No edit permissions for Amharic

3

ክርሽናን በሁሉ ቦታ እና ሁልጊዜ ማየት

በህይወታችን ተግባራዊ ኑሮ ውስጥ እያለን ክርሽና መንፈሳዊ ንቃታችንን እንዴት ለመቀስቀስ እንደምንችል ሲመራን ይገኛል፡፡ ይህንንም ንቃት ለማዳበር ሀላፊነታችንን ወይም ስራችንን መስራት ማቆም ማለት ሳይሆን የምንሰራውን ስራ ሁሉ ከክርሽና ንቃታችን ጋር አዛምደን መስራት ይገባናል ማለት ነው፡፡ እያንዳዳችን በተለያዩ ሙያዎች ላይ ተሰማርተን እንገኛለን፡፡ ነገር ግን በስራ የተሰማራነው ምን ዓይነት መንፈስ ይዘን ነው? ሁሉም የሚያስበው እንዲህ እያለ ነው፡፡ “ቤተሰቤን ለማስተዳደር እንድችል ሙያ መያዝ ይገባኛል፡፡” በእርግጥ ሕብረተሰብን፣ መንግስትንም ሆነ ቤተሰብን ለማስደሰት መጣር ይኖርብናል፡፡ ማናችንም ብንሆን ከዚህ ዓይነቱ ሀላፊነት ለመራቅ አንችልም፡፡ ቢሆንም ግን አንድ ሰው ሀላፊነቱን በትክክል ለመወጣት የሚችልበትን ንቃት ወይም አንደበት እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ ረጋ ያላለ አንደበት ያለው ሰው እንደ እብድ በመሯሯጥ ሀላፊነቱን በትክክል ሊወጣ አይችልም፡፡ ስለዚህም ሀላፊነታችንን በትክክል ለመወጣት ትክክለኛው ንቃት እንዲኖረን ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ትክክለኛ ሀላፊነት ለመወጣት የሚያስችለን ንቃት ዓለማዊ አንደበታችንን ለውጠን ክርሽናን ለማስደሰት ስንጥር ነው፡፡ የተመደበልንም የስራ ሀላፊነት መቀየር አለብን ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ለማን እንደምንሰራ እና ማንን ለማስደሰት መጣር እንደአለብን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ የተመደበልንን መደበኛ ስራ ማቋረጥ አይገባንም፡፡ ቢሆንም ግን በካማ ወይም በጋለ የግል ስሜታዊ ፍላጎት ለማርካት የተመሰረተ ስራ መሆን አይገባውም፡፡ ይህ በሳንስክሪት ቋንቋ የተገለፀው ቃል “ካማ” ማለት የጋለ የግል ስሜታዊ ፍላጎት ማለት ነው፡፡ ሽሪ ክርሽናም እንደገለፀልን የምንሰራው ስራ ሁሉ በካማ ወይም በግል የጋለ ፍላጎት የተመሰረተ መሆን አይገባውም፡፡ የብሀገቨድ ጊታም ትምህርት የተመሰረተው በዚሁ መመሪያ ነው፡፡

ለምሳሌ አርጁና በጦር ሜዳ ላይ ለውጊያ ቀርቦ እያለ ከዘመዶቹ ጋር ላለመዋጋት እና የግል ስሜቱን ለማርካት ከውጊያ አሻፈረኝ ለማለት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ሽሪ ክርሽና የአብዩ የመንግስተ ሰማያትን ጌታ ፍላጎት ለሟሟላት የተሰጠውን የጦርነት ሀላፊነት መወጣት እንደሚገባው አስገንዝቦት ነበር፡፡ በዓለማዊ መንገድ ስናየው ዘመዶቹን በመዋጋት መንግስትን ለመውረስ ፍላጎት እንደሌለው መግለጹ የሚያስከብር አቋም ይመስላል፡፡ ነገር ግን ሽሪ ክርሽና ይህንን አቋም አልደገፈለትም፡፡ ምክንያቱም የጦርነቱን ዓላማ ይዞ ግብ ለመምታት ሳይሆን የግል ጥቅሙን ለሟሟላት በመነሳሳቱ ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ልክ የአርጁና ጦረኝነት ክርሽናን ለማስደሰት እንደተቀየረም ሁሉ አንድ ሰው የሚሰራውን ስራ ማቆም አያስፈልገውም፡፡ መቀየር የሚያስፈልገው ግን ሁሌ የራሳችንን ስሜት ለማርካት ጥረት ከማድረግ ይልቅ የአብዩን የመላእክት ጌታ ፍላጎት ማርካትን ነው፡፡ ይህንንም ህልውናችንን ለመቀየር መንፈሳዊ እውቀት ያስፈልገናል፡፡ ይህም እውቀት ሁላችን የዓብዩ የመላእክት ጌታ ሀይል ቅንጣፊ አካላት መሆናችንን መገንዘብ ነው፡፡ ይህም ትክክለኛ ፍጹም የሆነ እውቀት ነው፡፡ ፍጹም ያልሆነ እውቀት ማሽንን እንዴት መጠገን እንደምንችል ያስተምረን ይሆናል፡፡ ፍጹም የሆነው እውቀት ግን የእኛ ፍጥረት ለዘለዓለም ከዓብዩ የጌታ ሽሪ ክርሽና ጋር ተነጥሎ ሊታይ እንደማይችል ማወቅን ነው፡፡ የእርሱም ቅንጣፊ አካል በመሆናችን የእኛ የጎደለው ደስታ ሊሟላ የሚችለው ሙሉ የሆነው የዓብዩ ጌታ ፍቅር ሲጨመርበት ነው፡፡ ለምሳሌ የእኔ እጅ ሊደሰት የሚችለው ከገላዬ ጋር እስከተያያዘ እና ገላዬን እሰካገለገለ ድረስ ነው፡፡ እጄ ሌላ ሰውን ብቻ በማገልገል ገላዬን ለማስደሰት አይችልም፡፡ እኛም የዓብዩ ጌታ ቅንጣፊ አካል በመሆናችን የእኛም ደስታ ሊመነጭ የሚችለው ዓብዩ ጌታን በማገልገል ነው፡፡ “አንተን በማገልገል ብቻ ደስታን አላገኝም” በማለት ሁሉም ሰው ሊያስብ ይችላል፡፡ “እኔ ልደሰት የምችለው እራሴን ብቻ በማገለገል ነው፡፡” ነገር ግን ይህ እኔ ራሴ የምንለው ማንን ነው? ይህም እኔ ራሴ የምንለው ነፍስን ወይም የክርሽናን ቅንጣፊ አካልን ነው፡፡

ማማይቫምሶ ጂቫ ሎኬ
ጂቫ ብሁታ ሳናታናሀ
ማናህ ሻሽትሀኒንድሪያኒ
ፕራክርቲ ስትሃኒ ካርሳቲ

“በዚህ ውስን ዓለም የሚገኙት ነዋሪ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ቅንጣፊ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህም ነፍሳት በዚህ በውስን ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ሀሳብን ከሚጨምረው ከስድስቱ ዓይነት ስሜቶች ጋር ብዙ ትግል ሲያደርጉ ይገኛሉ፡፡” (ብጊ፡ 15.7)

እነዚህም ጂቫዎች ወይም ነፍሳት በቁሳዊው ዓለም ግኑኝነት ምክንያት ከሙሉው የዓብዩ ጌታ አካል ተነጥለው ይኖራሉ፡፡ስለዚህም እራሳችንን መልሰን ከሙሉው የዓብዩ አካል ጋር ለማገናኘት በውስጣችን ያለውን የክርሽና ንቃታችንን በማዳበር ትጉህ ጥረት ማድረግ ይገባናል፡፡ ሰው ሰራሽ በሆነ መንገድ አብዩን ሽሪ ክርሽናን ረስተን እና ተነጥለን ለመኖር ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህም የማያዛልቅ ነው፡፡ ከዓብዩ ሽሪ ክርሽና ተነጥለን ለመኖር ስንሞክር በቁሳዊው ዓለም ሀይል ቁጥጥር እና ሕግ ስር እንውላለን፡፡ አንድ ሰው ከሽሪ ክርሽና ተነጥሎ የሚያስብ ከሆነ የሀሰት ራዕይ በተሞላበት የሽሪ ክርሽና የቁሳዊው ዓለም ሀይል ቁጥጥር ስር ይውላል፡፡ ይህም የሚመሰለው ልክ አንድ ሰው ከመንግስት ህግጋት ውጪ ተነጥሎ የሚያስብ ከሆነ በመንግስት የፖሊስ ሀይል ቁጥጥር ስር እንደሚውለው ነው፡፡ በዚህ ዓለም የሚገኙ ነፍሳት ሁሉ ተነጥለው ለመኖር ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ ይህም “ማያ” ወይም የሀሰት ራዕይ ይባላል፡፡ በግል፣ በአንድነት፣ በህብረተሰብም ሆነ በብሄርም ወይም በአጠቃላይ በዚህ ትእይንተ ዓለም ውስጥ ከዓብዩ ሽሪ ክርሽና ተነጥሎ ለመኖር አያዛልቅም፡፡ በዓብዩ ሽሪ ክርሽና መመካት እና ጠለላ ማድረግ እንዳለብን ስንረዳ እውቀት ያዝን ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ብዙ ሰዎች ሰላምን ለማግኘት ብዙ ጥረት ሲያደርጉ ይገኛሉ፡፡ ቢሆንም ግን ይህንን የሰላም ቀመር ወይም ፎርሙላ እንዴት እንደሚጨምሩበት እውቀቱ የላቸውም፡፡ የተባበሩት መንግስታትም ይህንን ሰላም በምድር ለመፍጠር ብዙ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ቢሆንም ግን ብዙ ጦርነት ሲካሄድ እናያለን፡፡

ያክ ቻፒ ሳርቫ ቡታናም
ብጃም ታድ አሀም አርጁና
ና ታድአስቲ ቪና ያት ስያን
ማያ ብሁታም ቻራቻራም

“በተጨማሪም፡ አርጁና ሆይ፡ እኔ የፍጥረታት ዘሮች ሁሉ ዋና መነሻ ነኝ፡፡ ምንም ዓይነት ተንቀሳቃሽም ሆነ የማይንቀሳቀሱ ፍጥረታት ከእኔ ውጪ ለመኖር አይችሉም፡፡” (ብጊ፡ 10.39)

ዓብዩ ሽሪ ክርሽና የመላ ትእይንተ ዓለም ባለቤት ከሁሉም በላይ ተመጋቢ እና የውጤቶች ሁሉ ተቀባይ ነው፡፡ እኛም የድካማችን ሁሉ ተመጋቢዎች ነን ብለን እናስብ ይሆናል፡፡ ይህም የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው፡፡ መገንዘብ የሚገባንም ነገር ቢኖር ክርሽና የሁሉ ነገር ባለቤት በመሆኑ በድካማችን ውጤት ተደሳች መሆን የሚገባው እርሱ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በቢሮ ውስጥ ሲሰሩ ይገኙ ይሆናል፡፡ የመስሪያ ቤቱም የንግድ ትርፍ ወደ ባለቤቱ እንደሚሄድ እና ለባለቤቱ እንደሚገባ ሰራተኞቹ ሁሉ የተገነዘቡ ናቸው፡፡ ቢሆንም ግን በባንክ ውስጥ ለምሳሌ ገንዘብ ተቀባይዋ “ብዙ ገንዘብ በእጄ አለ ሀላፊውም እኔው ነኝ” በማለት ገንዘቡን ወደ ቤትዋ ብተወስደው ችግር እንደሚመጣባት የተረጋገጠ ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የሰበሰብነውን ገንዘብ ሁሉ ለእራሳችን የስሜት እርካታ እንጠቀምበታለን ብለን የምናስብ ከሆነ በግል ጥቅም የተነሳሳ የጋለ ፍላጎት ወይም ካማ የተመሰረተበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በእኛ ቁጥጥር ስር ያለው ነገር ሁሉ የክርሽና ሀብት እንደሆነ የምንረዳ ከሆነ ነፍሳችን ነፃ የወጣች ናት ማለት ነው፡፡ ይህንንም ሀብት በእጃችን ይዘን እኛው እራሳችን የዚህ ሀብት ባለቤት ነን ብለን የምናስብ ከሆነ እኛ በማያ ወይም በፈጣሪ የቁሳዊ ዓለም ቁጥጥር ስር እንደሆንን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ አዋቂ ወይም ትክክለኛ ምሁር ሰው የሚባለው በዓለም ላይ የሚገኙት ፍጥረታት ሁሉ የዓብዩ የመንግስተ ሰማያት ጌታ ሽሪ ክርሽና መሆናቸውን የተረዳ ከሆነ ነው፡፡

ኢሻቫስያም ኢዳም ሳርቫም
ያት ኪንቻ ጃጋትያም ጃጋት
ቴና ትያክቴና ብሁንጂትሀ
ማ ግርድሃህ ካስያ ስቪድ ድሀናም

“በዚህ ትእይንተ ዓለም ውስጥ ለሚገኙት ተንቀሻቃሽም ሆኑ የማይንቀሳቀሱ ነገሮች ሁሉ ባለቤታቸው እና ተቆጣጣሪያቸው ዓብዩ የመላእክት ጌታ ነው፡፡ ስለዚህም አንድ ሰው በዚህ ዓለም ላይ መቀበል ያለበት ለእራሱ የሚበቃውን፣ የሚያሰፈልገውን እና የተመደበለትን ብቻ ሲሆን አልፎ ተርፎ የሁሉም ሀብት ባለቤት ማን እንደሆነ በመረዳት ተጨማሪ ነገሮችን መውሰድ አይገባውም፡፡” (ኢሾ፡ ማንትራ 1)

“ኢሻቫሽያ” ወይም የሁሉም ነገር ባለቤት ዓብዩ ሽሪ ክርሽና መሆኑን መገንዘብ ያለብን እራሳችን ብቻ ሳንሆን ጠቅላላ በአገር እና በዓለም ደረጃ የሚገኙት የሕብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ ናቸው፡፡ በዚህም ዓይነት የዓለም አቀፍ ንቃት በምድር ላይ ሙሉ ሰላም መፍጠር ይቻላል፡፡ በተፈጥሮዋችን ብዙውን ጊዜ በጐ አድራጎት ማድረግ እናዘወትራለን፡፡ ከአገራችን፣ ከሕብረተሰብም፣ ከቤተሰቦቻችን ወይም በዓለም ከሚገኙት የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋርም ጓደኝነትን ለመፍጠር እንጣጣራለን፡፡ ነገር ግን ይህ ጓደኝነት የተመሰረተው ከቁሳዊ ዓለም ጋር በተያያዘ እና በተሳሳተ አንደበት ነው፡፡ ትክክለኛው እና ፍጹም የሆነው ጓደኛ ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና ነው፡፡ ጓደኞቻችንም ወይም የአገራችንን ሕብረተሰብ ወይም ጠቅላላ ምድርን ለመርዳት ከፈለግን እርሱን ማገልገል ይገባናል፡፡ የቤተሰቦቻችንንም ደህንነት የምንሻ ከሆነ የሽሪ ክርሽና ንቃታቸውን ለማዳበር እንዲበቁ ልንረዳቸው ይገባል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ብዙ ጥረት ሲያደርጉ እናያቸዋለን፡፡ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ፍጹም ውጤታማ ሆኖ አያገኙትም፡፡ ችግሩ ምን እንደሆነም ለመረዳት ያዳግታቸዋል፡፡ በቅዱሱ ሽሪማድ ብሀገቨታም ስነጽሁፍ ውስጥም እንደተጠቀሰው “አንድ ሰው ልጆቹን ወይም ተማሪዎቹን ከዚህ ዓለም ተደጋጋሚ ሞት እና ከቁሳዊው ዓለም ሰንሰለት የማያላቅቅ ከሆነ አባት፣ እናት ወይም መምህር መሆን አይገባውም፡፡” አባት በጌታ ክርሽና መንፈሳዊ ንቃት የዳበረ መሆን ይገባዋል፡፡ በተጨማሪም በእርሱ የሚተዳደሩት ገር የሆኑት ልጆቹ ሁሉ ከዚህ ከቁሳዊው ዓለም ተደጋጋሚ መወለድ እና መሞት ነፃ መሆን እንደሚገባቸው በማወቅ በጥብቅ ውሳኔ ልጆቹን ነፃ ለማውጣት ጥረት ማድረግ ይገባዋል፡፡ በዚህም ውሳኔ ፀንቶ ልጆቹ ከዚህ ስቃይ ከተሞላበት የቁሳዊ ዓለም ትውልድ እና ሞት ነፃ እንዲሆኑ ማስተማር እና ማሳደግ ይገባዋል፡፡ ይህንንም ከማድረጉ በፊት ግን እራሱን በዚህ ንቃት ያዳበረ ባለሙያ ማድረግ አለበት፡፡ በዚህም በክርሽና ንቃት እራሱን በደንብ ካዳበረ ልጆቹን ብቻ ሳይሆን የአገሩንም ሕብረተሰብ እና የዓለምን ሕብረተሰብ ሁሉ ሊያነቃ ይችላል፡፡ ነገር ግን እርሱ ራሱ በድንቁርና የተመሰጠ ከሆነ እንዴት አድርጎ ሌሎች በዚሁ ድንቁርና የተመሰጡትን የሕብረተሰብ ክፍሎች ሊያነቃ ይችላል? አንድ ሰው ሌሎችን ነፃ ለማውጣት የሚችለው በመጀመሪያ ደረጃ እራሱን ነፃ ማውጣት ሲችል ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው በቁሳዊው ዓለም የሀሰት ራዕይ ቁጥጥር ስር ስለሚገኝ ነፃ የሆነ ሰው በምድር ላይ ለማግኘት ያዳግታል፡፡ ቢሆንም ግን በክርሽና ንቃት የዳበረ ሰው በማያ ወይም በቁሳዊው ዓለም የሀሰት ራዕይ ሊጠቃ አይችልም፡፡ እርሱም ከሁሉም ሰዎች በላይ ነፃ ሆኖ ይገኛል፡፡ አንድ ሰው በፀሀይ ስር የተቀመጠ ከሆነ ጨለማ የሚባል ነገር በአጠገቡ ሊኖር አይችልም፡፡ ነገር ግን በሰው ሰራሽ መብራት ስር ተቀምጦ ከሆነ በድንገት ይህ ብርሀን ሊሰወር ይችላል፡፡ ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና ልክ እንደ ፀሀይ ይቆጠራል፡፡ ሽሪ ክርሽናም በሚገኝበት ስፍራ ሁሉ ጨለማ እና ድንቁርና ሊኖር አይችልም፡፡ ታላላቅ አዋቂ እና መንፈሳዊ ምሁራን ሁሉ ይህንን በጠራ መንገድ ተገንዝበውት ሲመሰክሩ ይገኛሉ፡፡

አሀም ሳርቫስያ ፕራብሀቮ
ማታህ ሳርቫም ፕራቫርታቴ
ኢቲ ማትቫ ብሀጃንቴ ማም
ቡድሀ ብሀቫ ሳማንቪታሀ

”እኔ የመላ መንፈሳዊ እና የቁሳዊው ዓለም መነሻ ነኝ፡፡ ሁሉም ነገር የሚመነጨው ከእኔ ነው፡፡ ይህንንም በደንብ የተገነዘበው አዋቂ ሰው ከልብ የመነጨውን ትሁት አገልግሎት እና አምልኮት ሲያቀርብልኝ ይገኛል፡፡” (ብጊ፡ 10.8)

በዚህም ጥቅስ ላይ “ቡድሀ” የተባለው ቃል ተጨምሮ እናየዋለን፡፡ ይህም የሚያመለክተው አዋቂ ወይም ታላቅ ምሁርን ነው፡፡ የዚህስ ምሁር አንደበት ምንድን ነው? እርሱም ሽሪ ክርሽና የሁሉም መሰረታዊ ምንጭ እና ሁሉም ነገር ከእርሱ እንደሚፈልቅ በጥራት የተረዳ ሰው ነው፡፡ በዚህ ዓለም የሚያየው ነገር ሁሉ ከዓብዩ ሽሪ ክርሽና የመነጨ መሆኑን በጥራት የተገነዘበ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የሚገኘው ዋናው የደስታ ምንጭ በወሲብ ግኑኝነት የተመሰረተ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም የወሲብ ፍላጎት በሁሉም ፍጥረታት እንደምናገኘውም ሁሉ አንድ ሰው ይህ ከወዴት እንደሚመነጭ ለመረዳት ይሻ ይሆናል፡፡ አዋቂ የሆነው ሰው ይህ የፍቅር ፍላጎት በንጹህ መንፈስ በክርሽና እንደሚገኝ ይገነዘባል፡፡ ይህንንም ንጹህ የሆነ የመንፈሳዊ ፍቅር ግኑኝነት ክርሽና በቭራጃ ይገኙ ከነበሩት ልጃገረዶች ጋር በነበረው ንጹህ የፍቅር ግኑኝነት ለመረዳት እንችላለን፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የምናያቸው ነገሮች ሁሉ በክርሽና እና በመንፈሳዊው ዓለም በንጹህና የጠራ ደረጃ እናገኛቸዋለን፡፡ ልዩነታቸውም በዚህ ቁሳዊ ዓለም ላይ የምናገኛቸው ነገሮች በሙሉ ከመንፈሳዊው ዓለም የተገላቢጦሽ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ በክርሽና ውስጥም እነዚህ ባህሪያቶች ሁሉ በንጽህና መንገድ እና በጠራ መንፈስ እናገኛቸዋለን፡፡ ይህንንም በጠራ መንገድ እና በሙሉ እውቀት የተረዳ ሰው ንጹህ የክርሽና አገልጋይ ሊሆን ይችላል፡፡

ማሀትማናስ ቱ ማም ፓርትሀ
ዳይቪም ፕራክርቲም አሽሪታሀ
ብሀጃንቲ አናንያ ማናሶ
ግያትቫ ብሁታዲም አቭያያም

ሳታታም ኪርታያንቶ ማም
ያታንታሽ ቻ ድርድሀ ቭራታሀ
ናማስያንታሽ ቻ ማም ብሀክትያ
ኒትያ ዩክታ ኡፓሳቴ

”ኦ የፕርትሀ ልጅ ሆይ በዚህ ዓለም ያልተታለሉት እና የበለፀጉት አዋቂ ነፍሳት ሁሉ በመንፈሳዊው ጥላ ስር በእንክብካቤ ላይ ሆነው ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ሰዎች በሙሉ ልቦናቸው እኔን የሚያገለግሉት የእኔን አብይ የመንግስተ ሰማያት ጌትነት፣ የሁሉም ዋና መነሻ እና ከድክመት ነፃ መሆኔን በመረዳታቸው ነው፡፡ የእኔንም ዝና ሁሌ ሲያወድሱ ይታያሉ፡፡ በትጉህ የመንፈሳዊ ጥረት እና አምልኮት እነዚህ ታላላቅ ነፍሳት በሙሉ ልቦናቸው ለእኔ በመስገድ በፍቅር አግንነውኝ ለዘለዓለም ሲያገለግሉኝ ይታያሉ፡፡” (ብጊ፡ 9.13-14)

ይህስ “ማሀትማ” የተባለው ታላቅ ነፍስ ማነው? ይህም ሰው በከፍተኛው የመንፈሳዊው ሀይል የሚመራው ሰው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እኛ በክርሽና የዝቅተኛው ቁሳዊ ዓለም ሀይል ቁጥጥር ስር እንገኛለን፡፡ በተፈጥሮ እንደ ህያው ነፍስነታችን ደረጃችን ማእከላዊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ማለት እራሳችንን በክርሽና የሁለቱ ዓይነት ሀይላት በማናቸውም ጊዜ እንደፍላጎታችን የማዘዋወር መብት ተሰጥቶናል፡፡ (ዓለማዊ እና መንፈሳዊ)ክርሽና በማንም የማይተማመን ነፃ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እኛም የክርሽና ቅንጣፊ አካላት በመሆናችን ነፃ የመሆን አዝማሚያ አለን፡፡ ስለዚህም በየትኛው ሀይል ለመተዳደር እንደምንፈልግ የመምረጥ እድል አለን፡፡ በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥም ሆነን ስለ ሽሪ ክርሽና ከፍተኛ ሀይሉ ንቃት ሳይኖረን በድንቁርና ውስጥ ስለምንገኝ በዚህ በክርሽና ዝቅተኛው የቁሳዊ ዓለም ሀይል ተጠምደን እንገኛለን፡፡

አንዳንድ ፈላስፋዎች እዚህ ከምናየው ዓለም ውጪ ሌላ ዓለም የለም ብለው ያስተምራሉ፡፡ ይህንም የቁሳዊ ዓለም ችግር ለመወጣት ሕይወታችንን ባዶ በማድረግ እና እራሳችንን ባዶ ማድረግ ነው ብለው ያስተምራሉ፡፡ ነገር ግን ነፍሳት ዘለዓለማዊ ስለሆኑ ባዶ የሆነ ሕይወት ሊይዙ አይችሉም፡፡ በሞት ጊዜም ገላችን ተቀየረ እና ሕይወታችን ባዶ ሆነ ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ ከቁሳዊ ዓለም ቁጥጥር ነፃ ለመውጣት ከመጣራችን በፊት የምንሄድበት ቦታችን ወዴት እንደሆነ በመጀመሪያ ደረጃ መረዳት ይገባናል፡፡ መሄድ የምንፈልግበትን ቦታ የማናውቅ ከሆነ ግን እንዲህ የሚል አስተሳሰብ ይኖረናል፡፡ “ኦ ከፍተኛ እና ዝቅተኛው የተፈጥሮ ሀይል ምን እንደሆነ አናውቅም፡፡ የምናውቀውም ይህንን ቁሳዊ ዓለም ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ እዚሁ ቀርተን መክረሙን እና ማርጀቱን እንመርጣለን፡፡” ነገር ግን በብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መፅሀፍ ውስጥ ስለከፍተኛው እና ስለዝቅተኛው ሀይል ዓብዩ ጌታ በግልጽ መረጃውን ሰጥቶናል፡፡

በብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መጽሀፍ ውስጥ ሽሪ ክርሽና የተናገራቸው ቃላት በሙሉ ዘለዓለማዊነት ያላቸው፣ እውነት እና ፍጹም ሊቀየሩ የማይችሉ ናቸው፡፡ በምንም ዓይነት ሙያ ላይ ተሰማርተን ብንሆንም ወይም ምንም እንኳን አርጁና የጦር ሀይል ስራ ላይ ተሰማርቶ ቢገኝም መንፈሳዊ ለመሆን የሚያስፈልገን ንቃታችንን መቀየር እንጂ ሙያችንን መቀየር አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የግላችንን ስሜት ለማርካት በተመሰረተ ንቃት ላይ እንገኛለን፡፡ ቢሆንም ግን የግላችንን ፍጹም የሆነውን ስሜት እንዴት ለማርካት እንደምንችል ዘንግተነዋል፡፡ በመሰረቱ የግል ፍላጎት የለንም፡፡ ያለን ግን ዓለማዊ ስሜቶቻችንን የማርካት ፍላጎት ነው፡፡ መቀየር የሚገባንም ይህን ዓይነቱን ንቃታችን ነው፡፡ ይህንንም ፍጹም የሆነውን የግል መንፈሳዊ ፍላጎታችንን የሚያረካውን ንቃት መመስረት ይገባናል፡፡ ይህም ነፍሳችን በክርሽና ንቃት እንድትዳብር ማድረግ ነው፡፡

ይህስ እንዴት ሊከናወን ይችላል? በሕይወታችንስ በእያንዳንዱ ደረጃ ላይ እንዴት አድረገን የክርሽናን ንቃት ለማዳበር እንችላለን? በመሰረቱ ይህንን ለሟሟላት ክርሽና ቀላል አድርጎልናል፡፡

ራሶ ሀም አፕሱ ኮንቴያ
ፕራብሀስሚ ሻሺ ሱራዮህ
ፕራናቫህ ሳርቫ ቬዴሹ
ሻብዳህ ክሄ ፖሩሻም ንርሹ

”ኦ የኩንቲ ልጅ ሆይ (አርጁና) እኔ በውሀ የምገኝ ጣእም ነኝ፤ የፀሀይ እና የጨረቃ ብርሀን፤ በቬዲክ ጥቅሶች “ኦም” የተባለው ቃል፤ በሕዋ የሚገኘው ድምጽ እና በሰው ልጅ የሚገኘው ብቁነት ሁሉ እኔው ነኝ፡፡” (ብጊ፡ 7.8)

በዚህም ጥቅስ ውስጥ በሕይወታችን በሚገኘው በእያንዳንዱ ደረጃ ላይ እንዴት ሙሉ በሙሉ የክርሽና ንቃታችንን ለማዳበር እንደምንችል ሽሪ ክርሽና ግልጽ የሆነውን መረጃ ሰጥቶናል፡፡ በምድር ላይ የሚገኙት ነዋሪ ነፍሳት ሁሉ ውሀ መጠጣት የግድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የውሀም ጣእም የተለየ እና በጣም የሚያረካ ስለሆነ በጥማት ጊዜ ከንጹህ ውሀ ሌላ በጣም ሊያረካን የሚችል ፈሳሽ አይገኝም፡፡ በምድር ላይ ማንም በምርት ላይ የተሰማራ የንግድ ሰው እንደ ውሀ ጥማት ለማርካት የሚችል ፈሳሽ ነገር ለማምረት አይችልም፡፡ ስለዚህ በቀን በቀን ውሀ ጠጥተን እርካታውን በአገኘነው ቁጥር ሁሉ ፈጣሪ ጌታን ማመስገን እና ማስታወስን እንችላለን፡፡ በሕይወቱ በእያንዳንዱ ደረጃ ላይ ማንም ሰው ውሀን ከመጠጣት ሊቆጠብ አይችልም፡፡ ስለዚህም ፈጣሪ አምላክን ለማወደስ በእያንዳንዱ የሕይወታችን ምዕራፍ ውስጥ ዕድል ያለን መሆኑን መገንዘብ ይገባናል፡፡ ይህስ ዕድል እያለን እንዴት ዓብዩ አምላክን ለመርሳት እንችላለን?

እንደዚሁም ሁሉ ብርሀን በታየ ቁጥር ሽሪ ክርሽና እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ ብራህማጆይቲ ተብሎ የሚታወቀው በመንፈሳዊው ዓለም የሚገኘው የብርሀን ጮራ የሚመነጨው ከሽሪ ክርሽና አካል ነው፡፡ ይህ የምንገኝበት ቁሳዊው ዓለም ግን ከዚህ ጮራ ተሽፍኖ ይገኛል፡፡ የቁሳዊው ዓለም ፍጥረት በተፈጥሮ ጨለማ የሞላበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህንንም ፍጥረት በምሽት ጊዜ በቀላሉ ልንገነዘበው እንችላለን፡፡ ይህም ጨለማ ቁሳዊ ዓለም እንደ ሰው ሰራሽ ፍጥረት ቀን በፀሀይ ማታ በጨረቃ እና በኤሌክትሪክ ሀይል ብርሀን የሚሰጥ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ታድያ ይህ ብርሀን ወደዚህ ዓለም የሚንፀባረቀው ከወዴት መንጭቶ ነው? ፀሀይ የብርሀን ሀይል የምታገኘው ብራህማጆይቲ ከሚባለው ከመንፈሳዊው ዓለም የሚመነጨው የብርሀን ጮራ ነው፡፡ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ምንም ዓይነት ፀሀይ ጨረቃ ወይም ኤሌክትሪክ አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም በመንፈሳዊው ዓለም ሁሉም ብርሀን የሚቀርበው በብራህማጆይቲ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ምድር ላይ የፀሀይን ጮራ በቀን በቀን ባየን ቁጥር ዓብዩ የመንግስተ ሰማያትን ጌታ ሽሪ ክርሽናን ለማስታወስ እንችላለን፡፡

የቬዲክም ማንትራ ወይም ጥቅሶች ሁልግዜ የሚጀምሩት “ኦም” በተባለው ቅዱስ ቃል ነው፡፡ እነዚህም ጥቅሶች በተደገሙ ቁጥር ሽሪ ክርሽና “ኦም” በሚለው ድምጽ ተወክሎ ስለሚገኝ ሁሌ ልናስታውሰው እንችላለን፡፡ “ኦም” የሚለው ቃል እንደ “ሀሬ ክርሽና” የቅዱስ ስም ዓብዩ አምላክን የምናወድስበት ቃል ነው፡፡ “ኦም” የተባለው ቃል ሽሪ ክርሽና እራሱ በድምፅ ተወክሎ የሚገኝበት ነው፡፡ “ሻብዳ” ማለት ድምፅ ማለት ሲሆን በማናቸውም ጊዜ ማናቸውንም ዓይነት ድምፅ ስንሰማ ከዋናው መንፈሳዊው ንፁህ ድምጽ “ኦም” ወይንም የሀሬ ክርሽና ቅዱስ ስም ድምፅ ተወራርዶ የመጣ ድምፅ እንደሆነ መረዳት ይገባናል፡፡ በዚህ ቁሳዊ ዓለም የምናገኘው ድምፅ ሁሉ ከዚሁ ከዋናው መንፈሳዊ ድምፅ “ኦም” ተንፀባርቆ የመጣ ድምፅ ነው፡፡ ይህንንም ፈለግ ተከትለን በማናቸውም ጊዜ ድምፅ በሰማን ቁጥር፣ ወሀ በጠጣን ቁጥር፣ ብርሀን ባየንም ቁጥር ሁሉ ዓብዩ የመንግስተ ሰማያትን ጌታን ለማስታወስ እንችላለን፡፡ የዓብዩ ጌታ የሽሪ ክርሽና ንቃት ማለት ይህው ነው፡፡ በዚህም ስርዓት ዓብዩ ጌታ ክርሽናን ለ24 ሰዓት ለማስታወስ እንችላለን፡፡ በዚህም መንገድ ዓብዩ የመላእክት ጌታ ሽሪ ክርሽና ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ ሽሪ ክርሽና ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ነው፡፡ ቢሆንም ግን ይህንን ስርዓት በመከተል ክርሽና ሁልጊዜ በአጠገባችን ሆኖ በውን እንዳለ ሊሰማን ይችላል፡፡

በቬዲክ ቅዱስ ስነጽሁፎች እንደተገለጸውም ከዓብዩ አምላክ ጋር ለመቅረብ ዘጠኝ ዓይነት ስርዓቶች ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያውም ስርዓት “ሽራቫናም” ወይም ማዳመጥ ይባላል፡፡ ብሀገቨድ ጊታን በማንበብ የሽሪ ክርሽናን ንግግር አዳመጥን ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ከዓብዩ ከሽሪ ክርሽና ጋር በቅርበት ተዋሀድን ማለት ነው፡፡ (ክርሽና በማለት በጠቀስን ጊዜ ሁሉ ይህ ስም የሚያመለክተው ዓብዩ የመንግስተ ሰማያትን ጌታ ፈጣሪ አምላክን ነው፡፡) ከዓብዩ ጌታ ጋርም ቀርበን በመንፈሳዊ ንቃት በዳበርን ቁጥር እና ስለ ክርሽና ቃላቶች ስም እና ታሪክ ባዳመጥን ጊዜ ከቁሳዊው ዓለም የወረስነው የተበከለ አስተሳሰብ ሁሉ እየቀነሰ እና እየፀዳ ይመጣል፡፡ ሽሪ ክርሽናም በድምፅ፣ በውሀ፣ በብርሀን እና በሌላ ብዙ ፍጥረታት የተወከለ መሆኑን ስንረዳ ክርሽናን ለመርሳት ወይም ለመራቅ አንችልም፡፡ ሽሪ ክርሽናንም በእንደዚህ ዓይነት መንገድ ሁሌ የምናስታውሰው ከሆነ ከእርሱ ጋር ያለን ንቃት ዘለቄታ ያለው ይሆናል፡፡

ከክርሽና ጋር መጐዳኘት ልክ የፀሀይ ብርሀንን እንደ መቅረብ ይቆጠራል፡፡ ፀሀይ በምትንፀባረቅበት ቦታ ሁሉ የመበስበስ ባህርይ የለም፡፡ አንድ ሰው በፀሀይ ጮራ ስር ዘወትር የሚገኝ ከሆነ ከብዙ ህመሞች ለመዳን ወይም ላለመጋለጥ ይበቃል፡፡ በምዕራባውያን የመድሀኒት መፍትሄዎችም እንደምናየው የፀሀይ ጮራ ለተለያዩ ህመሞች እንደ መድሀኒት ሲታዘዝ እናያለን፡፡ በቬዲክ ስርዓትም በህመም የተበከለ ሰው ለመዳን ከፈለገ ፀሀይን በማምለክ እንዲድን መፍትሄው ተሰጥቶታል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ እኛም ከክርሽና ጋር በመጐዳኘት እና የክርሽና ንቃታችንን በማዳበር ከቁሳዊው ዓለም ህመማችን ለመዳን እንችላለን፡፡ የሀሬ ክርሽናንም ቅዱስ ስም በመዘመር ከክርሽና ጋር በቀላሉ ለመጐዳኘት እንችላለን፡፡ ውሀንም በማየት፣ ፀሀይን እና ጨረቃንም በማየት፣ ክርሽናን ማየት እና ማስታወስ እንችላለን፡፡ ክርሽናን በድምጽ ለመስማት እንችላለን ወይም የውሀ እርካታንም በማግኘት ክርሽናን ማጣጣም እንችላለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ክርሽናን የዘነጋንበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ይህንን የመንፈሳዊ ንቃታችንን በመቀስቀስ እና በማዳበር ክርሽናን የምናስታውስበትን መንገዶችን ማሰላሰል ይገባናል፡፡

ይህ ሽራቫናም ኪርታናም (ሽብ፡7 5 23) የተባለው ስርዓት ወይም ማዳመጥ እና መዘመር በጌታ ቼይታንም የተደገፈ ስርዓት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ጌታ ቼታንያ ከራማናንዳ ሮይ ከተባለው ትሁት አገልጋዩ እና ጓደኛው ጋር ንግግር ሲያደርግ ስለ መንፈሳዊ ንቃት እውቅና ስርዓቱ ምን እንደሆነ ጠይቆት ነበር፡፡ ራማናንዳም መልስ ሲሰጠው ስለ ቫርናሽራማ ድሀርማ፣ ሳንያሳ ወይም ምንኩስና መውሰድ እና ከስራ ሀላፊነት መውጣት እንዲሁም ሌሎች ስርዓቶችን ነግሮት ነበር፡፡ ነገር ግን ጌታ ቼታንያ እንዲህ አለው፡፡ “አይደሉም፡፡ እነዚህ ሁሉ ጥሩ አይደሉም፡፡” ብሎ ነገረው፡፡ በእያንዳንዱም ጊዜ ራማናንዳ ስርዓቶችን በተናገረ ጊዜ ጌታ ቼታንያ አላፀደቀውም ነበር፡፡ በየጊዜውም ሌላ የተሻለ ስርዓት አምጣ በማለት ደጋግሞ ይጠይቀው ነበር፡፡ በመጨረሻም ራማናንዳ ሮይ ከቬዲክ ስነፅሁፍ ጥቅስ በመውሰድ አንድ ሰው አምላክን ለማወቅ በግምታዊ ምርምር ጥረት ማድረግ ማቆም እንደሚገባው ተናገረ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዓይነት ግምት በተሞላበት ምርምር ማንም ሰው ፍፁም የሆነውን እውነት ለማግኘት አይችልም፡፡ ለምሳሌ ሳይንቲስቶች በሩቅ ሰለሚገኙት ኮከቦች እና ፕላኔቶች ግምት በተሞላበት ምርምር ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በትክክለኛ መንገድ ባልተገኘ እውቀት ምንም ዓይነት ድምደማ ላይ ሊደርሱ አይችሉም፡፡ አንድ ሰው ሕይወቱን በሙሉ በግምታዊ ምርምር ሊያጠፋ ይችላል ነገር ግን ምንም ዓይነት ውሳኔ ላይ ሊደርስ አይችልም፡፡

በተለይ ስለ ዓብዩ ፈጣሪ አምላክ ግምታዊ ምርምር ማድረግ ጥቅም የሌለው ልፋት ነው፡፡ ስለዚህም የሽሪማድ ብሀገቨታም ቅዱስ መጽሀፍ እንደሚገልጽልን ሁሉም ዓይነት የግምታዊ ምርምሮች መቆም አለባቸው፡፡ የተሰጠውም ትእዛዝ አንድ ሰው ትሁት መሆን እንደሚገባው እና እራሱንም ከምንም ሳይቆጥር እና ይህች የምንኖርባት መሬት ከትእይንተ ዓለም ጋር ስትወዳደር ከነጥብ በታች እንደሆነች በመንገዘብ በትሁትነት አምላክን መስማት እና ማገልገል ያስፈልገዋል፡፡ የኒው ዮርክ ከተማ በጣም ትልቅ ሆኖ ሊሰማን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከትእይንተ ዓለም ጋር ሲወዳደር ምድር ከነጥብ በታች እንደሆነች እንረዳለን፡፡ በትልቋ ምድር ላይም አሜሪካ ትንሽ መሆንዋን እንረዳለን፡፡ በትልቁ አሜሪካም ኒው ዮርክ ትንሽ መሆንዋን እንረዳለን፡፡ በኒው ዮርክም ውስጥም ከሚገኙት ስንት እና ስንት ሚሊዮን ሰዎች አንድ ሰው ከምንም እንደማይቆጠር እንረዳለን፡፡ እነዚህንም ሁሉ ስንገነዘብ ምን ያህል ትሁን መሆን እንደሚገባን ለመረዳት እንችላለን፡፡ ይህንን ዝቅተኛነታችንን ከትእይንተ ዓለሙ እና ከፈጣሪ አምላክ ጋር በማወዳደር እና ትምህርት በመውሰድ ልባችን በኩራት ሳይደለል ዓብዩ ጌታን በትሁትነት መቅረብ እና በፍቅር ማገልገል ይገባናል፡፡ ወደ እንቁራሪትም ፍልስፍና ውስጥ በመግባት ወጥመድ ውስጥ እንዳንገባ መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ አንድ ጊዜ በኩሬ ውስጥ አንድ እንቁራሪት ይኖር ነበር፡፡ ሌላው እንቁራሪት ጓደኛውም አትላንቲክ ውቅያኖስ የሚባለውን አይቶ እንደመጣ አጫወተው፡፡ በኩሬ ያለውም እንቁራሪት እንዲህ ብሎ ጠየቀው፡፡ “ኦ ይህ አትላንቲክ ውቅያኖስ የምትለኝ ምንድን ነው?”

ጓደኛውም እንዲህ አለው፡፡ “በጣም ትልቅ የሆነ ውሀ የተከማቸበት ውቅያኖስ ነው፡፡“

“ምን ያህል ትልቅ ይሆናል? ከዚህ ኩሬ እጥፍ ይሆናልን?”

“ኦ አይደለም ከዚህ ኩሬ በጣም የተለቀ ነው፡፡”

“ምን ያህል ትልቅ ቢሆን ነው? ከዚህ ኩሬ አስር ጊዜ ትልቅ ይሆናልን?” እንደዚህ በመሰለ ጥያቄ እንቁራሪቱ ለረጅም ጊዜ በመገመት ላይ ተገኝቶ ነበር፡፡ ታድያ ይህን በመሰለ ግምታዊ ምርምር ምን ያህል ቢሄድ ነው የታላቁን ውቅያኖስ ጥልቀት እና ስፋት ሊረዳ የሚችለው? የእኛም የምርምር ድርጅቶች ልምድ እና የማወቅ ሀይላችን ሁል ጊዜ የተወሰነ ባህርይ ያላቸው ናቸው፡፡ ዞረን ዞረን የእንቁራሪት ፍልስፍና ውስጥ እንገባለን፡፡ ስለዚህም የሽሪማድ ብሀገቨታም ቅዱስ መጽሀፍን እና አብዩን የመላእክት ጌታን ለመረዳት በግምታዊ ምርምር ላይ መሳተፍ አይገባንም፡፡ ምክንያቱም ይህ ጊዜ የሚያባክን እና ፋይዳ የሌለው ትግል ነው፡፡

ይህንንስ ግምታዊ ምርምር ካቆምን በኋላ ምን ማድረግ ይገባናል? የብሀገቨታም ቅዱስ መፅሀፍ እንደሚመክረን በትሁት ልቦና የአብዩን አምላክ መልእክትን በሙሉ ልቦና ማዳመጥ ይገባናል፡፡ ይህም መልእክት በብሀገቨድ ጊታ እና በሌሎች የቬዲክ ስነጽሁፎች ውስጥ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በቁራን እና የክርስትያን መጽሀፈ ቅዱስ ውስጥ መልእክቶቹ ይገኛሉ፡፡ የመንፈሳዊ ስልጣን ካለውም መምህር መልእክቱን ማዳመጥ እንችላለን፡፡ ዋናው መሰረታዊ ነጥቡ ግን ዓብዩ አምላክን ለመረዳት በግምታዊ ምርምር ሳይሆን ከመንፈሳዊ ባለስልጣኖች ወይም መምህራን መስማት ይገባናል፡፡ ታድያ የዚህ ማዳመጥ ጥቅሙ ምንድን ነው? አንድ ሰው በምንም ዓይነት ደረጃ ላይ ቢገኝም ማለትም ድሀ ወይም ሀብታም ሰው፣ አሜሪካዊ፣ አውሮፓውያን፣ ህንድ፣ የብራህማና ቄስ፣ ሹድራ ወይም የቀን ሰራተኛ ቢሆንም የዓብዩ አምላክን መንፈሳዊ መልእክት የሚሰማ ከሆነ ምንም እንኳን አምላክ በማንም ሀይል የማይረታ ቢሆንም በአገልጋዮቹ ፍቅር ግን ሊረታ ይችላል፡፡ አርጁና የሽሪ ክርሽና ጓደኛ ነበረ፡፡ ነገር ግን ሽሪ ክርሽና ምንም እንኳን ዓብዩ የመንግስተ ሰማያት ጌታ ቢሆንም ለአርጁና የሰረገላው ነጂ ለመሆን ፈቃደኛ ሆኖ ነበር፡፡ ይህም ከደረጃው ዝቅ ብሎ የሚገኝ አገልግሎት ነበር፡፡ አርጁና ያለውን ፍቅር ለክርሽና ያሳየው ነበር፡፡ ክርሽናም ያለውን ፍቅር እንዲህ በመሰለ ሁኔታ ለአርጁና ገለፀለት፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ክርሽና ልጅ በነበረበት ጊዜ በጨዋታ የአባቱን የናንዳ መሀራጅን ጫማ በራሱ ላይ አስቀምጦ ይሄድ ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎች ከአምላክ ጋር አንድ ለመሆን ብዙ ጥረት ሲያደርጉ እናያለን፡፡ ቢሆንም ግን ፍቅር በተሞላበት አገልግሎታችን አንድ መሆኑ ቀርቶ የሽሪ ክርሽና አባት ለመሆንም እንችላለን፡፡ በእርግጥ አምላክ የሁሉ አባት ነው የራሱ የሆነ ወላጅ አባትም የለውም፡፡ ቢሆንም ግን በፍቅር የሚያገለግለውን እንደ አፍቃሪ ጓደኛው ወይም እንደ አባቱ ሊቀበለው ይችላል፡፡ ክርሽና በፍቅር በሚያገለግሉት ለመረታት ፈቃደኛ ነው፡፡ ይህንንም የአምላክ ፍቅር ለማዳበር አንድ ሰው የአብዩን አምላክ መልእክት በደንብ መከታተል ይገባዋል፡፡

በሰባተኛው የብሀገቨድ ጊታ ምዕራፍ ውስጥ ዓብዩ ሽሪ ክርሽና እንዴት በተለያየ መንገድ እና በእያንዳንዱ የሕይወታችን ደረጃ ላይ እንዴት ሊገለፅልን እንደሚችል ጠቅሶልናል፡፡

ፑንዮ ጋንድሀህ ፕርትሂቭያም
ቻ ቴጃስ ቻስሚ ቪብሀቫሶ
ጂቫናም ሳርቫ ብሁቴሹ
ታፓሽ ቻስሚ ታፓስቪሱ

“እኔ የመጀመሪያው ንፁህ የመሬት ሽታ እና በእሳትም የምውለበለብ ሙቀት ነኝ፡፡ የሚኖሩ ነፍሳት ሁሉ ሕይወታቸው እኔው ነኝ፤ እንዲሁም የባህታውያን ሁሉ የፀሎት ግብ እኔው ነኝ፡፡” (ብጊ፡ 7.9)

“ፑንዮ ጋንድሃህ” የሚሉት ቃላቶች ሽታ የሚለውን ትርጉም ይዘው ይገኛሉ፡፡ ክርሽና ብቻ ጣእምን እና ሽታን ለመፍጠር ይችላል፡፡ በሰው ሰራሽነት ብዙ ሽቶዎች እና ሰንደሎች ልንሰራ እንችላለን፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሽታዎች በተፈጥሮ ከሚገኙት ሽታዎች ሊበልጡ አይችሉም፡፡ በተፈጥሮ የተሰጠውን ጥሩ ሽታ ስናሸት “ኦ ይኅው አምላኬ ወይም ይኀው ፈጣሪ” ማለት እንችላለን፡፡ ወይም በተፈጥሮ ያልተለመደ ሀይል ወይም በጣም በተፈጥሮ አስደናቂ ነገር ስናይ “ይኅው ክርሽና” ማለት እንችላለን፡፡ ወይም ደግሞ ማናቸውንም ዓይነት ተፈጥሮ የዛፍ ዓይነት፣ የተክል ዓይነት፣ የእንስሳ ዓይነት፣ ወይም አስደናቂ ሰው ስናይ ይህ ፍጥረት የሽሪ ክርሽና ቅንጣፊ አካል መሆኑን መረዳት ይገባናል፡፡ የዓብዩ አምላክ ቅንጣፊ የሆነው ነፍስ ከቁሳዊው ገላ ለቆ ሲወጣ ገላው መፈረካከስ እና መበስበስ ይጀምራል፡፡

ቢጃም ማም ሳርቫ ብሁታናም
ቪድሂ ፓርትሀ ሳናታናም
ቡድሂር ቡድሂማታም አስሚ
ቴጃች ቴጃስቪናም አሀም

“ኦ የፕርትሀ ልጅ ሆይ እኔ የሁሉም ነዋሪ ነፍሳት የመጀመሪያው መነሻ ዘር፣ የአዋቂዎች ሁሉ አዕምሮ፣ የጀግኖች ሁሉ ኃይል እኔው ነኝ፡፡” (ብጊ፡ 7.10)

በዚህም ጥቅስ ውስጥ እንደተገለፀው ሽሪ ክርሽና የነዋሪ ነፍሳት ሁሉ የሕይወት መነሻ ሆኖ ይገኛል፡፡ ሰለዚህም በዚህ ቁሳዊ ዓለም ሕይወት ውስጥ እንኳን እያለን ሽሪ ክርሽናን ለማየት እንችላለን፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ “ፈጣሪ አምላክን ልታሳየኝ ትችላለህን?” በእርግጥም ይቻላል፡፡ ፈጣሪ አምላክ በተለያየ መንገድ ሊታይ ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ዓይኑን ጨፍኖ “ፈጣሪን ለማየት አልፈልግም” ካለ እንዴት ተደርጐ ለማሳየት ይቻላል?

ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ጥቅስ ውስጥ “ቢጃም” የሚለው ቃል “ዘር” ማለት ነው፡፡ ይህም “ዘር” ዘለዓለማዊ ወይም ሰናታና ተብሎ ይታወቃል፡፡ አንድ ሰው በጣም ትልቅ የሆነ ዛፍ ለማየት ይችላል፡፡ ነገር ግን የዚህ ትልቅ ዛፍ መነሻው ምንድን ነው? መነሻውም ዘሩ ነው፡፡ ይህም የተጠቀሰው “ዘር” ዘለአለማዊ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ነፍሳት ውስጥ ይኅው የኑሮ ዘር ይገኛል፡፡ ገላችን የተለያየ ደረጃዎችን ሲያልፍ ይታያል፡፡ በእናት ሆድ ውስጥ ሲያድግ ይታያል፡፡ እንደ ህፃንም ይወለዳል፡፡ እንደልጅነትም ሲያድግ ይታያል፡፡ ወደ ወጣትነትም ይቀየራል፡፡ ቢሆንም ግን የመጀመሪያው የህያውነት ዘር ግን ባለበት እንዳለ ይቆያል፡፡ ስለዚህም ዘለዓለማዊ ተብሎ ይታወቃል፡፡ በግልፅ አይታወቀንም እንጂ ገላችን በየጊዜው ወይም በየሴኮንዱ ሲቀያየር ይገኛል፡፡ ቢሆንም ግን ቢጃም ወይም “ዘሩ” ወይም በውስጥ ያለው የመንፈሳዊው ቅንጣፊ(ነፍስ) አይቀያየርም፡፡ በእያንዳንዱ የዘለዓለማዊ መንፈሳዊ ቅንጣፊ ውስጥም የሚገኘው ዘር ክርሽና እራሱ እንደሆነም በብሀገቨድ ጊታ ተገልጾልናል፡፡ ይህም ማለት ክርሽና የሁሉ ነፍሳት ዘለዓለማዊ ዘር ሁኖ ይገኛል፡፡ የአዋቂዎች ሁሉ አዕምሮ እርሱው ሆኖ ይገኛል፡፡ ማንም ሰው የክርሽና በረከት ካልደረሰው በቀር አዋቂ ሊሆን አይችልም፡፡ እያንዳንዱም ሰው ከሌላው በላይ በጣም አዋቂ ለመሆን ጥረት ሲያደርግ ይገኛል፡፡ ነገር ግን የክርሽናን በረከት ካላገኘ አዋቂ ለመሆን አይችልም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ አዋቂ ሰው ባጋጠመን ጊዜ ሁሉ እንዲህ ማሰብ ይገባናል፡፡ ”ይህ የላቀ አዕምሮ ክርሽና ነው” እንደዚህም ሁሉ በገለፃ ወይንም በክርክር የሚያሳምን ሰው ባህርይ የሚመጣው ከክርሽና መሆኑን መገንዘብ ይገባናል፡፡

ባላም ባላቫታም ቻሃም
ካ ማ ራጋ ቪቫርጂታም
ድሀርማቪሩድሆ ብሁቴሹ
ካሞ ስሚ ብሀረታርሻብሀ

”እኔ ቅን ፍላጐት የሌለው ሀይል ካላቸው ፍጥረታት ሁሉ ሀይላቸው እኔው ነኝ፡፡ ከሀማይኖታዊው መመሪያ ውጪ ያልሆነውም የወሲብ ፍላጐት ምንጭ እኔው ነኝ፡፡ ኦ የብሀረታዎች ጌታ” (አርጁና) (ብጊ፡ 7.11)

ዝሆኖች እና የጐሬላ ዝንጀሮዎች በጣም ሀይል ያላቸው እንስሶች ናቸው፡፡ ይህም ሁሉ ሀይላቸው የሚመጣው ከሽሪ ክርሽና መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ የሰው ልጅም ይህንን ዓይነት ሀይል በራሱ ጥረት ሊያገኘው አይችልም፡፡ ነገር ግን የክርሽና በረከትን ካገኘ የሰው ልጅ ከዝሆን በላይ ሺህ ጊዜ የሚበልጥ ሀይል ሊያገኝ ይችላል፡፡ በኩሩክሼትራ ጦርነት ጊዜ ታላቁ ተዋጊ ብሂማ የነበረው ሀይል ከዝሆን ሀይል ከአስር ሺህ እጥፍ በላይ እንደነበረ ይነገርልታል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ከሀይማኖታዊ ስርአት ውጪ ያልሆነ የወሲብ ፍላጎት ምንጭ ወይም “ካማ” ክርሽና እራሱ እንደሆነ መረዳት ይኖርብናል፡፡ ይህስ ጠንካራ የወሲብ ፍላጎት(ካማ) ምንድን ነው? ይህም ብዙውን ጊዜ ሰዎች እንደሚረዱት የወሲብ ግኑኝነት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በእዚህ ጥቅስ ውስጥ ክርሽና የገለፀው የወሲብ ግኑኝነት ወይም ካማ ግን የሀይማኖት ስርአትን የተከተለ ነው፡፡ ይህም ማለት ጥሩ ልጆችን በትዳር ጊዜ ለመውለድ የሚደረገው የወሲብ ግኑኝነት ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው በዓብዩ ሽሪ ክርሽና መንፈሳዊ ንቃትን የሚያዳብሩ ልጆችን ወልዶ ለማሳደግ የሚችል ከሆነ ከሺህም በላይ በወሲብ ግኑኝነት ካሰፈለገ ሊሰማራ ይችላል፡፡ ነገር ግን ልጆቹን ከውሻና ከድመት ያልተሻለ ዓለማዊ አንደበት ይዘው እንዲያድጉ ከሆነ የወሲቡ ግኑኝነት ከሀይማኖታዊ ስርዓት ውጪ ነው፡፡ በሀይማኖታዊ እና በሰለጠነ ሕብረተሰብ ውስጥ የጋብቻ ስርዓት የሚፈፀመው ባለትዳሮቹ በወሲብ ተገናኝተው ጥሩ ልጆችን ወልደው በጥሩ መንፈስ እንዲያሳድጓቸው ነው፡፡ ስለዚህ በጋብቻ ውስጥ የሚፈፀመው የወሲብ ግኑኝነት በሀይማኖታዊ ስርዓት የተደገፈ ነው፡፡ ከትዳር ውጪ የሚገኝ የወሲብ ግኑኝነት ግን ከሀይማኖታዊ ስርዓት ውጪ ነው፡፡ በመሰረቱ በመሎክሴ እና በባለትዳር መሀከል ብዙም ልዩነት አይገኝም፡፡ የሚወስነው ግን የባለትዳሮች የወሲብ ግኑኝነት ምን ያህል የሀይማኖታዊ ስርዓት የተከተለ መሆኑ ነው፡፡

ዬ ቻይቫ ሳትቪካ ብሀቫ
ራጃሳስ ታማሳሽ ቻ ዬ
ማታ ኤቬቲ ታን ቪድሂ
ና ትቭ አሀም ቴሹ ቴ ማዪ

”የሁሉም ነፍሳት አንደበት ጥሩም ይሁን፣ ጥልቅ ፍላጎት የተሞላበትም ይሁን ወይም ድንቁርና የተሞላበት ቢሆንም እነዚህ ሁሉ የሚፈጠሩት በእኔ ሀይል ነው፡፡ እኔ በሁሉም ዘንድ እገኛለሁ፡፡ ቢሆንም ግን ተነጥዬ የመኖሩም ሀይል አለኝ፡፡ እኔ በዚህ ቁሳዊ ዓለም በሚገኙት የተፈጥሮ ሕግጋት ቁጥጥር ስር አይደለሁም፡፡” (ብጊ፡ 7.12)

አንድ ሰው ክርሽናን እንዲህ ብሎ ሊጠይቀው ይችላል፡፡ “እንደገለፅከው አንተ ድምፅ እንደሆነክ፣ ውሀ፣ ብርሀን፣ ሽታ፣ የሁሉም ዘር ሀይል፣ የወሲብ ፍላጎት እንደሆንክ ሁሉ ተናግረሀል፡፡ ይህ ማለት አንተ የምትገኘው በጥሩ አንደበት ብቻ ነውን?” በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ሶስት ዓይነት የህልውና ባህሪዎች አሉ፡፡ እነዚህም የጥሩ ረጋ ያለ ባህሪይ፣ ያልተረጋጋ ባህሪይ እና የድንቁርና ባህሪዎች ናቸው፡፡ እስከ አሁንም ድረስ ክርሽና እንደገለፀው እርሱ በጥሩ ባህሪይ ውስጥ እንደሚገኝ ነው፡፡ (ለምሳሌ የሀይማኖት ስርዓትን የተከተለ በትዳር ውስጥ የሚገኝ የወሲብ ግኑኝነት)ታድያ ሌሎቹስ የህልውና ባህርዮች? ክርሽና በሌሎቹ ባህርዮች ውስጥ አይኖርም ማለት ነውን? ለዚህም ክርሽና መልስ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፡፡ “በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ የምናያቸው ባህሪዎች ሁሉ ከሶስቱ የህልውና ባህሪዎች እየተቀላቀሉ የሚገኙ ባህሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህም ከጥሩ ካልተረጋጋ እና ከድንቁርና ባህሪዎች ተቀላቅለው የመጡ ናቸው፡፡ በሁሉም ደረጃ እነዚህ ሁሉ ባህሪዎች የሚፈጠሩት በእኔው ነው፡፡” እነዚህ የህልውና ባህሪዎች በክርሽና የሚፈጠሩ ስለሆኑ ሁልግዜ በእርሱ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ፡፡ እርሱ ግን በእነዚህ ብህርዮች ቁጥጥር ስር አይገኝም፡፡ ክርሽና ከእነዚህ ከሶስቱ የህልውና ባህሪያት ውጪ ተሻግሮ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ በድንቁርና አንደበት የሚፈጠሩት መጥፎ እና ክፉ ነገሮች ሁሉ ተበርዘው የሚመነጩት ከክርሽና ሀይል ነው፡፡ ይህ እንዴት ወይም ለምን ሊሆን ቻለ ብሎ አንድ ሰው ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ የኤሌክትሪክ ኢንጂኔር የመብራት ሀይልን አመነጨ እንበል፡፡ በቤታችን ውስጥም ይህንን የመብራት ሀይል ተሰራጭቶ ለፍሪጅ የቅዝቃዜ አገልግሎት እና ለምድጃ የሙቀት አገልግሎት ስንጠቀምበት እንገኛለን፡፡ ቢሆንም ግን ይኅው መብራት ከመብራት ሀይሉ ባለሥልጣን ሲመጣ ቀዝቃዛ ወይም ሙቅ ሆኖ አይመጣም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በዓለም የምናያቸው የህልውና ባህሪዎች በነፍሳት ዘንድ የተለያዩ ደረጃዎች ይዘው እናያቸዋለን፡፡ ከክርሽና ሲመነጩ ግን በንፁህ እና በአንድ ዓይነት ደረጃ ላይ ሆነው ሲሰራጩ እናገኛቸዋለን፡፡ ስለዚህ ክርሽና አንዳንድ ጊዜ የቅብዝብዝነትን እና የድንቁርናን ባህሪ የሚያመነጭ መስሎ ይታያል፡፡ ነገር ግን እንደ መብራት ሀይሉ ባለስልጣን ክርሽና ንጹህ ባህሪን ሲያመነጭ ይገኛል፡፡ ልክ እንደ መብራት ሀይል ተጠቃሚው ሰው የቅዝቃዜ የመብራት ሀይል እና የማሞቂያ የመብራት ሀይል ብሎ ልዩነቱን አያመነጭም፡፡

የሁሉም ባህሪ ሀይል የሚመነጨው ከክርሽና ነው፡፡ የቬዳንታ ሱትራ ቅዱስ ስነፅሁፍም እንደሚገልፅልን፡ “አትሀቶ ብራህማ ጂግናስያ ጃንማዲ አስያ ያታሀ” (ሽብ፡1 1.1) ሁሉም ነገር የሚመነጨው ከዓብዩ የመንግስተ ሰማያት ጌታ ነው፡፡ ህያው ፍጥረታትም መጥፎ ወይም ጥሩ ብለው የሚገነዘቡትም ከራሳቸው በመነጨ ውስን አስተሳሰብ ነው፡፡ ሽሪ ክርሽና ግን በቁሳዊ ዓለም ሕግጋት ውስን ባለመሆኑ በእርሱ ላይ የመጥፎ እና የጥሩ ባህሪያት በመለያየት መንጭተው አይገኙም፡፡ እርሱ ለዘለዓለም ፍፁም ጥሩ ነውና። እኛ ግን በዚህ በቁሳዊ ዓለም ውስጥ ውስን ሆነን የተፈጠርን ስለሆንን በነዚህ በሚፈራረቁ ባህሪያት እየተጠቃን በስቃይ ውስጥ እንገኛለን፡፡ የእነዚህ ሁሉ የባህሪያት ንፁህ የመነሻ ሀይል ምንጭ ሁልግዜ ክርሽና ሆኖ ይገኛል፡፡

« Previous Next »