ማንትራ አስራ ስድስት
ፑሳን ኤካርሴ ያማ ሱርያ ፕራጃፓትያ
ቭዩሀ ራስሚን ሳሙሀ
ቴጆ ያት ቴ ሩፓም ካልያና ታማም
ታት ቴ ፓስያሚ ዮ ሳቭ አሶ ፑሩሳህ ሶ ሀም አስሚ
ፑሻን — የምንትከባከበን ጌታ ሆይ፣ ኤካ ርሴ — ቀዳማዊው ፈላስፋ፣ ያማ — ዋነኛው ተቆጣጣሪ፣ ሱርያ — የሱርያዎች (ታላላቅ አገልጋዮች) መድረሻ፣ ፕራጃፓትያ — ለፕራጃፓቲዎች ጥሩ የሚመኝ (የሰው ልጆች ዘር መነሻዎች)፣ ቭዩሀ — በቸርነትህ አስወግድልን፣ ራስሚን — ይህንን ጮራ፣ ሳሙሀ — በቸርነትህ አውርደው፣ ቴጃሀ — የሚያንጸባርቀውን፣ ያት — በዚህም፣ ቴ — ያንተን፣ ሩፓም — ቅርጽ፣ ካልያና ታማም — ታላቅ ተስፋ የሚሰጥ፣ ታት — ያንኛው፣ ቴ — የአንተ፣ ፓሽያሚ — ለማየት እችል ይሆናል፣ ያህ — አንድ ሰው እንዲህ ከሆነ፣ አሶ — እንደ ፀሐይ፣ አሶ — ያንኛው፣ ፑሩሻሀ — የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ፣ ሳህ — እኔ፣ አሀም — እኔ፣ አስሚ — በእኔ
ኦ ጌታዬ ሆይ፤ አንተ ቀዳማዊው የፍልስፍና ሁሉ ምንጭ ነህ። መላ ጠፈርን የምንትንከባከብ፣ የተፈጥሮ መመሪያዎች ሁሉ የበላይ ተቆጣጣሪ፣ የትሑት አገልጋዮችህ ሁሉ መድረሻ፣ ለሰው ልጆች ዘር ሁሉ በጐ የምትመኝ፣ ደስታ የተሞላበት አቅዋምህን በትክክል እንድመለከተው፣ እባክህ ይህንን መንፈሳዊ ጮራህን ገለል አድርግልኝ። እኔ ትሑት የፀሐይ ጌታ እንደመሆኔ፣ አንተ ደግሞ የዘለዓለማዊው መንፈሳዊው ዓለም እና የመላው ቁሳዊ ዓለም ዓብይ ጌታ ነህ፡፡
ፀሐይ እና የፀሐይ ጮራ የማይነጣጠሉ እና፣ በሙቀት እና በጮራ ዓይነታቸው የተመሳሰሉ ናቸው። እንደዚሁም ሁሉ፣ ዓብዩ ጌታ እና ሕያው ፍጥረታት ሁሉ፣ በዓይነታቸው የተመሳሰሉ ናቸው። ፀሐይ አንድ ብትሆንም እንኳን፣ በጮራዋ ውስጥ የሚገኙት ሞለኪዩሎች በመላው ህዋ ውስጥ በመሰራጨት፣ በቁጥር ሊተመኑ አይችሉም። የፀሐይ ጮራ የፀሐይ ከፊል ወገን ነው። የፀሐይ ሙቀት እና የፀሐይ ጮራ ፀሐይን ይወክላሉ። የቬዲክ መጻሕፍት እንደሚገልጹልን፣ በፀሐይ ውስጥ የፀሐይ ጌታ ይኖራል። እንደዚሁም ሁሉ በታላቁ የመንፈሳዊው ዓለም “ጎሎካ ቭርንዳቫን” ውስጥ፣ ዓብዩ ጌታ ዘለዓለማዊ እንቃስቃሴውን በደስታ እያሳለፈ ይገኛል። በብራህማ ሰሚታ እንደተረጋገጠልንም “ብራህማ ጅዮቲ” ተብሎ የሚታወቀው የመንፈሳዊው ዓለም ብርሃን የሚመነጨው፣ ከዚሁ “ከጎሎካ ቭርንዳቫን” ነው። (ብሰ፡ 5፡ 29)
ቺንታመኒ ፕራካራ ሳድማሱ ካልፓ ቭርክሻ
ላክሻ ቭርቴሹ ሱራብሂር አብሂፓላያንታም
ላክሽሚ ሳሃስራ ሳታ ሳምብህራማ ሴቭያማናም
ጎቪንዳም አዲ ፑሩሻም ትም አሀም ብሀጃሚ
“I worship Govinda, the primeval Lord, the first progenitor, who is tending the cows fulfilling all desires in abodes filled with spiritual gems and surrounded by millions of wish-fulfilling trees. He is always served with great reverence and affection by hundreds of thousands of Lakṣmīs, or goddesses of fortune.”
በብራህማ ሰሚታ ውስጥ እንደተገለጸው፣ “የብራህማ ጆይቲ” መንፈሳዊ ጮራ የሚመነጨው ከታላቁ መንፈሳዊ ዓለም ከጎሎካ ቭርንዳቫን ነው። ይህም የሚመሰለው ልክ የፀሐይ ጮራ ከፀሐይ እንደሚመነጭ ነው። አንድ ጻድቅ ነፍስ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ሆኖ ከዚህ ከሚያንፀባርቀው መንፈሳዊ ጮራ ባሻገር አልፎ ለመሄድ እስካልቻለ ድረስ፣ የዓብዩ ጌታን መንፈሳዊ ዓለም በትክክል ሊረዳ አይችልም።
በዓብዩ ጌታ ዓብይ ሰብአዊነት የማያምኑ መንፈሳውያን ወደዚህ ወደ “ብራህማ ጆይቲ” የሚያዘግሙ ሲሆኑ፣ በዚህም መንፈሳዊ ጮራ የተሰወሩ በመሆናቸው የዓብዩ ጌታን ትክክለኛው የመንፈሳዊ ዓለም መኖሪያንም ሆነ ትክክለኛ መንፈሳዊ መንፈሳዊ አካል ሊያውቁት አይችሉም። በዚህም በተወሰነ የመንፈሳዊ ብልጽግናቸው የዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽናን ደስተኛ እና መንፈሳዊ ቅርጹን ፈጽሞ ሊያውቁት አይችሉም። ስለዚህም በዚህ በሽሪ ኡፓኒሻድ ጥቅስ ውስጥ የተገለጸልን፣ ዓብዩ ጌታ ይህንን የብራህማ ጅዮቲ መንፈሳዊ ጮራ ገለል እንዲያደርግልን እና ትሑት እና ንጹሕ አገልጋዮቹ ሁሉ፣ መንፈሳዊ አካሉን ለማየት እንዲበቁ መማጸንን ነው።
ሰብአዊ ያልሆነውን የዓብዩ ጌታ “ብራህማ ጅዮቲን” በመረዳት፣ ብዙ ተስፋ የሚሰጡ ዕድሎችን እናገኛለን። በልባችን ውስጥ የሚገኘውን የጌታ መንፈስ ወይም “ፓራማትማን” በመረዳት ደግሞ፣ ዓብዩ ጌታ በመላው ጠፈር ውስጥ የተሰራጨ እንደሆነ በመረዳት ተጨማሪ ተስፋ የሚሰጥ የዓብዩ ጌታን ኅይል ለማወቅ እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ ወደ ዓብዩ ጌታ ፊት ለፊት ለመቅረብ የቻሉት ትሑት አገልጋዮች ደግሞ፣ ከሁሉም በላይ የሚሆን መንፈሳዊ ተስፋን ሊሰጡ የሚችሉ ገጽታዎቹን ለማየት ይበቃሉ። ዓብዩ ጌታ የፍልስፍና ሁሉ መነሻ እና ምንጭ በመሆኑ እና የመላው ጠፈር ተንከባካቢ እና በጎ የሚመኝም እንደመሆኑ፣ ሰብአዊ ገጽታ የሌለው ሆኖ ሊገኝ አይችልም። የሽሪ ኡፓኒሻድም ድምደማ ይህ ነው። “ፑሳን” ወይም “ተንከባካቢ” የሚለው ቃል ትልቅ ትርጉም አለው። ምንም እንኳን ዓብዩ ጌታ መላ ጠፈርን የሚንከባከብ ቢሆንም፣ ትሑት አገልጋዮቹን ደግሞ በተለየ መንገድ እየተንከባከባቸው ይገኛል። ይህንን ሰብአዊ ያልሆነውን “ብራህማ ጆይቲን” በመሻገር እና የዓብዩ ጌታን አስደሳች እና ዘለዓለማዊ አካሉን በማየት፣ ትሑት አገልጋዮቹ የዓብዩ ጌታን መላ ፍጹምነት መረዳት ይችላሉ።
ይህንንም በሚመለከት “በብሀገቨት ሳንዳርብሀ” ውስጥ ሽሪላ ጂቫ ጎስዋሚ እንዲህ በማለት ገልጾልናል። “ፍጹም እውነትን በትክክል ለመረዳት የምንችለው፣ የዓብዩ ጌታን መንፈሳዊ እና ሰብአዊ አካል እና አቋም በቀጥታ ለመረዳት በቻልንበት ወቅት ነው። ዓብይ እንደመሆኑም መላ መንፈሳዊ ኃይላትን ሁሉ በተሟላ መንገድ በማስተዳደር ላይ ነው። ይህንን የተሟላውን የመንፈሳዊ ኃይሉን “ብራህማ ጆይቲን” በመረዳት ብቻ ልንገነዘበው አንችልም።” ስለዚህ “ብራህማን” ተብሎ የሚታወቀውን የመጀመሪያ ደረጃ መንፈሳዊ ዕውቀትን በመያዝ ብቻ፣ ለመረዳት የምንችለው የዓብዩ ጌታን ከፊል ኅይል ብቻ ነው። “ብሀጋቫን” ከሚባለው ቃል ውስጥ የመጀመሪያው “ብሀ” የሚለው ቃል ሁለት ትርጉም አለው። ይህም በመጀመሪያ ደረጃ “ተንከባካቢ” የሚል ትርጉም ሲኖረው፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ “ጠለላ የሚሰጥ” የሚል ትርጉም ይዞ ይገኛል። ሁለተኛው “ጋ” የሚለው ቃል ደግሞ “መሪ” ወይም “ፈጣሪ” የሚል ትርጉም አለው። “ቫን” የሚለው ቃል፣ እያንዳንዱ ሕያው ፍጥረታት በእርሱ ውስጥ እንደሚኖሩ እና፣ እርሱም በእነሱ ውስጥ እንደሚኖር ነው። ስለዚህ ይህ “ብሀጋቫን” የሚለው መንፈሳዊ ቃል የሚያመለክተው፣ ዓብዩ ጌታ ፍጹም ዕውቀት፣ ፍጹም ኅይል እና፣ ፍጹም ሀብት ያለው ሲሆን፣ መንፈሳዊ ሕሊናውም በቁሳዊ ዓለም አስተሳሰብ ፈጽሞ ያልተበረዘ ነው።
ዓብዩ ጌታ ያልደፈረሰ ንጹሕ መንፈስ ያላቸውን ትሑት አገልጋዮቹን በተለየ መንገድ ይንከባከባቸዋል። በትሑት አገልጋይነትም ብቁ እንዲሆኑ የሚያስፈልጋቸውን መመሪያ ሁሉ ያቀርብላቸዋል። የትሑት አገልጋዮቹ መሪ እንደመሆኑም፣ ለሚያቀርቡት የፍቅር አግልግሎት በረከቱን በመስጠት፣ ምኞታቸውን ሁሉ ያሳካላቸዋል። ከጊዜም በኋላ ትሑት አገልጋዮቹ፣ ከዓብዩ ጌታ ጋር ዓይን ለዓየን ለመገናኘት ይበቃሉ። ይህ ዕድል የሚሰጣቸው በረከት በተሞላበት በመንፈሳዊ ልቦናው ፈቃደኝነት ነው። ይህንን በመሰለ መንገድ ዓብዩ ጌታ ትሑት አገልጋዮቹ ሁሉ ወደ ከፍተኛው የመንግሥተ-ሰማያት መኖሪያው “ጎሎካ ቭርንዳቫና” እንዲሄዱ ዕድል ይሰጣቸዋል። ፈጣሪ እንደመሆኑም ለትሑት አገልጋዮቹ ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን ብቃት በመስጠት፣ ወደ እርሱ እንዲመለሱለት የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ ሁሉ ያቀርብላቸዋል። ዓብዩ ጌታ የፈጣሪዎች ሁሉ ዓብይ ፈጣሪ ነው። ቀዳማዊ ፈጣሪ እንደመሆኑም፣ እርሱን የሚፈጥር ምንም ኅይል የለም። በተጨማሪም የራሱን ከፊል ውስጣዊ ኅይል በመፍጠር፣ ከራሱ ከፊል ወገኖች ጋር ጊዜውን ሁሉ በደስታ ያሳልፋል። ቁሳዊው ዓለም በቀጥታ የተፈጠረው በእርሱ ሳይሆን “ፑሩሻ” ተብሎ በሚታወቀው በከፊል ወገኑ ሲሆን፣ በዚህም ከፊል ወገኑ ይህንን ቁሳዊ ዓለም በተደጋጋሚ ሲፈጥር እና ሲንከባከብ ይገኛል። ከጊዜም በኋላም፣ መላ የቁሳዊ ዓለም ፍጥረትን ይደመስሳል። መላው ሕያው ፍጥረታት ሁሉ የተነጠሉ የዓብዩ ጌታ ከፊል ወገኖቹ ናቸው። ይሁን እንጂ ከእነዚህም መሀከል የተወሰኑት ሕያው ፍጥረታት (ነፍስ) እንደ ፈጣሪ ጌታ ለመሆን በነበራቸው የቅናት መንፈስ እና የግል ስሜቶቻቸን ለማርካት በነበራቸው ምኞት፣ ዓብዩ ጌታ ወደ እዚህ ጊዜያዊ ቁሳዊ ዓለም በመምጣት ስሜታቸውን ለማርካት እንዲታገሉ እና በሐሰታዊ ልቦና ተሞልተው እንደ ጌታ ለመሆን እንዲታገሉ፣ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በተፈጥሮ አሟልቶላቸው ይገኛል።
የዓብዩ ጌታ ከፊል ወገኖች የሆኑት ሕያው ፍጥረታት ሁሉ፣ በመላው የቁሳዊው ዓለም በመሰራጨታቸው፣ መላው ዓለም በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ለእነዚህ ሕያው ፍጥረታትም ጌታ የመሆን ምኞታቸው በቁሳዊው ዓለም ውስጥ እንዲሳካላቸው፣ ዓብዩ ጌታ የሚያስፈልጋቸውን አሟልቶላቸው ይገኛል። ዳሩ ግን ዓብዩ ጌታ ምን ጊዜም ቢሆን የበላይ ተቆጣጣሪ እና ዓብዩ ጌታ በመሆን ለዘለዓለም ይኖራል። በቁሳዊ ዓለም ውስጥ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ የሚገኘውም የራሱ ከፊል ወገን “ፓራም አትማ” ተብሎ የሚታወቅ ዓብይ ጌታ ሲሆን፣ ከሦስቱ “ፑሩሻዎች” አንዱ ነው።
በሕያው ፍጥረታት “አትማ” ወይም ነፍስ እና በዓብዩ ጌታ (ፓራም አትማ) መሀከል በጣም ትልቅ ልዩነት ይገኛል። ፓራም አትማ ዓብዩ ተቆጣጣሪ ሲሆን፣ አትማ ወይም ነፍስ ደግሞ በቁጥጥር ሥር ያለች ናት። ስለዚህ ሁለቱም በተለያዩ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። በልባችን ውስጥ የሚገኘው ፓራም አትማ ወይም ዓብዩ ጌታ፣ ነፍስን ሁሌ በመደገፍ እና በመምራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ከነፍስ ወይም ከሕያው ፍጥረታት ፈጽሞ የማይለይ አጋራቸው ነው።
በመንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ተስፋፍቶ የሚገኘው “ብራህማን” ተብሎ የሚታወቀውን የዓብዩ ጌታ ከፊል አካል የብርሃን ጮራ በማናቸውም ጊዜ ለመደምሰስ አይቻልም። ይህም ክስተት ሕያው ፍጥረታት በዚህ ህዋ ውስጥ ንቁ ሆነው በተከሰቱበትም እና ባልተከሰቱበትም ጊዜ ሆነ ቁሳዊ ዓለም በሚደመሰስበት ጊዜ “ብራህማን” ሳይደመሰስ ለዘለዓለም የሚኖር ነው። በተጨማሪም “ጂቫ ሻክቲ” ወይም ሕያው ፍጥረታት በቁሳዊ ዓለም ትስስር ውስጥም እያሉም ሆነ በጻድቅነት ደረጃ እያሉ “ብራህማን” ፈጽሞ አይደመሰስም። ዓብዩ ጌታ የብራህማን እና የፓራም አትማ ምንጭ እንደመሆኑም ሁሉ፣ የሕያው ፍጥረታት እና የቁሳዊ ዓለምም ሁሉ መነሻ እና ምንጭ እርሱ ራሱ ሆኖ ይገኛል። ይህንን ፍጹም የሆነ መንፈሳዊ ዕውቀት የተረዱ ሁሉ፣ በዓብዩ ጌታ ትሑት አገልግሎት ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። እነዚህም ንጹሕ እና በመንፈሳዊ ዕውቀታቸው የዳበሩ ትሑት አገልጋዮች ሁሉ፣ ከዓብዩ ጌታ ጋር ከልብ ቅርበት ያላቸው ናቸው። ከሌሎች ትሑት አገልጋዮችም ጋር ሲገናኙም ሁሌ ዓብዩ ጌታን ሲያወድሱ እና ስለ መንፈሳዊ ታሪኮቹ ሲወያዩ ይገኛሉ። ነገር ግን ልክ እንደ ትሑት አገልጋዮቹ የተሟላ መንፈሳዊ ዕውቀት የሌላቸው እና የብራህማን እና የፓራማትማ ዕውቀት ብቻ ያላቸው ሁሉ፣ የትሑት አገልጋዮችን መንፈስ እና አገልግሎት ሲያወድሱ አይታዩም። ዓብዩ ጌታ ትሑት አገልጋዮቹ ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ዕውቀት እንዲቀስሙ መንገዱን ያሳያቸዋል። ይህንንም ዓይነት በረከት በማቅረብም ያላቸው ድንቁርና ሁሉ ከሕሊናቸው እንዲጠፋ ያደርገዋል። ግምታዊ መንፈስ ያላቸው ፈላስፋዎቹ እና የዳበረ መንፈሳዊ እውቅና የሌላቸው ዮጊዎች ግን፣ ይህንን ዓይነት በረከት ከዓብዩ ጌታ አያገኙም። ምክንያቱም በራሳቸው ጥረት በመተማመን፣ ዓብዩ ጌታን ለመረዳት በትግል ላይ ስለሚገኙ ነው። “በካትሀ ኡፓኒሻድ” (ካኡ፡ 1:2:23) ውስጥም እንደተገለጸው ዓብዩ ጌታ ሊገለጽልን የሚችለው፣ በትሑት አገልግሎታችን የምናወድሰው ከሆነ ብቻ ነው። ስለዚህ ሽሪ ኡፓኒሻድ የሚያስተምረን የዓብዩ ጌታን በረከት እና ለጋስነት እንድናገኝ ነው። ይህም ሊገኝ የሚቻለው፣የብራህማ ጅዮቲን መለስተኛ መንፈሳዊ ዕውቀትን ተሻግረን፣ ዓብዩ ጌታን በትክክል ለመረዳት ስንበቃ ነው።