No edit permissions for Amharic

ማንትራ ሁለት

ኩርቫን ኢቬሀ ካርማኒ
ጂጂቪሴክ ቻታም ሳማህ
ኤቫም ትቫዪ ናንያትሄቶስቲ
ና ካርማ ሊፕያቴ ናሬ

ኩርቫን — በተከታታይ ማድረግ፣ ኤቫ — ታድያ፣ ኢሀ — በዚህ ሕይወት ርዝማኔ ውስጥ፣ ካርማኒ — ሥራ፣ ጂጂቪሴት — አንድ ሰው ለመኖር መሻት አለበት፣ ሳታም — አንድ መቶ፣ ሳማህ — ዓመታት፣ ኤቫም — በመኖር፣ ትቫዪ — በአንተ፣ ና — አይደለም፣ አንያትሀ — አማራጭ፣ ኢታህ — በዚህ መንገድ፣ አስቲ — ይኖራል፣ ና — አይደለም፣ ካርማ — ሥራ፣ ሊፕያቴ — ሊተሳሰር ይችላል፣ ናሬ — ለሰው ልጅ

ይህንንም ዓይነት ሕይወት በመከተል፣ አንድ ሰው ለብዙ መቶ ዓመታት ለመኖር መሻት ይችላል፡፡ ከተወሰነለት ድርሻው በላይ ሳይወስድ በመሥራትም፣ ከተፈጥሮ የካርማ ወይም የተፈጥሮ ሕግ የመጣስ መተሳሰር ነጻ ሊሆን ይችላል፡፡ ከካርማ ነጻ ለመሆን፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ከዚህ ዓይነቱ ጥንቃቄ ውጪ ሌላ ምንም አማራጭ አይኖርም፡፡

በተፈጥሮው ማንም ሰው ቢሆን ያለወቅቱ ለመሞት ፍላጎት የለውም፡፡ ሁሉም ሰው በተቻለው መጠን ለረጅም ዓመታት ለመኖር ጥረት የሚያደርግ ነው፡፡ ይህም ዓይነቱ አዝማምያ የሚታየው በግለሰብነት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በኅብረተሰብም ደረጃ ነው፡፡ ይህም በማኅበረሰብ እና በብሔራዊ ደረጃም ጭምር ነው፡፡ የሰው ልጅም ሆነ ማናቸውም ፍጥረታት፣ የሕይወታቸውን ዕድሜ ለማራዘም ብዙ ትግል ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ የቬዲክ ዕውቀት እንደሚገልጽልንም፣ ይህ በተፈጥሮ፣ በሁሉም ሕያው ፍጥረታት ላይ የሚታይ አዝማምያ ነው። ሕያው ፍጥረታት (ነፍሶች) ዘለዓለማዊ ናቸው፡፡ ቢሆንም ግን፣ እያንዳንዱ ፍጥረት በዚህ ቁሳዊ ዓለም እና ጠፈር ውስጥ በቁሳዊ አካል ተወልዶ በመተሳሰር ላይ እያለ፣ የተሰጠውን ገላ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደስራው የመቀያየር ግዳጅ አለበት፡፡ ይህም ሂደት የነፍስ ከአንዱ ገላ ወደ ሌላው ገላ መፍለስ ወይም “ካርማ ባንደና” ይባላል፡፡ የምናገኘውም ቁሳዊ ገላ የሚከሰተው ከምናደርገው ድርጊት እና ከያዝነው ልቦና አንጻር ነው፡፡ ሕያው ፍጥረታት በዚህ ዓለም ላይ ለሚገኘው ሕይወት ሲባል ሥራ መሥራት ግዳጃቸው ነው፡፡ ይህም የቁሳዊው ዓለም ወይም የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡ የተፈጥሮንም ሕግ ሳይከተል የሚኖር እና የሚጠበቀበትን ሥራ የማይሠራ ሰው፣ ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ የፈለሰ እንደመሆኑ፣ ሕይወቱ ስቃይ የተሞላበት ሊሆን ይችላል። ይህም ዓይነቱ አዝማምያ ወደዚህ ቁሳዊ ዓለም፣ በተደጋጋሚ በመመላለስ እና የተለያዩ ፍጥረታት ቁሳዊ ገላዎችን በመላበስ እንዲወለድ ያስገድደዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በቁሳዊ ጠፈር ውስጥ የሚገኙት ሕያው ፍጥረታት ሁሉ፣ በተደጋጋሚ የመወለድ እና የመሞት ግዳጅ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሕያው ፍጥረታት፣ የሰውን ልጅ ሕይወት ዕድል ሲያገኙ ግን ከዚህ ከተደጋጋሚ ሞት እና መወለድ የማምለጥ ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ ከዚያም “ካርማ” ከሚባል የተፈጥሮ ሰንሰለት ተፈተው ለማምለጥ ይችላሉ፡፡ ነፍስም ከዚህ ቁሳዊ ዓለም ተለይታ ወደ መንፈሳዊው ዓለም በመሄድ ትጸድቃለች። እነዚህ “ካርማ፣ አካርማ፣ ቪካርማ” የሚባሉት ቃላት በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ በዝርዝር ተገልጸዋል፡፡ በቬዲክ ሥነጽሑፎች ውስጥ እንደተገለጸው፣ “ካርማ” የሚባለው የተፈጥሮን ሕግ ተከትለን የምንሠራቸውን ሥራዎች ነው፡፡ ከተደጋጋሚው ሞት እና መወለድ ሰንሰለት ነጻ የሚያደርገን መንፈሳዊ ድርጊት ሁሉ ደግሞ “አካርማ” ይባላል፡፡ በተፈጥሮ የተሰጠንን ነጻነት ያለአግባብ ሳንጠቀም የምናደርገው ድርጊት ሁሉ ወደ ዝቅተኛው የተፈጥሮ ትውልድ እንድናመራ የሚያበቃን ድርጊት ነው። ይህ ዓይነቱ ሥራ “ቪካርማ” ይባላል፡፡ ከእነዚህም ሦስት ዓይነት የሥራ ዓይነቶች ዐዋቂ በሆኑት ሰዎች የሚመረጠው፣ ከካርማ እና ከቪካርማ ሰንሰለት ነጻ ሊያወጣን የሚችለውን የሥራ ዓይነት ነው። ይህም “አካርማ” የተባለው ነው፡፡ ተራ የሆኑ ሰዎች በዚህ ዓለምም ሆነ በገነት ውስጥ ዕውቅናን እና ከፍ ያለ ማዕረግን ለማግኘት፣ ጥሩ ሥራን ለመሥራት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን በንቃታቸው የዳበሩ እና በመንፈሳቸው የሠለጠኑ ሰዎች ዓለማዊ ሥራ ከሚፈጥረው የተፈጥሮ እሥራት ፈጽሞ ነጻ ለመሆን የሚሹ ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ አእምሯቸው የዳበሩ ሰዎች፣ በዚህ ዓለም ላይ የሚደረገው ጥሩም ሆነ መጥፎ ሥራ ሁሉ ወደ እዚህ ዓለም የሚያስተሳስረን ድርጊት እንደሆነ የተረዱ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የሚመርጡት ሥራ ሁሉ፣ የዓለማዊ ጥሩ እና መጥፎ ሥራ ከሚያመጡት ውጤት ሁሉ ነጻ ሊያስወጣቸው የሚችለውን መንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ነው፡፡ ይህንንም መሳዩ ነጻ ሊያወጣ የሚያስችለው መንፈሳዊ አገልግሎቶች በእነዚህ በኡፓኒሻድ ገፆች ውስጥ ተዘርዝሮ የቀረበው ነው፡፡

የሽሪ ኡፕኒሻድ መጽሐፍ መልእክቶች “ጊታ ኡፕኒሻድ” ተብሎ በሚታወቀው የብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በዝርዝር ተመዝግቧል፡፡ የብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መጽሐፍ ከኡፕኒሻድ መጻሕፍት ሁሉ እንደ ክሬም ወይም እንደ ማር ወለላ የሚታይ ነው፡፡ በብሀገቨድ ጊታ መጽሐፍ ጥቅስ (ብጊ 3፡9-16) ውስጥ በዓብዩ ጌታ እንደተገለጸው፣ አንድ ሰው በቬዲክ መጻሕፍት ውስጥ የቀረቡትን ትእዛዞች የማይከተል እና የሚጠበቅበትን የማያከናውን ከሆነ “ናይሽካርማ” ወይም “አካርማ” ደረጃ ላይ ለመድረስ አይችልም፡፡ በእነዚህ ሥነጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱት ትምህርቶች፣ የሰውን ልጅ ኑሮ እና የሥራ ዓይነት የሚወስኑለት እና በተፈጥሮ ከዓለማዊ ኑሮ ነጻ እንዲሆን የተሰጡ መመሪያዎች ናቸው፡፡ እነዚህም መመሪያዎች ቀስ በቀስ የዓብዩ ጌታን ኅያልነት እና ባለቤትነትን እንድንረዳ እና እንድንገነዘብ የሚያደርጉን ናቸው። የዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያትን ጌታ “ቫሱዴቭ” ወይም “ክርሽናን” ለመረዳት ዕድል ስናገኝም ትክክለኛ እና ጠቃሚ የሆነ ዕውቀትን አገኘን ማለት ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ንጹሕ ልቦና ያለው ሰው በተፈጥሮ በሚገኙት ሁኔታዎች ማለትም የዓለማዊ ደግነት፣ ለትርፍ በጋለ ፍላጎት መጣር ወይም በድንቁርና ውስጥ ለመግባት አይጋለጥም፣ ወይም ደግሞ በእነዚህ ዓይነት አመመካከት እና ግንዛቤ አይጠቃም፡፡ የሚሰራውም ሥራ ሁሉ ነጻ ከሚያደረገው ከመንፈሳዊው አገልግሎት ወይም “ከናይሽካርምያ” ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ይህም ዓይነቱ ሥራ ከተደጋጋሚ ሞት እና መወለድ ነጻ ሊያደርገን ይችላል፡፡

በይፋ ለመግለጽ፣ ለዓብዩ ጌታ ትሑት አገልግሎትን ለማቅረብ ከተዛመደ ሥራ ይልቅ፣ ማንም ሰው ቢሆን ሌላ ዓይነት ዓለማዊ ስሜቱን ለማርካት ሥራ መሥራት አያስፈልገውም፡፡ መንፈሳዊ ንቃት የጐደለበት ዝቅተኛ ሕይወትንም በመምራት ላይ እያለን፣ ይህንን ወደመሰለ የትሑት አገልግሎት መንፈስ፣ በቅልጥፍና ለመዘዋወር ያዳግተን ይሆናል፡፡ የጀመርነውን እና ውጤት የሚያስገኘውን ዓለማዊ ሥራ ወዲያውኑ ለመተው ያዳግተን ይሆናል፡፡ እንደሚታወቀው በዚህ ዓለም ኑሮ ውስጥ የተጠመደ ሰው ሁሉ፣ ስሜታዊ ደስታን የሚሰጥ ሥራ ላይ ከመሰማራት ወደኋላ አይልም፡፡ ይህም ዓይነት ጉጉት ስላለበት በቅጽበት ወይም ከጊዜ በኋላ ስሜትን ሊያረኩ በሚችሉ ሥራዎች ላይ ከመሰማራት አይቆጠብም፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ተራ የሆነ ዓለማዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው ሁሉ ለግል ስሜታዊ ጥቅሙ ሲል በዓለማዊ ሥራ ላይ በመሰማራት ሲታገል ይታያል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህም ዓይነቱ ትግል ከግለሰብ ጥቅም ደረጃ ባሻገርም በመሄድ ኅብረተሰብን፣ ብሔርን፣ የሰው ልጅን በጠቅላላ በመወከል እና የተለያየ ስምን በመያዝ የሚከናውን ተግባር ነው፡፡ እንዲያውም ልብ የሚስቡ ስሞች በመያዝ እና “አልተሪዝም፣ ሶሻሊዝም፣ ኮምዩኒዝም፣ ናሽናሊዝም፣ ሂዩማኒተሪያኒዝም” በማለት እየተሰየሙ ሲካሄዱ ይታያሉ፡፡ እነዚህም “ኢዝሞች” የሰውን ልጅ አእምሮ የሚስቡ የካርማ ካንዳ (በካርማ የሚያስተሳስሩ) የተለያዩ ስሞች ናቸው፡፡ ነገር ግን በኢሾፓኒሻድ የቬዲክ መልእክቶች እንደተገለጹልን ምንም እንኳን የእነዚህ “ኢዝሞችን” ሕይወትን ለመከተል ብንፈልግም፣ እንቅስቃሴያችን ሁሉ ከዓብዩ ጌታ ጋር የተያያዘ ወይም ዓብዩ ጌታን የሚወክል መሆን ይገባዋል፡፡ የቤተሰብ አስተዳዳሪ፣ አልትሩይስት፣ ሶሻሊስት፣ ኮሚኒስት፣ ናሽናሊስት ወይም ሂዩማንተርያን መሆን የሚያስከፋ ነገር አይደለም፡፡ ቢሆንም ግን፣ የምናደርጋቸው ድርጊቶች በሙሉ “ከኢሻቫስያ” ወይም ከዓብዩ ጌታ ትእዛዝ የማይወጣ ሆኖ አምላክን በፍቅር የሚያካትት አገልግሎት መሆን ይገባዋል፡፡

በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና እንደገለጸው (ብጊ 2፡40) “ለዓብዩ ጌታ የሚቀርቡት ትሑት አገልግሎቶች ሁሉ በጣም አስፈላጊ በመሆናቸው፣ በትንሽ የቀረበች አገልግሎት እንኳን የሰውን ልጅ በጣም ከሚያስፈራ አደጋ ልታድነው ትችላለች፡፡” ከሁሉም በላይ የሚያስፈራው አደጋ ከሞት በኋላ ሰው የመሆን ዕድልን አጥተን ከ8,400,000 የተለያዩ ፍጥረታት አንዱ ሆኖ በመፈጠር፣ ወደ ተደጋጋሚው ሞት እና ትውልድ እንደገና መግባት ነው።”
አንድ ሰው በተፈጥሮ ያገኘውን የሰው ልጅ ሕይወት ይዞ፤ የቀረበለትን የመንፈሳዊነት ዕድል ሳይጠቀም በመቅረት፣ ከሞት በኋላ ወደ ዝቅተኛ የተፈጥሮ አካል የወደቀ ከሆነ፣ እንደሚያሳዝን ዕድለ ቢስ ፍጡር ይቆጠራል፡፡ ዓለማዊ ስሜቶቹ ስለሚያታልሉትም፣ በሞኝነት የተጠቃ ሰው እንዲህ ዓይነቱ ደረጃ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል አይረዳም፡፡ ስለዚህ በሽሪ ኢሾፓኒሻድ እንደተገለጸልን ኃይላችንን ሁሉ የኢሻቫስያን ወይም የዓብዩ ጌታን መንፈስ እንድናዳብርበት መጠቀም ይኖርብናል፡፡ በዓለማዊ ሕይወት በመጠመድ፣ ለብዙ ዓመታት ለመኖር እንሻ ይሆናል፡፡ ይህም ዓይነት ረጅም ዕድሜ ምንም ዓይነት ጥቅም የለውም፡፡ ዛፍ ለብዙ ዓመታት እና ለብዙ ሺህ ዓመታት ለመኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ረጅም ሕይወት ማግኘት ፋይዳው ምንድን ነው? እንደ ቃልቻ መተንፈስ፣ እንደ አሳማና ውሾች ደጋግሞ መወለድ፣ እንደ ግመል ማመንዠክ ትልቅ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በዓብዩ ጌታ ፍቅር የተመሠረተ ትንሽ ትሑት የሆነ አገልግሎት ማቅረብ ግን፤ ከሺህ ዓመታት ዕድሜ እና የዓብዩ ጌታ ፍቅር ካልተጨመረበት፣ ምንም ከሚያክል የአልትሩይዝም እና የሶሻሊዝም ሥርዓቶች በላይ ነው፡፡

አልትሩዪስቲክ ሥራዎችን በሽሪ ኢሾፓኒሳድ መንፈስ ተመስጠው፣ የሚሠሯቸው ከሆነ፣ ልክ እንደ ካርማ ዮጊ ይሆናሉ። እንዲህ ዓይነት ሥራዎች በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ተገልጸዋል፡፡ (ብጊ 18፡5-9) እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች ወደ ተደጋጋሚው የፍጥረታት ሞት እና መወለድ አደጋ ከመጋለጥ ይድናሉ። ምንም እንኳን እነደዚህ ዓይነቶች ተግባራት ዓብዩ አምላክን በከፊሉ አካተው የሚያጠቃልሉ ሥራዎች ቢሆኑም ለሠራተኛው መንፈሳዊ ፋይዳ ያላቸው ናቸው። ምክንያቱም በሚቀጥለው ትውልዱ፣ ቢያንስ ቢያንስ የሰው ልጅ የመሆን ዕድል እንዲያገኝ ያደርጉታል፡፡ ይህንንም ተደጋሚ ዕድል በመጠቀም ከዚህ ዓለም ነጻ ወጥቶ ወደ መንፈሳዊው ዓለም ለመመለስ ዕድሉን ይሰጡታል፡፡

ወደ ዓብዩ አምላክ በሚያተኩር አገልግሎት ላይ እንዴት መሳተፍ እንደምንችል፤ በብሀክቲ ራሳምርታ ሲንድሁ መጽሐፍ ውስጥ በሽሪላ ሩፓ ጎስዋሚ በዝርዝር ትምህርቱ ቀርቦልናል፡፡ ይህንንም መጽሐፍ “ኔክታር ኦፍ ድቮሽን” ብለን ሰይመን አቅርበነዋል፡፡ በሽሪ ኡፓኒሻድ መንፈስ ለመመራት ለሚፈልጉ ትሑት አገልጋዮች ሁሉ፣ ይህንን በጣም አስፈላጊ መጽሐፍ በማንበብ እንዲመሩ በትሕትና እናሳስባለን፡፡

« Previous Next »