No edit permissions for Amharic

ማንትራ ሦስት

አሱራ ናማ ቴ ሎካ
አንድሄና ታማሳቭርታህ
ታምስ ቴ ፕሪትያብሂ ጋቻንቲ
ዬ ኬ ቻትማ ሃኖ ጃናሀ

አሱርያህ — ለሰይጣናት የሚሆን፣ ናማ — ስሙ ዝና ያለው፣ —እነዚያ፣ ሎካህ — ፕላኔቶች፣ አንድሄና — በድንቁርና፣ ታማሳ — በጭለማ፣ ዓቭርታህ — የተሸፈነ፣ ታን — እነዚያ ፕላኔቶች፣ ቴ — እነርሱ፣ ፕሬትያ — ከሞት በኋላ፣ አብሂጋቻንቲ — ወደ ውስጥ መግባት፣ ዬ — ማናቸውም ሰው፣ ኬ — ሁሉም፣ ቻ — እና፣ አትማ — ሀናህ — ነፍሰ ገዳይ፣ ጃናህ — ሰዎች

ይህንን ብርቅ የሆነውን የመንፈሳዊ አገልግሎት የመስጠት ዕድላቸውን የሚያባክኑ እና የከሀዲያን መንፈስ ያላቸው ሰዎች ሁሉ፤ ልክ እንደ ነፍስ አጥፊዎች የሚቆጠሩ ሲሆን፤ ከሞትም በኋላ እምነት ወደሚጎድልባቸው ዓለማዊ ፕላኔቶች ያመራሉ፡፡ እነዚህም ፕላኔቶች የመንፈሳዊነት ድንቁርና፣ ጨለማነት እና ስቃይ የተሞላባቸው ናቸው፡፡

የሰው ሕይወት ከእንስሳ ሕይወት ተለይቶ የሚታየው፣ የሰው ልጅ መንፈሳዊ ሕይወቱ ግብ እንዲመታ የከበደ ኃላፊነት ስለተሰጠው ነው፡፡ ይህንንም ከባድ ኃላፊነት ተረድተው መንፈሳቸውን በዚህ ኃላፊነት የመሰጡ ሁሉ “ሱራ” ወይም መለኮታዊ ይባላሉ፡፡ ይህንን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት ፈቃደኛ ያልሆኑ እና ስለዚህም ኃላፊነት ምንም ዓይነት ዕውቀት የሌላቸው “አሱራ” ወይም መለኮታዊ ያልሆኑ እና ሰይጣናት ይባላሉ፡፡ በመላ ትዕይንተ ዓለም ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ሁሉ፣ ከእነዚህ ዓይነት ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ “በርግ ቬዳ” ውስጥ እንደተገለጸው “ሱራ” ወይም መለኮታዊ የሆኑ ሁሉ፣ ዓላማቸው ወደ ቪሽኑ ወይም ወደ ዓብዩ ጌታ የፍቅር አገልግሎት ያተኮረ ሲሆን፣ ሥራቸው እና እንቅስቃሴያቸውም የሚካሄደው ከዚያው አንጻር ነው። በዚህም ምክንያት የሚጓዙበት መንገድ ሁሉ፣ ልክ እንደ ፀሐይ ነጸብራቅ ብርሃን የተሞላበት ይሆናል፡፡

በአእምሮው የዳበረ ዐዋቂ ሰው ሁሉ ማስታወስ የሚገባው ነገር ቢኖር፤ ነፍስ የሰው ልጅን የትውልድ ዕድል ለማግኘት የምትችለው፣ ከብዙ ሚሊዮን በላይ የሚቆጠር ተደጋጋሚ ሞት እና ትውልድ አሳልፋ ነው፡፡ ይህም መላ ቁሳዊው ዓለም አንዳንድ ጊዜ እንደ ውቅያኖስ ይመሰላል፡፡ የሰው ልጅ ትውልድ ደግሞ፣ ልክ ውቅያኖስን ለማሻገር እንደተሠራ መርከብ ይመሰላል፡፡ የቬዲክ ዕውቀት፣ አቻርያዎች ወይም መንፈሳዊ መምህራን ደግሞ፣ ልክ እንደ መርከቡ መሪ ባለሙያዎች እና አመቺ ንብረቶች ይመሰላሉ፡፡ የሰው ልጅ ገላ አካላት ደግሞ መርከቡን ወደ መድረሻው ለማድረስ እንደሚረዱት ንፋስ ይቆጠራሉ፡፡ የሰው ልጅ ይህንን ሁሉ ንብረት ይዞ፣ በአግባቡ ለመንፈሳዊ ንቃቱ የማይጠቀምበት ከሆነ እንደ “አትማሀ” ወይም እንደ ነፍሰ ገዳይ ይቆጠራል፡፡ ሽሪ ኢሾፓኒሻድ በግልጽ እንደሚያስተምረንም፣ እንዲህ ዓይነቶቹ የነፍስ አጥፊዎች፣ ጨለማ እና ድንቁርና ወደተሞላበት ስፍራ በተደጋጋሚ በመሄድ ለስቃይ ይጋለጣሉ፡፡

የአሳማዎች፣ የውሾች፣ የግመሎች እና የአህዮች የቀን መኖ ልክ እንደኛው የቀን እንጀራ አስፈላጊ ነው፡፡ ቢሆንም ግን እንደምናየው የእንስሳቱ የቀን መኖ የሚቀርብላቸው ጭንቀት በተሞላበት እና ብዙውን ጊዜ ደስ በማያሰኝ መንገድ ነው፡፡ ለሰው ልጅ ግን፣ በተፈጥሮ አማካኝነት፣ እነዚህ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ሀብቶች አመቺ በሆነ መንገድ ቀርበውለታል፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ ሕይወት፣ ከእንስሳ ሕይወት ጋር ሲወዳደር፣ በጣም አስፈላጊ እና ከፍተኛ ዋጋ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ከአሳማ እና ከሌሎች እንስሳትስ የበለጠ ሕይወት፤ ለሰው ልጅ በተፈጥሮ ለምን ተሰጠ? ይህንን በመሰለ መንገድስ፣ ለመንግሥት ድርጅት የሚሠራ ሰው፣ ከተራ የካምፓኒ ሠራተኛ በላይ ለምን የተሻለ ማዕረግ ተሰጠው? ለዚህም ምክንያቱ ለመንግሥት የተመደበ ሠራተኛ የተሰጠው ኃላፊነት የበላይነት ስላለው ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የሰው ልጅ የሚጠበቅበት ኃላፊነት ከእንስሳት ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ ማዕረግን የያዘ በመሆኑ ነው፡፡ እንስሳት ያላቸው ኃላፊነት የጐደለባቸውን ሆድ መሙላት ብቻ ነው፡፡ ይህንንም በመሰለ መንገድ የዘመኑ ሥልጣኔያችን ይህን የመሰለው የጐደለ ሆድ የመሙላት ችግራችን እየጨመረ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡ በተሞሸረ መንገድ የቀረበውን ዘመናዊ ሰው ሲቀርቡት እና፣ ስለ መንፈሳዊ ንቃቱ ፍላጐት እንዲያድርበት ቢጠይቁት፣ ሆዱን ለመሙላት ብቻ መሥራት እንደሚፈልግ እና ራስን የማወቅ ጥናት ለተራበ ሰው እንደማያስፈልገው አድርጎ ይናገራል፡፡ ቢሆንም ግን የተፈጥሮ ሕግጋት በጨከነ መንገድ የሚሠሩ ስለሆኑ ምንም እንኳን ራስን የማወቅ ጥናቱን ትቶ ሆዱን ብቻ ለመሙላት የሚታገል ቢሆንም፣ በሥራ ፈትነት ጭንቀት ላይም የሚሰቃይበት መንገድ በተፈጥሮ ይከሰታል፡፡

ይህ የሰው ልጅ ሕይወት የተሰጠን ልክ እንደ እንስሳት ወይም እንደ አህዮች፣ አሳማዎች እና እንደ ውሾች የትግል ኑሮ ለመኖር አይደለም፡፡ የተሰጠን ግን፣ የመንፈሳዊ ሕይወትን ዓላማ ግብ ለማድረስ እንድንጠቀምበት ነው፡፡ ራስን የማወቅ ጥናታችን ላይ ለመሰማራት ጉጉት የሌለን ከሆንም ተፈጥሮ በከባድ ሥራ ላይ እንድንሰማራ ታስገድደናለች፡፡ በአሁኑ ዘመን የሰው ልጆች ልክ እንደ አህዮች እና ጋሪ እንደሚጎትቱ እንስሳት ከባድ ሥራ እንዲሠሩ ተገደው ይታያሉ፡፡ መለኮታዊ ያልሆኑ “አሱራዎች” ወዴት ዓይነት ስፍራ ሂደው በምን ዓይነት ሥራ ላይ እንደሚሰማሩም በሽሪ ኡፓኒሻድ ውስጥ በዚሁ ጥቅስ ላይ ተገልጿል፡፡ የሰው ልጅ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሳይወጣ የቀረ ከሆነ፣ “አሱራዎች” ወደሚኖሩበት ፕላኔቶች ሊሸጋገር ወይም ወደ ዝቅተኛ የፍጥረታት ሕይወት፣ በረከሰ መንገድ እንዲሸጋገር ይገደዳል፡፡ በዚህም ሕይወቱ ጨለማ እና ድንቁርና የተሞላበት ዓይነት ኑሮ ውስጥ ለመኖር ይገደዳል፡፡

በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ እንደተገለጸው (ብጊ 6፡ 41-43) ምንም እንኳን የሰው ልጅ ወደ ራስን የማወቅ መንፈሳዊ ጥናቱ ቢያተኩርም ሥርዓቱ በተሟላ መንገድ የመንፈሳዊ ንቃቱን ያልጨረሰ ከሆነ፣ በመጪው ትውልዱ በ“ሱቺ” ወይም “ሽሪማት” ወይም ንጹሕ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ይወለዳል፡፡ ይህም በተፈጥሮ የሚዘጋጅለት የጀመረውን መንፈሳዊ ሥርዓት እንዲጨርስ ዕድል ለመስጠት ነው፡፡ “ሱቺ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው፣ በመንፈሳዊነት የበለጸገ “ብራህማና” ወይም ቄስ ማለት ነው፡፡ “ሽሪማት” ማለት ደግሞ፣ “ቫይሻ” ወይም የንግድ ወይም የአርሶ አደር ቤተሰብ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ራስን የማወቅ ጥናቱ፣ በዚህ ሕይወት ያልተሳካለት ሁሉ፣ በሚቀጥለው ሕይወቱ ውስጥ እንዲቀጥልበት የተሻለ ትውልድ ይኖረዋል፡፡ ይህም በቀድሞ ሕይወቱ በትሑትነት የመንፈሳዊ ንቃቱን ሞክሮ ስላልተሳካለት ነው፡፡ ራስን የማወቅ መንፈሳዊ ጥናቱ ያልተሳካለት እና የወደቀ ፍጡር የተከበረ እና የበለጸገ ቤተሰብ ውስጥ ለመወለድ ዕድል የሚያገኝ ከሆነ፣ መንፈሳዊ ጥናቱ የተሳካለት አገልጋይ ምን ዓይነት ጥሩ ዕድል እንደሚገጥመው ለመገመት አያዳግትም፡፡ ዓብዩ ጌታን ለመረዳት ብቻ እንኳን ጥረት በማድረግ አንድ ሰው በንጉሳዊ ወይም ሀብት በሞላበት ቤተሰብ ውስጥ ለመወለድ ይበቃል፡፡ ነገር ግን ይህንን ዓይነት ጥረት ፈጽሞ የማያደርጉት፣ በሐሰታዊ ራእይ የተታለሉ፣ በዓለማዊ ሕይወት የተመሰጡ እና በዓለማዊ ስሜታዊ ደስታ ላይ ብቻ የሚያተኩሩት ሁሉ፣ ጨለማ እና ድንቁርና ወደተሞላበት የሲኦል ፕላኔቶች ያመራሉ፡፡ ይህም በመላ የቬዲክ ሥነጽሑፎች ሁሉ ተገልጿል። ይህንንም የመሰሉት “አሱራዎች” አንዳንድ ጊዜ እንደሃይማኖታውያን ተመስለውም ይቀርባሉ፡፡ ቢሆንም ግን ያላቸው ዓላማ ሁሉ፣ ዓለማዊ ፍላጎታቸውን ለሟሟላት ብቻ ነው፡፡ በብሀገቨድ ጊታም (ብጊ 16፡17-18) ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሰዎች “አትማ ሳምብሀቪታ” ተብለው ተሰይመዋል፡፡ ይህም ማለት ኅያልነታቸው የሚታወቀው በማታለል ሲሆን፣ በዚህ ማዕረግ ላይ የሰፈሩትም ድንቁርና በተሞላባቸው ሰዎች ጥቆማ እና ባከማቹት በራሳቸው ቁሳዊ ሀብት ምክንያት ብቻ ነው፡፡ እነዚህ አሱራዎች ራስን የማወቅ ጥናት ላይ ያልተሰማሩ፣ ስለ “ኢሳቫሽያ” ዕውቀት የሌላቸው፣ ዓብዩ ጌታ የመላ ትዕይንተ ዓለም ባለቤት መሆኑን ያልተረዱ ሲሆን፣ ከሞት በኋላም፣ ድንቁርና ወደተሞላበትም ስፍራ እንደሚሄዱ የታወቀ ነው፡፡

ይህንንም ትምህርት ለማጠቃለል የሰው ልጅ ሕይወት የተሰጠን፣ ሀብትን ለማከማቸት በመፍጨርጨር እና ያለንን ዓለማዊ ችግር ብቻ ባልተረጋጋ መንገድ ለመፍታት አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ሕይወት ዓላማ ግን፣ በዚህ በቁሳዊ ዓለም ውስጥ በሥጋዊ ገላ ተጠምደን የምንታገልበትን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ነው፡፡ ይህም ለሰው ልጅ ሕይወት የተሰጠን ዕድል፤ በሂደቱ የተፈጥሮ ሕግጋትን ተከትሎ፣ ቀድሞ ካደረግናቸው ጥሩ ወይም መጥፎ እንቅስቃሴዎች አኳያ ነው።

« Previous Next »