No edit permissions for Amharic

1

የደስታ መንገድ

በዚህ ዓለም ላይ የምንገኝ እያንዳንዳችን ደስታን ስንሻ እንገኛለን፡፡ ቢሆንም ግን ፍፁም የሆነው እና ትክክለኛው ደስታ ምን እንደሆነ የተገነዘብንበት ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ በተለያዩ ማስታወቂያዎች ላይ ብዙ ደስታን ሊሰጡ ስለሚችሉ ነገሮች ቀርበው እናያለን፡፡ ቢሆንም ግን በጣም ጥቂት የሚሆኑ ሰዎች ፍፁም በሆነ ደስታ ላይ ተሰማርተው ይታያሉ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ፍፁም ደስታ የሚገኘው ከጊዜያዊ እና ከዓለማዊ ኑሮ ሳይሆን ከዚህ ዓይነቱ ኑሮ ባሻገር በመሆኑ ነው፡፡ ይህንንም የተገነዘቡ ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ በብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መጽሀፍም ውስጥ ለአርጁና የተገለፀለት ይህ አይነቱ ፍፁም የሆነው ደስታ ነው፡፡

በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ደስታ ተሰማን ብለን የምናስበው በስሜቶቻችን እርካታ ነው፡፡ ለምሳሌ ድንጋይ ስሜት ስለሌለው ደስታ እና ስቃይ ሊሰማው አይችልም፡፡ ንቃተ ሕሊናቸው የዳበረ ፍጥረታት ንቃተ ሕሊናቸው ካልደበረ ሌሎች ፍጥረታት ደስታ እና ስቃይን በላቀ መንገድ ሊያዩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ዛፎች በሕይወት እያሉ ንቃት አላቸው፡፡ ቢሆንም ግን ንቃታቸው የዳበረ አይደለም፡፡ ዛፎች በአንድ ቦታ ቁመው ብዙ ዓይነት የአየር ፀባይ እየተፈራረቀባቸው ለብዙ መቶ ዓመታት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ብዙ ስቃይ አይሰማቸውም፡፡ የሰው ዘር ግን እንደ ዛፍ ለሶስት ቀን ወይም ከዚያም በታች ቁም ቢባል ትእግስት ሊኖረው አይችልም፡፡ ከዚህም መረዳት የምንችለው እያንዳንዱ ህያው የሆነ ፍጡር የሚሰማው ደስታ ወይም ስቃይ ከዳበረው ንቃቱ አንፃር ነው፡፡

በዚህ ቁሳዊ ዓለም ላይ የምናየው ደስታ ትክክለኛው እና ፍጹም የሆነ ደስታ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ዛፍ ደስተኛነቱን ቢጠየቅ እዚያው አንድ ቦታ ላይ ለዓመታት መቆሙ ደስታ ሊሰጠው የሚችል እንደሆነ ሊናገር ይችላል፡፡ “ይህን የሚፈራረቅብኝን ንፋስ፣ ፀሀይ እና በረዶውን እየተቋቋምኩ በደስታ እኖራለሁ፡፡” የሚል ስሜት ሊኖረው ይችላል፡፡ ለሰው ልጅ ግን ይህ ዓይነት ኑሮ በጣም አሰልቺ፣ ያልበለፀገና ደስታንም ሊሰጠው የማይችል ዓይነት ኑሮ ነው፡፡ በዓለም ላይ የተለያየ ደረጃ ያላቸው ፍጥረታት ይገኛሉ፡ የሚሰማቸውም ስቃይ እና የሚያረካቸው ደስታ እንደ ደረጃቸው የተለያየ ሆኖ እናገኝዋለን፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ እንስሳ ሌላ እንስሳ በአጠገቡ ሲታረድ ቢያይም ሳር መጋጡን አያቆምም፡፡ ምክንያቱም እርሱም በቀጣይ የዚህን ስቃይ ፅዋ እንደሚቀምስ እና ተረኛ እንደሚሆን ስለማይገነዘብ ነው፡፡ ሳር በመጋጡም ደስተኛ እንደሆነ ብቻ ያሰባል እንጂ በሚቀጥለው ተራውም እርሱም ታርዶ ለስቃይ እንደሚበቃ አይገነዘብም፡፡

እንደዚህም በመሰለ ሁኔታ የተለያየ ዓይነት ስቃይ እና ደስታ በምድር ላይ እንዳለ እንረዳለን፡፡ ቢሆንም ግን ከፍተኛ የደስታ ምንጭ የምናገኘው ከየት ነው? ስለዚህም ዓብዩ ሽሪ ክርሽና በብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መፅሀፍ ውስጥ ለአርጁና እንዲህ ብሎ ገልፆለታል፡፡

ሱክሀም አይያንቲካም ያት ታድ
ቡድሂ ግራህያም አቲንድርያም
ቬቲ ያትራ ና ቻይቫያም
ስትሂታሽ ቻላቲ ታትቫታሀ

“በዚያም ደስታ በሞላበት ጥልቅ ሀሳብ (ሳማድሂ) አንድ ሰው ወሰን ሊኖረው በማይችል መንፈሳዊ ደስታ ተመስጦ የመንፈሳዊ ስሜቶቹን ሲያረካ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደረጃም የበቃ ህያው ከዚህ ከእውነተኛው ደስታ በፍፁም ርቆ ለመሄድ እና ለመረበሽ አይችልም፡፡” (ብጊ 6 21)

ቡድሂ ማለት አዕምሮ ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ደስታን ለማግኘት ከፈለገ አዕምሮው የዳበረ መሆን ያስፈልገዋል፡፡ እንስሶች እንደ ሰው ፍጡር የዳበረ አዕምሮ ስለሌላቸው ሕይወታቸውን በተለያየ መንገድ እንደሰው አስደስተው ለማሳለፍ አቅም የላቸውም፡፡ አንድ የሰው ሬሳ እጅም፣ አፍንጫም፣ ዓይኖችም እና ሌሎች የደስታ ብልቶች ቢኖሩትም ምንም ዓይነት ደስታን ሊያገኝ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ደስታን ሊረካ የሚችለው መንፈሳዊው ነፍስ ከገላው ለቅቆ በመሄዱ ነው፡፡ በመሆኑም የተጋደመው ገላ የመደሰት ሀይል የለውም፡፡ ይህንንም ጠለቅ ብሎ አንድ ሰው ቢመረምር በተገኘው ደስታ ይረካ የነበረው ገላው ሳይሆን በገላው ውስጥ የምትኖረው መንፈሳዊዋ የዓብዩ አምላክ ቅንጣፊ ነፍሱ ናት፡፡ ምንም እንኳን የገላ ስሜቶቻችን በምናገኘው ደስታ በመርካት ላይ ይገኛሉ ብለን ብናስብም በደስታው የሚረካው ፍጡር ግን በገላችን ውስጥ የምትገኘው ነፍሳችን ናት፡፡ ይህችም የዓብዩ አምላክ ቅንጣፊ የሆነችው ነፍስ ደስተኛ የመሆን ሀይሏ ዘለዓለማዊ ነው፡፡ ቢሆንም ግን በዚህ ቁሳዊ ዓለም ተወልደን እና በቁሳዊ ገላ ተሸፍነን እስካለን ድረስ ይህ ፍፁም የሆነው ደስታ ሁልጊዜ ሊከሰትልን አይችልም፡፡ ብዙውን ጊዜም ባንረዳውም በደስታ ልትረካ የምትችለው ነፍስ ናት እንጂ ገላው አይደለም፡፡ ነፍስ የሌለችበት ገላ ደስታን ሊሰጠን አይችልም፡፡ ለምሳሌ አንድ ወንድ ልጅ ነፍሷ ከስጋዋ የተላቃቀውን የአንዲት ቆንጆ ልጅ ገላ ሊረካበት አይችልም፡፡ ይህም የሚያሳየን ደስታውን ሊያረካ የምትችለው ነፍስ ናት እንጂ ገላ እንዳልሆነ ነው፡፡ ይህችም ነፍስ በገላ ተሸፍና ደስታን በመርካት ላይ የምትገኝ ብቻ ሳትሆን ስጋችን እንዲዳብር እና እንዲያድግ ሀይልም የምትሰጥ ናት፡፡ ነፍስ ከስጋ ስትለይ ደግሞ ገላ መበታተን፣ መላሸቅ እና መበስበስ ይጀምራል፡፡

ነፍስ በደስታ የምትረካ ከሆነ የራስዋ የሆነ ስሜት እንደአላት እንረዳለን፡፡ አለበለዛ ግን በደስታ መርካት አትችልም፡፡ የቬዲክ ስነጽሁፎች እንደሚያስተምሩን ነፍስ ምንም እንኳን ከአቶም ያነሰ ልክ ቢኖራትም በደስታ የምትረካው እሷው ሆና ትገኛለች፡፡ በቬዲክ ስነጽሁፎች እንደምንማረው የነፍስን ስፋት እና ርዝመት ለመለካት ያዳግታል፡፡ ቢሆንም ግን ነፍስ መለኪያ የላትም ማለት አይደለም፡፡ አንድ ፍጥረት ነጥብን የሚያክል ሆኖ እያለ ርዝመት እና ስፋት የለውም ብለን ልንወስን እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በማይክሮስኮፕ አተኩረን ይህንን ነጥብ ብናየው ስፋት እና ርዝመት እንደ አለው እንገነዘባለን፡፡ እነደዚሁም ሁሉ ነፍስ መለኪያ አላት፡፡ ነገር ግን ይህንን በቁሳዊው ዓይናችን ለማየት አዳጋች ነው፡፡ ልብስ ወይም ቀሚስ ስንገዛ በገላችን ስፋት እና ቁመት ልክ ነው ፡፡ ይህች የዓብዩ አምላክ ቅንጣፊ አካል ነፍስም የራስዋ የሆነ ቅርፅ አላት፡፡ ገላችንም ይህችኑን ነፍስ እያገለገለ በእድገት እየዳበረ ይገኛል፡፡ ነፍስ የሰብአዊ ባህርይ የላትም ለማለትም አንችልም፡፡ ነፍስ እራስዋ ሰብአዊ ፍጡር ናት፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ፈጣሪ አምላክ ዓብዩ ሰብአዊ አምላክ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከእርሱም ተቀንጥሳ የምትገኘው ነፍስም እንደ ዓብዩ የመላእክት ጌታ ሰብአዊ ፍጡር ሆና ትገኛለች፡፡ አባት ሰብአዊነት እና የግል የሆነ ባህርይ አለው ከተባለ ልጁም እንደዚሁ የአባቱ ባህርያት ይኖሩታል፡፡ ይህንንም ባህሪይ በልጁ ካየን አባቱም እንደ ልጁ እነዚህን ባህሪያት ይዞ እንደሚገኝ እንረዳለን፡፡ ታድያ እኛ የዓብዩ ፈጣሪ አምላክ ልጆች ሆነን እና የሰብአዊ ባህሪይ እያለን እንዴት አባታችን ሰብአዊ ፍጡርነት የለውም ለማለት እንችላለን?

”አቲንድርያም” ማለት ፍጹም የሆነውን ደስታን ለማግኘት ከእነዚህ ዓለማዊ ከሆኑ ሰሜቶቻችን ተላልፈን እና ተሻግረን መሄድ አለብን ማለት ነው፡፡ “ራማንቴ ዮጊኖ ናንቴ ሳትያናንዳ ቺድ አትማኒ” ለመንፈሳዊ ኑሮ በጣም ቅን ፍላጎት ያላቸውም ዮጊዎች ሀሳባቸውን በልባቸው በሚገኘው የአምላክ አብይ ነፍስ ላይ በታላቅ ጥረት በማተኮር ከፍተኛ ደስታ በማግኘት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ጥረት ፍጹም ደስታ የማይገኘበት ቢሆን ኑሮ እነዚህ ዮጊዎች ስሜቶቻቸውን በብዙ ጥረት ለመቆጣጠር አይበቁም ነበር፡፡ ስሜቶቻቸውንም ለመቆጣጠር ይህንን ዓይነት ትግል የሚያደርጉ ከሆነ ምን ያህል ደስታ በመንፈሳዊ ፈለጋቸው ቢያገኙ ነው? ይህ የሚያገኙት የመንፈሳዊ ፍፁም የሆነ ደስታ “አናንዳ” ይባላል፡፡ ይህም ማለት ወሰን የሌለው ደስታ ማለት ነው፡፡ ይህስ እንዴት ዓይነት ደስታ ነው? ነፍስ ዘለዓለማዊ ናት፡፡ ዓብዩ የመላእክት ጌታም ዘለዓለማዊ ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በሁለቱ መሀከል የሚገኘው የፍቅር ልውውጥም ዘለዓለማዊ ነው፡፡ በአዕምሮውም የዳበረ ሰው ብልጭልጭ እና ጊዜያዊ ከሆነው ከቁሳዊው ዓለም ስሜታዊ ደስታ ርቆ ዘለዓለማዊ ወደሆነው መንፈሳዊ ደስታ ትኩረቱን ያደርጋል፡፡ ይህም ዓይነቱ ከዓብዩ አምላክ ጋር ያለን የመንፈሳዊ ግኑኝነት “ራሳ ሊላ” ይባላል፡፡

ስለ ሽሪ ክርሽናም በቭርንዳቨን ከነበሩት ከእረኛ ልጃገረዶች ጋር የነበረውን ራሳ ሊላ ከዚህ በፊት ሰምተናል፡፡ ይህም የነበራቸው ግኑኝነት በቁሳዊው ዓለም እንደምናየው የገላ ቅርበት አይደለም፡፡ ይህም ግኑኝነት በውስጣዊ ስሜቶቻቸው የተመሰረተ የመንፈሳዊ ደስታ ነበር፡፡ አንድ ሰውም ይህ ዓይነቱን ደስታ ለመረዳት አዕምሮው የዳበረ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ በአላዋቂነት ወይም በሞኝነት የተጠቃ ሰው ግን ደስታውን ከዚህ ከጊዜያዊና ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ለማግኘት ጥረቱን ሲያደርግ ይታያል፡፡ በሕንድ አገር ውስጥ የሸንኮራ አገዳ ምን እንደሆነ ሰምቶ፣ አይቶና ቀምሶ የማያውቅ ሰው ነበር፡፡ ሰዎችም ሸንኮራ አገዳ ሲታኘክ በጣም ይጣፍጣል ብለው ነግረውት ነበር፡፡ እርሱም “ሸንኮራ አገዳ ምን ይመስላል?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም “ሸንኮራ አገዳ ሸንበቆ ይመስላል” ብለው ይነግሩታል፡፡ ይህም ሞኝ ሰው ያገኘውን ሸምበቆ ሁሉ ማኘክ ይጀምራል፡፡ ታድያ በዚህ ዓይነት መንገድ እንዴት አድርጎ የሸንኮራ አገዳን ጣፋጭነት ሊያጣጥም ይችላል? እንደዚሁም ሁሉ እኛም በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ደስታን ለማግኘት እንሻለን፡፡ ይህንንም ደስታ ለማግኘት የምንሞክረው የቁሳዊ ገላችንን የስሜት እርካታ በማላመጥ ነው፡፡ ስለዚህም ፍጹም የሆነውን የመንፈሳዊ ንጹህ ደስታ ለመርካት አንችልም፡፡ የቁሳዊው ዓለም ደስታ ለጊዜው በደስታ የሚያረካን ይመስለናል፡፡ ነገር ግን ፍጹም የሆነ ደስታ አይሰጠንም፡፡ ምክንያቱም ጊዜያዊ እና ዘለቄታ የሌለው ደስታ ስለሆነ ነው፡፡ ይህም ልክ በሰማይ ላይ ለጥቂት ሰኮንድ እንደምናየው የመብረቅ ብልጭታ ሊመሰል ይችላል፡፡ ትክክለኛው ነጎድጓድ ግን ከብልጭታው አልፎ ተርፎ በጣም ሀይል ያለው የተፈጥሮ ክስተት መሆኑን መገንዘብ ይገባናል፡፡ በዚህም ዓለም ላይ የሰው ልጅ ትክክለኛው ደስታ ምን እንደሆነ ለማወቅ ስለአልተረዳ ከፍጹሙ የደስታ መንገድ አፈንግጦ ወጥቶ እናየዋለን፡፡

ትክክለኛውን የደስታ ምንጭ ለማግኘት መከተል የሚገባን ስርዓት የዓብዩ ሽሪ ክርሽናን መንፈሳዊ ንቃት በማዳበር ነው፡፡ የሽሪ ክርሽናም ንቃታችንን በማዳበር የመንፈሳዊ አዕምሮዋችን እየላቀ በሄደ ቁጥር እና መንፈሳዊ እርምጃችንን በቀጠልን ቁጥር ውስጣዊው ፍጹም የሆነው ደስታችንም እየጨመረ ይመጣል፡፡
በዚህም የመንፈሳዊ ደስታ እየረካን በሄድን ቁጥር የዓለማዊው የደስታ ፍላጎት እየቀነሰ ይመጣል፡፡ በዚህም መንገድ ፍጹም የሆነውን እውነተኛ ፈለግ ስንከተል ስህተተኛ ከሆነው የደስታ ፈለግ እየለቀቅን እንመጣለን፡፡ በዚህም ስርዓት አንድ ሰው በመንፈሱ ዳብሮ የክርሽናን ንቃት ከአገኘ ውጤቱስ ምን ሆኖ ይገኛል? ይህም በብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መጽሀፍ ውስጥ እንደሚከተለው ተጠቅሷል፡፡

ያም ላብድህቫ ቻፓራም ላብሃም
ማንያቴ ናድሂካም ታታሀ
ያስሚን ስትሂቶ ና ዱክሄና
ጉሩናፒ ቪቻልያቴ

“በዚህም ደረጃ ላይ የደረሰ ሕያው ከዚህ በላይ ምንም ዓይነት የበለጠ ደስታ እንደማይገኝ ተገንዝቧል፡፡ በዚህም ደረጃ ላይ ሆኖ ምንም ዓይነት ነገር ግር ሊያሰኘው አይችልም፡፡ ይህም ምንም እንኳን በከፍተኛ ችግር ላይ ወድቆ እንኳን ቢሆንም ነው፡፡” (ብጊ፡ 6 22)

አንድ ሰው በዚህ ደረጃ ላይ ሲደርስ እና ሌላ ምንም ዓይነት ታላቅ የቁሳዊ ዓለም ዝና እና ውጤቶችንም እንኳን ቢያገኝ እነዚህን የቁሳዊ ዓለም ውጤቶች ከምንም ሊቆጥራቸው አይችልም፡፡ በዚህም ዓለም ላይ ብዙ የተለያዩ ቁሳዊ ነገሮችን ለማግኘት ጥረት ስናደርግ እንገኛለን፡፡ ይህም እንደ ሀብት፣ የሴት ልጅ እውቅና፣ ቁንጅና፣ እውቀት የመሳሰሉትን ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው በዓብዩ ሽሪ ክርሽና ንቃቱ የዳበረ ከሆነ እንዲህ በማለት ማሰብ ይጀምራል፡፡ “በዓለም ላይ ምንም ዓይነት ውጤት ብናገኝ ከዚህ በላይ ሊሆን አይችልም፡፡” እንደዚሁም ሁሉ የዓብዩ ሽሪ ክርሽና ፍቅር በጣም ሀይል ያለው እንደመሆኑ ትንሿ ጣእም እንኳን የሰውን ልጅ ከከፍተኛው አደጋ ልታድን ትችላለች፡፡ ይህንንም የአብዩን ሽሪ ክርሽና ንቃት ጣእም እያጣጣምን ስንጓዝ ለሌላው የቁሳዊው ዓለም ደስታ ተብለው ለሚጠሩት ሁሉ ምንም ጣእም እንደማይኖረን እየተረዳን እንመጣለን፡፡ በዚህም የክርሽና ንቃቱ ጠንክሮ የዳበረ ሰው በዓለም ላይ ሊገኝ የሚችል ማንኛውም አደጋ ሊረብሸው አይችልም፡፡ በዚህም ዓለም ላይ በቁጥር የማይተመኑ የተለያዩ አደጋዎች ይገኛሉ፡፡ ቢሆንም ግን እነዚህን አደጋዎች እያየን እንደሞኝ ዓይናችንን በመሸፈን መኖር አይገባንም፡፡ በሞኝነታችንም የአደጋዎቹን መሰረታዊ መነሻ ለማወቅ ከመሻት ይልቅ አደጋዎችን ለመሸሽ የምንችለበትን መንገድ ስንፈጥር እንኖራለን፡፡ በሕይወታችን ውስጥ በብዙ አደጋዎች በመጋለጥ ላይ እንገኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እራሳችንን በክርሽና መንፈሳዊ ንቃት በማዳበር ወደ ዓብዩ የመላእክት ጌታ የምንሄድበትን መንገድ ብናዘጋጅ ለዚህ ዓለም መከራዎች ምንም ግድ ሊሰጠን አይችልም፡፡ አስተሳሰባችንም እንዲህ ይሆናል፡ “አደጋዎች ይመጣሉ ይሄዳሉ፡ ስለዚህ እንደ አመጣጣቸው ይመለሱ፡፡” በቁሳዊ ዓለም ኑሮ ለተወሳሰበ ሰው እና እራሱንም ይህ ጊዜያዊ ገላዬ ነኝ ብሎ ለሚያስብ ሰው እንዲህ ዓይነቱን የላቀ አስተሳሰብ ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ያገኘዋል፡፡ ነገር ግን በክርሽና ንቃቱ በዳበረ ቁጥር እንዲህ ዓይነቱ ከቁሳዊው ገላ ጋር የተነጻጸረው ዓለማዊ ሀሳብ እየቀነሰለት ይመጣል፡፡

በሽሪማድ ብሀገቨታም ቅዱስ መጽሀፍም ውስጥ ይህ ቁሳዊ ትእይንተ ዓለም ልክ እንደ ታላቅ ውቅያኖስ ተመስሎ ተገልጿል፡፡ በዚህም ትእይንተ ዓለም በሚልዮን እና በቢልዮን የሚቆጠሩ ፕላኔቶች በመንሳፈፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ በነዚህም ፕላኔቶች ውስጥ ስንት እና ስንት የአትላንቲክን እና የፓስፊክን የመሳሰሉ ብዙሀን ውቅያኖሶች እንደሚገኙ ከቬዲክ ስነፅሁፎች መረዳት እንችላለን፡፡ ይህም መላ የትእይንተ ዓለም እንደ ትልቅ የመከራ የትውልድ እና የሞት ውቅያኖስ ተመስሎ ተገልጿል፡፡ ይህንንም ታላቅ የድንቁርና ውቅያኖስ ተሻግሮ ለመሄድ የጠነከረ መርከብ ያስፈልገናል፡፡ ይህም የጠነከረ መርከብ የዓብዩ ሽሪ ክርሽና የሎተስ እፅዋት የመሰለው እግሩ ነው፡፡ በዚህም መርከብ ላይ ወዲያውኑ መሳፈር ይገባናል፡፡ የሽሪ ክርሽናም የሎተስ እፅዋት የመሰለውም እግር ትንሽ ናት ብለንም መጠራጠር አይገባንም፡፡ ምክንያቱም ይህ ግዙፍ የትእይንተ ዓለም እራሱ እንኳን ያረፈው በእግሩ ላይ ነው፡፡ ይህንንም የሽሪ ክርሽናን እግር መጠለያው ያደረገ ሰው ይህንን የትእይንተ ዓለም ውቅያኖስ ልክ በጥጃ ዱካ እንደተሞላ ውሀ በቀላሉ ተሻግሮ ለመሄድ እንዲችል ያበቃዋል፡፡ ይህችንም የምታክል የውሀ ክምችት አንድ ሰው በቀላሉ ተሻግሮ ለመሄድ አያዳግተውም፡፡

ታም ቪድያድ ዱክሀ ሳምዮጋ
ቪዮጋም ዮጋ ሳምጅኒታም

“ይህም የዓብዩ ጌታ ንቃት በቁሳዊ ዓለም ግኑኝነታችን ከሚመጡ መከራዎች ሁሉ ሙሉ ነፃነትን የሚሰጥ ነው፡፡” (ብጊ፡ 6.23)

ለመቆጣጠር በተሳነን የዓለማዊ ስሜት ምክንያት በዚህ ቁሳዊ ዓለም ላይ ተጠምደን እና ተወሳስበን እንገኛለን፡፡ የቬዲክ የዮጋ ስርአትም የሚያስተምረን ይህንኑን ያልተገራ የዓለማዊ ስሜታችንን ጥማት ለመቆጣጠር እንድንችል ነው፡፡ በተለያየ መንገድም ይህንን የዓለማዊ ስሜቶቻችንን ለማርካት ያለንን ትግል ለማቆም ከጀመርን ወደ መንፈሳዊው የደስታ ፈለግ በቀላሉ ለመመለስ እንችላለን፡፡ በዚህም ስርአት ሕይወታችንን የተሳካ ለማድረግ እንችላለን፡፡

ሳ ኒሽቻዬና ዮክታቭዮ
ዮጎ ኒርቪና ቼታሳ
ሳንካልፓ ፕራብሀቫን ካማምስ
ትያክትቫ ሳርቫን አሼሻታ
ማናሳቬንድርያ ግራማም
ቪኒያምያ ሳማንታታሀ

ሻኔይህ ሻኔይህ ኡፓራምድ
ቡድሀያ ድህርቲ ግርሂታያ
አትማ ሳምስትሀም ማናህ ክርትቫ
ና ኪንቺድ አፒ ቺንታዬት

ያቶ ያቶ ኒሽቻላቲ ማናሽ
ቻንቻላም አስትሂራም
ታታስ ታቶ ኒያምያይታድ
አትማኒ ኤቫ ቫሻም ናዬት

በብሀገቨድ ጊታም ቅዱስ መጽሀፍ እንዲህ ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ ”አንድ ሰው በዮጋ ስርአት ሲሰማራ አንደበቱ የማይወላወል እና በእምነቱ የጠነከረ መሆን አለበት፡፡ ዓለማዊ ፍላጎቶቹንም ሁሉ ሳያማርጥ እርግፍ አድርጎ በመተው ስሜቶቹን ሁሉ ከሁሉም ወገን በአዕምሮው በመቆጣጠር እና ረጋ ያለ መንፈስ ላይ መገኘት ይኖርበታል፡፡ በዚህም መንገድ ቀስ በቀስ በሙሉ እምነት በጥልቅ ትኩረት ሀሳቡን በእራስ ላይ ብቻ በማተኮር አዕምሮው ወደ ሌላ የስሜታዊ ደስታ ከመሄድ እንዲቆጠብ መግራት ይኖርበታል፡፡ ሀሳባችን ግን የቅብዝብዝነት ባህርይ ስላለው ወዲህ እና ወዲያ በመሄድ ረጋ ያለ መንፈስ ሳይኖረው በመዘዋወር ትግል ሲያደርግ ይገኛል፡፡ ቢሆንም ግን ከዚህ እንዲቆጠብ በማድረግ ቅብዝብዙን ሀሳባችንን በራስ ወይም በነፍስ ቁጥጥር ስር ማዋል ይገባናል፡፡” (ብጊ፡ 6.24-26)

ሀሳባችን ሁል ጊዜ እንደተረበሸ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ወዲህ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወዲያ ሲመላለስ ይታያል፡፡ የቬዲክንም የዮጋ ስርዓት በመከተል ይህንን ሀሳባችንን ጎትተን ወደ ክርሽና ንቃት ልናመጣው እንችላለን፡፡ ሀሳባችንም የክርሽናን ንቃትን ትቶ ወደ ሌላ ቁሳዊ ዓለም ተስቦ የሚገኝበት ምክንያት ከዚህ በፊት በብዙ ትውልዶች በዚሁ የቁሳዊ ዓለም ውስጥ ደስታን ለማግኘት ብዙ ትግል ያደረግንበት በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ሰው የክርሽና ንቃቱን ሲጀምር በመጀመሪያው ደረጃ አስቸጋሪ ሆኖ ሊያገኘው ይችላል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ዓይነት እንቅፋቶች እየተቋቋምን ለመምጣት እንችላለን፡፡

ለዚህም ችግር የምንበቃው ሀሳባችን ሁሌ በዓለማዊ ደስታ በቀላሉ የሚቀሰቀስ በመሆኑ እና ከአንድ ሀሳብ ወደ ሌላ ሀሳብ በመዝለል ላይ ስለሚገኝ በክርሽና ንቃት ላይ ለማተኮር አዳገች ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ በስራችን ላይ ተሰማርተን እያለን ከዚህ በፊት ከአስር፣ ከሀያ፣ ከሰላሳ፣ ከአርባ ዓመታት በፊት ስናደርጋቸው የነበሩት ትዝታዎች በሀሳባችን ውስጥ ያለ ምንም ምክንያት በድንገት ጥልቅ ብለው ሲገቡ እንረዳለን፡፡ እነዚህም ሀሳቦች የሚመጡት በሀሳባችን ስር ተመዝግበው ስለሚገኙ እና ወደ ላይ አልፎ አልፎ ከፍ በማለት በወቅቱ ያለንን ሀሳባችን ሲያቃውሱ እናገኛቸዋለን፡፡ ረጋ ያለን ኩሬ ብንቀሰቅሰው ከታች ያለው ጭቃ ሁሉ ወደ ላይ ሊወጣ ይችላል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ሀሳባችን በእነዚህ የቀድሞ ትዝታዎች መረበሽ ሲጀምር ብዙ የተዘነጉትን እና ለብዙ ዓመት ተቀብረው የነበሩትን ነገሮች ሁሉ የማስታወስ ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ ኩሬውንም ካልበጠበጥነው ጭቃው ወደታች እንደዘቀጠ ይገኛል፡፡ ይህም የቬዲክ የዮጋ ስርአት ሀሳባችንን በመግራት እነዚህን በመንፈሳዊ ሀሳብ እንዳንሰምጥ የሚረብሹንን ትዝታዎች ወደ ታች አዝቅጠን እንድናስቀምጣቸው የሚረዳን ስርዓት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ እና ሀሳባችንን በቁጥጥር ስር ለማዋል ብዙ ህግጋቶች ተመስርተው ይገኛሉ፡፡ እነዚህንም ህግጋቶች እና መቆጣጠርያ ስርአቶች ብንከተል ቀስ በቀስ ሀሳባችንን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንችላለን፡፡ ይህም እንዲሳካ ብዙ ማድረግ የሚገባን እና ማድረግ የማይገባን ነገሮች አሉ፡፡ አንድ ሰው ሀሳቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ኮስተር ብሎ ለመሞከር የሚፈልግ ከሆነ እነዚህን ህግጋቶች መከተል ይገባዋል፡፡ እንደ ፈቃዱ የሚያደርግ ከሆነ ግን እንዴት ሀሳቡን ለመቆጣጠር ይችላል? ሀሳባችንም በመጨረሻ የተገራ ከሆነ እና ትኩረቱ ሁሉ ወደ ዓብዩ ሽሪ ክርሽና ከሆነ ሙሉ ሰላም እና ረጋ ያለ መንፈስ ይኖረናል፡፡

ፕራሻንታ ማናሳም ሂ ኤናም
ዮጊናም ሱክሀም ኡታማም
ኡፓቲ ሻንታ ራጃሳም
ብራህማ ብሁታም አካልማሳም

“አንድ ዮጊ የሆነ ሰው ሙሉ ልቦናውን በእኔ ላይ ብቻ ለማተኮር የበቃ ከሆነ ከሁሉም በላይ የሆነውን ደስታ ለማግኘት ይችላል፡፡ ይህንንም ዓይነት የመንፈስ ደስታ ላይ ሲሆንም ከዚህ ቁሳዊ ዓለም መንፈስ ነፃ የወጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ሀሳቡም ሳታወላውል በሰላም ላይ ትገኛለች፡፡ ለቁሳዊው ዓለም ያለው የጋለ ፍላጎቱ ሁሉ ቀዝቅዞ ይገኛል፡፡ ከሀጥያትም ነፃ ሆኖ ይገኛል፡፡” (ብጊ፡ 6.27)

ሀሳባችን በየጊዜው የተለያዪ ቁሳዊ አካሎችን በመጠቀም ደስታን ለመፍጠር ጥረት ያደርጋል፡፡ እንዲህም ብለን እናስባለን፡፡ “ይህ ደስታን ሊሰጠኝ ይችላል” ወይም “ያ ሊያስደስተኝ ይችል ይሆናል፡፡ እዚህ ወይም እዚያ ብሄድ ደስታን ላገኝ እችላለሁ፡፡” በማለት ሀሳባችን ሁልጊዜ በየቦታው ሲጐትተን ይገኛል፡፡ ይህም የሚመሰለው ባልተለጐመ የፈረስ ጋሪ ላይ እንደተቀመጠ እና እንደሚጓዝ ሰው ነው፡፡ በዚህም ጋሪ ላይ ተቀምጦ የሚገኝ ሰው ፈረሱ ወዴት እንደሚወስደው ለመቆጣጠር ምንም ሀይል የለውም። ነገር ግን በዝምታ እና በጭንቀት ቁጭ ብሎ ወዴት እንደሚሄድ ማየት ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው በክርሽና ንቃት ላይ የተሰማራ ከሆነ ግን እነዚህን እንዳልተለጐመ ፈረስ የሚጋልቡትን ሀሳቦች ሁሉ በቀላሉ ለመግራት ሀይሉ ይኖረዋል፡፡ ይህንንም የክርሽና ንቃት በቀላሉ ለማዳበር የሚቻለው የዓብዩ ሽሪ ክርሽናን ቅዱስ ስም ለዘወትር በመዘመር ነው፡፡ “ሀሬ ክርሽና ሀሬ ክርሽና ክርሽና ክርሽና ሀሬ ሀሬ፡ ሀሬ ራማ ሀሬ ራማ ራማ ራማ ሀሬ ሀሬ” ይህንንም ፈለግ በመከተል እራሳችንን በዓብዩ ሽሪ ክርሽና አገልግሎት ላይ መላ ሕይወታችንን ማሰማራት ይገባናል፡፡ ይህም ረጋ ያለ መንፈስ የሌለውን እና ከዚህ ወደዚያ የሚጎትተንን ሀሳባችንን በቁጥጥር ስር እንድናስውለው ያስችለናል፡፡ አለበለዛ ግን ይህንን የቁሳዊ ዓለም ጊዜያዊ ደስታ ከትውልድ ትውልድ እያሳደድን ፋይዳ በሌለበት የደስታ ምንጭ ላይ ጊዜያችንን በማሳለፍ በከንቱ ሕይወታችንን ስናባክን እንገኛለን፡፡

ይንጃን ኤቫም ሳዳትማናም
ዮጊ ቪጋታ ካልማሳሀ
ሱክሄ ና ብራህማ ሳምስፓርሻም
አትያንታም ሱክሃም አሽኑቴ

“በራሱ መንፈሳዊ ሀሳብ ላይ ብቻ በማተኮር ከቁሳዊ ዓለም መንፈስ ነፃ በመሆን ይህ ዮጊ ከፍተኛውን የደስታ ደረጃ በማግኘት ከላቀው የዓብዩ ጌታ መንፈስ ጋር ተጣምሮ ይገኛል፡፡” (ብጊ፡ 6.28)

በሙሉ ልቦናው ለሚያገለግለው ሰው ሁሉ ሽሪ ክርሽና መጠለያ ሆኖ ይገኛል፡፡ አንድ አገልጋዩ በጭንቀት እና በመከራ ላይ ቢሆንም እንኳን ክርሽና ከዚህ ዓይነቱ ፈተና ሊያድነው ይችላል፡፡ በብሀገቨድ ጊታ እንደተጠቀሰውም ሽሪ ክርሽና የሁሉም ትሁት ጓደኛ ነው፡፡ ይህንንም የዘነጋነውን ጓደኝነት መቀስቀስ ይገባናል፡፡ ይህንንም ለመቀስቀስ የምንችልበት ስርዓት የክርሽና ንቃት እና የአገልግሎት ስርአት ነው፡፡ ይህንን ስርዓት መከተል የዚህን ቁሳዊ ዓለም ተራ የደስታ ምንጭ ለማግኝት ያለንን ትግል እንድናቆም ይረዳናል፡፡ ይህም የቁሳዊ ዓለም የደስታ ጉጉት ከክርሽና እንድንርቅ የሚያደርገን እንቅፋት ነው፡፡ ክርሽና በልባችን ውስጥ በመቀመጥ ሁልጊዜ ወደ እርሱ እንድንመለስ እየጠበቀን ነው፡፡ ቢሆንም ግን እኛ የዚህን ቁሳዊ እና ጊዜያዊ ዓለም ፍራፍሬ በጉጉት በመመገብ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህም ዓለማዊ ጉጉት መቆም ይገባዋል፡፡ እራሳችንንም በመንፈሳዊ ማንነታችን ተመርኩዘን፤ ንፁህ ነፍሳት ሆነን መገኘት ይጠበቅብናል፡፡

« Previous Next »