ማንትራ ዘጠኝ
አንድሀም ታማህ ፕራቪሻንቲ
ዬ ቪድያም ኡፓሳቴ
ታቶ ብሁያ ኢቫ ቴ ታሞ
ያ ኡ ቪድያያም ራታሀ
አንድሀም — የረከሰ ድንቁርና፣ ታማህ — ጨለማነት፣ ፕራቪሻንቲ — መግባት፣ ዬ — እነዚያ ሰዎች፣ አቪድያም — በድንቁርና፣ ኡፓሳቴ — የሚያመልኩ፣ ታታህ — ከዚያም በላይ፣ ብሁያህ — በተጨማሪም፣ ኢቫ — እንዲህ፣ ቴ — እነርሱ፣ ታማሀ — በጨለማ ውስጥ፣ ዬ — እነዚያ ሰዎች፣ ኡ — ጭምር፣ ቪድያያም — ዕውቀት በተሞላበት ባህል፣ ራታህ — የተሰማሩ
ድንቁርና በተሞላበት ዓለማዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚሰማሩ ሁሉ፣ ጉዞዋቸው ጭለማ ወደተሞላበት የድንቁርና ኑሮ፣ ወይም ክልል የሚያመራ ነው፡፡ ከእነርሱም በላይ በሚገኝ የድንቁርና ሥራ ላይ የተሰማሩት ሰዎች ደግሞ፣ ሳያውቁ እናውቃለን በሚል መንፈስ በድንቁርና ውስጥ በገፋ መንገድ የሰመጡ ሰዎች ናቸው፡፡
ይህ ማንትራ የሚያቀርብልን “በቪድያ” እና “በአቪድያ” መሀከል ያለውን ልዩነት ነው። አቪድያ ወይም ድንቁርና፣ ያለ ጥርጥር የሰውን ልጅ ሕይወት ዓላማ ስኬታማ እንዳይሆን የሚያደርግ እና፣ አደጋ ወደተሞላበት ሕይወት እንዲያመራ የሚያደርግ ነው። ቪድያ ወይም ዕውቀት ራሱ ድግሞ፣ በትክክል ካልተመራ የሰውን ልጅ ለበለጠ አደጋ ሊያጋልጥ የሚችል ነው፡፡ የሽሪ ኡፓኒሻድ ማንትራ ከቀድሞው ጊዜ ይልቅ ለአሁኑ ዘመን ትውልድ፣ በጣም ወቅታዊ የሆነ ጥቅስ ነው፡፡ ምክንያቱም የዘመኑ ሥልጣኔ ብዙኃኑን ኅብረተሰብ በተሳሳተ መንገድ ለማስተማር በመገስገስ ላይ ነው፡፡ ውጤቱን እንደምናየውም፣ ከነዚህ ከተማሩት የሰው ልጆች ውስጥ በኑሮ ደስታኛ ያልሆኑ ቁጥራቸው በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህም በቁሳዊ ዓለም ሥልጣኔ ለመበልጸግ ሲጥሩ በሚደርስባቸው ጫና ሲሆን፣ ይህም የተከሰተው ለሕይወታቸው በጣም አስፈላጊ የሆነውን መንፈሳዊ ንቃታቸውን ባለማዳበራቸው ነው።
በመጀመሪያው ማንትራ በግልጽ እንደተጠቀሰው፣ “ቪድያ” ማለት ዓብዩ ጌታ የሁሉም ነገር ባለቤት እንደሆነ መረዳት ማለት ነው፡፡ ይህንን ዕውቀት መዘንጋት ወደ ድንቁርና ዓለም ያመራናል፡፡ የሰው ልጅ ይህንን የመሰለ ዕውቀት በዘነጋ ቁጥር፣ ሁሌ በጨለማ ውስጥ እንደሚዋጥ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ የዓብዩ ጌታን ንቃት ያላካተተ ሥልጣኔ በልዩ ልዩ የትምህርት ዘርፍ፣ ለሰፊው ሕዝብ የሚቀርብ ከሆነ፣ ከመሀይምነት በላይ አደገኛ ሊሆን ይችላል፡፡
የተለያዩ የንቃት ደረጃ ካላቸው ሰዎች ወይም “ካርሚዎች፣ ግያኒዎች እና ዮጊዎች” መሀከል፣ ካርሚዎች የሚባሉት በዓለማዊ ስሜታዊ ደስታ ለመርካት፣ በጉጉት የሚሳቡ እና ለዚህም ምኞት በተግባር የሚሰማሩ ናቸው፡፡ በአሁኑ ዘመን የትውልድ ሥልጣኔ ውስጥ እስከ 99.9 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች፣ ስሜታቸውን ለማርካት በሚጠቅም እንቅስቅሴ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ እነዚህም እንቅስቃሴዎች በተለያየ ርእስ እና በሰንደቅ ዓላማ ተመስለውም ሊመጡ ይችላሉ፡፡ “ልማት፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ ለሌሎች የበጎ አድራጎት ማድረግ፣ የፖለቲካ ንቅናቄ ወዘተ የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ከሞላ ጐደል የተመኘነውን የስሜት ፍላጎት ለማርካት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ የሚከናወኑትም፣ ልክ በመጀመሪያው ማንትራ እንደተገለጸው የዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ንቃትን በማያካትት ሁኔታ ነው።
በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ በጉልህ እንደተጠቀሰውም፣ (ብጊ 7፡15) በዓለማዊ ስሜታዊ ደስታ ላይ የተሰማሩ ሁሉ፣ እንደ “ሙድሀ” ወይም ልክ ከእንስሳ እንዳልተሻለ እና የአህያን ባህሪያት እንደለበሱ ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡ ይህም ምሳሌ የተሰጠበት ምክንያትም፣ ብዙውን ጊዜ አህያን እንደ አላስተዋይ ምሳሌ አድርገን ስለምንጠቅስ ነው፡፡ በዚህ ትርፍ ለማይገኝበት በዓለማዊ እና ስሜታዊ ደስታ ውስጥ የተሰማሩ ሰዎች ሁሉ፣ በሽሪ ኡፓኒሻድ እንደተገለጸው፣ “አቪድያን” ወይም ድንቁርናን የሚያመልኩ ናቸው፡፡ በትምህርት ስም ይህንን ዓይነት የድንቁርናን ሥልጣኔ ለማስፋፋት የሚጥሩ ሰዎች ሁሉ፣ በዓለማዊ ስሜታዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከተሰማሩት ሰዎች በላይ፣ ለኅብረተሰቡ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ የትምህርት ሥልጣኔ፣ ልክ በኮብራ እባብ ጭንቅላት ላይ ለማጌጥ እንደተቀመጠ አደገኛ ጌጣ ጌጥ ይቆጠራል፡፡ በዚህም ሁኔታ ያጌጠው የኮብራ እባብ ካላጌጠው እባብ የበለጠ አደገኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ በሀሪ ብሀክቲ ሱድሆዳያ (3፡11) መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው፣ የዓብዩ አምላክን መንፈሳዊ ህላዌ የማያካትት ትምህርት የመስጠት ሥልጣኔ፣ ልክ የሞተ ገላን እንደማጋጌጥ ይመሰላል። በህንድ አገር ሆነ በሌሎች አገሮች ውስጥ እንደሚታየው፣ አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በሐዘን ላይ ያሉት ሐዘንተኛ ቤተሰቦች እና ቤተዘመዶች ደስ እንዲላቸው በማለት፣ ሬሳውን በደንብ አጋጊጠው ወደ መቃብር ሲጓዙ ይታያሉ፡፡ ይህን በመሰለ ድርጊት በዘመኑ ሥልጣኔም የማይቀረውን የቁሳዊ ዓለምን ጭንቀት እና ችግር፣ በተለያየ መንገድ ስንሸፋፍነው እንታያለን፡፡ እንደዚህም ዓይነት እንቅስቃሴዎች ሁሉ፣ ዞሮ ዞሮ ዓለማዊ ስሜቶቻችንን ለማርካት የሚደረጉ ናቸው፡፡ ቢሆንም ግን ከስሜቶቻችን በላይ ሐሳብ ይገኛል፡፡ ከሐሳብ በላይ ደግሞ አእምሮ አለ፡፡ ከአእምሮ በላይ ደግሞ ነፍስ ትገኛለች፡፡ ስለዚህ የትምህርት ሁሉ ዋና ዓላማ፣ ስለ ነፍስ ወይም ራስን ስለማወቅ ጥናት መሆን ይገባዋል፡፡ ይህ ጥናት ትልቅ ፋይዳ የሚኖረው በነፍስ እና የነፍስ መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ትኩረት በማድረግ ነው፡፡ ወደ እዚህ ዓይነቱ ንቃት የማያመራ ዕውቀት ደግሞ “አቪድያ” ወይም ድንቁርና በመባል ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ይህንን ዓይነቱን ዓለማዊ ንቃት የማናዳብር ከሆነ ኅብረተሰቡን ወደ ድንቁርና ዓለም እየመራነው ነው ማለት ነው፡፡
በብሀገቨድ ጊታ እንደተገለጸው (ብጊ 2፡42, 7፡15) እነዚህ አሳሳች መምህራን “ቬዳ ቫዳ ራታ” እና “ማያያፓህርታ ግያና” ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህም መምህራን ከሃዲያን እና በንቃታቸውም ከሰፊው ኅብረተሰብ በታች የሆኑ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ “ቬዳ ቫዳ ራታ” የሚባሉት መምህራን ደግሞ ራሳቸውን ልክ እንደ ቬዲክ ዕውቀት ሊቅ አድርገው የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከቬዲክ ዕውቀት ዋና ዓላማ በጣም አፈንግጠው የሄዱ በመሆናቸው፣ የቬዲክ ትምህርትን ከማን መውሰድ እንዳለብን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል። በብሀገቨድ ጊታ እንደተጠቀሰው (ብጊ 15፡15) የቬዲክ ዕውቀት ዋናው ዓላማ ዓብዩ ጌታን በትክክል ለማወቅ እና ለመረዳት ነው፡፡ ከዚህ በተቃረነ መንገድ ግን፣ እንዲህ ዓይነቶቹ አሳሳች መምህራን፣ በዓለማዊ ውጤቶች እና በቁሳዊው ዓለም ውስጥ ወደሚገኘው ገነት ለመግባት ጥረት የሚያደርጉ ናቸው።
በማንትራ አንድ እንደተጠቀሰው፣ ዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ የሁሉም ነገር ባለቤት ነው፡፡ ስለዚህ በሕይወት ለሚያስፈልገን ነገር እና፣ እንደሚገባን ለቀረበልን ነገር ሁሉ ደስተኛ መሆን ይገባናል፡፡ የቬዲክ ዕውቀት ዋናው ዓላማ፣ መላ ሕያው ፍጥረታት የዓብዩ ጌታን መንፈሳዊ ልእልና እንዲያነቃቁ እና እንዲያዳብሩ ማድረግ ነው፡፡ ይህም ዓይነቱ መልእክት በዓለም ላይ በሚገኙ መንፈሳዊ መጻሕፍት ሁሉ ተጠቅሷል፡፡ የዚህ መልእክትም ጠቀሜታ በቸልተኝነት እና በሞኝነት የተጠቁ ዓለማዊ ሰዎች ሁሉ፣ በመንፈሳዊ ንቃት እንዲዳብሩ ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የሃይማኖቶች ሁሉ ዋና ዓላማ፣ ሕያው ፍጥረታትን ወደ ዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ዓለም ለመመለስ ነው፡፡
ቢሆንም ግን እነዚህ “ቬዳ ቫዳ ራታ” ተብለው የሚታወቁት ሰዎች የቬዳዎች ሁሉ ዓላማ ከዓብዩ ጌታ የነበረንን እና የዘነጋነውን ግንኙነታችንን በትክክል እንድንረዳው መሆኑን በማስተማር ፋንታ፣ ወደ ከፍተኛዎቹ ደስታ ወደሚገኝባቸው ዓለማዊ ፕላኔቶች በመግባት፣ ስሜታችንን ሁሉ ለማርካት እንችላለን ብለው ያስተምራሉ፡፡ ወደ እዚህ ቁሳዊ ዓለም ወርደን እንድንጠመድ ያደረገንም ዋነኛው መነሻ፣ ይኸው ስሜታችንን ለማስደሰት የምናደርገው ጉጉት እና ጥረት ነው፡፡ እነዚህም አሳሳች መምህራን፣ የቬዳዎች ዓላማ ለዚሁ መድረሻ ነው ብለው ያስተምራሉ፡፡ በዚህ ዓይነቱ መንገድ የሰው ልጆችን በማስተማር የቬዲክ ዕውቀት ዓላማ ምን እንደሆነ በተሳሳተ መንገድ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም የፑራና የቬዲክ መጻሕፍትን አንቋሸው ሲመለከቱ ይታያሉ፡፡ እነዚህ የፑራና መጻሕፍት መንፈሳዊ ሥልጣን ያላቸው የቬዲክ መጻሕፍት ሲሆኑ፣ የተዘጋጁትም ማንም ሰው በቀላሉ እንዲረዳቸው በተደረገ መንገድ ነው፡፡ እነዚህ “ቬዳ ቫዳ ቭራታ” የተባሉት ሰዎች ግን፣ ስለ ቬዳዎች ትምህርት የራሳቸው የሆነ ትርጉም ሰጥተውት ይገኛሉ፡፡ ይህም አቀራረብ፣ ሥልጣን ያላቸውን መንፈሳዊ መምህራን ፈለግ በማይከተል መንገድ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜም በመሀላቸው ከሚገኙት አጥፊ ሰዎች መሀከል አንዱን በመምረጥ፣ ልክ እንደ ታላቅ የቬዲክ ዕውቀት መምህር በማስመሰል ሲያቀርቡት እና ኅብረተሰቡን ሲያሳስቱ ይታያሉ። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች በዚህ ማንትራ ውስጥ “ቪድያያም ራትሀ” በመባል በተወገዘ መንገድ በትክክል ተጠቅሰው ይገኛሉ፡፡ “ቪድያም” የሚለው ቃል የሚገልጸው ስለ ቬዳዎች ትምህርት መማር ነው፡፡ ቬዳዎች የዕውቀት (ቪድያ) ሁሉ መጀመሪያ ናቸው፡፡ “ራትሀ” ማለት ደግሞ “የተሰማሩ” ማለት ነው፡፡ “ቪድያም ራትሀ” ማለት “በቬዳዎች ዕውቀት ትምህርት ላይ የተሰማሩ ማለት ነው፡፡” በዚህ የተገለጹት የቬዳ ዕውቀት መምህራን እና ተማሪዎች የተወገዙበት ምክንያት ግን፣ የቬዳዎችን ዓላማ በተሳሳተ መንገድ ለማስተማር በመሰማራታቸው ነው፡፡ ይህም አቀራረብ የተወገዘው፣ ሥልጣን ያላቸውን መንፈሳዊ መምህራን ባለመከተላቸው ነው። እነዚህ “ቬዳ ቭራታ” ተብለው የሚታወቁት መምህራን ለእያንዳንዱ የቬዳ ዕውቀት ቃላት የራሳቸውን የሆነ ትርጉም በመስጠት፣ ትምህርቱን በተሳሳተ መንገድ የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ የቬዲክ ዕውቀት ከተለያዩ መንፈሳዊ ሥልጣን ካላቸው መጻሕፍት የተቀነባበረ እና ትምህርቱም መሰጠት የሚገባው ሥልጣን ካላቸው እና ሲወርድ ሲዋረድ ከመጡ መንፈሳዊ መምህራን እንደሆነም የተረዱ አይደሉም፡፡
አንድ ሰው የቬዳዎችን መንፈሳዊ መልእክት በትክክል ለመረዳት፣ ሥልጣን ወዳለው መንፈሳዊ መምህር መቅረብ ይገባዋል፡፡ ይህም መመሪያ በሙኩንዳ ኡፓኒሻድ (ሙኡ፡ 1፡2፡12) የተሰጠ ነው፡፡ እነዚህ “ቬዳ ቫዳ ቭራታ” የተባሉት መምህራንም የራሳቸው የሆነ አቻርያ ወይም መምህር አላቸው፡፡ እነዚህም መምህራን ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣው የመንፈሳዊ የዲቁና ሥርዓት የመጡ አይደሉም፡፡ በዚህ ምክንያት የተነሳ የቬዳዎችን ትምህርት በተሳሳተ መንገድ በማስተማር፣ የሰውን ልጅ ወደ ተሳሳተ የድንቁርና መንገድ በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ መምህራን ምንም የቬዳ ዕውቀት ከሌላቸው ሰዎች በላይ በድንቁርና ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡
“ማያያፓህርታ ግያና” የሚባሉት የሰው ልጆች ክፍል ደግሞ፣ ራሳቸውን እንደ “አምላክ” አድርገው የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ደግሞ፣ ራሳቸውን እንደ አምላክ አድርገው የሚያምኑ ሲሆኑ፣ ከራሳቸው በቀር፣ ሰዎች ሌላ አምላክን ማምለክ እንደማይገባቸው የሚያስቡ ናቸው፡፡ ሀብት ያለውን ሰው ግን ከማምለክ ወደኋላ አይሉም፡፡ ዳሩ ግን ዓብዩ የመላእክት ጌታን ፈጽሞ ሲያመልኩ አይታዩም፡፡ እንደነዚህም ዓይነቶቹ ሰዎች የራሳቸውን ድንቁርና ፈጽሞ ለመረዳት ያዳገታቸው ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰዎች የራሳቸውን ድንቁርና ለመረዳት ተስኗቸው እያለ፣ እንዴት ዓብዩ ጌታ ራሱ በፈጠረው የቁሳዊው ዓለም የሐሰት ራእይ ወይም “ማያ“ ለመጠመድ ቻለ በማለት ያሰላስላሉ? ዓብዩ ጌታ ራሱ በፈጠረው የቁሳዊው ዓለም የሐሰት ራእይ ወይም “ማያ” ለመጠመድ ከቻለማ፣ “ማያ” ከእርሱ በላይ ኅይል አላት ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነት ሰዎች ዓብዩ ጌታ ፍጹም ኅይል ያለው ስለመሆኑ ለመረዳት የሚችሉ ቢሆኑም፤ “በማያ” ወጥመድ ሥር ግን እንዴት ለመታሰር እንደማይችል መረዳት ያዳግታቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ራሳቸውን እንደ አምላክ የሚቆጥሩ ሰዎች፣ ይህንን የመሰለ ጥያቄዎችን በትክክል ለመመለስ አይችሉም፡፡ ራሳቸውንም እንደ አምላክ በመቁጠር ብቻ የሐሰት ማዕረጋቸውን በማደላደል፣ ደስተኞች ለመሆን ይጥራሉ፡፡