ጌታ አገልግሎት የያዘውን መንፈሳዊ ሰው ጥላ በማንጸባረቅ፣ ግብረገብ በጎደለበት ዓለማዊ ኑሮ ላይ ተመስጠው ይገኛሉ። እራሳቸውንም እንደ መንፈሳዊ አባት እና እንደ ዓብዩ ጌታ ተወካይ በማድረግ ሲያቀርቡ ይታያሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ አስመሳዮች በንጹሕ መንፈሳውያን፣ በአቻርያዎች እና መንፈሳዊ ሥርዓትን በትክክል በሚከተሉ መንፈሳውያን ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም። ምክንያቱም፣ የቬዲክ መመሪያዎችን በትክክል ስለማይከተሉ ነው። “አቻርዮፓሰና” ወይም መንፈሳዊ ሰው “ለአቻርያዎች” ወይም ለትክክለኛ የዓብዩ ጌታ መምህራን አክብሮት ማቅረብ እና ፈለጋቸውን መከተል ይገባዋል።” ዓብዩ ሽሪ ክርሽናም በብሀገቨድ ጊታ (ብጊ 4:2) ውስጥ ይህንኑ መልእክት ገልጾታል። “ኤቫም ፓራምፓራ ፕራፕታም” ይህ ታላቁ የዓብዩ ጌታ ሳይንሳዊ ዕውቀት መተላለፍ የሚገባው፣ ሲወርድ ሲዋረድ ከሚመጣው የዲቁና ሥርዓት ነው። ቢሆንም ግን፣ ብዙ አስመሳዮች እርስ በራሳቸው እንደ አቻርያ በመሰያየም፣ ሰፊውን ሕዝብ ሲያታልሉ ይገኛሉ። እነዚህም አስመሳዮች፣ የቀድሞ አቻርያዎችን ፈለግ ፈጽሞ ሲከተሉ አይታዩም።

እንዲህ ዓይነቶቹ አስመሳዮች፣ ለሰው ልጅ ኅብረተሰብ ትልቅ ጠንቅ ናቸው። የመንፈሳዊ አስተዳደር መንግሥት ስለሌለም በመንግሥት እጅ ሳይቀጡም በቀላሉ በማለፍ ኅብረተሰቡን ሲያታልሉ ይገኛሉ። ዳሩ ግን በዓብዩ ጌታ የተደነገገውን የተፈጥሮ ሕግጋት ለማምለጥ አይችሉም። የሚያደርጉትም የአስመሳይነት መንፈሳዊ ሥራ ሁሉ፣ ዓለማዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት የሚደረግ ጥረት ነው። ይህም በብሀገቨዲ ጊታ (ብጊ 16፡ 19–20) ውስጥ ተገልጿል። “በመንፈሳዊነት ስም የሚነግዱ ከሃዲያን እና ምቀኞች ሁሉ፣ ድንቁርና ወደተሞላበት ፕላኔቶች ይጓዛሉ።” በሽሪ ኡፓኒሻድም እንደተገለጸው እንዲህ ዓይነቶቹ አስመሳዮች የማታለል “መንፈሳዊ” ሥራቸውን ከፈፀሙ በኋላ፣ በሕይወተ ሕልፈት ወቅት ወደ ዝቅተኞቹ ዓለማት ይጓዛሉ።

« Previous Next »