ማንትራ አስራ አራት
ሳምብሁቲም ቻ ቪናሳም ቻ
ያስ ታድ ቬዶብሀያም ሳሀ
ቪናሴና ምርትዩም ቲርትቫ
ሳምብሁትያምርታም አስኑቴ
ሳምብሁቲም — ዘለዓለማዊው የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ፣ መንፈሳዊ ቅዱስ ስሙ፣ መንፈሳዊ ቅርጹ፣ ታሪካዊ ድርጊቶቹ፣ ዓይነቱ፣ ጓዙ ሁሉ፣ የተለያዩት መኖሪያዎቹ ወዘተ፣ ቻ — እና፣ ቪናሳም — ጊዜያዊው እና ቁሳዊው የመላእክት ክስተቶች፣ የሰው ፍጥረታት፣ እንስሳት ወዘተ፤ ይህም በሐሰት መጠሪያ ስማቸው፣ ዝናቸውን፣ ቻ — ጨምሮ፣ ያህ — እንዲህ የሚያደርግ፣ ታት — እንደዚህ፣ ቬዳ — የሚያውቅ፣ ኡብሀያም — ሁለቱንም፣ ሳሀ — ተያይዞ፣ ቪናሴና — ሁሉም ነገር ለመደምሰስ እንደሚበቃም ሁሉ፣ ምርትዩም — ሞት፣ ቲርትቫ — ተሸጋግሮ፣ ሳምብሁትያ — በዘለዓለማዊው የዓብዩ ጌታ ቤተ መንግሥት፣ አምርታም — ሞት የማይኖርበት፣ አስኑቴ — ይደሰታል
ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽናን፣ ቅዱስ ስሙን፣ አቋሙን፣ ባሕርዩን እና ታሪኩን እንዲሁም ይህንን የፈጠረውን ጊዜያዊ ቁሳዊ ዓለም፣ መላእክትን፣ ሰዎችን፣ እንስሳትን ሁሉ በትክክል ለይተን መረዳት ይገባናል፡፡ አንድ ሰው እነዚህን ሁሉ በትክክል የሚረዳ ከሆነ፤ ሞትን እና ይህንን ቁሳዊ ጠፈር በቀላሉ ለመሸጋገር ሲችል፤ ወደ ዘለዓለማዊው መንፈሳዊ መንግሥተ-ሰማያትም በመመለስ፣ ዘለዓለማዊ ሕይወትን፣ ደስታን እና ዕውቀትን ለማግኘት ይችላል፡፡
የሰው ልጅ “ዘመናዊ ሥልጣኔ” ተብሎ በተሰየመው እሽቅድድሙ፣ በርካታ ቁሳዊ ነገሮችን ለማምረት ችሏል። እነዚህም የጠፈር መጓጓዣዎችን እና የአቶሚክ ቦምብ ኅይልንም ይጨምራል። ቢሆንም ግን ሰዎች እንዳይሞቱ፣ በተደጋጋሚ እንዳይወለዱ፣ እንዳያረጁ ወይም ምንም ዓይነት በሽታ እንዳይነካቸው ለማድረግ ብቃት አላሳየም። አንድ ዐዋቂ ሰው እንዴት እንደነዚህ ዓይነቶቹን ስቃይ እና መከራዎች መግታት እንደሚቻል ሳይንቲስቶችን ቢጠይቃቸው፤ ሳይንስ ወደፊት እየገሰገሰ በመሆኑ ወደፊት የሰው ልጅ ፈጽሞ እንዳይታመም፣ እንዳያረጅ እና እንዳይሞት ለማድረግ እንችላለን በማለት ይመልሳሉ። እንዲህ ዓይነቱ መልስ፣ ሳይንቲስቶች ስለ ቁሳዊ ዓለም ሕግጋት ግንዛቤያቸው የወደቀ መሆኑን ያሳየናል። በቁሳዊ ዓለም ውስጥ እስካለን ድረስ እያንዳንዳችን በተፈጥሮ ጥብቅ ሕግጋት ውስጥ የምንተዳደር ነን። እያንዳንዳችንም ሕያው ፍጥረታት፣ ስድስቱን የተፈጥሮ ደረጃዎች ማለፍ ግዳጃችን ነው። እነዚህም መወለድ፣ ማደግ፣ ለጥቂት ጊዜ መኖር፣ መውለድ፣ ማርጀት እና በመጨረሻም መሞት ናቸው። በቁሳዊው ዓለም ውስጥ ማናቸውም ሕያው ፍጥረታት፣ ከእነዚህ ከስድስቱ የተፈጥሮ ሕግጋት ውጪ ለመንቀሳቀስ አይችሉም። ስለዚህ መላእክትም ሆኑ፣ የሰው ልጆች፣ እንስሳት ወይም ተክሎች ሁሉ፣ በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ እስከ ዘለዓለም ለመኖር አይችሉም።
የሕይወት ርዝመት እንደ እያንዳንዱ የሕይወት ዝርያዎች ይለያያል። ለምሳሌ መልአኩ ጌታ ብራህማ፣ በዚህ ቁሳዊ ጠፈር ውስጥ፣ ከፍጥረታት ሁሉ የበላይ የሆነ ዕድሜ ያለው እና በትሪሊዮን የሚቆጠር ዓመታት ሊኖር የሚችል ነው። በዓይን መታየት የማይችሉት ህዋሳት ግን፣ ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ይኖራሉ። ይሁን እንጂ ማናቸውም ሕይወት ያላቸው ዝርያዎች ሁሉ በዚህ ቁሳዊ ጠፈር ውስጥ ለዘለዓለም ሊኖሩ አይችሉም። ፍጥረታት በተፈጥሮ ውስን በሆነ መንገድ ይወለዳሉ፣ ለጥቂት ጊዜም ይኖራሉ፣ በመቀጠል ለመኖር ዕድል ካገኙም በኋላ ያድጋሉ፣ ይዋለዳሉ፣ ከዚያም ቀስ በቀስ ማርጀት ይጀምራሉ፣ በመጨረሻም ይሞታሉ። በዚህ ዓይነቱ የተፈጥሮ ሕግጋት በመተዳደርም፣ በጠፈር ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩት የተለያዩ ጠፈር አስተዳዳሪዎች ወይም ብራህማዎች እንኳን፣ ዛሬ ወይም ነገ ከመሞት የሚተርፉ አይደሉም። በዚህም ምክንያት በቬዲክ ሥነጽሑፎች ውስጥ፣ መላው የጠፈር ቁሳዊው ዓለም “ማርትያ ሎካ” ተብሎ ይታወቃል። ይህም ሞት የሚገኝበት ጠፈር ማለት ነው።
ሳይንቲስቶች እና የፖለቲካ ሰዎች፣ ፋይዳ በሌለው ምርምር ይህንን የቁሳዊ ዓለም ሞት የማይገኝበት ዓለም ለማድረግ በመሞከር ላይ ናቸው። ምክንያቱም፣ ሞት ስለማይገኝበት መንፈሳዊው ዓለም ምንም ዓይነት ዕውቀት ስለሌላቸው ነው። ስለዚህም ዕውቀት በቬዲክ መጻሕፍት ላይ የተመረኮዘ አንዳችም ዕውቀት የላቸውም። እነዚህ መጻሕፍት ስለዚህ ርእስ በጥልቅ የዘገበ መረጃ አላቸው። ይህም ዕውቀት ሙሉ በሙሉ በተለያዩ ማስረጃዎች ሊደገፍ የሚችል ነው። ይሁን እንጂ የወቅቱ ዘመናዊ ሰው ከቬዳዎች፣ ከፑራናዎች እና ከተለያዩ ተመሳሳይ መጻሕፍቶች ዕውቀቱን ለመቅሰም እንደሚያስፈልግ የተገነዘበ አይደለም።
ከቪሽኑ ፑራና የሚከተለውን ጥቅስ እናገኛለን። (6:7:61)
ቪሽኑ ሻክቲ ፓራ ፕሮክታ
ሼትራ ግያክህያ ታትሀ ፓራ
አቪድያ ካርማ ሳሚግንያ
ትሪቲያ ሽክቲር ኢሽያቴ
ዓብዩ ጌታ ቪሽኑ፣ የመንግሥተ-ሰማያት ሁሉ ጌታ፣ የተለያዩ ኅይልን ይዞ ይገኛል። እነዚህም “ፓራ” ወይም ከፍተኛ እና “አፓራ” ዝቅተኛ ተብለው ይታወቃሉ። ሕያው ፍጥረታት ሁሉ በከፍተኛው ኃይሉ ተመድበው ይገኛሉ። ሕያው ያልሆነው ተወሳስበን የምንገኝበት የቁሳዊው ዓለም ግዑዝ አካል ደግሞ፣ በዝቅተኛው ኃይሉ ተመድቦ የሚገኝ ነው። ይህ የቁሳዊ ዓለም የተፈጠረው በዓብዩ ጌታ ኅይል እና ፈቃድ ነው። ይህ ዓለም ሕያው ፍጥረታትን ሁሉ፣ እንደምኞታቸው በዓለማዊ ቅዠት በመሸፈን፣ በድንቁርና ወይም “አቪድያ” ውስጥ እንዲቆዩ እና እንደፍላጎታቸው በዓለማዊ ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ ያደርጋቸዋል። በሌላ አኳያ ደግሞ፣ ሌላ ለየት ያለ የዓብዩ ጌታ ከፍተኛ ኅይልም ይገኛል። ይህም ከቁሳዊ ዓለም ዝቅተኛ ኅይል እና ከሕያው ፍጥረታት ሁሉ የተለየ ነው። ይህ የዓብዩ ጌታ ከፍተኛው ኅይል ዘለዓለማዊ እና ሞት የማይገኝበት መንፈሳዊ ዓለሙ ነው። ይህም በብሀገቨድ ጊታ መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ተብሎ ተገልጿል። (ብጊ 8:20)
ፓራስ ታስማት ቱ ብሀቮ ንዮ
ቭያክቶ ቭያክታት ሳናታናህ
ያህ ሳ ሳርቬሹ ብሁቴሹ
ናስያትሱ ና ቪናስያቲ
መላው የቁሳዊው ዓለም ፕላኔቶች ማለትም የበላይ፣ የዝቅተኛውና የመሀከለኛው ዓለማት፤ ፀሐይን፣ ጨረቃን እና ቪነስን ሁሉ ጨምሮ በመላው ጠፈር ተበትነው ይገኛሉ። እነዚህም ፕላኔቶች ለመኖር የሚችሉት ቢበዛ እስከ ጌታ ብራህማ የዕድሜ መጨረሻ ጊዜ ብቻ ነው። ነገር ግን አንዳንዶቹ በዝቅተኛው ዓለም የሚገኙት ዓለማት፣ በጌታ ብራህማ የአንድ ቀኑ መጨረሻ ላይ የሚደመሰሱ ናቸው። ከዚያም በኋላ ደግሞ፣ በሚቀጥለው የጌታ ብራህማ ቀን ላይ እንደገና ይፈጠራሉ። በከፍተኛው ዓለማት ለሚገኙት ፕላኔቶች ሁሉ፣ ከእኛው ዓለም ጋር ሲወዳደር የጊዜው መጠን የተለየ እና የረዘመ ሆኖ ይገኛል። ለምሳሌ የምድር ላይ አንድ ዓመት፣ በአንዳንድ በከፍተኛው ዓለም ውስጥ በሚገኙት ፕላኔቶች ላይ ሲተመን፣ ለእነሱ ሀያ አራት ሰዓት ወይም አንድ ቀን እና አንድ ሌሊት ብቻ ይሆናል። አራቱ በመሬት ላይ የሚገኙት የቬዲክ ዘመናት (ሳትያ፣ ትሬታ፣ ድቫፓራ እና ካሊ ዘመናት) የሚቆዩበት ጊዜ በከፍተኛው ዓለማት ጊዜ ሲቆጠር፣ አስራ ሁለት ሺህ ዓመታት ነው። ይህም ጊዜ በአንድ ሺህ ሲባዛ፣ የጌታ ብራህማን አንድ ቀን እና አንድ ሌሊት ብቻ ይሰጠናል። የሌሊቱም ርዝመት ከቀኑ ጋር የተመሳሰለ ነው። እነዚህም ቀናት እና ሌሊቶች ተደምረው የጌታ ብራህማን ወራት እና ዓመታትን ይሰጡናል። የጌታ ብራህማም ዕድሜ እስከ አንድ መቶ ዓመታት የሚደርስ ነው። በጌታ ብራህማም ዕድሜ መጨረሻ ላይ፣ በጠፈር ላይ የሚገኙት መላ የቁሳዊው ዓለማት ሁሉ ይደመሰሳሉ።
በቬዲክ መጻሕፍት እንደተገለጸው፤ እንደ ፀሐይ እና እንደ ጨረቃ የመሳሰሉት ከፍተኛ ፕላኔቶች፣ ማርትያ ሎካ ተብለው የሚታወቁት ፕላኔቶች፣ የምንኖርባት ምድር እና በዝቀተኛው ጠፈር የሚገኙት ፕላኔቶች ሁሉ፣ በጌታ ብራህማ ቀን መጨረሻ ላይ ሁሉም በጠቅላላ ወደ እልቂት ውቅያኖስ ውስጥ ይገባሉ። በዚህም ወቅት ማናቸውም ሕያው ፍጥረታት ሁሉ፣ ንቃተ ሕሊናቸው ግሁድ ሆኖ አይኖሩም። ቢሆንም ነፍስ እንደመሆናቸውም ሁሉ፣ ሕያው በመሆን እንደገና እስኪፈጠሩ ድረስ፣ ያለ ንቃት ገሀድ ሳይሆኑ በዓብዩ ጌታ ናራየን መንፈሳዊ ገላ ውስጥ ጸንተው ይኖራሉ። የዚህ ዓይነቱ ያልተከሰተ የፍጥረታት ደረጃ “አቭያክታ” ተብሎ ይታወቃል። እንደዚህም ሁሉ፣ የብራህማ ዕድሜም ሲያከትም፣ መላ ቁሳዊ ጠፈር ተደምስሶ ፍጥረታት ሁሉ እንደገና ወደ “አቭያክታ” ደረጃ ያዘግማሉ። ቢሆንም ግን ከእነዚህ ሁለት ዓይነት የተሰወሩ ክስተቶች ሌላ፣ ለሕያው ፍጥረታት ሁሉ የተሰወረ ክስተት አለ። ይህም የመንፈሳዊው ዓለም ወይም መንግሥተ-ሰማያት ነው። በዚህም መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ፣ ቁጥራቸው ሊተመን የማይችል መንፈሳዊ ፕላኔቶች ይገኛሉ። እነዚህ መንፈሳዊ ፕላኔቶች ግን፣ ለዘለዓለም የሚኖሩ ናቸው። በብራህማ ዕድሜ መጨረሻ ላይ መላው ቁሳዊው ዓለም ሲደመሰስ፣ እነዚህ መንፈሳዊ ፕላኔቶች ግን፣ ለዘለዓለም ሳይደመሰሱ የሚኖሩ ናቸው።
በዚህ ቁሳዊ ጠፈር ውስጥ በቁጥር የማይተመኑ ብዙ ፕላኔቶች ይገኛሉ። እያንዳንዱ ቁሳዊ ጠፈር በተለያዩ ብራህማ ተብለው በሚታወቁ መላእክት የሚተዳደሩ ናቸው። መላው የቁሳዊው ዓለም ጠፈር፣ ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር ሲነጻጸር አንድ አራተኛ (ኤካፓድ ቪብሁቲ) የሚሆን የዓብዩ ጌታ ዝቅተኛው ኃይሉ ነው። ከጌታ ብራህማዎች ግዛት ውጪ ግን፣ የመንፈሳዊው ዓለም ይገኛል። ይህም ሦስት አራተኛ ወይም “ትሪፓድ ቪብሁቲ” የሚሆን፣ የዓብዩ ጌታ ከፍተኛው ኅይል ወይም “ፓራ ፕራክርቲ” ተብሎ የሚታወቀው ነው።
በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ የሚኖረው ዋነኛው እና ፈላጭ ቆራጩ ጌታ፣ ዓብዩ የመንፈሳዊው ዓለም ጌታ፣ ሽሪ ክርሽና ነው። በብሀገቨድ ጊታ ውስጥም እንደተገለጸው (ብጊ 8:22) ወደ ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና ልንቀርብ የምንችለው፣ ፍቅር በተሞላበት ትሑት እና ባልተበከለ መንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ነው። በግያና (ፍልስፍና)፣ ዮጋ (ምስጢራዊ ኅይል) እና ካርማ (ዓለማዊ ሥራዎች) በመሳሰሉት ሥርዓቶች ዓብዩ ሽሪ ክርሽናን ልንቀርበው አንችልም። ዓለማዊ ሰዎች በሥራቸው ወደ ከፍተኛው የቁሳዊ ዓለም (ስቫርጋ ሎካ) ሊሸጋገሩ ይችሉ ይሆናል። እነዚህ ፕላኔቶች ፀሐይን እና ጨረቃን ያካትታሉ። እንደዚሁም ሁሉ ግያኒዎች እና ዮጊዎች ወደ ከፍተኛው ዓለማት ሊሸጋገሩ ይችላሉ። እነዚህም የማሃር ሎካ፣ ታፓ ሎካ እና ብራህማ ሎካን ያካትታሉ። ትሑት መንፈሳዊ አገልግሎትን በማቀረብ፣ ወደ ዓብዩ ጌታ ለመመለስ ብቁ ሲሆኑ ደግሞ፣ ወደ መንፈሳዊው ዓለም ለመጓዝ ይችላሉ። ይህም እንደ እምነታቸው፣ የዓብዩ ጌታ የመንፈሳዊ ገላ ጮራ ወደሚገኝበት የመንፈሳዊ ዓለሙ ስፍራ (ብራህማጆይቲ) ወይም “ቫይኩንትሀ” ወደሚባሉት መንፈሳዊ ፕላኔቶች ለመጓዝ መብት ይኖራቸዋል። ለዚህም መንፈሳዊ ብቃታቸው ይወስናል። በእርግጥ የሚታወቀው ግን፣ ማንም ሕያው ፍጥረት በመንፈሳዊ ትሑት አገልግሎት ብቁ ያልሆነ ከሆነ፣ ወደ ማናቸውም መንፈሳዊ ፕላኔቶች መጓዝ አይችልም።
በቁሳዊው ዓለማት ውስጥ ከጌታ ብራህማ ጀምሮ፣ ምድር ላይ እስከሚገኙት ጉንዳኖች ድረስ፣ እያንዳንዱ ፍጥረት የቁሳዊው ዓለም ጌታ ለመሆን የሚጥሩ ናቸው። ይህም የቁሳዊው ዓለም በሽታችን ነው። በዚህም በሽታ እስከተበከልን ድረስ እያንዳንዳችን ሕያው ፍጥረታት ሥጋዊ ገላን በመቀያየር ደጋግመን ወደዚህ ቁሳዊ ዓለም መወለድ እና መሞታችን የማይቀር ነው። ማናቸውም ሕያው ፍጥረታት ሰውም ሆነ፣ መላእክት ወይም እንስሳ ጊዜያቸው ሲደረስ በሁለቱ ዓይነት እልቂቶች ሁሉም መደምሰሳቸው አይቀርም። እነዚህም ሁለቱ እልቂቶች በጌታ ብራህማ ቀን መጨረሻ ላይ እና በጌታ ብራህማ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የሚከናወኑ ናቸው።
ቢሆንም ግን ይህንን ተደጋጋሚ የትውልድ፣ የእርጅና፣ የሕመም እና የሞት ሥርዓትን ለማቆም ከፈለግን፣ ወደ መንፈሳዊው ዓለም ለመመለስ ጥረት ማድረግ ይገባናል። በዚህ መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ፣ ከዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ ከሽሪ ክርሽና ወይም ከከፊል ፍጹም ወገኑ ከጌታ ናራያን ጋር፣ ለዘለዓለም በደስታ ለመኖር እንችላለን። ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና እና ፍጹም የሆኑት ከፊል ወገኖቹ፣ በእያንዳንዱ መንፈሳዊ ፕላኔቶች ውስጥ ይገኛሉ። ይህም “በሽሩቲ ማንትራ” የተገለጸ ነው። (ጎፓል ታፓኒ ኡፓኒሻድ - ጎታኡ፡ 1:21) “ኤኮ ቫሲ ስርቫ ጋህ ክርሽና ኢድያህ ኤኮ ፒ ሳን ባሁድሀ ዮ ቫብሃቲ"
ማናቸውም ፍጥረታት ቢሆኑ፣ ከሽሪ ክርሽና በላይ ሊሆኑ አይችሉም። በተወሰነ ደረጃ በዚህ ቁሳዊ ዓለም ላይ ያሉ ፍጥረታት ግን፣ የቁሳዊ ዓለም ጌታ ለመሆን ብዙ ጥረት ሲያድረጉ ይታያሉ። ይሁን እንጂ ሁሉም በተፈጥሮ ሕግጋት ቁጥጥር ሥር ናቸው። በተደጋጋሚ መወለድ እና መሞት የሚሰቃዩ ፍጥረታት ናቸው። አልፎ አልፎ ግን ዓብዩ ሽሪ ክርሽና መንፈሳዊ ትምህርትን ለማስተማር በተደጋጋሚ ይመጣል። የሚሰጠው መሠረታዊ ትምህርቱም በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ የሚገኙ ፍጥረታት ሁሉ በትሑት መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ ነው። በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ የዓብዩ ጌታ የመጨረሻው ትምህርቱም ይህ ነበር። ብሀገቨድ ጊታ (ብጊ 18:66) “ሳርቫ ድሀርማ ፓሪትያጅያ ማም ኤካም ሸራናም ቭራጃ” “እነዚህ የተለያዩ ዓይነት የሃይማኖት ሥርዓቶችን ትተህ ወደ እኔ በቀጥታ ተመለስ።” ነገር ግን ብዙ አሳሳች መምህራን በዚህ ቃሉ ላይ የራሳቸውን ትርጉም በመስጠት ብዙኃኑን ሰው በማታለል ላይ ይገኛሉ። ኅብረተሰቡ ወደ መንፈሳዊው ዓለም እንዲመለስ የሚረዳ ትምህርትን ከመስጠት ይልቅ፣ በጎ አድራጎትንን እና ሆስፒታልን የመሰለ ድርጅት ማቋቋም፣ የመንፈሳዊ ዓላማችን ግብ ለመምታት ይቻላል በማለት ያስተምራሉ። የሰው ልጆች በጊዜያዊ በጎ አድርጎት ሥራ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ይገፋፋሉ። ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት የጎደለበት እንቅስቃሴ፣ ፍጹም የሆነ መንፈሳዊ ደስታን ለሕያው ፍጥረታት ማምጣት አይችልም። እንዲህን ዓይነቶቹ ሰዎች የተለያዩ የመንግሥት እና የከፊል የመንግሥት ድርጅቶችን በማቋቋም የተፈጥሮን የቁጣ ኅይል ለመቆጣጠር ይሞክራሉ። ሆኖም ይህንን የተፈጥሮ ቁጣ ኅይል ለማብረድ፣ ምንም አቅም የላቸውም። ብዙ ሐሰተኛ ሰዎችም የብሀገቨድ ጊታ ታላላቅ ምሁሮች ተብለው በኅብረተሰቡ ዘንድ ገነው ይታያሉ። ቢሆንም እነዚህ ሐሰተኛ ሰዎች በጊታ ውስጥ የተገለጸውን እና እንዴት የተፈጥሮን ቁጣን ማቀዝቀዝ እንደሚቻል ሳይረዱ በማለፍ ሲያስተምሩ ይታያሉ። ኃያሉን የተፈጥሮ ቁጣን ማቀዝቀዝ የምንችለው በዓብዩ ጌታአገልግሎር የተመሰጠ ንቃተ ሕሊና ስናዳብር ብቻ ነው። ይህም በብሀገቨድ ጊታ (ብጊ 7:14) ውስጥ ተገልጾልናል።
በዚህም በኢሾፓኒሻድ ጥቅስ ላይ እንደተማርነው፣ አንድ ሰው “ሳምብሁቲን” (ዓብዩ ጌታን) እና “ቪናሻን” (ቁሳዊ ዓለም) በትክክል ለይቶ ማወቅ ይገባዋል። አንድ ሰው ቁሳዊ ዓለምን በመረዳት ብቻ ሊድንም ሆነ ሊጸድቅ አይችልም። ምክንያቱም ከጊዜ በኋላ ተደጋጋሚ የቁሳዊው ዓለም እልቂት ስለሚመጣ፣ የቀሰመው ዕውቀቱ ሁሉ ጊዜያዊ በመሆኑ ነው። “አሀኒ አሀኒ ብሁታኒ ጋቻንቲሀ ያማላያም” ሆስፒታሎችን በመክፈት ብቻ በቁሳዊው ዓለም ኑሮ ሊጸድቅ አይችልም። አንድ ሰው ሊድን ሆነ ሊጸድቅ የሚችለው የዘለዓለማዊ ሕይወት እና መንፈሳዊ የደስታ ኑሮ እንዳለ ሲገነዘብ ነው። መላው የቬዲክ ዕውቀት የሚያስተምረን ይህንኑ የዘለዓለማዊ እና የደስታ መንፈሳዊ ኑሮ እንዲኖረን ነው። የሰው ልጅ ስሜቶቹን ለማርካት በጊዜያዊ ቁሳዊ ነገሮች ጉጉት በቀላሉ ይታለላል። ቢሆንም ለጊዜያዊው የስሜታችን ደስታ የምናደረገው መስዋእት ሁሉ፣ የተሳሳተ እና ክብራችንንም የሚቀንስ ነው።
ስለዚህ እራሳችንን በማዳን፣ ሌሎች ሰዎችንም ወደ በጎ መስመር ለመምራት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይህም እውነታውን ብንወደውም ባንወደውም ወይም ባንቀበለውም ማለት ነው። ከተደጋጋሚው ትውልድ እና ሞት ለመዳን ከፈለግን፣ ለዓብዩ ጌታ ትሑት አገልግሎትን ማቅረብ ግዳጃችን ነው። ሌላ ድርድር የለውም። ይህም ወሳኝ እና ለነፍስም አስፈላጊ የሆነ ሥርዓት ነው።