ማንትራ አስር
አንያድ ኤቫሁር ቪድያያ
ንያድ አሁር አቪድያያ
ኢቲ ሱስሩማ ድሂራናም
ዬ ናስ ታድ ቪቻቻክሺሬ
አንያት — የተለየ፣ ኤቫ — በእርግጥ፣ አሁህ — ተብሏል፣ ቪድያያ— ዕውቀት በተሞላበት ባህል፣ አንያት — የተለየ፣ አሁህ — ተብሏል፣ አቪድያያ — ድንቁርና በተሞላበት ባህል፣ ኢቲ — ታድያ፣ ሱስሩማ — እንደሰማሁት፣ ድሂራናም — ከማይረበሹት ሰዎች፣ ዬ — እነማን፣ ናህ — ለእኛ፣ ታት — ያንኛው፣ ቪቻቻክሺሬ — እንደተገለጸው
ጠቢብ የሆኑት ምሁራን እንደገለጹትም፣ ዕውቀት ከተሞላበት ባህል የላቀ ውጤት ሲገኝ፣ ድንቁርና ከተሞላበት ባህል ደግሞ የተለየ ኅብረተስቡን የሚያቆለቁል ውጤት ይገኛል፡፡
በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ በአሥራ ሦስተኛው ምዕራፍ (ብጊ 13-8-12) እንደተገለጸው የሰው ልጅ ባህሉን እና ዕውቀቱን በሚከተለው መንገድ ማዳበር ያስፈልገዋል፡፡
(1) አንድ ሰው ለሌሎች ያለውን ክብር ከፍ በማድረግ፣ እርሱ ራሱ በአክብሮት እንዲታይ ማድረግ ይገባዋል፡፡
(2) አንድ ሰው የራሱን ስም እና ዝና ከፍ ለማድረግ፣ በመንፈሳዊ ሥርዓት የዳበረ ሰው እንደሆነ አድርጎ ማስመሰል አይገባውም፡፡
(3) አንድ ሰው በማናቸውም ድርጊቱም ሆነ በሐሳቡ ወይም በቃላቱ ለሌሎች የሥጋት እና የጭንቀት መነሻ መሆን አይገባውም፡፡
(4) ምንም እንኳን አንድ ሰው በሌሎች የሚተነኮል ቢሆንም፣ ከፍተኛ ትዕግሥት የማድረግ አቅም እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡
(5) አንድ ሰው ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት እውነትን በተመረኮዘ መንገድ እንጂ፣ በማጭበርበር፣ በማታለል ወይም አስመሳይ በሆነ መንገድ መቅረብ አይገባውም፡፡
(6) አንድ ሰው ዕውቅና ያለውን እና ብቁ የመንፈሳዊ ንቃት ያለውን መንፈሳዊ አባት መቅረብ ይገባዋል፡፡ ለዚህም መንፈሳዊ አባት ዕምነቱን በመስጠት አገልግሎትን ማቅረብ እና ተገቢ የሆኑ ጥያቄዎችንም መጠየቅ ይገባዋል፡፡
(7) አንድ ሰው ወደ መንፈሳዊ ራስን የማወቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ፣ የቬዲክ መጻሕፍትን ማንበብ እና የተደነገጉትንም የሚያግዱ መንፈሳዊ መመሪያዎችን መከተል ይገባዋል፡፡
(8) አንድ ሰው የተገለጹትን የቬዲክ ሥነጽሑፍ እና ትእዛዛትን በጥሞና በማስተዋል፣ በጽኑ ሕሊናው እንዲከታተል ያስፈልጋል፡፡
(9) እነዚህን ራስን የማወቅ መንፈሳዊ ጥናቶችንም በመከታተል፣ መራቅ ከሚገቡን ዓለማዊ ተግባሮች ሁሉ ፈጽሞ መወገድ ይገባናል፡፡
(10) አንድ ሰው ገላውን በበቂ ሁኔታ ለመንከባከብ ከሚያስፈለገው በላይ ሀብት በመሰብሰብ ጊዜውን ማባከን አይገባውም፡፡
(11) አንድ ሰው ራሱን (ነፍሱን) ሥጋዊ ገላው እንደሆነ አድርጎ በመቁጠር፣ በስሕተት ማሰብ እና መኖር አይገባውም፡፡
እንዲሁም ከሥጋዊ ገላው ጋር የተዛመዱትንም ሁሉ የራሱ በማድረግ ማሰብ አይገባውም፡፡
(12) አንድ ሰው ሥጋዊ ገላውን እስከያዘ ድረስ፣ ተደጋግመው ከሚመጡት ከመወለድ፣ ከማርጀት፣ ከመታመም እና ከመሞት መከራዎች መራቅ እንደማይችል መረዳት እና ማስታወስ ይገባዋል፡፡ የዚህ መከራ የተሞላበት የሥጋዊ ገላ ስቃዮችን በቁሳዊ መንገድ ለመወጣት መጣር ዘለቄታዊ ፋይዳ የለውም፡፡ ትክክለኛው መንገድ ግን መንፈሳዊ ንቃትን በማዳበር፣ ወደ መንፈሳዊው ዓለም መመለስ እና ከእነዚህ መከራዎች ለመውጣት፣ ዘለዓለማዊ መፍትሔን ማግኘት ነው፡፡
(13) አንድ ሰው በሕይወቱ መንፈሳዊ ንቃቱን ለማዳበር ከሚያስችለው ነገር በላይ፣ ቁሳዊ ሀብቶችን ለማግኝት ጉጉት እንዲኖረው አያስፈልግም፡፡
(14) በቬዲክ ሥነጽሑፎችም ውስጥ ከተጠቀሰው በላይ፣ አንድ ሰው ለሚስቱ፣ ለልጆቹ ወይም ለመኖሪያ ቤቱ ያለውን ኅይል ሁሉ፣ ከሚገባው በላይ በመሰዋት፣ መንፈሳዊ ንቃቱን የሚያደናቅፍ ደረጃ ላይ ከመድረስ መቆጠብ ያስፈልገዋል፡፡
(15) አንድ ሰው በሚፈለጉ እና በማይፈለጉ ዓለማዊ ቁሳዊ ነገሮች፣ ምኞት እና ጉጉት እንዲሁም እንቅስቃሴ ላይ በመሰማራት፣ ከአግባቡ በላይ ለመደሰት መጣር ወይም መጨነቅ አይገባውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የደስታ እና የጭንቀት ስሜቶች ሁሉ የሚመነጩት፣ ከዓለማዊ አንደበታችን እና ከሐሳባችን በመሆኑ ነው፡፡
(16) አንድ ሰው የዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ የሽሪ ክርሽና ትሑት አገልጋይ በመሆን፣ በጸና አንደበት ሊያገለግለው ይገባል፡፡
(17) አንድ ሰው መንፈሳዊ ንቃትን ለማዳበር የሚያስችል፣ ገለል እና ጭር ያለ ወይም ሰላም የሰፈነበት ቦታ ውስጥ ለመሆን ጉጉት ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ ለመንፈሳዊ ንቃት ምንም ጉጉት የሌላችው ሰዎች ከበዛበት አካባቢም መራቅ ያስፈልገዋል፡፡
(18) አንድ ሰው መንፈሳዊ ዕውቀት ዘላለማዊ መሆኑን እና ዓለማዊው ዕውቀት ግን ከሞት ጋር የሚያከትም የመሆኑን ልዩነት፣ ለኅብረተሰቡ በትክክል ለማስረዳት፣ በሳይንስ እና በፍልስፍና ዕውቀት ውስጥ መሰማራት ይገባዋል፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አሥራ ስምንት መመሪያዎች ትክክለኛ ዕውቀትን ለማዳበር እንድንችል የሚያበቁን ናቸው፡፡ ከእነዚህ መመሪያዎች ውጪ የሆኑት ድርጊቶች ሁሉ ወደ ድንቁርና ሊያመሩን የሚችሉ ናቸው፡፡ ታላቁ አቻርያ እና መምህር ሽሪላ ብሀክቲቪኖድ ታኩር እንደገለጹት፣ መላው የተለያዩ ዓይነት የቁሳዊ ዓለም ዕውቀቶች ሁሉ፣ ራስን የማወቅ ንቃት ላይ ለማይሳተፍ ሁሉ፣ በሐሰታዊው ራእይ እንዲጠመድ የሚያደርጉት ናቸው። እንዲህ ዓይነት ዓለማዊ ዕውቀትን ብቻ ማዳበር፣ ከእንስሳ ያልተሻለ ደመ-ነፍሳዊ ባሕሪ እንዲኖረን ያደርጉናል። በዚህም በሽሪ ኡፓኒሻድ ውስጥ የቀረበልን መመሪያ ይኸው ነው፡፡ በቁሳዊው ዓለም ዕውቀት ብቻ መራመድ፣ የሰውን ልጅ እንስሳን ወደመሰለ ነገረ-ባህሪ እንዲቀየር ያደርገዋል፡፡ አንዳንድ ዓለማዊ የሆኑ የፖሎቲካ ሰዎች፣ እራሳቸውን ልክ እንደ መንፈሳዊ ሰው በማስመሰል፣ የአሁኑን ጊዜ ዓለማዊ ሥርዓት ሰይጣናዊ ነው በማለት ድምጻቸውን ያሰማሉ።በማለትም ግን በብሀገቨድ ጊታ እንደተገለጸው ትክክለኛ እና ፍጹም የሆነውን ዕውቀት ለማስተማር ደንታ የማይሰጣቸው ሆነው ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ይህንን ሰይጣናዊ ብለው የሚሰብኩበትን ሥልጣኔ ለመለወጥ አንዳችም ኅይል የላቸውም፡፡
በአሁኑ የሥልጣኔ ዘመን፣ አንዳንድ ወጣት ራሱን እንደቻለ ሰው በማሰብ፣ ለሌሎች ዕድሜያቸው ለገፋ ሰዎች ምንም ዓይነት ክብር ሲሰጥ አይታይም፡፡ በዩኒቨርስቲም ውስጥ ቢሆን ሥነ ምግባርን ያላካተተት ዕውቀት ስለሚሰጣቸው፣ አንዳንድ ከኮሌጅ የተመረቁ ልጆች ዕድሜያቸው የገፉውን የኅብረተሰብ አካሎች ሲያሸብሩ ይታያሉ፡፡ ስለዚህ ሽሪ ኡፓኒሻድ ከበድ ባለ መንገድ እንደሚያስጠነቅቀን፣ የድንቁርና ባህል ከትክክለኛው ዕውቀት ከተሞላበት ባህል የተለየ መሆኑን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የተቋቋሙት የዩኒቨርስቲ ተቋሞች ራስን ስለማወቅ ጥናት ምንም ዓይነት ዕውቀት ይዘው ሲቀርቡ አይታዩም። ስለዚህም የሚያቀርቡት ዕውቀት ሁሉ፣ በመንፈሳዊ ትምህርት ደጋን የተራቆቱ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የተመረቁት ሳይንቲስቶች፣ ሌሎች አገሮችን ለመደምሰስ የሚችል አጥፊ መሣሪያዎችን ለመሥራት በሥራ እና በምርምር ተጠምደው ይታያሉ። በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት ዩኒቨርስቲዎች ስለ ብራህማቻርያ ወይም የመንፈሳዊ ትምህርት መመሪያዎች፣ ምንም ዓይነት ትምህርት ሲሰጡ አይታዩም፡፡ ከመንፈሳዊ መጻሕፍት መመሪያዎችም ቢሆን፣ ምንም ዓይነት እምነት በመያዝ በማስተማር ላይ አይገኙም። መንፈሳዊ ትምህርቶችን ቢሰጡም እንኳ፣ እንዲያው ለስም እና ለዝና ነው እንጂ፣ መመሪያዎቹን በተግባር ለማዋል አይደለም፡፡
ስለዚህ በኅብረተሰብ እና በፖሎቲከኞች መሀከል ብቻ ሳይሆን፣ በሃይማኖታዊ ኅብረተሰብም መሀከል ቢሆን ብዙ የእርስ በርስ ጥላቻ ይታያል፡፡
ብሔራዊ ስሜቶች እና ዘረኝነትም፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሁሉ ተስፋፍተው ይገኛሉ፡፡ የዚህም ዋና መሠረታዊ ምክንያት፣ ድንቁርና የተሞላበት ዕውቀት ለሰፊው ሕዝብ በመቅረቡ ነው፡፡ ማንም ሰው ቢሆን፣ ይህቺን በሰፊው የትዕይንተ ዓለማት ውስጥ የምትገኘውን የተሟላች መሬት፣ ልክ እንደ ትንሽ የውሀ እና የአፈር ክምችት አድርጐ አያያትም፡፡ ምክንያቱም ዓብዩ ጌታ ምድርን ሲፈጥራት፣ በሁሉም ረገድ የተሟላች አድርጐ ነው፡፡ ፕላኔቶችን በህዋ ውስጥ ለዘመናት በትክክለኛ መንገድ እንዲንሳፈፉ ለማድረግ ዓብዩ ጌታ አመዛዝኖ ፈጥሯቸዋል። በእርግጥ ወሰን ከሌለው ከሰፊው የትዕይንተ ዓለም ጠፈር ጋር ሲነጻጻሩ እነዚህ የምናያቸው ቁሳዊ ፕላኔቶች፣ ልክ በአየር ውስጥ እንደሚታዩ የአቧራ ብናኞች ይቆጠራሉ፡፡ የጠፈር መንኮራኩሮችን የሚነዱት የሳይንስ ሰዎች ሁሉ፣ በሥራቸው ውጤት ከፍ ያለ ኩራት ይሰማቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን እነዚህን የተሟሉ እና ልክ እንደ ግዙፍ መንኮራኩሮች የሚቆጠሩት ፕላኔቶችን ሁሉ የሚያሽከረክረው ዓብዩ ጌታ መሆኑን ዘንግተዋል።
ከእነዚህም ከምናያቸው ፕላኔቶች ባሻገር፣ በቁጥር ሊተመኑ የማይችሉ ሌሎች የፕላኔት ሥርአቶች እና ፀሐዮችም ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳን እኛም በረቂቅነት የምንገኝ የዓብዩ ጌታ ቅንጣፊ አካል ሆነን ብንገኝም እንኳ እነዚህን በቁጥር ሊተመኑ የማይችሉ ፕላኔቶችን ለመረዳት እና ለመቆጣጠር ስንጥር እንገኛለን፡፡
በዚህም ምክንያት፣ በእነዚህ በቁሳዊ ዓለም ውስጥ በሚገኙ ፕላኔቶች ውስጥ በተደጋጋሚ ስንወለድ፣ በበሽታ እና በእርጅና ተሰቃይተን ስንሞት እንታያለን፡፡ በአሁኑ ዘመን የሰው ልጅ ዕድሜ እስከ አንድ መቶ ዓመት ቢደርስ ነው፡፡ እንዲያውም ግን ይህ ዕድሜ ቀስ በቀስ እስከ ሀያ ወይም ሰላሳ ዓመት ድረስ እየቀነሰ ሲመጣ እናየዋለን፡፡ ድንቁርና በተሞላበት ባህል የተመሰጡ ሰዎች፣ ይህንን ዓለም በብሔራዊ ግዛት ከፋፍለው እና ስሜታዊ ደስታቸውን በሚያረካ መንገድ አደረጃጅተው፣ ለዚህ ዘለቄታ ለሌለው ሕይወት ሲደክሙ ይታያሉ፡፡ ይህንንም ክልል ለመጠበቅ በጣም አስቸጋሪ የሆነውን ብሔራዊ ክልላቸውን በዘዴ አቅደው እና አስፍረው ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት፣ እያንዳንዱ ብሔራዊ ክልል ኅብረተሰብ ከሌላው ክልል ኅብረተሰብ ጋር ላለመጋጨት፣ ጭንቀት በተሞላበት መንገድ ሲኖሩ ይታያሉ፡፡ ከኅምሳ በመቶ በላይ የሚሆነው የያንዳንዱ አገር ኅይል እና ጥረት የሚውለው፣ ለመከላከያ ስለሚሆን ያላቸው ኅይል ባክኖ ይገኛል፡፡ ትክክለኛ የሆነውን መንፈሳዊ ዕውቀት ለማዳበር ግን ጥረት ሲያድረጉ አይታዩም፡፡ ዳሩ ግን ሰዎች በዓለማዊ ሕይወት እና በመንፈሳዊ ዕውቀት የዳበሩ መስሏቸው በትዕቢት ላይ ይገኛሉ፡፡
ስለዚህ ይህ የሽሪ ኡፓኒሻድ መጽሐፍ ከስሕተተኛ ዕውቀት እንድንርቅ ይመራናል፡፡ የብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መጽሐፍም፣ እንዴት ትክክለኛ የሆነውን ፍጹም ዕውቀት ለማግኘት እንደምንችል ይገልፅልናል፡፡ ይህ ማንትራ አስር እንደሚገልጸው ፍጹም ዕውቀት ሊገኝ የሚችለው፣ “ድሂራ” ከሆነ ሰው ነው፡፡ ድሂራ ማለት በቁሳዊ ዓለም ቅዠት ፈጽሞ ሊረበሽ የማይችል መንፈሳዊ ሰው ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው በመንፈሳዊ ንቃት የዳበረ ሰው ካልሆነ በስተቀር፣ በዓለማዊ ስሜቶች ሳይረበሽ መኖር አይችልም፡፡ በመንፈሳዊ ንቃት የዳበረ ሰው፣ ለዓለማዊ ነገሮች ጉጉት የለውም ወይም ቁሳዊ ነገር ሲጎልበት በቀላሉ ሊረበሽ የሚችል ሰው አይደለም፡፡ ድሂራ የሆነ መንፈሳዊ ሰው ቁሳዊ ገላችን እና ዓለማዊ ሐሳባችን የተፈጠሩት ከቁሳዊው ዓለም ጋር በነበረን የቀድሞ ትውልድ ግንኙነት እንደሆነ የተረዳ ሰው ነው፡፡ ሥጋዊ ገላው በተፈጥሮ የተገኘ እንደመሆኑም፣ የአፈጻጸም ሂደቱን ተቀብሎ በአግባቡ ለመንፈሳዊ ዓላማ ይጠቀምበታል፡፡
ሥጋዊ ገላችን እና ዓለማዊው ልቦናችን በአንድነት ሲሆኑ ለነፍሳችን እንቅፋት ሆነው ይገኛሉ፡፡ ዘለዓለማዊ ሕይወት በሚገኝበት የመንፈሳዊ ዓለም ውስጥ፣ ነፍስ የራስዋ የሆነ ንጹሕ የመንፈሳዊ አገልግሎት ሚና ዓላት፡፡ ከመንፈሳዊው ዓለም በተቃረነ መንገድ፣ ይህ የቁሳዊ ዓለም ዘለዓለማዊ ሕይወት የሌለው ሆኖ ይገኛል፡፡ ነፍስ በቁሳዊ ገላዎች ውስጥ ሠርጻ እስከኖረች ድረስ፣ ቁሳዊው ገላ ሕይወት ያለው መስሎ ይታያል፡፡ ሕይወት የሚመነጨው ግን ነፍስ በቁሳዊው ገላ ውስጥ በመገኘቷ ብቻ ነው፡፡ ይህቺም ነፍስ የዓብዩ ጌታ ወገን እና ቁራሽ አካል ናት፡፡ በእርሱም ምክንያት መላው የትዕይንተ ዓለም በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
ድሂራ ተብለው የሚታወቁት መንፈሳውያን፣ ይህንን ሁሉ ዕውቀት የቀሰሙት ከሌሎች ዐዋቂ መንፈሳዊ ባለሥልጣናት ሲሆን ይህንንም መንፈሳዊ ዕውቀት ሊረዱ የቻሉት፣ መንፈሳዊ መመሪያዎችን በጥሞና በመከተል ነው፡፡
እነዚህን መንፈሳዊ መመሪያዎች ለመከተል፣ አንድ ሰው ከመንፈሳዊ አባት ወይም መምህር ዲቁና በመውሰድ ትምህርቱን መቅሰም እና ማገልገል ይኖርበታል፡፡ በዚህም ግንኙነት መንፈሳዊ ዕውቀት እና የቬዲክ መመሪያዎች ከመምህሩ ወደ ዲያቆኑ ይተላለፋሉ፡፡ ይህንን የመሰለው ዕውቀት ከማንኛውም ዓለማዊ የትምህርት ተቋሞች የሚገኝ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ድሂራ ለመሆን የሚችለው፣ እውቅና ካለው መንፈሳዊ መምህር በጥሞና እና በትሕትና ሲያዳምጥ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ አርጁና፣ ከዓብዩ ጌታ ክርሽና ትምህርቱን በጥሞና በማዳመጥ ድሂራ ለመሆን በቅቷል፡፡ ስለዚህ ትክክለኛው ዲያቆን ወይም ተማሪ የአርጁናን ፈለግ መከተል ይገባዋል፡፡ መንፈሳዊ መምህሩም ዓብዩ ጌታን የሚወክል መሆን ይገባዋል፡፡ ቪድያ ወይም መንፈሳዊ ዕውቀትን የመቅሰም ሥርዓትም የሚገኘው “ድሂራ” ወይም በመንፈሱ የማይረበሸውን መንፈሳዊ ሰው በመቅረብ ነው፡፡
ድሂራ ያልሆነ ሰው ወይም በድሂራ መምህር ሥር ሆኖ ያልሠለጠነ ሰው፣ መንፈሳዊ መምህር ሊሆን አይችልም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚታዩት የፖሎቲካ መሪዎች፣ ልክ እንደ ድሂራ ሆነው ተመስለው ይታያሉ፡፡ ድሂራ ባለመሆናቸውም ግን ከእነርሱ ፍጹም የሆነ ዕውቀት ሊጠበቅ አይቻልም፡፡ በሀሳባቸው ሁሉ እንዴት ገቢያቸውን ለማጠናከር እንደሚችሉ በማተኮር ሲሯሯጡ የሚታዩ ናቸው፡፡ ታድያ እንደነዚህን የመሰሉ የኅብረተሰቡ አካሎች፣ እንዴት አድረገው የአገሪቱን ሕዝብ ራስን ወደ ማወቅ መንፈሳዊ ንቃት ሊመሯቸው ይችላሉ? ስለዚህ አንድ ሰው ፍጹም የሆነውን ራስን የማወቅ ጥናት ለመከታተል ከፈለገ፣ ድሂራ የሆነውን ሰው መቅረብ ይገባዋል፡፡