ማንትራ ሰባት
ያስሚን ሳርቫኒ ብሁታኒ
አትማይቫብሁድ ቪጃናታህ
ታትራ ኮ ሞሃህ ካህ ሶካ
ኤካትቫም አኑፓስያታህ
ያስሚን — በዚህ ሁኔታ ላይ፣ ሳርቫኒ — ሁሉም፣ ብሁታኒ — ሕያው ፍጥረታት፣ አትማ — የቺት ካና — ወይም የመንፈሳዊ ቅንጣቢዎች፣ ኤቫ — ብቻ፣ አብሁት — እንዲህ የሚኖር፣ ቪጃናትሀ — የሚያውቅ ሰው፣ ታትራ — በዚያም፣ ካህ — ምን፣ ሞሃህ — የሐሰት ራዕይ፣ ካህ — ምን፣ ሶካህ — ጭንቀት፣ ኤካትቫም — በዓይነት አንድ የሆነ፣ አኑፓስያታሀ — ሥልጣን ባለው አገላለጽ የሚያይ ወይም ሁልጊዜ በዚህ መንገድ ብቻ የሚያይ፡፡
ሕያው ፍጥረታት ሁሉ የዓብዩ ጌታ ከፊል ቅንጣቢ ሆነው፣ ከዓብዩ ጌታ ጋርም በዓይነታቸው የተመሳሰሉ መሆናቸውን በትክክል የተረዳ ሰው፣ በእውነቱ ዕውቀት ያለው ሰው ነው፡፡ ይህንንስ ዕውቀት ይዞ ምን ዓይነት ጭንቀት ወይም ሐሰታዊ ራእይ ላይ ሊወድቅ ይችላል?
ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው፣ “ከማድህያም አዲካሪ” እና “ከኡተማ አዲካሪ” በስተቀር፣ ማንም ሰው ቢሆን ትክክለኛውን የሕያው ፍጥረትን መንፈሳዊ ደረጃ የተረዳ አይደለም፡፡ ሕያው ፍጥረታት ከዓብዩ ጌታ ጋር በዓይነታቸው የተመሳሰሉ ናቸው፡፡ ይህም ልክ እንደ እሳት ክፋይ ወይም ቅንጣቢዎች ይመሰላል፡፡ እነዚህም የእሳት ቅንጣቢዎች በብርሃን እና በሙቀት ዓይነታቸው ከእሳቱ ጋር የተመሳሰለ ቢሆኑም እሳቱ ራሱ ግን አይደሉም፡፡ ምክንያቱም በውስጣቸው የሚገኘው የብርሃን እና የሙቀት ኅይል፣ ከእሳቱ ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር የማይችል ስለሆነ ነው፡፡ “መሀ ብሀገቫት” ተብሎ የሚታወቀው የዓብዩ ጌታ ትሁት እና ታላቅ አገልጋይ፤ ሁሉንም ሕያው ፍጥረታት በአንድ ደረጃ ላይ ማየት የሚችለው፤ ለሚያየው ነገር ሁሉ በውስጡ የዓብዩ ጌታ ኅይል መኖሩን በትክክል ስለሚረዳ ነው፡፡ በኅይል አመንጪው እና በኃይሉ መሀከል ብዙም ልዩነት ስለሌለ፣ በሁለቱም መሀከል ያለውን አንድነት ለመረዳት አያዳግትም፡፡ በዝርዝር ስናየው፣ ምንም እንኳን ሙቀት እና ብርሃን ከእሳት የተለዩ መሆናቸውን የምንረዳ ብንሆንም፣ እሳት ያለ ብርሃን እና ሙቀት ምንም ትርጉም ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለዚህ ሦስቱም እሳት፣ ብርሃን እና ሙቀት አንድነት ያላቸው እና ተነጣጥለው የማይታዩ ናቸው፡፡
በዚህ ማንትራ ወይም ጥቅስ ላይ እንደተገለጸው “ኤካትቫም አኑፓሽያታሀ” የሚለው ቃል የሚያሳየን፣ አንድ ሰው መላ ሕያው ፍጥረታትን ማየት የሚገባው፣ ከቬዲክ ሥነጽሑፎች ዕውቀት አኳያ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከታላቁ እና ምሉእ ከሆነው ዓብይ ጌታ በከፊል የተፈጠሩት እያንዳንዱ ሕያው ፍጥረታት፣ ከዓብዩ ጌታ ጋር እስከ ስምንት በመቶ የሚሆን በዓይነት ተመሳሳይነት እንዳላቸው በቬዳዎች ተገልጿል። ቢሆንም ግን፣ ዓይነቶቹ ከዓብዩ ጌታ ጋር በመጠን ሊወዳደሩ አይችሉም፡፡ እነዚህ ተመሳሳይ ዓይነቶች፣ ረቂቅ በሆነ መጠን በሕያው ፍጥረታት ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ የዚህ ምክንያትም፣ ሕያው ፍጥረታት ሁሉ ረቂቅ የሆኑ የዓብዩ ጌታ የከፊል ወገን በመሆናቸው ነው፡፡ ሌላ ምሳሌ ለመስጠትም፣ ጨውን እንመልከት፡፡ በአንድ የውቅያኖስ ውሀ ጠብታ ውስጥ የሚገኘው የጨው መጠን፣ በውቅያኖሱ ውስጥ ከሚገኘው የጨው መጠን ጋር፣ ፈጽሞ ሊወዳደር አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ በኬሚካል ዝርዝር ጥናት ብናየው፣ በጠብታው ውስጥ የሚገኘው ጨው፣ በዓይነቱ ውቅያኖስ ውስጥ ከሚገኘው ጨው ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡ ስለሆነም ሕያው ፍጥረታት ከዓብዩ ጌታ ጋር በዓይነትም ሆነ በመጠን እኩል ቢሆኑማ፣ በተፈጥሮ ወይም በቁሳዊ ዓለም ሕግጋት ቁጥጥር ሥር ሊሆኑ አይችሉም ነበር፡፡ ቀደም ብሎ በተገለጹት ጥቅሶችም ውስጥ እንደቀረበው፣ ማናቸውም ሕያው ፍጥረታት ሆኑ መላእክትንም ጭምር፣ የዓብዩ ጌታን ዓይነት እና መጠን ሊያልፉም ሆነ ሊወዳዳደሩም አይችሉም፡፡ ስለዚህ ይህ ”ኤካትቫም“ የሚለው ቃል፣ ማለት ሕያው ፍጥረታት ሁሉ ከዓብዩ ጌታ ጋር እኩል ናቸው ማለት አይደለም፡፡ የሚያሳየን ግን፣ ተመሳሳይነት እንዳላቸው ብቻ ነው፡፡ ይህም የሚመሰለው፣ ልክ የአንድ ቤተሰብ ፍላጎት አንድ እንደመሆኑ፣ ወይም የአንድ ብሔር ፍላጎት አንድ እንደመሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት ደግሞ ምንም እንኳን በውስጣቸው የተለያዩ የቤተሰብ ወይም የብሔር አባላት ቢኖሩም እንጂ ማለት ነው፡፡ ሕያው ፍጥረታትም፣ የዓብዩ ጌታ ቤተሰብ እንደመሆናቸው፣ ያላቸው የመደሰት ፍላጐት እና ዓብዩ ጌታ ያለው ፍላጐት አንድ ነው፡፡ ከቬዲክ ሥነጽሑፎች እንደምንማረው እያንዳንዳቸው ሕያው ፍጥረታት የዓብዩ ጌታ አገልጋዮች ናቸው፡፡ በብሀገቨድ ጊታም እንደተገለጸው (ብጊ 7፡5-6) በመላ ትዕይንተ ዓለም ውስጥ የሚገኙት እያንዳንዳቸው ሕያው ፍጥረታት፣ ከዓብዩ ጌታ የማዕከላዊ ኃይሉ የመነጩ ናቸው፡፡ እነዚህም ሕያው ፍጥረታት አዕዋፋትን፣ በደረታቸው የሚጓዙ ፍጥረታትን፣ ጉንዳኖችን፣ የውሀ ፍጥረታትን፣ ዛፎችን ወዘተ ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ፍጥረታት፣ በዓብዩ ጌታ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ በመሀከላቸውም የፍላጐት ግጭት አይኖርም፡፡
የእነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት ፍላጐትም መደሰት ነው፡፡ ይህም በቬዳንታ ሱትራ (ቬሱ 1፡1፡12) ውስጥ ተገልጿል፡፡ “አናንዳ ማያ ብህያሳት” በተፈጥሮ አማካኝነት እያንዳንዱ ሕያው ፍጥረት እና ዓብዩ ጌታ ዘለዓለማዊ ደስታን ለማግኘት ፍላጎት ያላቸው ናቸው፡፡ በዚህ በቁሳዊው ዓለም ውስጥ ተጠምደው የሚገኙት ሕያው ፍጥረታት ሁሉ፣ ደስታን ለማግኘት ሁልጊዜ የሚጥሩ ናቸው፡፡ ዳሩ ግን ደስታን ለማግኘት የሚጥሩበት መንገድ የተሳሳተ ነው። ፍጹም ደስታን ለማግኘት ከዚህ ከዓለማዊ ኑሮ የተለየ መንፈሳዊ ኑሮ መኖሩን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ በዚህ በመንፈሳዊው ዓለምም ዓብዩ ጌታ በቁጥር ሊተመኑ ከማይችሉ ትሑት እና አፍቃሪ አገልጋዮቹ ጋር፣ በፍጹም ደስታ ውስጥ በመኖር ላይ ነው። በዚህ መንፈሳዊ ስፍራ ላይ ምንም ዓይነት ዓለማዊ መንፈስ አይገኝም፡፡ ስለዚህ ይህ ደረጃ “ኒርጉና” በመባል ይታወቃል፡፡ በኒርጉና ደረጃ ላይ እያለን፣ ደስታ ሊሰጠው ከሚችለው ከዓብዩ ጌታ ፍላጎት ውጪ፣ ምንም ዓይነት የተለያየ ወይም የተቃረነ ፍላጎት አይኖረንም፡፡ በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ግን፣ ደስታ ሊሰጠው የሚገባው አካል (ዓብዩ ጌታ) በመሀከላችን ስለሌለ፣ እርስ በእርሳችን መሀል ብዙ ግጭት ሲፈጠር ይታያል፡፡ የደስታ ሁሉ ማእከል ዓብዩ ጌታ ነው፡፡ እርሱም ልብ በሚማርከው “ራሳ ዳንስ” ተብሎ በሚታወቀው በአገልጋዮቹ መሀከል የሚገኘው ዓብዩ ጌታ ነው፡፡ እኛም ከዓብዩ ጌታ ጋር በመሆን ያለ ምንም ቅራኔ ከእርሱ ጋር በደስታ መኖር የሚገባን ነን። የመንፈሳዊ ፍላጎቶች ሁሉ ታላቁ ደረጃ ይኸው ነው፡፡ አንድ ሰው ይህንን ያልተቃረነ አንድነት ካገኘ፣ ሐሰታዊ ራእይ ወይም “ሞሀ” እና ትካዜ “ሶካ” የሚባሉት ሁሉ ይጠፋሉ፡፡
ዓብዩ አምላክ በመሀሉ የሌለበት ሥልጣኔ ሁሉ፣ በሐሰታዊ ራእይ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሥልጣኔ መጨረሻው ረብሻ እና ትካዜ ነው፡፡ በአሁኑ ዘመን በሚገኙ ፖለቲከኞች የተፈጠረው ሥልጣኔ ሁሉ፣ በሥጋት የተሞላ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ በማናቸውም ጊዜ የፖለቲካ ይዘታቸው ሊቀያየር እና ሊፈርስ ስለሚችል ነው፡፡ ይህም የዓለማዊ ክስተቶች ጊዜያዊነት የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡ በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ እንደተገለጸው፣ የተወሳሰበውን የተፈጥሮን ሕግጋት በቀላሉ ለማለፍ የሚችሉት፣ ሙሉ ልቦናቸውን ለዓብዩ ጌታ የሚያቀርቡት ትሑት አገልጋዮቹ ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ የሐሰት ራእይን እና ጭንቀት የተሞላበትን ሕይወት ለማስወገድ ከፈለግን እና፣ በመሀላችን በአንድነት ላይ የተመሠረተ ፍላጎትን ለማግኘት የምንሻ ከሆነ፣ ዓብዩ ጌታን በሕይወታችን ውስጥ በመሀከላችን ማድረግ ይኖርብናል፡፡
የሥራችን ውጤት ሁሉ፣ ዓብዩ ጌታን ለማስደሰት መቅረብ ይኖርበታል፡፡ ሁሌ የግል ስሜቶቻችንን ለማስደሰት ብቻ መጣር አይገባንም፡፡ ዓብዩ ጌታንም ለማስደሰት በምናደርገው ጥረት ሁሉ “አትማ ብሁታ” ወይም ቀደም ብሎ የተጠቀሰውን፣ በአንድነት ላይ የተመሠረተውን ፍላጐት ማግኘት እንችላለን፡፡ በዚህ ማንትራ ወይም ጥቅስ ውስጥ የተገለጸው “ብራህማ ብሁታ” የሚለው ቃል እና፣ በብሀገቨድ ጊታ (ብጊ 18፡54) ውስጥ በተገለጸው ቃል ላይ ምንም ዓይነት ልዩነት አይገኝም፡፡ በልባችን ውስጥ የሚገኘው “ዓብዩ አትማ” ወይም “ዓብዩ ነፍስ” ዓብዩ ጌታ ራሱ ነው፡፡ ረቂቅ የሆነችው “አትማ” ደግሞ፣ ሕያው ፍጥረት፣ ነፍስ ናት፡፡ “ፓራም አትማ” ወይም በልባችን ውስጥ የሚገኘው ዓብዩ ነፍስ፣ መላ ሕያው ፍጥረታትን ለመንከባከብ ኅይል ያለው ነው፡፡ ከአገልጋዮቹ በሚገኘው ትሑት እና የፍቅር አገልግሎትም፣ ዓብዩ ጌታ በደስታ ይማረክበታል፡፡ ይህም አባት ልጆቹን ወልዶ በመንከባከብ፣ በእነርሱም ፍቅር እና ደስታ እርሱ ራሱ ደስታውን ለማግኘት እንደሚችል ይመሰላል፡፡ እነዚህም ልጆች አባታቸውን ተከትለው የሚታዘዙ ከሆነ፣ በቤተሰብ ውስጥ ግጭት ሳይኖር፣ በሰላም ለመኖር ይችላሉ፡፡ አንዱ የተባበረ ፍላጎታቸው አባትን ለማስደሰት በመሆኑ፣ በቤተስቡ ውስጥ ያለው ኑሮ፣ ደስታ የተሞላበት ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህንንም በተመሰለ መንገድ ፍጹም በሆነው በመንፈሳዊው ቤተሰብ ውስጥም የምንታዘዘው “ፓራ ብራህማን”፣ ወይም የታላቁ የዓብዩ ጌታ መንፈስ ይገኛል፡፡
ፓራ ብራህማም ልክ እንደ እያንዳንዳችን ሕያው ፍጥረት እና ዓብይ ግለሰብ ሆኖ ይገኛል፡፡ ዓብዩ ጌታም ሆነ እያንዳንዳችን ሕያው ፍጥረታት፣ ሰብአዊነት የሌለን አይደለንም፡፡ በመሠረቱ ሕያው ፍጥረታት ሁሉ፣ የተሟላ መንፈሳዊ ደስታ፣ ዕውቀት እና ዘለዓለማዊ ሕይወት ያላቸው ናቸው፡፡ የመንፈሳዊ ዓለም ሕይወትም፣ ይህን በመሰለ ደረጃ ላይ ይገኛል። አንድ ሰው ይህንን የመሰለውን መንፈሳዊ ደረጃ በትክክል ሲረዳም በቅጽበት ልቦናውን ሁሉ ለዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና ለመስጠት ዝግጁ ይሆናል፡፡ ቢሆንም ይህንን የመሰለ “ማሀትማ” ወይም ታላቅ መንፈሳዊ ሰው፣ በቀላሉ የሚገኝ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህንን ዓይነቱን ንቃት ለማግኘት የምንችለው፣ በከፍተኛ ቁጥር ተደጋግሞ ከሚመጣው ትውልድ በኋላ ነው፡፡ በዚህ መንፈሳዊ ንቃት በትክክል ከዳበርን በኋላ፣ ምንም ዓይነት የሐሰት ራእይ ውስጥ፣ ወይም ዓለማዊ ትካዜ እና ጭንቀት ውስጥ አንወድቅም፡፡ በቁሳዊው ዓለም ውስጥም በመኖር ላይ እያለን፣ ከስቃይ እና ከመከራ ነጻ ለመሆን እንችላለን፡፡
ተደጋጋሚው ሞት እና መወለድም ይቆማል፡፡ በዓለማዊ መንፈስ በተቃወሰ ሕይወታችን ውስጥ ግን፣ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ይከሰታሉ፡፡
ከዚህ የሽሪ ኡፓኒሻድ ማንትራ ወይም ጥቅስ የምናገኘው መልእክት ይህንን ይመስላል፡፡