No edit permissions for Amharic

5

ወደ ዓብዩ መጓዝ

ኡዳራህ ሳርቫ ኤቫይቴ ግያኒ
አትማቭያ ሜ ማታም
አስትሂታሀ ሳ ሂ ዩክታማ
ማም ኤቫኑታማም ጋቲም

“ትሁት አገልጋዮቼ ሁሉ ያለ ምንም ጥርጥር የላቁ እና የከበሩ ናቸው፡፡ በእኔ ሀያልነት በእውቀት ዳብሮ የሚያገለግለኝ ሁሉ በውስጤ እንደሚኖር አድርጌ አየዋለሁ፡፡ በእኔም የትሁት መንፈሳዊ ስርአት በመሰማራት ወደ እኔ በቀላሉ ለመድረስ ይችላል፡፡” (ብጊ፡ 7.18)

በዚህም ጥቅስ ሽሪ ክርሽና እንደገለፀው ወደ እርሱ የሚቀርቡትን አገልጋዮች ሁሉ በደስታ ይቀበላቸዋል፡፡ እነዚህም የተጨነቁ፣ ሀብት ፈላጊዋች፣ ተመራማሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ግን በመንፈሳዊ እውቀት ዳብሮ የሚቀርበው ሰው ለእርሱ በጣም ውድ መሆኑን እየገለፀልን ነው፡፡ ሌሎች ወደ ክርሽና በተለያየ ዓለማዊ ምኞቶች የሚቀርቡትን ሁሉ ክርሽና በደስታ ይቀበላቸዋል፡፡ ምክንያቱም ከጊዜ በኋላ በዚሁ ቅርበት ከቀጠሉ ቀስ በቀስ እውቀት የተሞላበት የአገልጋይ ደረጃ ላይ ሊደርሱ ስለሚችሉ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ መንፈሳዊ እውቀት የሌለው ሰው ሀብትን ለማግኘት ወደ ቤተክርስትያን መሄድ እና መፀለይ ይጀምር ይሆናል። ከጊዜ በኋላ ግን ይህንን ሀብት ማግኘት ካልቻለ ወደ ፈጣሪ አምላክ ልቡን ሰጥቶ መፀለይ ያቆማል፡፡ ከቤተክርስቲያኑም ጋር ያለውን ግኑኝነት ሁሉ ለማቆም ይወስናል፡፡ የግል ፍላጎታችንንም ለማርካት ፈጣሪ አምላክን መቅረብ አደጋው ይህው ነው፡፡ ለምሳሌ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ብዙ የጀርመን ወታደር ሚስቶች ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ፀሎት ያደርጉ ነበር፡፡ ይህም ወታደር ባሎቻቸው ወደ ጦርነት በመሄዳቸው በህይወት እንዲመለሱላቸው ፈልገው ስለነበረ ነው፡፡ ነገር ግን ባሎቻቸው ሁሉ በጦር ሜዳ ላይ ሕይወታቸው በማለፉ እምነታቸው ሁሉ ጠፍቶ ወደ ከሀዲያን መንፈስ ተቀይረው ነበር፡፡ በእንደዚህም ዓይነት ሁኔታ ዓብዩ አምላክን የትእዛዛችን አቅራቢ ልናደርገው እንሞክራለን፡፡ በፈቃዱም ትእዛዛችንን ሳያሟላ ከቀረ ፈጣሪ አምላክ ሊኖር አይችልም ብለን እንደመድማለን፡፡ ዓለማዊ እና ቁሳዊ የሆነ ነገርም ለማግኘት ፀሎት ማድረግ ውጤቱ ይህው ነው፡፡

ከዚህም ታሪክ ጋር የተያያዘ የአንድ ድሁርቫ የሚባል የአምስት ዓመት እና ከንጉሳውያን ቤተሰብ የተወለደ ልጅ ነበረ፡፡ በአንድ ወቅትም ንጉሱ ስምምነት በማጣቱ ንግስቲቷን ከማእረግ አውርዶ ፈታት፡፡ ከዚያም ሌላ ሴት በትዳር በመያዝ ንግስት እንድትሆንም አበቃት፡፡ ይህችም አዲስ ንግስት የልጁ የድሁርቫ የእንጀራ እናት ሆነች፡፡ ይህችም እንጀራ እናት በድሁርቫ በጣም ምቀኝነት የሚያጠቃት ነበረች፡፡ አንድ ቀንም ድሁርቫ በአባቱ ጉልበት ላይ ቁጭ ብሎ እያለ ልትሰድበው በቃች፡፡ “አንተ የአባትህ ጉልበት ላይ ልትቀመጥ አይገባህም” ብላ ተናገረች “ምክንቱም አንተ ከእኔ ስላልተወለድክ ነው፡፡” ከዚያም ልጁን ቁጭ ካለበት ከአባቱ ጉልበት ጎትታ አወረደችው፡፡ ልጁም በዚህ ሁኔታ በጣም ተናደደ፡፡ ልጁ የተወለደውም ከሻትርያ ወይም የጦር ሠራዊት ቤተሰብ የተወለደ በመሆኑ በቀላሉ የቁጠኝነት ባህርይ ነበረው፡፡ ድሁርቫም ይህንን እንደ ትልቅ ውርደት አድርጐ ስለወሰደው ከንግስትነት ማዕረግ ወደወረደችው እናቱ ሄደ፡፡

“ውድ እናቴ ሆይ የእንጀራ እናቴ ከተቀመጥኩበት ከአባቴ ጉልበት ላይ ጐትታ አዋረደችኝ፡፡”

እናቱም እንዲህ አለችው፡፡ “ውድ ልጄ ሆይ እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ? አባትህ ለእኔ ምንም ግድ ስለማይስጠው ምንም ልረዳህ የምችለው ነገር አይኖረኝም።”

ልጁም እንዲህ ብሎ መጠየቅ ጀመረ፡፡ “ታድያ እንዴት አድርጌ ነው ይህንን ለመበቀል የምችለው?”

እናቱም እንዲህ ብላ መከረችው፡፡ “ልጄ ሆይ ለመበቀል እንድትችል ሊረዳህ የሚችል ቢኖር ዓብዩ ፈጣሪ አምላክ ብቻ ነው”

እርሱም በችኮላ “ኦህ ዓብዩ ፈጣሪ አምላክ የት ነው?” ብሎ ጠየቀ ፡፡

እናቱም እንዲህ አለችው፡፡ “እኔ እንደምረዳው ብዙዎች ባህታውያን ወደ ጫካ በመግባት ዓብዩ አምላክን ለመቅረብ እና ለማየት ይሻሉ፡፡ በዚህም ጫካ ውስጥ ዓብዩ አምላክን ለማየት ብዙ ፀሎት ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡”

ድሁርቫም ወዲያውኑ ወደ ጫካ በመግባት ያገኘውን አውሬዎች አንበሳም ሆነ ዝሆኖችን “አንተ ዓብዩ አምላክ ነህ?” እያለ በመጠየቅ በመላ ጫካው መዞር ጀመረ፡፡ ድሁርቫም ዓብዩ አምላክን ለማየት በጣም ትልቅ ፍላጎት ነበረው፡፡ በዚህም ግዜ ዓብዩ ፈጣሪ አምላክ ሽሪ ክርሽና ናራዳ የተባለውን አገልጋዩን ሂዶ ድሁርቫን እንዲያነጋግረው ጠየቀው፡፡ ናራዳም ወዲያውኑ ወደ ጫካው በመሄድ ድሁርቫን አገኘው፡፡

ናራዳም እንዲህ አለው፡፡ “ውድ ልጄ ሆይ አንተ ከንጉሳውያን ቤተሰብ የተወለድክ ነህ፡፡ በዚህም ጫካ ውስጥ ገብተህ ይህንን ሁሉ ድካም እና ችግር እንድታይ አያስፈልግም፡፡ ስለዚህም ወደ ቤተ መንግስትህ ብተመለስ ይሻላል፡፡ እናት እና አባትህ ስለአንተ ብዙ ሳይጨነቁ አይቀሩም፡፡” ብሎ ገለፀለት፡፡

ድሁርቫም እንዲህ አለው፡፡ “እባክህ እንዲህ በማለት ከዓላማዬ እንዳፈነግጥ አታድርገኝ፡፡ ስለ ዓብዩ ፈጣሪ አምላክ የምታውቅ ከሆነ ወይም እንዴት እንደማየው የምታቅ ከሆነ ብትነግረኝ ጥሩ ነው። አለበለዛ ግን ብትሄድልኝ እና ባትረብሸኝ እመርጣለሁ፡፡” ብሎ ነገረው፡፡

ናራዳም ይህ ልጅ ዓብዩ አምላክን የማየት ትልቅ ፍላጎት እንደአለው በመረዳቱ በድቁና ስርዓት እንደ ተማሪው አድርጎ ተቀበለው፡፡ “ኦም ናሞ ብሀገቨቴ ቫሱዴቫያ” ተብሎ የታወቀውንም አብይ ማንትራ ወይም የፀሎት ማህሌት ሊሰጠው በቃ፡፡ ድሁርቫም ይህንን ማንትራ በትህትና ደጋግሞ በመዘመሩና ንፁህ የሆነ ደረጃ ላይ በመድረሱ ዓብዩ አምላክ አንድ ቀን ከፊቱ ሊቀርብለት በቃ፡፡

”ዓብዩ ፈጣሪ አምላክም እንዲህ አለው፡፡ “ልጅ ድሁርቫ እኔ ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” “ከእኔም የፈለከውን ጠይቀህ ማግኘት ትችላለህ” ብሎ ነገረው፡፡

ልጁም እንዲህ በማለት መለሰ፡፡ “ጌታዬ ሆይ ይህንን ሁሉ ፀሎት እና መከራ ለማሳለፍ የተመኘሁት የአባቴን መንግስት እና ሀብት ለመውረስ ነበረ፡፡ ነገር ግን አሁን አንተን ለማየት በቅቻለሁ፡፡ ሌሎች ታላላቅ ባህታውያን እና መንፈሳውያን አንተን በቀላሉ ለማየት አይችሉም፡፡ ታድያ የእኔ ልፋት ትርፉ ምኑ ላይ ነው? ቤተ መንግስቴንም ጥዬ የመጣሁት የማይረባውን የቤተመንግስት ቁሳቁስ ለመውረስ ነበር፡፡ አሁን ግን አንተን የመሰለ ውድ የሆነ ዕንቁ አግኝቻለሁ፡፡ ስለዚህም በልቤ ደስተኛ ሰለሆንኩኝ ከአንተ ምንም የምጠይቀው ነገር አይኖረኝም፡፡” ብሎ ገለፀለት፡፡

ከዚም ታሪክ እንደምንረዳው ምንም እንኳን አንድ ሰው የደኅየ ወይም በጭንቀት ላይ ያለ ቢሆን እና ዓብዩ ፈጣሪ አምላክን ለማየት እንደ ልጅ ድሁርቫ የወሰነ ከሆነ እና ለማየት ከበቃ ምንም ዓይነት ቁሳዊ ሀብት ሊያስደስተው እና ሊመኝም አይችልም፡፡ የቁሳዊ ዓለምንም ሀብት መፈለግ ሞኝነት መሆኑን መገንዘብ ይችላል፡፡ ይህንንም የዓለማዊ ምትሀት እርግፍ አድርጎ ትቶ ፍፁም የሆነው ደስታ ወደሚገኝበትም የዓብዩ አምላክ ቤተ መንግስት ለመሄድ ይዘጋጃል፡፡ አንድ ሰው በሽሪ ክርሽና የመንፈሳዊ ንቃት የዳበረ ከሆነ ምንም ዓይነት የዓለማዊ ቁሳቁሶችን ለመመኘት አያደላም፡፡

ግያኒ ወይም አዋቂ ምሁር ሰው ዓለማዊ ቁሳቁሶች ሁሉ ጊዜያዊ ደስታን ብቻ እንደሚሰጡ የተረዳ ነው፡፡ እነዚህም ቁሳዊ ሀብቶች በሶስት ዓይነት ደረጃ የሰውን ሕይወት የሚያጓድሉ ናቸው፡፡ አንዱም ከስራው ትርፍ ለማግኘት እንዲጥር ያደረገዋል፡፡ ሌላው በሀብቱ ሰዎች እንዲያከብሩት ጥረት ያደርጋል፡፡ ሌላው በሀብቱ ዝና ያለው ሰው እንዲሆን ይጥራል፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ ሀብቶች ቢኖሩንም ሀብታችን ከገላችን ጋር የተያያዘ ስለሆነ በሞት ገላችንን ጥለን ስንሄድ እነዚህን ሀብቶች ሁሉ ወደ ኋላ ትተናቸው እንሄዳለን፡፡ ሞት በሚመጣበትም ጊዜ ሀብታም መሆናችን ቀርቶ ነፍስ ብቻ እንሆናለን፡፡ በሕይወታችን ከሰራነውም ስራ አንፃር ወደ አዲስ ገላ ገብተን እንደገና ለመወለድ እንበቃለን፡፡ በብሀገቨድ ጊታም ውስጥ እንደተጠቀሰው አንድ አዋቂ የሆነ ሰው በዚህ ዓይነት ዓለማዊ ምኞት አይታለልም፡፡ ምክንያቱም ምንን ከምን ለይቶ የሚረዳ ሰው በመሆኑ ነው፡፡ ታድያ ይህንን እውቀት ይዞ እንዴት በዚህ ዓለም የሚገኘውን ጊዜያዊ ሀብት ለማሳደድ ይመኛል? በመንፈሳዊ እውቀት የዳበረ ሁሉ እንዲህ በማለት ያሰላስላል፡፡ “ከሽሪ ክርሽና ዓብዩ የመላእክት ጌታ ጋር ዘለዓለማዊ የሆነ ግኑኝነት አለኝ፡፡ አሁን ከሽሪ ክርሽና ጋር ያለኝን ግኑኝነት ጠበቅ አድርጌ በማዳበር ሽሪ ክርሽና ወደ መንፈሳዊ ቤተመንግስቱ እንዲወስደኝ ጥረት ማድረግ ይኖርብኛል፡፡”

በዚህ ዓለም ላይ ከሽሪ ክርሽና ጋር ያለንን ግኑኝነት ለማዳበር እና ወደ እርሱም ለመመለስ አሰፈላጊው ነገር ሁሉ ቀርቦልን ይገኛል፡፡ የሕይወታችንም ዋና ዓላማ ይህ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ የሚያስፈልገንም ነገር ሁሉ በዓብዩ ፈጣሪ አምላክ ቀርቦልን ይገኛል። እነዚህም መሬት፣ እህል፣ ፍራፍሬ፣ ወተት፣ መጠለያ እና ክዳን የመሳሰሉትን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ እኛም የሚጠበቅብን በሰላም መኖር እና የክርሽና ንቃታችንን ማዳበር ብቻ ነው፡፡ የሕይወታችን ዓላማም ይኅው ነው፡፡ ዓብዩ የመንግስተ ሰማያት ጌታ ባቀረበልን ምግብ፣ መጠለያ፣ መከላከያ፣ የጋብቻ የወሲብ ዕድል እና በቀረበልን ነገር ሁሉ ደስተኛ መሆን ሲገባን ከሚያሰፈልገን በላይ ግን ሀብት ለማግኘት ጥረት ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብናል፡፡ የስልጣኔ ምልክት አንድ ሰው “ቀለል ያለ ኑሮ እና ከፍ ያለ አስተሳሰብ” ሲኖረው ነው፡፡ የተፈጥሮ ምግብን እና ወሲብን በፋብሪካ ውስጥ ልናመርታቸው አንችልም፡፡ እነዚህ ሁሉ በዓብዩ ፈጣሪ አምላክ የቀረቡልን ናቸው፡፡ የእኛም ሀላፊነት እነዚህ በተፈጥሮ የቀረቡልልን ሁሉ በመጠቀም የዓብዩ የመላእክት ጌታ መንፈሳዊ ንቃታችንን ማዳበር ነው፡፡

ምንም እንኳን ዓብዩ ፈጣሪ አምላካችን በዚህ ዓለም ላይ በሰላም እንድንኖር ሁሉንም ነገር ቢሰጠን እና መንፈሳዊ ንቃታችንን በማዳበር ወደ እርሱ እንድንመለስ ብቃቱን ቢጨምርልንም እኛ ግን ሳንጠቀምበት እንገኛለን፡፡ ሕይወታችንም በአጭሩ ሊቀጭ ይችላል፡፡ በረሀብ የሚጠቁ፣ መጠለያ የሌላቸው፣ ትዳር የሌላቸው ወይም ከተፈጥሮ ጥቃት ከለላ የሌላቸው ብዙሀን የሕብረተሰብ አካሎች ይገኛሉ፡፡ ይህም ካሊ ዩጋ ተብሎ የሚታወቀው የጥል እና የብጥብጥ ዘመን ጫና ነው፡፡ ስለዚህም ጌታ ቼይታንያ ይህን የሚያስቀይም ዘመን በማየቱ መንፈሳዊ ሕይወታችን በታታሪነት እንድንቀሰቅስ አጥብቆ መክሮናል፡፡ እንዴትስ ይህንን ማድረግ እንችላለን? ቼታንያ መሀፕራብሁም ለዚሁ ቀመሩን ወይም ፎርሙላውን ሰጥቶናል፡፡

ሀሬር ናማ ሀሬር ናማ ሀሬር ናመይቫ ኬቫላም
ካላዎ ናስት ኤቫ ናስት ኤቫ ናስት ኤቫ ጋቲር አንያትሀ
(ቼ ቻ አዲ 17.21)

“ሁል ጊዜ የሀሬ ክርሽናን ቅዱስ ስም ዘምር” ይህንንም ቅዱስ ስም ለመዘመር ምንም እንኳን በፋብሪካ ውስጥ ወይም በሲኦል መንገድ ዳር ወይም በታላቅ ህንፃ ውስጥ የምትኖር ብትሆንም የቦታ ለውጥ ለመዘመር አይወስንህም፡፡ ስለዚህ መዘመርህን አታቋርጥ፡፡ “ሀሬ ክርሽና ሀሬ ክርሽና ክርሽና ክርሽና ሀሬ ሀሬ ሀሬ ራማ ሀሬ ራማ ራማ ራማ ሀሬ ሀሬ” ይህም ስርዓት የገንዘብ ወጪ አይኖረውም፣ እንቅፋት አይኖረውም፣ የጎሳ ልዩነት አይጠይቅም እንዲሁም የገላ ቀለም ልዩነት አይጠይቅም፡፡ ማናቸውም ሰው ሊያደርገው የሚችል ስርዓት ነው፡፡ ዋነኛው ሀላፊነታችን ይህንን ቅዱስ ስም መዘመር እና ማዳመጥ ብቻ ነው፡፡

አንድ ሰው ወደ ክርሽና ንቃት ከቀረበ እና ስልጣን ባለው መምህር ስር በመተዳደር የክርሽና ንቃቱን የሚያዳብር ከሆነ ወደ ዓብዩ ፈጣሪ አምላክ መመለሱ የተረጋገጠ ነው፡፡

ባሁናም ጃንማናም አንቴ
ግያናቫን ማም ፕራፓድያቴ
ቫሱዴቫ ሳርቫም ኢቲ ሳ
ማሃትማ ሱዱርላብሀሀ

“ከብዙ ትውልድ እና ሞት በኋላ በመንፈሳዊ እውቀት የተመሰጠ ሰው ሙሉ ልቦናውን ለእኔ ይሰጣል፡፡ ይህም እኔ የሁሉም ነገር መነሻ እና መድረሻ መሆኔን በትክክል ስለሚረዳ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱም ታላቅ መንፈስ ያለው ሰው በርካታ ሆኖ አይገኝም፡፡” (ብጊ 7.19)

ዓብዩ ፈጣሪ አምላክን ለማወቅ የሚደረገው የፍልስፍና ምርምር በጣም ብዙ ትውልድ ሊጠይቅ ይችላል። ዓብዩ የመላእክት ጌታን ለማወቅ በጣም ቀላል ነው፡፡ ቢሆንም ግን የማወቁ ስርአት በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ የክርሽናንም ቅዱስ ስም በመዘመር ስርዓቱን በቀጥታ ለሚቀበሉ ሁሉ ሽሪ ክርሽናን ለማወቅ በጣም ቀላል ሆኖ ያገኙታል፡፡ ነገር ግን ክርሽናን በምርምር እና በፍልስፍና እውቀታቸውን በማስፋፋት ለመረዳት የሚጥሩ ሁሉ ክርሽናን ለማወቅ በጣም የሚከብድ ሆኖ ያገኙታል፡፡ ምክንያቱም ክርሽናን ሊቀበሉ የሚፈልጉት ምርምራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በመሆኑ ይህ ስርዓት ብዙ ትውልድ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ “ታትቫቪት” ተብለው የሚታወቁ ፍፁም እውነትን በትክክል የተረዱ መንፈሳውያን ይገኛሉ፡፡ እነዚህም መንፈሳውያን ይህ ፍፁም የሆነው የዓብዩ ታላቅነት ለሁለት ሊከፈል እንደማይችል የተረዱ ናቸው፡፡ ይህ ፍፁም የሆነው እውነት ለሁለት የተከፈለ አይደለም፡፡ የፈጣሪ ጌታ አብይነት በአንድ ፍፁም የሆነ በማይከፈል የእውነት ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ይህንንም ፍፁም እውነት በትክክል የተረዳ ሰው “ታትቫ ቪት” ተብሎ ይታወቃል፡፡

ክርሽና እንደገለፀው ይህ ፍፁም የሆነው እውነት በሶስት መንገድ ወይም ስርዓት ሊታወቅ ይችላል፡፡ “ብራህማን ፓራማትማ እና ብሀገቫን” ከእነዚህም ሶስቱ ፍፁም እውነቶች የመጀመሪያው ሰብዓዊነት የሌለው በመንፈሳዊው ዓለም ተሰራጭቶ የሚገኘው እና ከዓብዩ የመላእክት ሁሉ ጌታ የሚመነጨው የብርሀን ጮራ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በልባችን ውስጥ ተቀምጦ የሚገኘው ዓብዩ የመንግስተ ሰማያት ጌታ ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ በመንፈሳዊው ዓለም የሚገኘው ዓብዩ የመላእክት ጌታ ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የዓብዩ አምላክን ፍፁም እውነት ለማወቅ የሚደረገው ጥረት ከእነዚህ ከሶስቱ አንፃር ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው አንድን ትልቅ ተራራ በጣም ርቀት ካለው ቦታ አይቶ ስለ ተራራው አንዳንድ ባህርይ ሊረዳ ይችላል፡፡ ወደ ተራራውም ቀረብ ሲል ደግሞ ዛፎችን እና የተራራውን ቅርፅ በተሻለ መንገድ ሊረዳ ይችላል፡፡ ተራራውም ላይ ወጥቶ የሚራመድ ከሆነ ደግም ምን ዓይነት የተለያዩ ዛፎች እና ተክሎች እንዳሉት ምን ዓይነት እንስሶች እንደሚኖሩበት ሁሉ በትክክል ሊረዳ ይችላል፡፡ ስለ ዓብዩ የመላእክት ጌታ ፍፁም እውነት የመረዳቱ ዓላማው አንድ ነው፡፡ ነገር ግን መንፈሳውያን ይህንን ፍፁም እውነት የሚረዱት ከተለያየ አመለካከት በመሆኑ የመረዳቱ አስተሳሰባቸው የተለየ ነው፡፡ ከሌላ ምሳሌም እንደምንረዳው የፀሀይ ነፀብራቅ፣ ክብ የፀሀይ ቅርፅ እና ፀሀይ እራስዋን እንደ ምሳሌ ለመጠቀም ይቻላል፡፡ ፀሀይን የሚሞቅ ሰው ፀሀይ ውስጥ እንደሚኖር ፍጡር ስለፀሀይ የተረዳ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ፀሀይ ውስጥ የሚገኝ ፍጡር ግን ስለ ፀሀይ ለመረዳት አመቺ ቦታ ላይ ሆኖ ይገኛል፡፡ የፀሀዩ ነፀብራቅ በመንፈሳዊ ዓለም ተሰራጭቶ እንደሚገኘው የዓብዩ የመላእክት ጌታ የገላ ጮራ ይመሰላል፡፡ ክብ ሆኖ ከሩቅ የሚታየው የፀሀይ ቅርፅም በልባችን እንደሚገኘው የዓብዩ አምላክ ሊመሰል ይችላል፡፡ በፀሀይ ውስጥ የሚኖረው የፀሀይ አምላክ ደግሞ በመንፈሳዊው ዓለም እንደሚገኘው እንደ ዓብዩ የመንግስተ ሰማያት ጌታ ሊመሰል ይችላል፡፡ በዚህም ምድር ላይ እንደምናየው ብዙሀን የተለያዩ ነዋሪ ፍጥረታት ይገኛሉ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ከቬዲክ ስነጽሁፎች እንደምንማረው በፀሀይ ላይም ብዙሀን የተለያዩ ፍጥረታት ይገኛሉ፡፡ ልዩነታችን ግን የእኛ ገላ በአፈር እንደተሸፈነ ሁሉ የእነርሱ ገላ ደግሞ በእሳት የተሸፈነ ነው፡፡

በዚህ ቁሳዊ ምድራችን ላይ አምስት ዓይነት ቁሳዊ ነገሮች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም አፈር፣ ውሀ፣ እሳት፣ አይር እና ባዶ ቦታ ናቸው፡፡ በተለያዩም ፕላኔቶች ውስጥ በእነዚህ የተመሰረቱ የተለያዩ ክስተቶች አሉ፡፡ ምን ዓይነት የፍጥረታት ገላ መኖር እንደሚገባውም የሚወስነውም ምን ዓይነት ክስተት ፕላኔቱ እንደሚኖረው ነው፡፡ ሁሉም ፕላኔቶች አንድ ዓይነት ክስተት ይኖራቸዋል ብለን ማሰብ አይገባንም፡፡ ቢሆንም ግን አምስቱም ቁሳዊ ነገሮች በሁሉም ፕላኔቶች ስለሚገኙ ተመሳሳይነትም እንደ አለ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ በአንዳንድ ፕላኔቶች አፈር በብዛት ሊገኝ ይችላል፡፡ ሌላው ፕላኔት ላይ ደግሞ እሳት ወይም ውሀ አየር ባዶ ቦታ በብዛት ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህም ገና ለገና ሌሎች ፕላኔቶች የእኛን የመሰለ ክስተት የላቸውምና ፍጥረታት ሊኖሩ አይችሉም ብለን ማሰብ አንችልም፡፡ የቬዲክ ስነፅሁፎች እንደሚያስተምሩን በቁጥር ሊተመኑ የማይችሉ ፕላኔቶች እንደሚገኙ እና በእያንዳንዳቸውም ፕላኔቶች በተለያዩ ቁሳዊ ገላዎች ተሸፍነው የሚኖሩ ፍጥረታት እንደሚኖሩ ተገልጾልን ይገኛል፡፡ አንዳንድ ቁሳዊ ቅንብር በማድረግ ወደ እነዚህ ቁሳዊ ፕላኔቶች ለመጓዝ እንችል ይሆናል፡፡
ቢሆንም ግን ዓብዩ የመላእክት ጌታ ወደሚገኝባቸው መንፈሳዊ ፕላኔቶች ለመግባት እራሳችንን በመንፈሳዊ ንቃት ማዳበር ያስፈልገናል፡፡

ያንቲ ዴቫ ቭርታ ዴቫን
ፒትርን ያንቲ ፒትር ቭርታሀ
ብሁታኒ ያንቲ ብሁቴጅያ
ያንቲ ማድ ያጂኖ ፒ ማም

“ለትእይንተ ዓለሙ አስተዳዳሪ መላእክት የሚሰግዱ ሁሉ ወደ እነዚሁ መላእክት ወደሚገኙበት ይወሰዳሉ፡፡ ለአለፉት አባቶቻቸው የሚሰግዱ ሁሉ በሞት ግዜ ወደ እነዚሁ አባቶች ወደሚገኙበት እንደገና ይወለዳሉ፡፡ እኔን የሚያመልኩ ደግሞ ከእኔ ጋር ለመኖር ይበቃሉ፡፡” (ብጊ፡ 9.25)

ወደ ከፍተኛ ፕላኔቶች ለመሄድ የሚፈልጉ ሁሉ ጉዞዋቸውን ወደ እነዚሁ ፕላኔቶች ማድረግ ይችላሉ፡፡ ጐሎካ ቭርንዳቫን ተብሎ ወደሚታወቀው የሽሪ ክርሽና ፕላኔት ለመሄድ የሚፈልጉ ሁሉ የክርሽና ንቃታቸውን በማዳበር ወደ እዚህ ፕላኔት ለመሄድ ይችላሉ፡፡ ወደ ህንድ አገር ለመሄድ ስንፈልግ ይህ አገር ምን እንደሚመስል ብዙ መረጃዎችን ስንሰበስብ እንገኛለን፡፡ ስለአገሩም ለመረዳት የምንችለው በመጀመሪያ በምንሰበስበው መረጃ ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ወደ ዓብዩ አምላክ መንፈሳዊ ፕላኔት መረጃውን ለማግኘት ከፈለግን መስማት እና ማዳመጥ ይገባናል፡፡ በድንገት ተዘጋጅቶ እና ተነስቶ መሄድ አይቻልም፡፡ በቬዲክ ስነፅሁፎች ውስጥ ብዙ መረጃዎች ልናገኝ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ “ብራህማ ሰሚታ” እንዲህ የሚል ገለፃ ይሰጠናል፡፡

ቺንታመኒ ፕራካራ ሳድማሱ ካልፓ ቭርክሻ
ላክሻ ቭርቴሹ ሱራቢ አብሂፓላያንታም
ላክሽሚ ሳሃስራ ሻታ ሳምብህራማ ሴቭያማናም
ጐቪንዳም አዲ ፑሩሻም ታም አሀም ብሀጃሚ
(ብሰ፡ 5.29)

“እኔ የምሰግድለት ጎቪንዳ ከሁሉ ቀድሞ የነበረ፣ የመጀመሪያው የዘር ሁሉ መነሻ፣ በላሞች እረኝነት የተሰማራ፣ የመንፈሳዊ ዕንቁ በሞላበት መኖርያ ሆኖ የሁሉን ፍላጎት የሚያሟላ፣ ጥሩ ፍላጎትን በሚያሟሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ዛፎች የተከበበ፣ ሁልጊዜ በመቶ እና በሺህ በሚቆጠሩ ላክሽሚ ወይም ጐፒዎች ተከቦ በታላቅ ክብር እና ፍቅር የሚሰገድለት ነው፡፡”

እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ገለፃዎችም በተለይ በብራህማ ሰሚታ ውስጥ ተሰጥተው ይገኛሉ፡፡

ይህንንም ፍፁም የሆነ እውነት ለመረዳት የሚጥሩ ሁሉ እንደመረዳት ዓላማቸው በተለያየ ወገን ተከፋፍለው ይገኛሉ፡፡ ወደ ብራህማን የዓብዩ ጌታ ጮራ የሚያተኩሩት በጌታ ሰብአዊ ባህርይ የማያምኑ ብራህማቫዲስ ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ብዙዎች ይህንን ፍፁም የሆነ እውነት ለመረዳት የሚጥሩ ሁሉ በመጀመሪያ ጊዜ ብራህማጆይቲን (የጌታ የብርሀን ጮራ) ለመረዳት ይበቃሉ፡፡ “ፓራም አትማ” ተብሎ የሚታወቀውን በልባችን ውስጥ ወደሚገኘው የዓብዩ የመላእክት ጌታ ትኩረት የሚያደርጉ ደግሞ “ፓራማትማቫዲስ” ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ዓብዩ የመላእክት ጌታ በከፊል ወገኑ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ትኩረት በሞላበት ፀሎትም በልባችን የሚገኘውን የጌታን አካል ለመረዳት እንችላለን፡፡ በሁሉም ፍጥረታት ልብ ብቻም ሳይሆን በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ በሚገኝ በእያንዳንዱ አቶም ውስጥ ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ይህም የፓራም አትማ እውቀት ሁለተኛው የእውቀት ደረጃ ነው፡፡ ሶስተኛው እና የመጨረሻው ደረጃ ደግሞ “ብሀገቫን” ተብሎ የሚታወቀው ዓብዩ የመላእክት ጌታን እንደ ዓብዩ ሰው የማወቁ ደረጃ ነው፡፡ እነዚህም ሶስት ዓይነት የእውቀት ደረጃዎች ስለሚገኙ በአንድ ትውልድ ብቻ ዓብዩ የመላእክት ጌታን ለማግኘት አዳጋች ሆኖ ይገኛል፡፡ ባሁናም ጃንማናም አንቴ (ብጊ፡ 7.19) አንድ ሰው ዕድሉ ሆኖ በረከት የሞላበት ከሆነ ይህንን የከፍተኛ ደረጃ እውቀት በሴኮንድ ውስጥ ሊያገኘው ይችላል፡፡ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ዓብዩ አምላክን በንፁህ አንደበት ለመረዳት ብዙ ዓመታት ወይም ብዙ ትውልድ ሊጠይቅ ይችላል፡፡

አሀም ሳርቫስያ ፕራብሀቮ
ማታሀ ሳርቫ ፕራቫርታቴ
ኢቲ ማትቫ ብሀጃንቴ ማም
ቡድሀ ብሀቫ ሳማንቪታሀ

“እኔ የመላ ቁሳዊው ዓለም እና የመንፈሳዊው ዓለም መነሻ ነኝ፡፡ ሁሉም ነገር የሚመነጨው ከእኔ ነው፡፡ ይህንንም በትክክል የተረዳው አዋቂ ሰው ለእኔ ሙሉ ልቦናውን ሰጥቶ እኔን በፍቅር ሲያገለግለኝ እና ሲሰግድልኝ ይገኛል፡፡” (ብጊ፡ 10.8)

የቬዳንታ ሱትራም ስነፅሁፍ እንደሚገልፀው ፍፁም እውነት የምንለው የሁሉም ፍጥረታት መነሻ የሆነውን ነው፡፡ ሽሪ ክርሽናም የሁሉም ነገር መነሻ መሆኑን በእምነት የተቀበልን እና በዚሁም አንፃር የምንሰግድለት ከሆነ የቁሳዊ ዓለም ወጥመዳችን በሰኮንድ ውስጥ ሊፈታ ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው በዚህ ለማመን የሚያዳግተው እና እንደዚህ የሚል ከሆነ “ኦ ዓብዩ አምላክ ማን እንደሆነ ማየት እፈልጋለሁ” ውጤቱ የግድ ደረጃ በደረጃ የሚያስኬደው ይሆናል፡፡በመጀመሪያ ሰብአዊ ያልሆነውን የብራህማን ጮራ መረዳት ያስፈልገው ይሆናል፡፡ ከዚያም ፓራማትማ የተባለውን በልብ ውስጥ የሚገኘውን የዓብዩ አምላክን አካል ይረዳ ይሆናል፡፡ ወደ መጨረሻውም ደረጃ ሲደርስ “ኦ ዓብዩ የመላእክት ሁሉ ጌታ ይህ ነው፡፡” ብሎ የሚረዳበት ጊዜ ይደርሳል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ዓብዩ ጌታን የማወቅ ስርዓት በጣም ብዙ ጊዜ ሊፈጅ የሚችል ነው፡፡ በእንደዚህም ዓይነት ስርዓት ለብዙ ዓመታት ምርምር የሚያደርግ በመጨረሻው ፍፁም የሆነው እውነት “ቫሱዴቫ ሳርቫም ኢቲ” (ብጊ፡ 7.19) ዓብዩ ጌታ የሁሉ መድረሻ መሆኑን ይረዳል፡፡ ቫሱዴቫ ማለት በሁሉም ቦታ ማለት ነው፡፡ ቫሱዴቫ የሽሪ ክርሽና ስም ነው፡፡ ቫሱዴቫ ማለት “በሁሉም ቦታ የሚኖር” ማለት ነው፡፡ ቫሱዴቫ የሁሉም ነገር መነሻ መሆኑን የተረዳ ሁሉ ሙሉ ልቦናውን ለትሁት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ማም ፕራፓድያቴ ማለትም ይማረካል ማለት ነው፡፡ ይህም ዓይነት የመማረክ ስረዓት ከፍተኛው መድረሻችን ነው፡፡ ወደ እዚህም ደረጃ አንድ ሰው ወዲያውኑ ሊደርስ ይችላል ወይም ከብዙ ትውልድ እና ምርምር በኋላ ለመድረስ ይችል ይሆናል፡፡ በሁለቱም መንገድ ግን በመጨረሻ ሙሉ ልቦናን መስጠት እና ለዓብዩ ጌታ መማረክ ያስፈልገናል፡፡ “ዓብዩ የመንግስተ ሰማያት ጌታ ከሁሉም በላይ ሲሆን እኛም የእርሱ አገልጋዮች ነን፡፡” በማለት መረዳት ይኖርብናል፡፡

ይህንንም በመረዳት አዋቂ የሆነው ሰው ብዙ ትውልድ ከመጠበቅ ይልቅ ለሽሪ ክርሽና ወዲያውኑ ልቦናውን ይሰጣል፡፡ ሽሪ ክርሽና በምድር ላይ ለወደቁት ውስን ነፍሳት የሰጠው መንፈሳዊ መረጃ በርህሩህነቱ መሆኑን አዋቂው ሰው የተረዳ ነው፡፡ እኛ ሁላችን ውስን ነፍሳት እና በዚህ ቁሳዊ ዓለም ላይ በሶስት ዓይነት መከራዎች ስንሰቃይ የምንገኝ ነን፡፡ ዓብዩ ፈጣሪ አምላካችንም እነዚህን ዓይነት መከራዎች አምልጠን የምንሸሽበትን መንገድ እና ሙሉ ልቦናችንን በመስጠት እንዴት ነፃ ልንወጣ እንደምንችል አሳይቶናል፡፡

አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ “ዓብዩ የመላእክት ጌታ ግብታዊ መድረሻችን ከሆነ እና ሙሉ ልቦናችንንም ለእርሱ መስጠት የሚገባን ከሆነ ለምን በዓለም ላይ ብዙ የተለያየ የሀይማኖት ስርዓቶች ይገኛሉ?” ይህም ጥያቄ በሚቀጥለው ጥቅስ መልስ ተሰጥቶታል፡፡

ካሜይስ ቴይስ ቴይር ህርታ ግያና
ፕራፓድያንቴ ንያ ዴቫታሀ
ታም ታም ኒያማም አስትሀያ
ፕራክርትያ ኒያታህ ስቫያ

“በዓለማዊ ምኞት አዕምሮ ዋቸው የተመሰጡ ሁሉ መላእክቶችን በማምለክ እና የማምለኪያ ህግጋቶቻቸውን በመከተል እንደ መላእክቶቹ ፍላጎት ሲያመልኳቸው ይገኛሉ፡፡” (ብጊ፡ 7.20)

በዚህ ዓለም ላይ የተለያዩ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ እያንዳንዳቸውም በተለያየ የቁሳዊ ዓለም ባህርይ የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይም እንደምናየው ብዙ ሰዎች ከዚህ ቁሳዊ ዓለም ነፃ ለመውጣት ጥረት ሲያደርጉ አይገኙም፡፡ መንፈሳዊ ፈለግ የሚከተሉ ከሆነም የመንፈሳዊ ሀይል ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ይገኛሉ፡፡ በህንድ አገር ውስጥ ሰዎች ወደ ባህታውያን በመሄድ እንዲህ ብሎ መጠየቃቸው የተለመደ ነው፡፡ “ስዋሚጂ መድሀኒት ሊሰጡኝ ይችላሉን? እንዲህ ከመሰለ በሽታ ለመፈወስ እሻለሁ፡፡” ገና ለገና የዶክተሮች ወጪ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል በማለት ወደ ባህታውያን ብሄድ ተአምር ሊፈጥሩልኝ ይችላሉ ብለው ያስባሉ፡፡ በህንድ አገር ውስጥ በየሰው ቤት እየሄዱ የሚሰብኩ አስመሳይ ባህታውያንም ይገኛሉ፡፡ አንድ ግራም ወርቅ ብትሰጡኝ ተአምር በማድረግ ወደ መቶ ግራም ወርቅ እቀይርላችኋለሁ ብለው ይሰብካሉ፡፡ ሰዎቹም እንዲህ በማለት ያስባሉ፡፡ “አምስት ግራም ወርቅ አለኝ፡፡ ሁሉንም ብሰጠው አምስት መቶ ግራም ሊሆንልኝ ይችላል” ብለው ያስባሉ፡፡ እንዲህም እያሉ እነዚህ አስመሳይ ባህታውያን ሁሉን ወርቅ ከሰፈሩ ሰብሰበው ይጠፋሉ። ይህ ነው በሽታችን፡፡ ወደ ባህታውያን፣ ወደ ቤተመቅደስ ወይም ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ አንደበታችን በዓለማዊ እና ቁሳዊ ነገሮች ጉጉት የተሞላ ነው፡፡ ቁሳዊ ወይም ዓለማዊ ጥቅም ለማግኘትም ወደ መንፈሳዊ ሕይወት በመሰማራት እና ዮጋን የመሰለ ስርአት መጠለያ በማድረግ ገላችንን እና ጤንነታችንን ለማሻሻል ጥረት ስናደርግ እንገኛለን፡፡ ነገር ግን ጤንነታችንን ለማሻሻል ለምን ወደ ዮጋ ስርዓት መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ምግባችንን በመቆጣጠር እና በየጊዜው ስፖርታዊ ልምምድ በማድረግ ጤንነታችንን ለመንከባከብ እንችላለን፡፡ ለምን ወደ ዮጋ ስርዓት መሄድ ያስፈልገናል? ይህም ፍላጎት የሚመነጨው በብሀገቨድ ጊታ እንደተጠቀሰው “ካሚስ ቴይስ ቴይር ህርታ ግያና” (ብጊ፡ 7 20)እራሳችንን ወይም ገላችንን በጥንካሬ ብቁ ለማድረግ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ አምላክን የትእዛዛችን ፈፃሚ እንዲሆን በማድረግ የዓለማዊ ምኞታችንን ለማርካት እንጥራለን፡፡

ሰዎች በዓለማዊ ፍላጎቶችም ተመስጠው የተለያዩ መላእክቶችን ሲያመልኩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ከዓለማዊ ኑሮ እንዴት አድርገው ፈልቅቀው እንደሚወጡ ምንም እውቀቱ የላቸውም፡፡ ይህንንም ዓለም እንዴት ለግል ሙሉ ጥቅማቸው እንደሚያውሉት ሲጥሩ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ በቬዲክ ስነጽሁፎች ውስጥ ይህንን የመሰለውን ፍላጎት ለሟሟላት ብዙ ዓይነት የተለያዩ መመሪያዎች ተሰጥተው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ከበሽታ ለመዳን ከፈለገ የፀሀይን ጌታ ቪቫሽቫንን ለማምለክ ይችላል፡፡ አንዲት ልጃገረድ ጥሩ ባል ለማግኘት ከፈለገች ጌታ ሺቫሽቫንን ለማምለክ ትችላለች፡፡ አንድ ሴት በጣም ውበት ያላት ሆና እንድትፈጠርም ከፈለገች የተመደበውን አምላክ ማምለክ ትችላለች፡፡ አንድ ሰው በእውቀቱ የላቀ መሆን ከፈለገም ሳራስቫቲ የተባለችውን መልአክ ማምለክ ይችላል፡፡ ይህንንም በመመልከት ብዙሀን ምእራባውያን ሂንዱዎች ፖሊይየስቲክ ወይም በብዙ አምላክ የሚያመልኩ ናቸው ብለው ድምዳሜ ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ዓይነቱ አምልኮት ለዓብዩ የመላእክት ሁሉ ጌታ ለአንዱ አብይ አምላክ አይደለም፡፡ አምልኮቱም በዓብዩ አምላክ ስር ለሚተዳደሩት ለተለያዩ መላእክቶች ነው፡፡ እነዚህም መላእክቶች ዓብዩ የመላእክት ጌታ ናቸው ብለን ማሰብ አይገባንም፡፡ ዓብዩ የመላእክት ጌታ እና ፈጣሪ አምላክ አንድ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ እንደ እኛ አገልጋይ ነፍሳት የሆኑ ብዙ መላእክቶች እንዳሉ መረዳት ይገባናል፡፡ ልዩነታችን ግን መላእክቶች እኛ ለመገመት የማንችለው ዓይነት ሀይል አላቸው፡፡ በዚህም ምድር ላይ መላ ህዝብን የሚመራ ንጉስ ወይም ፕሬዝደንት ሊኖር ይችላል፡፡ እነዚህም እንደእኛ ተራ ሰዎች ናቸው፡፡ ልዩነታቸው ግን ከእኛ የተለየ ሀይል ስለሚኖራቸው ነው፡፡ ከእነዚህም ሰዎች እርዳታ ለማግኘት እና ያላቸውን ሀይል ለጥቅማችን ለማዋል በተለያየ መንገድ ስናመልካቸው እንገኛለን፡፡ ነገር ግን ብሀገቨድ ጊታ ይህንን ዓይነት አምልኮት ወይም የመላእክትን አምልኮት ሲያወግዘው ይገኛል፡፡ ይህም የብሀገቨድ ጊታ ጥቅስ እንደሚገልፀው ይህንን የመሰለው መላእክትን የማምለክ ምኞት ከዓለማዊ ፍላጎቶች ጋራ የተያያዘ መሆኑን በግልፅ ያስረዳናል፡፡

የዚህ ቁሳዊ ህይወት መሰረቱ የጋለ ዓለማዊ ፍላጎት ነው፡፡ ይህንን ዓለም በመጠቀም ልንደሰትበት እንሻለን፡፡ ይህንንም ዓለም የምንወደው ስሜታችንን ሁሉ ሊያረኩ የሚችሉ ነገሮችን ስለሚያቀርብልን ነው፡፡ ይህም እራሳችንን ለማስደሰት ያለን የጋለ ፍላጎት ዓብዩ ጌታን ለማስደሰት የነበረን የጋለ ፍላጎት በምድር ላይ ገብቶ የተገላቢጦሽ ሆኖ በመምጣቱ ነው፡፡ በተፈጥሮ ነፍስ ዓብዩ አምላክን የምትወድ ናት፡፡ በዚህ ምድር ላይ ግን ይህ ያለን ፍቅር ስለተሸፈነ ዓብዩ አምላክን ዘንግተን ፍቅራችንን ወደ ዓለማዊ ቁሳቁስ አሸጋግረን እንገኛለን፡፡ የፍቅር አዝማሚያ ወይንም ባህሪ ከነፍስ ተነጥሎ የሚገኝ አይደለም፡፡ ስለዚህም ወይ ዓለማዊ ነገሮችን እንወዳለን ወይንም ደግሞ ዓብዩ የመላእክት ጌታን እንወዳለን፡፡ ከዚህም ዓይነት የፍቅር አዝማሚያ ልንወጣ አንችልም፡፡ በመሆኑም ብዙውን ጊዜ እንደምናየው አንድ ሰው ቤተሰብ ወይም ልጆች ከሌሉት ፍቅሩን ወደ ድመቶች እና ውሾች ሲያሸጋግረው ይገኛል፡፡ ለምን? ምክንያቱም ፍቅራችንን ለአንድ ነገር ለመግለፅ አዝማሚያ ስለአለን ነው፡፡ ይህንንም የዓብዩ አምላክ ፍቅር እና ፍፁም እውነት የተረዳን ካልሆንን ፍቅራችን እና እምነታችንን ወደ ድመቶች እና ውሾች ስናዘዋውረው እንታያለን፡፡ ፍቅር ሁልጊዜ ከነፍስ የማይለይ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የተፈጥሮ የዓብዩ አምላክ ፍቅር የተገላቢጦሽ ሆኖ ወደ ዓለማዊ የጋለ ፍላጎት ተሸጋግሮ እናየዋለን፡፡ ይህም የጋለ ፍላጎት ሳይሳካ ሲቀር በንዴት ላይ ስንወድቅ እንገኛለን፡፡ ንዴት ላይ ስንወድቅ ደግሞ የምናደርገውን ባለማወቅ ጥፋት ላይ ለመውደቅ እንበቃለን፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ስንደረስ ደግሞ ከነበረን ክብር እንወድቃለን ማለት ነው። በዚህ ዓለም ላይ የሚገኘው ስርዓት ይህንን መስሎ ይታያል፡፡ ያለንም ሀላፊነት ይህንን ስርዓት በመቀየር ዓለማዊ የጋለ ፍላጎትን ወደ ዓብዩ አምላክ ፍቅር መቀየር ነው፡፡ ዓብዩ የመላእክት ጌታን የምናፈቅር ከሆነ በዚህ ምድር የሚገኙትን ፍጥረታት ሁሉ ስንወድ እንገኛለን፡፡ ነገር ግን ዓብዩ የመላእክት ጌታን የማንወድ ከሆነ በዚህ ምድር ላይ ያሉትን ፍጥረታትን ሁሉ ለመውደድ ያዳግተናል፡፡ በዚህ ምድር ላይ ፍቅር አለን ብለን እራሳችንን እናታልል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ የጋለ ፍላጎታችንን ለሟሟላት የታቀደ ፍቅር እንጂ ንፁህ ፍቅር ሆኖ አይገኝም፡፡ ይህንንም የውሻን የመሰለ የጋለ ፍላጎት ያላቸው ሁሉ የሚያኮራውን የስሜት ባህርይ እንደአጡ ሆነው ይታያሉ፡፡ “ካሚስ ቴይስ ቴይር ህርታ ግያና” (ብጊ፡ 7.20)

በቬዲክ ስነፅሁፎች ውስጥ መላእክቶችን ለማምለክ የሚገባው ስርዓት እና ህግጋት ተገልፀው እናገኛቸዋለን፡፡ አንድ ሰው እነዚህ ስርዓቶች ለምን በቬዲክ ስነፅሁፎች ውስጥ እንደተገለፁ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ይህም አስፈላጊነት ስላለው ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ በዓለማዊ ፍቅርና የጋለ ፍላጎት የተመሰጡ ሰዎች ይህንን የዓለማዊ ፍላጎት ለሟሟላት ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህንም ፍላጎቶች የሚያሟሉት የዓብዩ አምላክ ተወካይ መላእክቶች በመቅረብ ነው፡፡ ይህም ስርዓት የተደነገገው እነዚህ ዓለማዊ ሰዎች መላእክቶችን በማምለክ ቀስ በቀስ የዓብዩ አምላክ የክርሽናን ንቃት ለማነቃቃት እንዲችሉ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ከሀዲ እና ከመንፈሳዊ ባለስልጣናት ትእዛዝ ውጪ በመውጣት አመፀኛ ከሆነ እንዴት ዓይነት ተስፋ ሊኖረው ይችላል? ስለዚህ አንዳንድ ሰው ለመንፈሳዊ ባለስልጣናት ያለው ታዛዥነት ሊከሰት የሚችለው እነዚህን መላእክቶች በማምለክ ሲጀምር ሊሆን ይችላል፡፡

ነገር ግን የዓብዩ የመላእክት ጌታን ታላቅነት ተረድተን በቀጥታ ለማምለክ የምንችል ከሆነ መላእክትን ለማምለክ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ዓብዩ የመላእክት ጌታን በቀጥታ የሚያመልኩ ለመላእክት ሁሉ ሙሉ አክብሮት ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህም ንፁህ አገልጋዮች ዓብዩ የመላእክት ጌታ ከመላእክት ሁሉ በላይ ሆኖ እንደሚገኝ ስለሚያውቁ እና እርሱን በማወደስ እና በማገልገል ላይ ስለሚገኙም ለመላእክት የተለየ አምልኮት ማድረግ አያስፈልጋቸውም፡፡ ቢሆንም ግን ለመላእክት ሁሉ ሙሉ አክብሮት ሲሰጧቸው ይገኛሉ፡፡ የዓብዩ የመላእክት ጌታ አገልጋይ ለመላእክት ይቅርና ለጉንዳን እንኳን አክብሮት ሲሰጥ የሚገኝ ነው፡፡ የዓብዩ ጌታ አገልጋይ ሁሉም ፍጥረታት የተለያየ ደረጃ ይኑራቸው እንጂ የዓብዩ ጌታ ክፋይ እና ቅንጣፊ መሆናቸውን የተረዱ ናቸው፡፡

ከዓብዩ ጌታ ጋር ባላቸውም ግኑኝነት ሁሉም ነፍሳት ክብር ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ስለዚህም የዓብዩ ጌታ አገልጋይ ሌሎችን ሁሉ “ፕራብሁ” ወይም “ውድ ጌታዬ ሆይ” ብሎ ይጠራቸዋል፡፡ ይህም ዓይነት ትህትና የዓብዩ ጌታ አገልጋይ የመጀመሪያ መመረቂያው ነው፡፡ የዓብዩ ጌታ አገልጋዮች ሩህሩህ እና ታዛዦች ናቸው፡፡ መልካም የሆነ ባህሪይ ያላቸው ናቸው፡፡ ለመደምደምም አንድ ሰው የዓብዩ የመላእክት ጌታ ትሁት አገልጋይ ከሆነ መልካም ባህሪያቶች ሁሉ ይከሰቱበታል፡፡ በተፈጥሮ ሁሉም ነፍሳት ፍፁም የሆነ ጥሩ ባህሪ ያላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ገብተው በጋለ የዓለማዊ ፍላጎቶች እና በጭካኔ በተሞላ መንፈስ ተበክለው ይገኛሉ፡፡ የወርቅ ቅንጣፊ አካል ወርቅ ነው፡፡ ፍፁም ሙሉ ከሆነው ከዓብዩ የመላእክት ጌታ የተቀነጠፈ ሁሉም ሙሉ ሆኖ ይገኛል፡፡

ኦም ፑርናም አዳሀ ፑርናም ኢዳም
ፑርናት ፑርናም ኡዳችያቴ
ፑርናስያ ፑርናም አዳያ
ፑርናም ኤቫ ቫሺሽያቴ

“ዓብዩ የመላእክት ጌታ ፍፁም እንከን የሌለው እና በሁሉም ረገድ የተሟላ ሆኖ ይገኛል፡፡ ፍፁም የተሟላ እና ፍፁም እንከን የሌለው በመሆኑም በዚህ ቁሳዊ ዓለም ላይ በእርሱ የተፈጠሩ ሁሉ ከእርሱ የሚመነጩ ፍጥረታት በመሆናቸው ፍፁም የተሟሉ፣ የተቀነባበሩ እና እንከን የለሽ ሆነው የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ፍፁም ሙሉ ከሆነው ከዓብዩ ጌታ የተፈጠሩ ሁሉ በሁሉም ረገድ የተሟሉ ሆነው ተፈጥረዋል። ዓብዩ ጌታ ፍፁም የተሟላ አካል የያዘ በመሆኑም ምንም እንኳን ብዙ የተሟሉ አካላት ከእርሱ ቢፈጠሩም እርሱ ለዘለዓለም ሳይጎድል ፍፁም የተሟላ ሆኖ ይኖራል፡፡” (ሽሪ ኡፓኒሻድ መቅድመ ጥቅስ)

እነዚህ ፍፁም እንከን የሌላቸውም ነፍሳት በዚህ ቁሳዊ ዓለም ላይ ወድቀው በመበከል ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ይህንን የክርሽና መንፈሳዊ ንቃትን በመቀስቀስ እንደገና ፍፁም እንከን ወደሌለው ደረጃ ለመድረስ ይችላሉ። ይህንንም ስርዓት በመከተል ፍፁም የሆነ ደስታን ልናገኝ እንችላለን፡፡ ይህንንም ዓለም በሞት ስንለይ ዘለዓለማዊ ደስታ እና እውቀት ወደሞላበት የዓብዩ ጌታ ቤተመንግስት ለመግባት ዝግጁ እንሆናለን፡፡

« Previous