ማንትራ አስራ ሰባት
ቫዩር አኒላም አምርታም
አትሄዳም ብሀስማንታም ሻሪራም
ኦም ክራቶ ስማራ ክርታም ስማራ
ክራቶ ስማራ ክርታም ስማራ
ቫዩህ — የሕይወት እስትንፋስ፣ አኒላም — ጠቅላላ የአየር ክምችት፣ አምርታም — ሊጠፋ የማይችል፣ አትሀ — አሁን፣ ኢዳም — ይህ፣ ብሀስማንታም — ወደ አመድነት ከተቀየረ በኋላ፣ ሻሪራም — ሥጋዊ ገላ፣ ኦም — ኦ ጌታዬ ሆይ፣ ክራቶ — ኦ የመስዋእቶች ሁሉ ተደሳች፣ ስማራ — እባክህን አስታውስ፣ ክርታም — በእኔ የተደረገውን ሁሉ፣ ስማራ — እባክህ አስታውስ፣ ክራቶ — ኦ ዓብዩ ለሁሉም የምታበረክት፣ ስማራ — እባክህ አስታውስ፣ ክርታም — ያደረግሁልህን ሁሉ አስታውስ፣ ስማራ —እባክህ አስታውስ
ይህም ጊዜያዊ እና ሥጋዊ ገላ በመቃጠል አመድ ይሁን፡፡ ይህም የሕይወት እስትንፋሴ ወጥቶ ከመላው አየር ጋር ይዋሐድ፡፡ ጌታዬ ሆይ የምጠይቅህ ነገር ቢኖር ግን፣ አንተ የበላዩ ተጠቃሚ እንደመሆንህ፣ ለአንተ ያበረከትኩትን መስዋእት ሁሉ በመቀበል፣ ይህንን በደካማነቴ በፍቅር ያደረግሁልህን ነገር ሁሉ እንድታስታውስልኝ በማክበር እጠይቅሃለሁ፡፡
ይህ ጊዜያዊ እና ሥጋዊ ገላችን ለነፍሳችን ልክ እንደ እንግዳ የሆነ ልብስ ነው። ብሀገቨድ ጊታ (ብጊ 2:20) በግልጽ እንደሚጠቅሰው ይህ ሥጋዊ ገላችን በሞት ጊዜ እንደሚፈረካከሰው፣ ሕያው ነፍሳችን የምትደመሰስ እና የምትጠፋ አይደለችም። በመንፈሳዊነት ደረጃ ማንነቷ ለዘለዓለም የሚቀየር አይደለም። ሕያው ነፍስ ሰብአዊ ያልሆነች ወይም ቅርጽ የሌላት አይደለችም። እንዲያውም በተቃራኒ የሥጋዊ ገላችን ጊዜያዊ እንደመሆኑ፣ እንደ ነፍስ ዘለዓለማዊ ቅርጽ የለውም። ሥጋዊ ገላችን የሚወስደው ጊዜያዊ ቅርጽ ግን፣ በነፍስ ንቃተ ሕሊና የተቃኘ ነው። ማናቸውም ዓይነት ሕያው ፍጥረታት ሁሉ፣ ከመጀመሪው ጀምሮ ቅርጽ የሌላቸው አይደሉም። የተወሰነ መንፈሳዊ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች ግን፣ ይህንን የተረዱ አይደሉም። በዚህ ማንትራ ወይም ጥቅስ እንደተገለጸው ሕያው ፍጥረታት ሁሉ ከሞት በኋላም በሕይወት በመኖር እንደሚቀጥሉ ነው።
ተፈጥሮ በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ፣ የተለያዩ ቁሳዊ ገላዎችን ለሕያው ፍጥረታት ታቀርባለች። እነዚህንም ቁሳዊ ገላዎች ለሕያው ፍጥረታት የምታቀርበው፣ ከሚፈልጉት ወይም ከሚመኙት የዓለማዊ ስሜት አንጻር ነው። ለምሳሌ ዓይነ ምድርን መመገብ ለሚመኙ ፍጥረታት፣ ተፈጥሮ የአሳማ ወይም የከርከሮ ዓይነት ቁሳዊ ገላ ታቀርብላቸዋለች። ይህም ገላ ለእንደዚህ ዓይነት ምኞት ላላቸው ፍጥረታት አመቺ ነው። እንደዚሁም ሁሉ የሌሎች እንስሳትን ደም እና ሥጋ ለመመገብ ምኞት ያለው ፍጥረት፣ እንደ ነብር እና ጅብ የመሰለ ቁሳዊ ገላ በማግኘት፣ ለአደን አመቺ የሆኑ ጥርሶች፣ ጥፍር እና ጉልበት ያለው ሆኖ ይፈጠራል። የሰው ልጅ ግን የተፈጠረው የእንስሳትን ደም እና ሥጋ ለመመገብ አይደለም። እንደ አሳማ ዓይነ ምድርን ለመመገብም ምንም ምኞት የለውም። የሰው ልጆች ጥርስ የተፈጠረው ግን አትክልት፣ ፍራፍሬን እና ጥራጥሬን አላምጦ ለመመገብ ነው። ይሁን እንጂ የግድ ሥጋ ለመመገብ ለሚጥሩ ጥንታዊ ሰዎች የሚጠቅም ሁለት ክራንቻ ጥርሶች ተፈጥረውለታል።
ይህ የቁሳዊ ገላ ለእንስሳት እና ለሰው ልጅ (ነፍስ) በጣም እንግዳ የሆነ ገላ ነው። ልክ እንደ ሕያው ፍጥረታት (ነፍስ) ፍላጎትም በየጊዜው የሚቀያየር ቁሳዊ ወይም ሥጋዊ ገላ ነው። በዚህ በተደጋጋሚው የተፈጥሮ ዝግመተ ለውጥ ውስጥ፣ እያንዳንዱ ሕያው ፍጥረታት እንደ አዲስ በተወለዱ ቁጥር ገላቸውን ሲቀያይሩ ይገኛሉ። ምድር በውሀ ብቻ በተሞላችበት ጊዜ፣ ሕያው ፍጥረታት የውሀ ውስጥ እንስሳት ሆነው ተፈጥረው ነበር። ከዚያም ወደ ተክል ሕይወት መተላለፍ እና ከተክል ሕይወትም ወደ ትላትልነት መቀየር፣ ከዚያም የአእዋፍ ሕይወትን መያዝ ጀመሩ። ከአእዋፍም ወደ እንስሳ ገላ መቀየር ጀምሩ። በመጨረሻም ከእንስሳ ሕይወት ወደ ሰው ሕይወት መሸጋገር ጀመሩ። ከእነዚህ ሕያው ፍጥረታት ሁሉ፣ የሰው ልጅ ተፈጥሮ በበላይነት የዳበረ ስሜቶችን እና የመንፈሳዊ ዕውቀትን በትክክል ለመረዳት የሚያስችል ገላ ይዞ ይገኛል። በከፍተኛ ደረጃ የዳበረው መንፈሳዊ ስሜትም በዚህ ማንትራ ወይም ጥቅስ ውስጥ ተገልጾልናል። አንድ ሰው ይህንን ወደ አፈር የሚመለሰውን ቁሳዊ ገላ እርግፍ አድርጎ በመተው፣ የሕይወቱን እስትንፋስ ወደ ዘለዓለማዊው መንፈሳዊ ስፍራ ማምራት ይገባዋል። የሕያው ፍጥረታት ሥራ ሁሉ የሚሰራው በዚህ በቁሳዊ ገላችን ነው። ይህም የሚከናወነው በውስጣችን በሚገኘው የአየር ዝውውር ነው። ይህ ውስጣዊ አየር “ፕራና ቫዩ” ይባላል። ጥንታዊ እና የዘመኑ ዮጊዎች ወይም ባሕታውያን፣ ይህንን በቁሳዊ ገላችን ውስጥ የሚገኘውን አየር እንዴት እንደሚቆጣጠሩት ዕውቀታቸውን በማዳበር የሚገኙ ናቸው። የሰው ልጅ ነፍስም ከነበረችበት፣ በገላችን ውስጥ ከሚገኘው የአየር ክበብ ተነስታ ወደላይ ከፍ ከፍ በማለት በጭንቅላታችን “ብራህማ ራንድህራ” ተብሎ ወደሚታወቀው የአየር ክበብ መጠጋት ትችላለች። በዮጋ ኅይል ሙሉ በሙሉ የዳበረ ዮጊም ይህችን ነፍስ ከከፍተኛው የአየር ክበብ ውስጥ አምጥቆ ወደ ፈለገበት የጠፈር ፕላኔቶች ማስኬድ ይችላል። ይህ ዓይነቱ ሥርዓት የሚከናወነው የያዝነውን ቁሳዊ ገላ ለቆ በመሄድ፣ ወደ ሌላ ስፍራ ለመጓዝ ነው። በዚህም ማንትራ ወይም ጥቅስ ላይ እንደተገለጸው፣ ከፍተኛ ስኬት ተገኘ የሚባለው፣ ሕያው ፍጥረታት ይህንን ቁሳዊ ገላቸውን እርግፍ አድርገው በመተው ወደ ዘለዓለማዊው የመንግሥተ-ሰማያት ሲመለሱ ነው። ሕያው ፍጥረታት በዚህ መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ የተለየ የመንፈሳዊ ገላን ለመያዝ ብቁ ይሆናሉ። ይህ መንፈሳዊ ገላ ፈጽሞ ለሞት ወይም ለለውጥ አይጋለጥም።
በዚህ በቁሳዊ ዓለም ውስጥ ግን፣ ተፈጥሮ በግድ ቁሳዊ ገላችንን እንድንቀያይር ታስገድደናለች። ይህም የሚከናወነው ስሜቶቻችንን በተለያዩ ነገሮች ለማርካት ምኞት ስላለን ነው። ያሉን ስሜታዊ ምኞቶች ሁሉ በተለያዩ ፍጥረታት ገላዎች ሊሟሉ ይችላሉ። እነዚህ የዓለማዊ ስሜትን የማርካት ጉጉት፣ በተለያዩ ፍጥረታት ተወክለው ይገኛሉ። ይህም ከትናንሽ ተባዮች ጀምሮ እስከ ከፍተኛው እንደ ጌታ ብራህማ እና እስከ መላእክት ድረስ ነው። እያንዳንዳቸው እነዚህ ፍጥረታት በቁሳዊ ንጥረ ነገሮች እና በተለያዩ ቅርጾች የተሞለሞሉ፣ የተለያዩ ቁሳዊ ገላዎችን ይዘው ይገኛሉ። አእምሮው የላቀ ሰው የሚመለከተው ግን፣ እነዚህን የተለያዩ ገላዎች ሳይሆን፣ በውስጣቸው የሚገኘውን ሕያው መንፈስ ወይም ነፍስ ሁሉ በአንድ ደረጃ ላይ እንዳሉ ሆኖ ነው። በእነዚህ ቁሳዊ ገላዎች ውስጥ የምትገኘው ነፍስ፣ ከዓብዩ ጌታ የተለየች ከፊል ወገን ስትሆን፣ ምንም እንኳን በአሳማም ሆነ በመላእክት ገላ ውስጥ የምትገኝ ብትሆንም፣ በዓይነቷ ከዓብዩ ጌታ ጋር ተመሳሳይ ሆና ትገኛለች። በቀድሞ ሕይወታቸው ካሳለፉት አንጻር፣ ይህም በበጎ ተግባርም ሆነ ኃጢያት በተሞላበት፣ እያንዳንዱ ሕያው ፍጥረታት የተለያዩ ቁሳዊ ገላ ይዘው ይወለዳሉ። በንቃተ ሕሊናው በላቀ መንገድ የዳበረ ፍጡር ደግሞ የሰው ልጅ ሆኖ ይወለዳል። በብሀገቨድ ጊታም (ብጊ 7:19) እንደሚገልጸው፣ ስኬታማ የሆነው የሰው ዘር ከብዙ ትውልድ ሲወርድ ሲዋርድ በመጣው መንፈሳዊ ዕውቀቱ እና ሕሊናው፣ በመጨረሻ ላይ ሙሉ ልቦናውን ለዓብዩ ጌታ አገልግሎት ይሰጣል። ይህ የመንፈሳዊ ዕውቀት ባህል ከዳበረ ደረጃ ላይ ሲደርስ፣ የበለጸገው መንፈሳዊው ሰው፣ ሙሉ ልቦናውን ለዓብዩ ጌታ “ቫሱዴቫ” መንፈሳዊ አገልግሎት ያውለዋል። ስለ መንፈሳዊ አቋማችን ዕውቀት እያለን ሌሎች ሕያው ፍጥረታትም እንደ እኛው የዓብዩ ጌታ ከፊል አካል እንጂ፣ እንደ ዓብዩ ጌታ መሆን እንደማይችሉ ያልተረዳን ከሆንን ግን፣ እንደገና ወደዚህ ቁሳዊ ዓለም ደጋግመን መወለዳችን አይቀሬ ነው። እንዲያውም በመንፈሳዊ ዓለም ውስጥ በሚገኘው እና፣ “ብራህማ ጆይቲ” ተብሎ በሚታወቀው የዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ገላ ጮራ ውስጥ ተቀላቅለን ብንገኝም እንኳን፣ ከጊዜ በኋላ ወደ እዚህ ቁሳዊ ዓለም ተመልሰን መወለዳችን ወይም መውደቃችን አይቀርም።
ቀደም ብለው ከተገለጹት ማንትራዎች ወይም ጥቅሶች እንደምንረዳው፣ “ብራህማ ጆይቲ” የሚባለው ከዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ገላ የሚመነጨው የመንፈሳዊ ብርሃን ነጸብራቅ ወይም ጮራ ነው። ይህ ጮራ ሕያው እና ሙሉ ስሜት ባላቸው መንፈሳዊ ፍጥረታት የተሞላ ነው። አንዳንድ ጊዜም እነዚህ ሕያው ፍጥረታት ስሜቶቻቸውን ለማስደሰት ምኞት ያድረባቸዋል። በዚህም ምክንያት እንደ ምኞታቸው ወደ እዚህ የቁሳዊ ዓለም ውስጥ ቅዠት የተሞላበትን ጌትነትን በመያዝ ስሜቶቻቸውን ለማርካት ይቃጣሉ። በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ጌታ ለመሆን የምናደርገው ጥረት ሁሉ፣ ጊዜያዊ እና ቅዠት የተሞላበት በመሆኑ፣ የቁሳዊ ዓለም በሽታችን ሆኖ ይገኛል። በዚህም ፍላጎት ስሜታችንን ለማስደስት በምናልምበት ኑሮአችን ምክንያት፣ በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ የተለያዩ ቁሳዊ ገላዎችን በመያዝ፣ ደጋግመን በመወለድ ላይ እንገኛለን። ወደ ዓብዩ ጌታ የብርሃን ጮራ ብቻ እንደገና ለመቀላቀልም የያዝነው ዕውቀት የበሰለ መንፈሳዊ ዕውቀት አይደለም። ሙሉ ልቦናችንን ለዓብዩ ጌታ መስጠትን እና በፍቅር በማገልገል ግን፣ ወደ ከፍተኛው የመንፈሳዊ ደረጃ ላይ መድረስ እንችላለን።
በዚህ ማንትራ ወይም ጥቅስ ውስጥ እንደተጠቀሰው፣ በመንፈሱ የዳበረው ሰው ይህንን ቁሳዊ ገላ እና የቁሳዊ ዓለም አየርን ወደ ኋላ በመተው፣ ወደ መንፈሳዊው ዓለም ለመመለስ ጸሎቱን ያደርጋል። ትሑት አገልጋይ ያቀረባቸውን የፍቅር አገልግሎቶች እና ያደረገውን መንፈሳዊ መስዋዕትነት ሁሉ፣ ዓብዩ ጌታ እንዲያስታውስለት ጸሎቱን ያቀርባል። ይህም የሚሆነው በሞት ጊዜ ቁሳዊ ገላው ተቃጥሎ አመድ ከመሆኑ በፊት ነው። በዚህ ጊዜ የሚያደርገው ጸሎት፣ ቀድሞ ያደረጋቸውን ነገሮች ሁሉ በማስታወስ እና፣ የወደፊት መንፈሳዊ ግቡ ምን መሆን እንዳለበት በተገነዘበበት ደረጃ ላይ ነው። በቁሳዊ ዓለም ቁጥጥር ሥር የነበረው ሰው ግን፣ በሞት ጊዜ የሚያስታውሰው ሁሉ፣ ያደረጋቸውን አሰቃቂ ዓለማዊ ሥራዎች በመሆኑ፣ ከሞት በኋላም እንደ ዓለማዊ ሕሊናው፣ እንደገና በቁሳዊ ገላ ውስጥ በመግባት ለመወለድ ይበቃል። ይህም እውነታ በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ተጠቅሷል። (ብጊ 8:6)
ያም ያም ቫፒ ስማራን ብሀቫም
ትያጃቲ አንቴ ካሌቫራም
ታም ታም ኤቫኢቲ ኮንቴያ
ሳዳ ታድ ብሀቫ ብሀቪታህ
“አንድ ሰው በሕልፈተ ሕይወት ጊዜ የነበረው ንቃተ ሕሊና እና የሚያስታውሳቸው ነገሮች፣ ኦ የኩንቲ ልጅ ሆይ፣ ያ የያዘው ንቃተ ሕሊና የወደፊት ትውልዱን ይወስናል።”
በዚህ ጥቅስ ውስጥ እንደተጠቀሰው በሕልፈተ ሕይወት ጊዜ የሚኖረን ሐሳብ እና መንፈስ የወደፊቱን ትውልዳችንን ይወስናል። ይህም የማስታወስ ችሎታ ከሌላቸው ከእንስሳት በተቃረነ መንገድ ነው። በሞት አፋፍ ላይ ያለ ሰው ግን፣ በሕይወቱ ያደረጋቸውን ነገሮች በሙሉ ልክ እንደ ሕልም ሊያስታውሳቸው ይችላል። በዚህም ምክንያት ዓለማዊው ሰው ሐሳቡ ሁሉ፣ በቁሳዊ ዓለም ድርጊቶቹ የተሞላ ይሆናል። አንድ ሰው በዚህ ዓይነት ዓለማዊ ሕሊና፣ ወደ መንፈሳዊው ዓለም በመንፈሳዊ ገላ ለመግባት አይችልም። የዓብዩ ጌታ ትሑት አገልጋይ ግን ፍቅር የተሞላበትን መንፈሳዊ አገልግሎት በማቅረብ፣ ለዓብዩ ጌታ የፍቅር ስሜቱን ሲያዳብር ይገኛል። በሕልፈት ሕይወት ጊዜ ምንም እንኳን ትሑት አገልጋይ ያደረጋቸውን መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ለማስታወስ ባይችልም እንኳን፣ ዓብዩ ጌታ ያቀረበለትን መንፈሳዊ አገልግሎቶች ሁሉ፣ ፈጽሞ ሊዘነጋ አይችልም። በዚህ ጥቅስ ውስጥ የተገለጸው መልእክት፣ ዓብዩ ጌታ ትሑት አገልጋዩ ያደረገውን መንፈሳዊ መስዋእት ሁሉ እንዲያስታውስለት ነው። ዳሩ ግን ይህንን የመሰለ ማስታወሻ ባይኖርም እንኳን፣ ዓብዩ ጌታ ትሑት አገልጋዩ ያደረገለትን መንፈሳዊ አገልግሎቶች ሁሉ ፈጽሞ አይረሳቸውም።
ዓብዩ ጌታ ከትሑት አገልጋዩ ጋር ያለውን የቅርብ ግንኙነት በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ እንዲህ በማለት ግልጾልናል። (ብጊ 9፡ 30 – 34) “ምንም እንኳን አንድ ትሑት አገልጋይ በጣም የሚያስቀይም ተግባር ቢፈጽምም እንኳን፣ ወደ ትሑት መንፈሳዊ አገልግሎት በመመለስ በትክክል እስከተሰማራ ድረስ፣ እንደ መንፈሳዊ ሰው መቆጠር ይገባዋል። ምክንያቱም፣ በትክክለኛ መንፈሳዊ ፈለግ ላይ እንደገና በቅን ውሳኔ በመሰማራቱ ነው። በዚህ መንፈሳዊ ትሑት አገልግሎቱ፣ በቅልጥፍና ወደ ቀና መስመር የገባ ዘላቂ ሰላምን ሊያገኝ ይችላል። ኦ የኩንቲ ልጅ ሆይ! የእኔ ትሑት አገልጋይ ፈጽሞ ሊወድቅ እና ሊጠፋ እንደማይችል፣ ለሁሉም በይፋ መናገር ትችላለህ።” “ኦ የፕርትሀ ልጅ ሆይ! በእኔ ጠለላ ሥር የገቡ ሁሉ ምንም እንኳን ደከም ካለ ትውልድ የመጡ ቢሆኑም ወይም “ቫይሻዎች” (አርሶ አድር እና ነጋዴ)፣ “ሱድራ” (የቀን ሠራተኞች) እንዲሁም ሴቶች ቢሆኑም እንኳን፣ ሁሉም በጠቅላላ ወደ ከፍተኛው መንፈሳዊው ደረጃ ላይ መድረስ ይችላሉ።” ይህ በረከት ለእነዚህ ሁሉ የቀረበ ከሆነ፣ ለሌሎች ለብራህመና ወይም ለቀሳውስት፣ ለትሑት አገልጋዮች እና ለመንፈሳዊ ነገሥታቱም፣ ወደ ከፍተኛው መንፈሳዊ ደረጃ እንዴት በቀላሉ መድረስ እንደሚችሉ መገመት አይሳነንም። “ስለዚህ ወደ እዚህ ወደ ጊዜያዊው እና ስቃይ ወደሞላበት ዓለም እንደመምጣትህ፤ ፍቅር በተሞላበት በእኔ አገልግሎት ላይ ተሰማራ፣ ሐሳብም ሁሉ ወደ እኔ እንዲያተኩር አድርግ፣ የእኔ ትሑት አገልጋይም ሁን፣ ስግደትህን እና አምልኮትህንም ሁሉ አቅርብ። እነዚህን መንፈሳዊ ተግባራት በማድረግ እና ሐሳብህንም በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ በጥሞና በማተኮር፣ ያለ ምንም ጥርጥር ወደ እኔ ለመምጣት ትችላለህ።”
ሽሪላ ብሀክቲቪኖድ ታኩር ይህንን ጥቅስ እንዲህ በማለት ገልጸውልናል። “የሽሪ ክርሽናን ትሑት አገልጋይ እንደ ቅዱስ ሰው በመመልከት፣ በትክክልኛ ፈለግ ላይ እንዳለ መገንዘብ ይገባናል። ይህም ማለት ይህ አገልጋይ “ሱ ዱራቻራ” ቢሆንም እንኳን ነው። “ሱ ዱራቻራ” ማለት ጠበቅ ያላለ ባሕርይ የሌለው ማለት ነው። የዚህንም “ሱ ዱራቻራ” የሚለውን ቃል ፍሬ ነገር በትክክል መረዳት ያስፈልገናል። ወደዚህ ዓለም የመጣ ሰው ሁሉ፣ ሁለት ነገሮችን ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህም ቁሳዊ ገላውን መንከባከብ እና ራስን የማወቅ ጥናቱን ማዳበር ነው። በመጀመሪያ ደረጃ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ኃላፊነት መቋቋም፣ በአእምሮ ብልጽግና ላይ መሳተፍ፣ ንጽሕናን መጠበቅ፣ በትዕግሥት መጣጣር፣ ጤንነትን መንከባከብ፣ ለኑሮ ትግል ማድረግና ቁሳዊ ገላችንን መንከባከብ አስፈላጊ ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ራስን በማወቅ ጥናት ላይ በመሳተፍ፣ የዓብዩ ጌታ ትሑት አገልጋይ መሆን እንዳለብን መገንዘብ ነው። ይህንንም በመገንዘብ፣ ፍቅር በተሞላበት ትሑት አገልግሎት ላይ መሳተፍ ይኖርብናል። እነዚህ ሁለቱ እንቅስቃሴዎች ጎን ለጎን መሄድ ይገባቸዋል። ምክንያቱም በዚህ ዓለም ውስጥ የተወለደ ሁሉ፣ ቁሳዊ ገላውን ከመንከባከብ መራቅ የማይችል በመሆኑ ነው። ቢሆንም ግን በተቻለ መጠን ለቁሳዊ ገላችን የምናጠፋውን ጊዜ ለመቀነስ መጣር ይገባናል። ለዓብዩ ጌታ የምናቀርበው ትሑት አገልግሎት ደግሞ የበለጠ ከፍ ማለት ይገባዋል። ይህም እንዲህ እያለ ለዓብዩ ጌታ የምናቀርበው ትሑት አግልግሎት ከቁሳዊ ገላችን አገልግሎት ዝቅ ያለ ከሆነ አዝማሚያችን ዓለማዊ ለመሆን ይጋለጣል። ቢሆንም ግን ይህ ዓለማዊነት ለረጅም ጊዜ ሊቀጥል አይችልም። ምክንያቱም በዓብዩ ጌታ በረከት አማካኝነት፣ ትሑቱ አገልጋይ በቅጽበት ወደ መንፈሳዊነት ደረጃ ሊቀየር ይችላል። ስለዚህ ለዓብዩ ጌታ ትሑት አገልግሎትን ማቅረብ፣ ለሰው ልጅ ትክክለኛው መንፈሳዊው ፈለግ ነው። ምንም እንኳን አንድ ሰው በዚህ በትክክለኛው መንገድ ላይ እያለ አንዳንድ ጊዜ አንደበቱ ወደ ዓለማዊነት ቢያዘነብልም፣ ራሱን የማወቅ ጥናቱን ሲያሰናክልበት አይታይም።
የዚህ ፍቅር የተሞላበት የዓብዩ ጌታ የአገልግሎት በረከት፣ በጌታ ዓብይ ሰብአዊነት ለማያምኑ ሰዎች ሊቀርብላቸው አይችልም። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በጌታ የመንፈሳዊ ጮራ ወይም “ብራህማ ጆይቲ” ብቻ ስለሚያምኑ ነው።
ቀደም ብሎ በማንትራዎቹ እንደተጠቀሰው፣ ወደ ብራህማ ጆይቲ መንፈሳዊ ጮራ ከገቡ በኋላ፣ ወደ ዓብዩ ጌታ አልፈው ለመሻገር አይችሉም። ምክንያቱም በዓብዩ ጌታ ዓብይ ሰብአዊነት ስለማያምኑ ነው። ጊዜያቸውን የሚያባክኑትም በክርክር እና በግምታዊ አስተሳሰብ ላይ በመወያየት ብቻ ነው። ብሀገቨድ ጊታ (ብጊ 12:5)
አስራ ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ እንደተገለጸውም፣ እንደዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች፣ ድካማቸው ሁሉ የሚያተኩረው ፍሬ በማይሰጥ ነገር ላይ ብቻ ነው። በዚህ ማንትራ ወይም ጥቅስ ውስጥ የቀረቡት ጥቆማዎች ሁሉ፣ ከዓብዩ ጌታ ሰብአዊ ባሕሪይ ጋር በመንፈስ ለመገናኘት እንድንበቃ የሚያስችሉ ናቸው። የዓብዩ ጌታ ፍቅር የተሞላበት ትሑት እና መንፈሳዊ አገልግሎቶች በዘጠኝ ይከፈላሉ። (1) ስለ ዓብዩ ጌታ ማዳመጥ (2) ዓብዩ ጌታን ማመስገን (3) ዓብዩ ጌታን ሁሌ ማስታወስ (4) የሎተስ አበባ የመሰለውን የዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ እግሮች ማገልገል (5) ለዓብዩ ጌታ መስገድ (6) ለዓብዩ ጌታ ጸሎት ማድረግ (7) ዓብዩ ጌታን ማገልገል (8) ከዓብዩ ጌታ ጋር በጓደኝነት እና በፍቅር መቀራረብ (9) ሙሉ ልቦናችንን ለዓብዩ ጌታ ማቅረብ። ከእነዚህ ከዘጠኙ የዓብዩ ጌታ የትሑት አገልግሎት መመሪያዎች ውስጥ አንዱን ብቻ ወይም ዘጠኙንም ለመከታተል እንችላለን። እነዚህን መመሪያዎች በመከተል፣ አንድ ትሑት አገልጋይ ወደ ዓብዩ ጌታ ሁሌ ቅርብ ለመሆን ይችላል። እነዚህን መመሪያዎች የሚከተል ትሑት አገልጋዩ ሁሉ፣ በሕልፈተ ሕይወቱ ጊዜ ዓብዩ ጌታን ለማስታወስ ምንም ችግር አይገጥመውም። ከእነዚህ መመሪያዎች አንዱን ብቻ በትክክል በመከተል፣ የሚቀጥሉት ታላላቅ ትሑት አገልጋዮች ሁሉ፣ ከፍተኛውን የመንፈሳዊ ብቃት እና ስኬትን ለማግኘት በቅተዋል።
(1) ስለ ዓብዩ ጌታ በማዳመጥ ብቻ “ማሀራጅ ፓሪክሺድ” የሽሪማድ ብሀገቨታም መጽሐፍ ታዋቂ አድማጭ የተፈለገውን የመንፈሳዊ ብቃቱን እና ስኬቱን ለማግኘት ችሏል።
(2) ዓብዩ ጌታን በማመስገን ብቻ “ሱካዴቭ ጎስዋሚ” የሽሪማድ ብሀገቨታም መምህር መንፈሳዊ ብቃቱን እና ስኬቱን ለማግኘት ችሏል።
(3) ዓብዩ ጌታን ሁሌ በማስታወስ ብቻ “ፕራህላድ ማሀራጅ” መንፈሳዊ ብቃት እና ስኬቱን ለማግኘት በቅቷል።
(4) የዓብዩ ጌታን ሎተስ የመሰለውን እግሩን በማገልገል፣ የሀብት መልአክ የሆነችው “ላክሽሚ” መንፈሳዊ ብቃቷን እና ስኬቷን ለማግኘት በቅታለች።
(5) ለዓብዩ ጌታ በቤተ መቅደስ ውስጥ በመስገድ “ፕርቱ ማሀራጅ” የመንፈሳዊ ብቃቱን እና ስኬቱን ለማግኘት በቅቷል።
(6) ለዓብዩ ጌታ ምስጋናውን እና ጸሎቱን በማቅረብ “አክሩራ” መንፈሳዊ ብቃቱን እና ስኬቱን ለማግኘት በቅቷል።
(7) ለዓብዩ ጌታ አገልግሎትን በቀጥታ በማቅረብ “ሀኑማን” የመንፈሳዊ ብቃቱን እና ስኬቱን ለማቅረብ በቅቷል።
(8) ለዓብዩ ጌታ ትሑት ጓደኝነትን በማቅረብ “አርጁና” የመንፈሳዊ ብቃቱን እና ስኬቱን ለማግኘት በቅቷል።
(9) ያሉትን ንብረቶች እና ሀብቱን ሁሉ ለዓብዩ ጌታ ሙሉ በሙሉ በማቅረብ፣ ንጉሥ “ባሊ ማሀራጅ” የመንፈሳዊ ብቃቱን እና ስኬቱን ለማግኘት በቅቷል።
የዚህ ማንትራ ወይም ጥቅስ ገለጻዎች እና፣ መላ የቬዲክ ዝማሬ እና ትምህርቶች ሁሉ “ቬዳንታ ሱትራ” ተብሎ በሚታወቀው ሥነጽሑፍ ውስጥ ተጠቃለው ይገኛሉ። ይህም ማጠቃለያ “በሽሪማድ ብሀገቨታም” ውስጥ ተገልጾ ይገኛል። ሽሪማድ ብሀገቨታም ተብሎ የተሰየመው መጽሐፍ፣ የፍራፍሬ ዛፍን ከተመሰሉት ከቬዲክ ሥነጽሑፎች ሁሉ ልክ እንደበሰለው የዛፉ ፍራፍሬ እና ብልሃት እንደተሞላበት ዕውቀት ሆኖ የሚታይ መጽሐፍ ነው። በሽሪማድ ብሀገቨታም መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸው መልእክት ሁሉ፣ በማሀራጅ ፓሪክሺድ እና በሱካዴቭ ጎስዋሚ መሀከል፣ እንደ ውይይት ሆኖ ቀርቧል። የዚህም ጥቅስ መልእክት የተገለጸው፣ ውይይታቸውን እንደጀመሩ በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ነው። ስለ ዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ሳይንስ ማዳመጥ እና ዓብዩ ጌታን በቃል ማወደስ የትሑት መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉ መሠረታዊው አድራጎት ነው። መላው የሽሪማድ ብሀገቨታም መልእክት በሱካዴቭ ጎስዋሚ ተገልጾ፣ ሙሉ በሙሉ የተደመጠውም በመሀራጅ ፓሪክሺድ እና በቅርቡ በነበሩት ባሕታውያን ነበር። መሀራጅ ፓሪክሺድ ለሱካዴቭ ጎስዋሚ በርካታ ጥያቄዎች አቅርቦለት ነበር። ምክንያቱም ሱካዴቭ ጎስዋሚ፣ ከማናቸውም በጊዜው ከነበሩት መንፈሳዊ ዮጊዎች እና ሌሎች መንፈሳውያን ሁሉ፣ የበላይ የሆነ መንፈሳዊ መምህር ነበረ።
የማሀራጅ ፓሪክሺድ ዋናው ጥያቄ እንደሚከተለው ነበር። “በሞት አፋፍ ላይ ያለ ሰው ኃላፊነቱ ምንድን ነው?” ሱካዴቭ ጎስዋሚም እንዲህ በማለት መልስ ሰጥቶት ነበር።
ታስማድ ብሀረታ ሳርቫትማ
ብሀገቫን ኢሽቫሮ ሀሪህ
ሽሮታቭያህ ኪርቲታቭያስ ቻ
ስማርታቭያስ ቼቻታብሀያም
“ከማናቸውም ዓይነት ጭንቀት ነጻ ለመሆን የሚፈልግ ሰው ሁሉ፣ ዓብዩ ጌታን ማስታወስ፣ ማመስገን እና ስለ ዓብዩ ጌታ ምስጋና ማዳመጥ ይኖርበታል። ዓብዩ ጌታ ለሁሉም ነገር የበላይ መሪ፣ ማናቸውንም ችግር ሁሉ ሊያጠፋ የሚችል እና፣ በእያንዳንዱ ሕያው ፍጥረታት ልብ ውስጥ የሚገኝ ዓብይ ነፍስ ነው። (ሽብ 2.1.5)
ብዙሀኑ የሰው ልጅ ኅብረተስብ፣ ሌሊት ለረዘመ ሰዓታት በመተኛት እና በወሲብ ጊዜውን ሲያባክን ይገኛል። በቀን ላይ ደግሞ ሀብትን ለማከማቸት ሲሯሯጥ እና ቤተሰብን ለማስተዳደር በንግድ ስምሪት ላይ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች ስለ ዓብዩ ጌታ ለመጠየቅ፣ ለማዳመጥ እና ለማስታወስ ብዙ ትኩረት አይሰጡትም። የዓብዩ ጌታንም ትምህርት ለመማር በተለያዩ ምክንያቶች በመሸሽ እና በመተው ላይ ይገኛሉ፡፡ ከፊሉ ኅብረተሰብ የዓብዩ ጌታ መኖርን የሚደግፍ ቢሆንም፣ ዓብዩ ጌታ ሰብአዊ ባሕርይ እና፣ ስሜት እንደሌለው አድረገው የሚያስተምሩ ሰዎችም ይገኛሉ። ቢሆንም ግን በቬዲክ መጻሕፍት፣ በኡፓኒሻድ፣ በቬዳንታ ሱትራ፣ በብሀገቨድ ጊታ እና በሽሪማድ ብሀገቨታም እንደተገለጸው፣ ዓብዩ ጌታ ሙሉ ስሜት ያለው እና የሕያው ፍጥረታት ሁሉ የበላይ እንደሆነ ተደምድሞ ተገልጿል። የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ከዚህ ተነጥለው አይታዩም። ስለዚህ አንድ ሰው ስለ መንፈሳዊ እውቀት የተዛባ አመለካከት ያላቸውን ፖለቲከኞች እና ሌሎች ራሳቸውን እንደ ታላቅ የሚቆጥሩ አሳሳች መምህራንን ከማዳመጥ ይልቅ፣ ሕይወታችንን በማስተካከል፣ በመንፈሳዊ የፍቅር አገልግሎት ላይ ምንም ጊዜ ሳናጠፋ መሰማራት ይገባናል። የሽሪ ኡፓኒሻድ ትምህርትም የሚመራን ወደዚሁ በጎ መንፈሳዊ ተግባር ላይ እንድናተኩር ነው።
አንድ ሰው ትሑት መንፈሳዊ አግልግሎትን ማቅረብ የሚያዘወትር ካልሆነ እንዴት አድርጎ ዓብዩ ጌታን በሕልፈተ ሕይወቱ ጊዜ ለማስታወስ ይችላል? ገላው በአደጋ ሲጎዳ ወይም በሕመም የሚማቅቅ ከሆነ፣ እንዴት አድርጎ ያን ያደረገውን መንፈሳዊ መስዋዕት ሁሉ፣ ዓብዩ ጌታ እንዲያስታውስለት መጸለይ ይችላል? ለመንፈሳዊነት መስዋዕት ማድረግ ማለት፣ በዓለማዊ ብልጭልጭ ነገሮች ስሜቶቻችንን ለማርካት ከመጣር ይልቅ፣ መራቅ እና መቆጣጠር ማለት ነው። ይህንንም ሥነጥበብ ለመማር የምንችለው፣ ስሜቶቻችንን ሁሉ በዓብዩ ጌታ ትሑት አገልግሎት ላይ በመላ ሕይወታችን በማሰማራት ነው። ይህ የመንፈሳዊ አገልግሎት ልምድ፣ በሕልፈተ ሕይወት ጊዜ ዓብይ ጌታን በቀላሉ ለማስታወስ ይረዳናል።