No edit permissions for Amharic

4

የአዋቂዎች እና የሞኞች መንገድ

ክርሽና የዓብይነት ደረጃውን በግልጽ አድርጐ በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ አስረድቶናል፡፡ ቢሆንም ግን በተለያየ የዓለማዊ ኑሮ ምኞት ተጠቅተን ወደ እርሱ ተስበን አንገኝም፡፡ ይህ ለምንድን ነው? የዚህም ምክንያት በእራሱ በዓብዩ ክርሽና በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡

ዳይቪ ሂ ኤሻ ጉና ማዪ
ማማ ማያ ዱራትያያ
ማም ኤቫ ዬ ፕራፓድያንቴ
ማያም ኤታም ታራንቲቴ

“ይህንን በሶስት ዓይነት ባህሪ የተበረዘውን የቁሳዊው ዓለም መለኮታዊ ሀይሌን ለመቋቋም በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ለእኔ ሙሉ ልቦናቸውን ሰጥተው ለሚያገለግሉኝ ሁሉ እነዚህን ዓለማዊ ባህርያት በቀላሉ ሊሻገሯቸው ይችላሉ፡፡” (ብጊ፡ 7.14)

ይህ ቁሳዊው ዓለም በሶስት ዓይነት ባህሪያት የተሞላ ነው፡፡ ፍጥረታትም ሁሉ በእነዚህ በሶስት ዓይነት ባህሪያት ተጭነው ወይም ተገፋፍተው ይገኛሉ፡፡ በጥሩ ባህሪ የተመሰረተ አንደበት ካላቸው ብራህመና ተብለው ሊታወቁ ይችላሉ፡፡ ረጋ ያለ መንፈስ የሌላቸው ከሆነ ክሻትርያ ተብለው ሊታወቁ ይችላሉ፡፡ ረጋ ያለ መንፈስ የሌላቸው እና የድንቁርናም አንደበት ያላቸው ቫይሻ ተብለው ይታወቃሉ፡፡ በድንቁርና መንፈስ የሚጠቁ ከሆነ ደግሞ ሱድራ ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ይህም ዓይነት አንደበት በትውልድ ወይም በህብረተሰብ ደረጃ የተመሰረተ አይደለም፡፡ የተመሰረተውም በራሳቸው አንደበት ወይም ተፈጥሮ ባደራጀው ባህሪ መሰረት የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ነው፡፡

ቻቱር ቫርንያም ማያ ስርስታም
ጉና ካርማ ቪብሀጋሻሀ
ታስያ ካርታራም አፒ ማም
ቪድሂ አካርታራም አቭያያም

“እነዚህ ሶስቱ የቁሳዊው ዓለም ባህሪዎች፣ ከእነዚህም ጋር የተዛመዱት የስራ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም አራቱ የሰው ልጅ ሕብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ የተፈጠሩት በእኔው ነው፡፡ ምንም እንኳን ከእኔ የተፈጠሩ ቢሆኑም እኔ በዚህ የምሳተፍ፣ በዚህ ዓይነት ባህሪ የምጠቃ ወይም የምቀያየር አለመሆኔን መረዳት አለብህ፡፡” (ብጊ፡ 4.13)

ይህም ማለት ይህ በሽሪ ክርሽና የተመሰረተው አራቱ የሕብረተሰብ ኑሮ ስርዓት በአሁኑ ግዜ በሕንድ አገር እንደምናየው የተገላቢጦሽ የጐሳ ስርዓት ነው ማለት አይደለም፡፡ ክርሽና በግልጽ እንደጠቀሰው “ጉና ካርማ ቪብሀጋሻሀ” ብሎ ይህንን ገልፆታል፡፡ የሰው ልጅ ሕብረተሰብ የሚከፋፈለው በያዘው ባህሪ እና በተሰማራበት የስራ ዓይነት ነው፡፡ ይህም የሚያጠቃልለው በምድር ያሉትን ሰዎች ብቻ ሳይሆን በመላ ህዋ ውስጥ ለሚገኙት ፍጥረታት ሁሉ ነው፡፡ መረዳት ያለብን ነገር ቢኖርም ሽሪ ክርሽና በተናገረ ቁጥር መልእክቱ ሁሉ የሚያገለግለው ለዚህ ምድር ብቻ ሳይሆን ለመላው ትእይንተ ዓለም ፍጹም እውነት ይዞ የቀረበ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ሽሪ ክርሽና የመላ ፍጥረታት ሁሉ አባት መሆኑን ገልጾልናል፡፡ ይህም አባትነቱ ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለመላ እንስሶችም፣ ለባህር ፍጥረታት፣ ለዛፎች ሁሉ፣ ለአትክልቶች፣ ለትላትል፣ ለአእዋፍ እና ለበራሪ ንቦች ሁሉ አባት መሆኑ ተገልጾልናል፡፡ ሽሪ ክርሽና እንደገለፀው የመላው ትእይንተ ዓለም ፍጥረታት ሁሉ በሶስቱ የቁሳዊ ዓለም ባህሪያት ምትሀት ውስጥ በመገኘታቸው እና በዚህም ምተሀት ሰመመን ውስጥ ተሸፍነን ስለምንገኝ ዓብዩ ፈጣሪ አምላክን ለመረዳት ሲያዳግተን እንገኛለን፡፡

የዚህስ ምትሀት መሰረታዊ ፍጥረቱ ምንድን ነው? እንዴትስ ልንቋቋመው እንችላለን? ይህም በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ተገልጾልናል፡፡

ዳይቪ ሂ ኤሻ ጉና ማዪ
ማማ ማያ ዱራትያያ
ማም ኤቫ ዬ ፕራፓድያንቴ
ማያም ኤታም ታራንቲቴ

“ይህንን በሶስት ዓይነት ባህሪ የተበረዘውን የቁሳዊው ዓለም መለኮታዊ ሀይሌን ለመቋቋም በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ለእኔ ሙሉ ልቦናቸውን ሰጥተው ለሚያገለግሉኝ ሁሉ እነዚህን ዓለማዊ ባህርያት በቀላሉ ሊሻገሯቸው ይችላሉ፡፡” (ብጊ፡ 7.14)

የትኛውም ፍጥረት ቢሆን እነዚህን ሶስቱን የቁሳዊ ዓለም ባህሪያት በግምታዊ አዕምሮ ወይንም ምርምር ሊያስወግዳቸው አይችልም፡፡ እነዚህ ሶስቱ ባህሪያት በጣም ጠንካራ እና ለመቋቋም የሚያዳግቱ ናቸው፡፡ እንዴት በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ በእነዚህ ሶስቱ ባህሪያት ተጠምደን እንደምንገኝ አይሰማንምን? ይህ “ጉና” (ባህሪ) የተባለው የሳንስክሪት ቋንቋ ቃል ሌላው ትርጉሙ “ገመድ” ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው በሶስት ገመዶች ተጠምዶ ታስሮ ከሆነ እስራቱ ጠብቆ ለመንቀሳቀስ ያዳግተዋል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ እጆቻችን እና እግሮቻችን ሁሉ በእነዚህ በሶስቱ የጥሩ፣ ረጋ ያላለ እና የድንቁርና ባህሪያት ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ ታድያ ተስፋ ሊኖረን አይችልም ማለት ነውን? አይደለም? ሽሪ ክርሽና እንደገለፀውም ልቦናቸውን ለእርሱ ሰጥተው ለሚያገለግሉት ሁሉ ከዚህ ወጥመድ በቀላሉ ነፃ እንደሚወጡ አረጋግጧል፡፡ አንድ ሰው የክርሽና ንቃቱን በተለያየ መንገድ ካዳበረ ከዚህ ቁሳዊ ዓለም ወጥመድ በቀላሉ ነፃ እንደሚወጣ ተረጋግጧል፡፡

ሁላችንም የክርሽና ልጆች በመሆናችን በቀጥታ ከእርሱ ጋር ተዛምደን እንኖራለን፡፡ አንድ ልጅ ከአባቱ ጋር ባለመስማማት ሊርቅ ይችላል ነገን ግን ከአባቱ ጋር ያለውን ዝምድና ሊያጠፋ አይችልም፡፡ ከጊዜ በኋላም ማንነቱን ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ሲመለስም “እኔ የእከሌ ልጅ ነኝ ማለቱ የማይቀር ነው፡፡” ይህም ዝምድና ሊሰበር አይችልም፡፡ እኛም ሁላችን የዓብዩ የመንግስተ ሰማያት ጌታ ልጆች ነን፡፡ ይህም ከጌታ ጋር ያለን ዝምድና የዘለዓለም ነው፡፡ ቢሆንም ግን በአሁኑ በቁሳዊ ዓለም ህይወታችን ይህንን ዘንግተነው እንገንኛለን፡፡ ሽሪ ክርሽና ፍፁም የላቀ ሀያል፣ የላቀ ዝና፣ የላቀ ሀብት፣ የላቀ ቁንጅና፣ የላቀ እውቀት ያለው ነው፡፡ እንዲሁም ፍጹም የቁሳዊ ዓለም ገለልተኝነት ባህሪ አለው፡፡ እኛም ምንም እንኳን ከእርሱ ጋር ቅርብ የሆነ ጓደኝነት ቢኖረንም ይህንን ዘንግተነዋል፡፡ አንድ የሀብታም ሰው ልጅ አባቱን ረስቶ እና ቤቱን ለቅቆ ወደ እብድነት ቢቀየር መንገድ ላይ በመጋደም ሲተኛ ሊገኝ ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ለምግቡ ሲለምን ይገኝ ይሆናል፡፡ ይህም ሁሉ የሚከሰተው ሀብታም አባቱን ክዶ በመሄዱና በመዘንጋቱ ነው፡፡ በዚህም ጊዜ አንድ ሰው እንዲህ የሚሰቃየው የአባቱን ቤት ጥሎ በመሄዱ እና አባቱን በመዘንጋቱ ስለመሆኑ ቢያስረዳው ወይም አባቱ ሀብታም እና ግዙፍ ቤት እንዳለው ገልፆ ወደ አባቱ እንዲመለስ ቢመራው ይህ ሰው ጠቃሚ እና በጐ አድራጎታዊ ባህሪ አለው እንላለን፡፡

በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ በሶስት ዓይነት መከራዎች ስንሰቃይ እንገኛለን፡፡ እነዚህም መከራዎች ከእራሱ ከገላችን እና ከሀሳባችን የሚመነጩ፤ ከሌሎች ፍጥረታት የሚመነጩ እና ከተፈጥሮ አደጋዎች የሚመነጩ መከራዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን በቁሳዊው ዓለም ምተሀት ውስጥ ተጠምደን ስለምንገኝ እነዚህን መከራዎች ብዙውን ጊዜ አስተውለን አሰላስለናቸው አናውቅም፡፡ ቢሆንም ግን በዚህ ቁሳዊ ምድር ሁልጊዜ በሚፈራረቅ መከራዎች ውስጥ እንደምንገኝ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ አንድ ብቁ የሆነ ንቃት ያለው አዋቂ ሰው ለምን ሁል ጊዜ በመከራ ውስጥ እንደተጠመደ መጠየቅ ይገባዋል፡፡ “መከራ እንዲመጣብኝ አልፈልግም፡፡ ለምንድነው ሁልጊዜ የምሰቃየው?” ይህም ዓይነት ጥያቄ በአዕምሮዋችን ውስጥ ሲቀረጽ የክርሽናን ንቃታችንን ለማዳበር አመቺ ያደርገዋል፡፡

ሙሉ ልቦናችንንም ለሽሪ ክርሽና ስንሰዋ ክርሽናም በአክብሮት ይቀበለናል፡፡ ይህም ከአባቱ ቤት ጠፍቶ እንደተመለሰ ልጅ ሆኖ ይመሰላል፡፡ “አባቴ ሆይ በእኔ እና በአንተ ባለመግባባት ምክንያት ያንተን ጠለላ ትቼ በመሄዴ ብዙ መከራ ደርሶብኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ አንተው ተመልሻለሁ::” አባቱም ልጁን እቅፍ አድርጎ በመቀበል እንዲህ ይለዋል፡፡ “ልጄ ሆይ ወዲህ ቅረብልኝ፡፡ ከእኔ ርቀህ በመሄድህም ለዚህ ያህል ቀናት በብዙ ሀሳብ እና ጭንቀት ተጠምጄ ነበር፡፡ አሁን ግን በመመለስህ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡” አባት በዚህ መንገድ ሩህሩህነቱን ለልጁ ያሳየዋል፡፡ እኛም ፍጥረታት ሁሉ ይህንን በመሰለ ዓይነት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ማድረግ የሚገባንም ሙሉ ልቦናችንን ለሽሪ ክርሽና በመስጠት እርሱን ማገልገል ነው፡፡ ይህም አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ልጁስ ወደ አባቱ ሲመለስ አስቸጋሪ ስራ ሆኖ አግኝቶታልን? ይህም በተፈጥሮ ያለ ነው፡፡ አባት ሁልጊዜ ልጁን ለመቀበል ዝግጁ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ውርደትም የለውም፡፡ እራሳችንን ዝቅ አድርገን የአብዩን የመላእክት ጌታ እግሮች በአክብሮት ብንነካ ምንም ጉዳት አይኖረውም፣ አስቸጋሪም አይደለም፡፡ እንዲያውም ይህ ግርማ ሞገስ ያለው መንፈሳዊ አንደበት ነው፡፡ ለምንስ አናደርገውም? ሙሉ ልቦናችንን ለሽሪ ክርሽና በማቅረብ ወዲያውኑ በእርሱ ጠለላ ውስጥ ገብተን ከመከራዎች ሁሉ ለመዳን እንበቃለን፡፡ ይህም በሁሉም የቬዲክ ስነጽሁፎች ተረጋግጦልናል፡፡ በብሀገቨድ ጊታም መጨረሻ ላይ ሽሪ ክርሽና እንደዚህ ብሎ ገልጾልናል፡፡

ሳርቫ ድሀርማን ፓሪትያጃ
ማም ኤካም ሻራናም ቭራጃ
አሀም ትቫም ሳርቫ ፓፔብህዮ
ሞክሻዪሽያሚ ማ ሱቻሀ

“Abandon all varieties of religion and just surrender unto Me. I shall deliver you from all sinful reactions. Do not fear.” (Gītā 18.66)

“ማናቸውንም ዓይነት የተለያዩ እምነቶች እና ሀይማኖቶች ሁሉ እርግፍ አድረገህ በመተው ሙሉ ልቦናህን ለእኔ አቅርብ፡፡ እኔም ከማናቸውም ዓይነት የሀጥያት ውጤቶች አድንሀለሁ። ስለዚህም ምንም ዓይነት ፍርሀት አንዳይሰማህ፡፡” (ብጊ፡ 18.66)
እራሳችንን ከዓብዩ የመላእክት ጌታ እግር ስር ስናቀርብ ወዲያውኑ በእርሱ ድጋፍ እና ጠለላ ስር እንሆናለን፡፡ ከዚያም ጊዜ በኋላ ምንም ዓይነት ፍርሀት ሊኖረን አይገባም፡፡ ልጆች በወላጆቻቸው ጠለላ ስር ሲሆኑ ምንም ዓይነት ፍርሀት ሊኖራቸው አይችልም ምክንያቱም ወላጆቻቸው ልጆቹ እንዳይጠቁ ስለሚጠባበቋቸው ነው፡፡ “ማም ኤቫዬ ፕረፓድያንቴ” ክርሽና ቃሉን እንደሰጠው ሁሉ ማንም ሰው ልቦናውን ለክርሽና የሰጠ ከሆነ ምንም ዓይነት ፍርሀት ሊኖረው አይችልም፡፡

ይህስ ለክርሽና ልቦናችንን መስጠት ቀላል ነገር ከሆነ ለምን ሰዎች ልቦናቸውን አይሰጡም? ይህንን ከማድረግም ተቆጥበው ፈጣሪ አምላክም የለም ብለው የሚከራከሩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ተፈጥሮ እና ሳይንስ ብቻ እንጂ ፈጣሪ አምላክ የለም ብለው የሚያምኑ ብዙ አሉ፡፡ የተሳሳተ የሳይንሳዊ እውቀት መዳበር እና በቁሳዊው ዓለም የሚገኙት የህብረተሰቡ ዓለማዊ አመለካከት ህዝብን ወደ ተሳሳተ መንገድ እና ወደ እብደት ፈለግ እየመራው ነው፡፡ ከተፈጥሮ በሽታም እንደመዳን ወደተበከለ አንደበት በመስመጥ ላይ እንገኛለን፡፡ ሰዎች በፈጣሪ አምላክ ማመን ትተው ወደ ቁሳዊው ዓለም ደስታ ማተኮርም ጀምረዋል፡፡ የተፈጥሮም ስራ ፍጥረታትን ሁሉ በእነዚህ በሶስቱ የመከራ ዓይነቶች እያፈራረቀች እንደሚገባው ማሰቃየት ነው፡፡ እነዚህንም ሶስት ዓይነት መከራ እና ስቃዮች ተፈጥሮ 24 ሰዓት ሙሉ ስታስተዳድር ትገኛለች፡፡ ቢሆንም ግን እኛም እነዚህን መከራዎች በጣም በመላመዳችን የተነሳ ተቀብለነው በመገኘት “ተፈጥሮ ያመጣው ጣጣ ነው” በማለት እንገኛለን፡፡ ባለንም የቁሳዊ ዓለም እውቀት በጣም ኮርተን እንገኛለን፡፡ እንዲህም እናስባለን “ተፈጥሮ ሆይ የምቋቋመውን መከራ ስላሳየሽኝ ምስጋናዬን አቀርብልሻለሁ፡፡ እንደዚሁም ቀጥይበት” ብለን በመታለል ላይ እንገኛለን፡፡ እንደዚህም በማሰብ የተፈጥሮን መከራዎች ሁሉ የተቋቋምን ይመስለናል፡፡ ይህስ እንዴት ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም እንኳን የተለያዩ መከራዎችን ለመቋቋም ብንችልም ተፈጥሮ በአራቱ መከራዎች ሁሌ እንዳሸነፈችን ትገኛለች፡፡ እነዚህም መወለድ፣ መታመም፣ ማርጀት፣ እና መሞት ናቸው፡፡ እነዚህንስ መከራዎች ለመቋቋም ወይም ለማጥፋት የቻለ ሰው በዓለም ላይ ይገኛልን? ታድያ በእውቀት እና በስልጣኔ ምን ዓይነት ብልፅግና ውስጥ ነው የምንገኘው? የምንገኘውም በቁሳዊው ዓለም ህግጋት ተጠፍረን እና ታስረን ነው፡፡ ቢሆንም ግን የተፈጥሮን መከራዎች እያሸነፍን ነው በማለት እራሳችንን በማታለል ላይ እንገኛለን፡፡ ይህም “ማያ” ይባላል፡፡

ለዚህም ለገላችን አባት ለዓብዩ ጌታ ሙሉ ልቦናችንን ለመስጠት ያስቸግረን ይሆናል። ይህም በቂ ያልሆነ እውቀት ስላለን ወይም መንፈሳዊ ሀይል ስለሚጐለን ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን ክርሽና በምድር ላይ እንደሚገኝ ተራ የሆነ አባት አይደለም፡፡ ክርሽና ወሰን የሌለው ሙሉ እወቀት ያለው፣ ሙሉ ሀይል፣ ሀብት፣ ቁንጅና፣ ዝና ያለው እና ከዚህ ቁሳዊ ዓለም ጉጉት እርግፍ ያለ አንደበት ያለው ነው፡፡ ታድያ እራሳችንን እንደ እድለኞች በመቁጠር ወደእዚህ ዓይነቱ አባታችን በመሄድ የእርሱ ሀብት ወራሾች እና ተደሳቾች መሆን አይገባንምን? ይህም ሆኖ በቁሳዊው ዓለም ምትሀት ስር ስለተጠመድን ማንም ሰው ቢሆን ግድ የማይሰጠው ይመስላል፡፡ እንዲያውም ፈጣሪ አምላክ የለም በማለት እንሰብካለን፡፡ ለምንድነው እንዲህ ዓይነት ሰዎች ዓብዩ ጌታን ለመቅረብ የማይሹት? ይህም በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ በሚቀጥለው ጥቅስ ተጠቅሷል፡፡

ናማም ዱስክሪቲኖ ሙድሃህ
ፕራፓድያንቴ ናራድሀማህ
ማያያፓህርታ ግያና
አሹራም ብሀቫም አሽሪታሀ

“እነዚያ ህብረተሰቡን የሚያውኩ፣ በሞኝነት የሰመጡ፣ ከሰው ልጆች ሁሉ የበታች የሆኑ፣ እውቀታቸውም በቁሳዊ ዓለም የሀሰት ራዕይ የተወሰደባቸው፣ የአማኝነት አንደበት የሌላቸውና የከሀዲ አንደበት ያላቸው ሁሉ ለእኔ ሙሉ ልቦናቸውን ለመስጠት ያዳግታቸዋል፡፡” (ብጊ፡ 7.15)

ይህንንም በመሰለ ትንተና ሞኞች የሆኑ ሁሉ በዚህ መድረክ ላይ ተመድበው ይገኛሉ፡፡ “ዱስክሪቲ” የሚባሉት ከቅዱስ መጻህፍቶች ውጪ ወይም ከአምላክ ፍቃድ በተቃረነ መንገድ መኖር የሚሹ ማለት ነው፡፡ የዚህም የአሁኑ እምነት የጐደለው የቁሳዊ ዓለም ስልጣኔ የተመሰረተው እነዚህን የቅዱስ መፃህፍትን ትእዛዞች በመቃረን ነው፡፡ ፃድቅ ሰው እነዚህን ትእዛዞች አይቃረንም። እነዚህን ፃድቃኖች “ሱክርቲ” ከከሀዲዎቹ ወይም “ዱስክርቲ” የሚለይ ህግ መኖር አለበት፡፡
እያንዳንዱ የሰለጠነ ሕብረተሰብም የሚከተለው ቅዱስ ስነፅሁፎች አሉት፡፡ የክርስትና፣ የሂንዱ፣ የእስልምና ወይም የቡድሀዎች ቅዱስ ስነጽሁፎች ይኖራሉ፡፡ ዋናው መሰረታዊ ነጥቡ ግን እነዚህ ቅዱስ መፃህፍቶች ለህብረተሰቡ ቀርበው ይገኛሉ፡፡ እነዚህንም ቅዱስ መፃህፍቶች የማይከተል እንደ አፈንጋጭ ሆኖ ይታያል፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥም በሌላው ክፍያ የተጠቀሰው ደግሞ “ሙድሀ” ነው፡፡ ይህም አንደኛ ደረጃ ሞኝነት የሞላበት ማለት ነው፡፡ “ናራድሀማ” ማለት ደግሞ በህብረተሰቡ ውስጥ ዝቅተኛው ማለት ነው፡፡ “ማያያ ፓህርታ ግያና” ማለት ደግሞ እውቀቱ በ “ማያ” ወይም በቁሳዊው ዓለም ምትሀት የተወሰደበት ማለት ነው፡፡ “አሹራም ብሀቫም አሽሪታሀ” ማለት ደግሞ የለየላቸው ከሀዲያን ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን ለአባታችንን ሙሉ ልቦናችንን መስጠት ምንም ጉዳት ባይኖረውም ይህንን የመሰለ የከሀዲ አንደበት ያላቸው ሰዎች ልቦናቸው ለመስጠት ምንም ፍላጎት የላቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት እነደዚህ ዓይነት ፍጥረታት ሁሉ በትእይንተ ዓለም ውስጥ በሚገኙት የዓብዩ ጌታ አስተዳዳሪዎች መድረክ ላይ ለፍርድ ሲቀርቡ ይገኛሉ፡፡ በጥፋታቸውም ክፉኛ ሲቀጡ እና ሲሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ ልክ ወላጅ አባት አጥፊ ልጁን እንደሚቀጣው ተፈጥሮም ከሀዲያንን የመቅጣት ስርዓት አላት፡፡ ይሁንም እንጂ በንቃታችን እንድንዳብር ተፈጥሮ ብዙ ነገር እንደ ምግብ እና በቀን በቀን የሚያስፈልገንን ነገሮች ሁሉ ስታቀርብልን ትገኛለች፡፡ ይህም ሁሉ ነገር የቀረበልን በሀብት የበለፀገው የአባታችን ልጆች በመሆናችን ነው፡፡ ይህም የሽሪ ክርሽናን ሩህሩህነት ያሳየናል፡፡ ምንም እንኳን እኛ ሙሉ ልቦናችንን ያልሰጠነው ቢሆንም እርሱ ሁሉን አቅርቦልን ይገኛል፡፡ ይህንንም ዓይነት አስፈላጊ ነገሮችን ዓብዩ አምላክ በተፈጥሮ አማካኝነት ቢያቀርብልንም “ዱስክርቲ” የምንላቸው ምንም ልቦናቸውን ለመስጠት ፍላጎት የላቸውም፡፡ በቅዱስ መፃህፍትም የተደነገገውን ትእዛዝ ለመከተል አይሹም፡፡ ተደጋግሞ ከቅጣቱም የማይማር ሰው እንደ ሞኝ ይቆጠራል፡፡ ይህንንም ብርቅ የሰው ትውልድ ይዞ ሽሪ ክርሽናን ለመረዳት የማይጥር ሰው ከሰዎች ሁሉ እንደ ዝቅተኛ ሆኖ ይቆጠራል፡፡

እንስሶች ይበላሉ፣ ይተኛሉ፣ እራሳቸውንም ከአደጋ ይከላከላሉ እንዲሁም በወሲብ ሲሰማሩ ይታያሉ፡፡ ከፍ ያለ መንፈሳዊ ንቃትን ለማዳበር ብቁ ግን አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ይህ ዕድል ለሰው እንጂ ለዝቅተኛ ፍጥረታት የተሰጠ አይደለም፡፡ የሰው ልጅም ከፍ ያለ መንፈሳዊ ንቃቱን የማዳበር ዕድሉን የማይጠቀምበት ከሆነ እና ጊዜውን ሁሉ እንደ እንስሶች ካባከነ በሚቀጥለው ሕይወቱ ሰው የመሆን የወደፊት ዕድሉን አጥቶ እንስሳ ወደ መሆን ትውልድ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡ በዓብዩ የሽሪ ክርሽና በረከት ይህን የመሰለ የሰው ልጅ ገላ እና አዕምሮ ተሰጥቶናል፡፡ ነገር ግን የተሰጠበትን ዓላማ ካላሟላንበት ለምን ሽሪ ክርሽና ይህንን ዓይነት ገላ እንደገና እንዲሰጠን እንፈልጋለን? መገንዘብ የሚኖርብን ነገር ቢኖር ይህ የሰው ልጅ ገላ የመያዝ ዕድል የገጠመን ከብዙ ሚልዮን ትውልዶች በኋላ ነው፡፡ ይህም የሰው ትውልድ የሚሰጠን ዕድል ከነዚህ ከስምንት ሚልዮን በላይ ከሚሆኑ የተለያዩ ፍጥረታት ተደጋጋሚ ትውልድ እና ሞት ነፃ እንድንሆን ነው፡፡ ይህም ዕድል የተሰጠን በሽሪ ክርሽና ነው፡፡ ይህንንም በቀላሉ የማይገኝ ዕድል ካልተጠቀምንበት ከሰው ልጅ አስተሳሰብ በታች እንደሆንን አይቆጠርምን? አንድ ሰው ከዩኒቨርስቲ በባችለር ወይም በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቆ ይሆናል፡፡ ቢሆንም ግን እንደፍላጎቱ የቁሳዊው ዓለም የምትሀት ሀይል አዕምሮውን ለተራ ዓለማዊ ኑሮ እንዲያውለው ያደርገዋል፡፡ አዕምሮው የዳበረ አዋቂ ሰው ግን አዕምሮውን የሚጠቀምበት የእራሱ ማንነት ምን እንደሆነ ለመረዳት፣ ዓብዩ የመላእክት ጌታ ማን እንደሆነ ለማወቅ፣ ይህ ቁሳዊ ዓለም መሰረቱ ምን እንደሆነ ለመገንዘብ፣ ለምንስ በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ለስቃይ እንደተጋለጥን እና ለዚህስ ስቃይ ዘለዓለማዊው መፍትሄው ምን እንደሆነ ለመመርመር ነው፡፡

አዕምሮአችንን የተሽከርካሪ መኪና ለማምረት ወይም ስሜቶቻችንን ለማርካት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን ለማምረት እንጠቀምበት ይሆናል፡፡ ቢሆንም ግን መረዳት የሚገባን ነገር ቢኖር ይህ ዓይነቱ እውቀት ፍጹም የሆነ እውቀት አይደለም፡፡ እንዲያውም ይሄ በዚህ ዓይነት መንገድ የተሰማራው አዕምሮ የተዘረፈ ወይም የተሰረቀ አዕምሮ ነው፡፡ በተፈጥሮ አዕምሮ ለሰው ልጅ የተሰጠው የቁሳዊ ዓለም ችግሮችን እንዲረዳበት እና መፍትሄውን እንዲሻበት ሲሆን በተቃራኒ ግን አዕምሮ አለቦታው ተሰማርቶ እናየዋለን፡፡ ሰዎች መኪና በማምረት እና በመንዳት እውቀት ያገኙ ይመስላቸዋል። ነገር ግን መኪና ከመመረቱ በፊትም የሰው ልጅ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው እንደልቡ የመዘዋወር ሀይል ነበረው፡፡ በእርግጥ የመጓጓዣ አቅሙ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ቢሆንም ግን ይኅው አቅም እንደ አየር የመበከል እና የመንገድ መተናነቅን የመሰለ ችግሮች አስከትሏል፡፡ ይህም “ማያ” ይባላል፡፡ ብዙ ነገሮችን በቁሳዊው ዓለም ውስጥ በመፍጠር ላይ እንገኛለን፡፡ ነገር ግን እነዚሁ የምንፈጥራቸው ቁሳዊ ምርቶች ሁሉ ብዙ ችግሮችን እያሰከተሉብንም ይገኛሉ፡፡

በእንደዚህ ዓይነቶች ብዙ ዓይነት ቁሳዊ ፈጠራዎች ሀይላችንን ከምናባክን አዕምሮዋችንን ማን እንደሆንን እና ምን እንደሆንን ለመረዳት መጠቀም ይገባናል፡፡ ማናችንም ብንሆን ስቃይ አንወድም፡፡ ስለዚህም ይህ የዚህ ቁሳዊ ዓለም ስቃይ በእኛ ላይ ለምን በግድ እንደሚከሰት መመራመር ይገባናል፡፡ እውቀት እውቀት እያልንም የአቶሚክ ቦንብን ለመፍጠር በቅተናል፡፡ በዚህም እውቀታችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ፍጥረታትን በአጭር ጊዜ ለማውደም የመቻሉን ሀይል አግኝተናል፡፡ ይህም እንደ ታላቅ የእውቀት እርምጃ ታይቶ በከፍተኛ ኩራት ላይ እንገኛለን፡፡ ትክክለኛ እውቀት አገኘን ለማለት የምንችለው ግን ሞትን ከማምጣት ይልቅ ሞትን ማቆም ነው፡፡ ሞት በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ያለ ነገር ነው፡፡ እውቀታችንን ግን ይህንኑ ሞት በአንድ በተጣለ ቦንብ ብዙሀንን በማጥፋት ስንጠቀምበት እንታያለን፡፡ ይህም “ማያያፓህርታ ግያና” ተብሎ ይታወቃል፡፡ ይህም ማለት በምትሀት ተቀዝፎ የተወሰደ እውቀት ማለት ነው፡፡

ከሀዲዎች እና ሰይጣናዊ አንደበት ያላቸው ሁሉ ዓብዩ አምላክን ሲቋቋሙ እናያቸዋለን፡፡ እርሱም ዓብዩ እና አፍቃሪ አባታችን ባይሆን ኖሮ የጥዋት የፀሀይ ጮራን ለማየት አንበቃም ነበር፡፡ ታድያ ዓብዩ የመንግስተ ሰማያት ጌታን መቋቋም ምን ፋይዳ ይኖረዋል? በቬዲክ ስነፅሁፍ ውስጥ እንደተጠቀሰው ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህም “ዴቫ” እና “አሱራ” ወይም የመላእክት መንፈስ ያላቸው እና የከሀዲነት መንፈስ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህስ የመላእክት መንፈስ ያላቸው እነማን ናቸው? የዓብዩ የመላእክት ጌታ አገልጋዮች ሁሉ “ዴቫ” ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ምክንያቱም ባህርያቸው እንደ ዓብዩ አምላክ ስለሆነ ነው፡፡ ነገር ግን የዓብዩ አምላክን ስልጣን የማያከብሩ “አሱራ” ወይም ሰይጣናት ይባላሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ዓይነት ወገኖች በሰው ልጆች ዘንድ ለዘመናት አብረው ሲኖሩ የቆዩ ናቸው፡፡

ለሽሪ ክርሽና ሙሉ ልቦናቸውን የማይሰጡ አራት ዓይነት ሰዎች አሉ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ሙሉ ልቦናቸውን ለዓብዩ የመንግስተ ሰማያት ጌታ ለመስጠት የሚችሉ አራት ዓይነት ሰዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ተጠቅሰዋል፡፡

ቻቱር ቪድሀ ብሀጃንቴ ማም
ግያና ሱክርቲኖ አርጁና
አርቶ ጂግናሱር አርትሀርትሂ
ግያኒ ቻ ብሀረታርሻብሀ

”ኦ ከብሀረታዎች ሁሉ ምርጥ የሆንከው አርጁና ሆይ አራት ዓይነት በረከት የሞላባቸው ሰዎች ለእኔ ልቦናቸውን ሰጥተው ሲያገለግሉኝ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የተጨነቁ፣ ሀብት ፈላጊዎች፣ ተመራማሪዎች፣ እና ፍጹም የሆነውን እውቀት ለማግኘት የሚሹ ናቸው፡፡” (ብጊ፡ 7.16)

ይህ ቁሳዊ ዓለም ብዙ መከራ እና ጭንቀት የሞላበት ዓለም ነው፡፡ ይህም መከራ እና ስቃይ በረከት ያለውንም ሆነ በረከት የሌለውን ወይም ድሀውን እና ሀብታሙን ሲያጠቃ ይታያል፡፡ የክረምት ቅዝቃዜ ሁሉን በእኩል ሲያጠቃ ይገኛል፡፡ ክረምት በረከት ላለው ወይም ለሌለው ድሀ ወይም ሀብታም ብሎ አይለይም። በረከት ያለው እና በረከት የሌለው ሰው ልዩነቱ ግን በረከት ያለው ሰው በችግሩ ጊዜ ሁልጊዜ ዓብዩ የመላእክት ጌታን አስታውሶ ይፀልያል፡፡ ብዙውን ጊዜ እንደምናየው አንድ ሰው በጭንቀት ላይ ሲሆን ወደ ቤተክርስቲያን ሄዶ ይፀልያል፡፡ “ጌታዬ ሆይ በጠና ችግር ላይ ስለወደቅሁ እባክህ እርዳኝ” ብሎ ይፀልያል፡፡ ምንም እንኳን ይህ ሰው ለዓለማዊ ጥቅም ወደ ዓብዩ ጌታ ይቅረብ እንጂ በችግሩ ጊዜ ወደ ፈጣሪ በመቅረቡ በረከት እንደአለው ሰው ይቆጠራል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ አንድ ድሀ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ሊፀልይ ይችላል፡፡ “ጌታዬ ሆይ እባክህ ሀብቱን ስጠኝ፡፡” እንደዚሁም ሁሉ ተመራማሪዎች እና አዕምሮ ያላቸው ተፈጥሮን ለመረዳት ሁሌ ምርምር እንደአደረጉ ነው፡፡ “ፈጣሪ አምላክ ማነው?” ብለው በመጠይቅ ሳይንሳዊ ምርምር ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ እነዚህም በረከት እንዳላቸው ይቆጠራሉ፡፡ ምክንያቱም ምርምራቸው ፈጣሪ አምላክን ለማወቅ ስለሆነ ነው፡፡ በእውቀት ላይ ያለ ሰው “ግያኒ” ተብሎ ይታወቃል፡፡ ይህም ሰው ፍጹም ማንነቱን በትክክል የተረዳ ሰው ነው፡፡ ይህም ዓይነት “ግያኒ” የአብዩን ጌታ ሰብአዊነት በትክክል ላይረዳ ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን የዓብዩ የመላእክት ጌታን ጠለላ በመቅረቡ በረከት እንደ አለው ሰው ተቆጥሮ ይታያል፡፡ እነዚህ አራት ዓይነት ሰዎች “ሱክርቲ” ወይም በረከት ያላቸው ሰዎች እንደሆኑ ይታወቃሉ። ምክንያቱም ሁሉም በተለያየ መንገድ ዓብዩ አምላክን በመቅረብ ላይ ስለሚገኙ ነው፡፡

ቴሻም ግያኒ ኒትያ ዩክታ
ኤካ ብሀክቲር ቪሺሽያቴ
ፕሪዮሂ ግያኒኖ ትያርትሀም
አሀም ሳ ቻ ማማ ፕሪያሀ

”ከእነዚህም ዓይነት ሁሉ አዋቂ የሆነው፣ አንደበቱ በፍጹም እውቀት የተሞላው ሰው እና በሙሉ ልቦናው እኔን በማገልገል ከእኔ ጋር ቀርቦ የሚገኘው ሰው ከሁሉም በላይ ሆኖ ይገኛል፡፡ እኔም ለእርሱ በጣም ተወዳጅ ነኝ፡፡ እርሱም ለእኔ በጣም ተወዳጅ ነው፡፡” (ብጊ፡ 7.17)

ከእነዚህም ከአራት አይነቱ ሰዎች መሀከል ዓብዩ አምላክን በፍልስፍና ጥረት ለመረዳት የሚጥር ሰው እና የክርሽና ንቃቱን ለማዳበር የሚሻ ሰው “ቪሺሽያቴ” ይባላል ወይም ለዚህ ንቃት በጥሩ ደረጃ ዝግጁ እንደሆነ ሰው ይቆጠራል፡፡ ሽሪ ክርሽናም እንደገለፀው እንደዚህ ዓይነት ሰው ወዳጁ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ምክንያቱም የክርሽና ንቃቱን ከማዳበር ሌላ የተለየ ፍላጎት ስለሌለው ነው፡፡ ሌሎቹ ግን በዝቅተኛነት ይታያሉ፡፡ በዓለም ላይ ማናቸውንም ነገር ለማግኘት ብለን ለፈጣሪ መፀለይ አይገባንም፡፡ ይህንንም የሚያደርግ ሰው እንደተሞኘ ሰው ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም ሁሉን የሚያውቀው ፈጣሪ አምላክ በልባችን ውስጥ እንደሆነ እና በጭንቀትም ላይ ሆነን ወይም ሀብትን የምንፈልግ መሆኑን በግልጽ ስለሚረዳ ነው፡፡ አዋቂው ሰው ግን ይህንን በትክክል ስለሚረዳ ከጭንቀቱ ለመራቅ ፀሎት ሲያደርግ አይገኝም፡፡ የፀሎቱ ትኩረት ግን ዓብዩ የመላእክት ጌታን ማመስገን እና እንዴትስ ሀያል እንደሆነ ለሌሎች በማወደስ መገኘት ነው፡፡ ለግል ጥቅሙ፣ ለእለት እንጀራው፣ ለክዳን ወይም ለመጠለያው ብሎ ሲፀልይ አይገኝም፡፡ በንጹህ ልቦናው የሚያገለግል ሰው ሲፀልይ እንዲህ ይላል “ውድ ጌታዬ ሆይ ይህ ሁሉ የሚፈፀመው በሩህሩህነትህ ነው፡፡ በጭንቀት ውስጥም ያስገባኅኝ ልታስተምረኝ እና ልታድነኝ ነው፡፡ ከዚህም የበለጠ መከራ እና ስቃይ ውስጥ መውደቅ ይገባኝ ነበረ፡፡ ነገር ግን በሩህሩህነትህ ይህ መከራ እና ስቃይ እንዲቀልልኝ አድርገህልኛል፡፡” የትሁት አገልጋይ እና የማይረበሸው ንፁህ አገልጋይ አንደት እንዲህ ይመስላል፡፡

አንድ ሰው ሙሉ ልቦናውን በክርሽና ንቃት ካዳበረ ለቁሳዊው ዓለም ጭንቀት፣ ውርደት ወይም ክብር ማጣት ምንም ግድ አይሰጠውም፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ሁሉ ርቆ ስለሚገኝ ነው፡፡ እነዚህም ሁሉ ጭንቀቶች፣ ውርደት ወይም ክብር ማጣት የተያያዙት ከቁሳዊው ገላው ጋር ስለሆነ እና እርሱም ቁሳዊ ገላው እንዳልሆነ ስለሚረዳ ነው፡፡ ለምሳሌ ሶቅራጥስ ስለ ነፍስ ዘለዓለማዊነት የተረዳ ሰው ነበረ፡፡ ሞትም ከተፈረደበት በኋላ እንዴት ተደርጐ መቀበር እንደሚፈልግ ጠይቀውት ነበረ፡፡ እርሱም ሲመልስላቸው “በመጀመሪያ ደረጃ ልትይዙኝ ያሰፈልጋችኋል ብሎ መለሰላቸው” ይህም የሚያሳየን አንድ ሰው ገላው አለመሆኑን በትክክል ከተረዳ በሞት ጊዜ ምንም ሊረበሽ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ነፍስ ለመያዝ እንደማትቻል፣ ልትገረፍ፣ ልትገደል ወይም ልትቀበር እንደማትችል ስለሚያውቅ ነው፡፡ አንድ ሰው በክርሽና ንቃት እና ሳይንስ እውቀቱ የዳበረ ከሆነ እርሱ ገላው እንደአልሆነ እና የክርሽና ወገን እና ቅንጣፊ አካል መሆኑን የተረዳ ነው፡፡ ትክክለኛ ግኑኝነቱም ከክርሽና ጋር እንደሆነ የተገነዘበ ነው፡፡ ምንም እንኳን ነፍሱ በዚህ ጊዜያዊ ቁሳዊ አካል ውስጥ ተጠምዳ ብትገኝም ከሶስቱ የቁሳዊ ዓለም ባህሪያቶች ተወግዶ መኖር እንደሚገባው የተረዳ ነው፡፡ በሶስቱ የቁሳዊ ዓለም ባህሪያት የተጠቃ አይደለም፡፡ ማለትም የጥሩ ባህርይ፣ ረጋ ያለ መንፈስ የሌለው እና የድንቁርና መንፈስ ላይ ያለ ሰው ሲሆን የእርሱ ባህሪ ግን ክርሽናን ማገልገል ብቻ ሆኖ ይገኛል። አንድ ይህንን በትክክል የተረዳ ሰው “ግያኒ” ወይም አዋቂ ሰው ይባላል፡፡ እርሱም ለክርሽና በጣም ውድ ሆኖ ይገኛል፡፡ በጭንቀት ላይ ያለ ሰው ሀብት ሲያገኝ ዓብዩ ፈጣሪ ጌታን ይረሳ ይሆናል፡፡ ግያኒ ግን ዓብዩ አምላክን በትክክል የተረዳ ስለሆነ በምቾትም ላይም ሆኖ አገልጋይ መሆኑን ፈጽሞ አይረሳም፡፡

በዓብዩ አምላክ ሰብአዊነት የማያምኑ የተለዩ የግያኒ ወገኖች አሉ። እነርሱም የሰብአዊ ቅርጽ የሌለው አምላክን ለማምለክ አስቸጋሪ ስለሚሆን የአምላክን ቅርጽ በሀሳባችን መፍጠር አለብን ብለው ያምናሉ፡፡ እነዚህም በሞኝነት የተመሩ እንጂ ትክክለኛ ግያኒዎች አይደሉም፡፡ ማንም ሰው የሀያሉ የዓብዩ አምላክን ቅርጽ በሀሳቡ መፍጠር አይችልም፡፡ አንድ ሰው የመሰለውን በሀሳቡ መቅረጽ ይችላል ነገር ግን ይህ ግምታዊ እንጂ ፍጹም የሆነው የዓብዩ አምላክ ቅርጽ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ አንዳንድ ሰዎች የዓብዩ አምላክን ቅርጽ በሀሳባቸው ሲገምቱ ይገኛሉ፡፡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ዓብዩ አምላክ ምንም ቅርጽ የለውም ብለው ይሟገታሉ፡፡ እነዚህ ሁለቱም ዓይነት ሰዎች ግያኒ ተብለው ሊታወቁ አይችሉም፡፡ የዓብዩ ፈጣሪ አምላክን ቅርጽ ገምተው የሚያሰላስሉ “አይኮኖክላስትስ” ተብለው ይታወቃሉ፡፡ በህንድ አገር በሂንዱ እና በእስላሞች መካከል በነበረው የረብሻ ጊዜ ሂንዱዎች ወደ መስጊድ በመሄድ ጥፋት ያደርሱ ነበር፡፡ እስላሞችም እንደዚሁ ወደ ሂንዱ ቤተ መስቀዶች በመሄድ የአምላክን ቅርጾች እና ምስሎች ሁሉ ያወድሙ ነበረ፡፡ በዚህም መንገድ ሁለቱም የሂዱን ማምለኪያ ወይም የእስልምናን ማምለኪያ አወደምነው በማለት ያሰቡ ነበር፡፡ እንደዚህም ሁሉ በማህተመ ጋንዲ የትግል እንቅስቃሴ ጊዜ ብዙ ሰዎች በመንገድ ይገኙ የነበረቱን የፖስታ ሳጥኖች እየዞሩ ያወድሟቸው ነበረ። በዚህም መንገድ እነዚህ ሰዎች የመንግስትን የፖስታ ድርጅት አፈረስን ብለው ያሰቡ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ግያኒ ተብለው ሊታወቁ አይችሉም፡፡ ይህ በእስልምና፣ በሂንዱ፣ በክርስትና እና ክርስቲያን ባልሆኑ መካከል ያለው ግጭት እና ብጥብጥ በድንቁርና ህልውና ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ነው፡፡ አንድ ንጹህ እውቀት ያለው ሰው ወይም ግያኒ ዓብዩ የመላእክት ጌታ ወይም ፈጣሪ አንድ ብቻ እንደሆነ የተረዳ ሰው ነው፡፡ የእስላም ፈጣሪ አምላክ የሂንዱ ወይም የክርስትና ፈጣሪ አምላክ ብሎ ነገር የለም፡፡

ይህ በድንቁርና የተመሰረተ የሰው ልጅ ፈጠራ ነው፡፡ ትክክለኛው አዋቂ ሰው ዓብዩ አምላክ አንድ አብይ መንፈሳዊ ደረጃ ላይ እንደአለ የተረዳ ነው፡፡ አንድ ሰው ዓብዩ አምላክ ከቁሳዊው ዓለም ባህሪዎች በላይ የሆነ እና ፍጹም መንፈሳዊ አንድ አብይ አካል መሆኑን የተረዳ ሰው በትክክል አምላክን እንደተረዳ ይታወቃል፡፡ ዓብዩ አምላክ ሁልጊዜ ከአጠገባችን እና በልባችንም ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በሞትም ከዚህም ገላ እና ዓለም ስንለይ ዓብዩ አምላክ አብሮን ይሄዳል፡፡ ወደ እዚህ ዓለምም እንደገና በትውልድ ስንመጣ እርሱም ሁሌ አብሮን ይገኛል፡፡ የምናስበውን እና የምናደረገውን ነገር ሁሉ በጥሞና ይከታተላል፡፡ ታድያ እራሳችንን ወደ እርሱ የምናዞረው መቼ ነው? እርሱም ሁልጊዜ እኛን እንደጠበቀ ነው፡፡ በድንገትም ሀሳባችንን ወደ እርሱ ስናዞር እርሱም እንዲህ ይለናል፡፡ “ልጄ ሆይ ወደ እኔ ና — ሳቻ ማማ ፕሪያሀ — አንተ በእኔ ለዘልአለም የምትፈቀር ነህ፡፡ ወደ እኔ በመመለስህም በጣም ደስታ ተሰምቶኛል፡፡”

ግያኒዎች ወይም አዋቂዎች ሁሉ የዓብዩ አምላክን ሳይንሳዊ እውቀት በትክክል የተረዱ ናቸው። አንድ ሰው የዓብዩ አምላክ ጥሩ መሆኑን ብቻ ሲረዳ በመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኝ እውቀት እንደያዘ ይታወቃል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ዓብዩ አምላክ ምን ያህል ኃያል እና ጥሩ መሆኑን ደግሞ የተረዳ በእውቀቱ የዳበረ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህም ዓይነቱ እውቀት እንደ ሽሪማድ ብሀገቨታም እና እንደ ብሀገቨድ ጊታ በመሳሰሉት የቬዲክ ስነጽሁፎች በትንተና ተገልጿል፡፡ በዓብዩ አምላክም እውቀት ለመዳበር የሚሻ ሰው ሁሉ እነዚህን ስነፅሁፎች በተለይ ብሀገቨድ ጊታን በጥሞና ማጥናት ይገባዋል፡፡

ኢዳም ቱ ቴ ጉህያታማም
ፕራቫክስያሚ አናሱያቬ
ግያነም ቪግያና ሳሂታም ያጅ
ግያትቫ ሞክሻያሴ ሹብሀት

“ውድ አርጁና ሆይ አንተ ምንጊዜም ቢሆን በእኔ የምቀኝነት ባህርይ ስለሌለህ ይህንን ሚስጢራዊ ታላቅ እውቀት ለአንተ ልገልፅልህ መርጫለሁ፡፡ ይህንንም እውቀት በመረዳት ከቁሳዊው ዓለም መከራ ሁሉ ነፃ ለመሆን ትችላለህ፡፡” (ብጊ፡ 9.1)

በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ የተገለፀው የዓብዩ አምላክ እውቀት በጣም ሚስጢራዊ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህም በግያና ወይም በስውራዊ ብልሀት አገላለፅ የተሞላ እና በቪግያና ወይም በሳይንሳዊ እውቀትም የተመሰረተ ነው፡፡ እንደዚሁም ሆኖ በሚስጢራዊ እና ስውር እውቀቶች የተሞላ ሆኖ ይገኛል፡፡ ታድያ ይህንን ዓይነት እውቀት እንዴት አንድ ሰው ሊረዳው ይችላል? ይህም ሊሆን የሚችለው ይኀው እውቀት በዓብዩ አምላክ ሲገለፅ እና እውቀቱ ባለው በዓብዩ አምላክ የምድር ተወካይ ሲገለፅ ነው፡፡ ስለዚህም ሽሪ ክርሽና በብሀገቨድ ጊታ እንደገለፀው በዚህ ዓለም ላይ የሀይማኖታዊ እውቀት በወደቀ ቁጥር እርሱ ራሱ ይህንኑ የመንፈሳዊ እውቀት ለማስተማር ወደ ምድር ይመጣል፡፡

የዓብዩ አምላክ እውቀት በገዛ የግል ጥቅም ስሜታችን በተነሳሳ ገለፃ ሊከሰት አይችልም፡፡ ንጹህ ልቦናዊ መንፈሳዊ አገልግሎት በግል የስሜታዊ ጥቅም ትንተና ሊገለጽ አይችልም፡፡ ይህ ገለፃ የሳይንሳዊ ሂደት የያዘ ነው፡፡ ሽሪላ ሩፓ ጎስዋሚ እንደገለፀው “ከቬዲክ ንፁህ እውቀት ጋራ ያልተያያዘ የመንፈሳዊ ባህርይ ህብረተሰቡን ሁሉ የሚያውክ ነው፡፡ “አንድ ሰው ወደዚህ ጣፋጭ እና ከልብ የመነጨ የፍቅር አገልግሎት ላይ መሰማራት ያለበት በመንፈሳዊ እውቀት፣ በክርክር እና ምክንያቱን በጥልቅ በመረዳት ነው፡፡ ይህም ደረጃ ላይ የደረሰ ሁሉ እውቀቱን በትክክል ወደ ሌሎች ለማስተላለፍ ይችላሉ፡፡ የክርሽና ንቃት እንደ ተራ የስሜታዊ ንቃት ብቻ ሆኖ መገኘት የለበትም፡፡ በሙሉ ልቦና ዓብዩ አምላክን ማወደስ፣ መደነስ እና መዘመር ሁሉ በሳይንሳዊ መንገድ ጥቅሙ እና ምክንያቱ ሊገለጽ የሚችል ነው፡፡ ይህንንም ለመረዳት የሳይንሳዊ ሂደት ይኖረዋል፡፡ ይህ የመንፈሳዊው አገልግሎት ከአምላክ ጋር በፍቅር የተመሰረተ ግኑኝነት አለው፡፡ ክርሽና መንፈሳዊ አገልግሎትን ለሚያቀርብ አዋቂ ሰው ፍቅር አለው፡፡ አዋቂውም ሰው ለክርሽና እንደዚሁ ፍቅር አለው፡፡ ክርሽና ይህንኑ ፍቅራችንን ዓይቶ ከሺህ በላይ አድርጎ ፍቅሩን ይመልስልናል፡፡ እኛ ውስን ፍጡራን ታድያ ምን ዓይነት የፍቅር ሀይል አለን? ክርሽና ወሰን የሌለው ከፍተኛ ፍቅር ለእኛ ይዞ ይገኛል፡፡

« Previous Next »