No edit permissions for Amharic

ማንትራ ስድስት

ያስ ቱ ሳርቫኒ ብሁታኒ
አትማኒ ኤቫኑፓስያቲ
ሳርቫ ብሁቴሹ ቻትማናም
ታቶ ና ቪጁጉፕሳቴ

ያህ — እርሱ፣ ቱ — ነገር ግን፣ ሳርቫኒ — ሁሉም፣ ብሁታኒ — ሕያው ፍጥረታት፣ አትማኒ — ከዓብዩ ጌታ ጋር በተዛመደ መንገድ፣ ኤቫ — ብቻ፣ አኑፓሽያቲ — ሥርዓት ባለው መንገድ የሚያይ፣ ሳርቫ ብሁቴሹ — በእያንዳንዱ ሕያው ፍጥረታት፣ ቻ — እና፣ አትማናም — በልብ የሚኖረው ጌታ፣ ታታህ — ከዚያም በኋላ፣ ና — አይደለም፣ ቪጁጉፕሳቴ — ማንንም አይጠላም

በዓለም ላይ የሚገኙትን ነገሮች በሙሉ ከዓብዩ ጌታ ጋር አዛምዶ የሚያይ፤ በምድር የሚገኙት ፍጥረታት በሙሉ የዓብዩ ጌታ ከፊል እና ቁራሽ መሆናቸውን የተገነዘበ፤ ዓብዩ ጌታም በሁሉም ነገር ውስጥ የሚገኝ እንደሆነ የተረዳ ሁሉ፣ ምንም ነገርን ወይም ማናቸውንም ፍጥረታት ሊጠላ አይችልም፡፡

ይህ ገለጻ የሚያሳየን “መሀ ብሀጋቨት” የሆነን ሰው ወይም ሁሉንም ነገር ከዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ ጋር አነጻጽሮ ለማየት አቅም ያለው ታላቅ ሰው መሆኑን ነው፡፡ ዓብዩ ጌታ በአጠገባችን መኖሩን የምናውቅበት አመለካከት፣ በሦስት ዓይነት ደረጃ ይከፈላል፡፡ ከነዚህም ከሦስቱ ዓይነቶች አንዱ፣ “ካኒሽታ አዲካሪ” ተብሎ የሚታወቀው፣ ዝቅተኛው ዓይነት አመለካከት ያለው ሰው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰው እንደ ሃይማኖቱ ወደ ቤተ መቅደስ፣ ቤተ ክርስቲያን ወይም መስጊድ በመሄድ፣ የተሰጠውን መንፈሳዊ ሥርዓት በመከተል፣ ሲሰግድ ወይም ሲያመልክ ሊገኝ ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ እንደነዚህ ዓይነት አገልጋዮች ዓብዩ ጌታ በቤተ መቅደስ እንጂ በሌላ ቦታ ያለ አይመስላቸውም፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎቶች ውስጥ ካሉትም ካህናት፣ የትኛው በምን መንፈሳዊ ብቃት ላይ እንደደረሰ፣ ወይም የትኛው ካህን በዓብዩ ጌታ መንፈስ እና ንቃት የዳበረ እንደሆነም ለይተው አያውቁም፡፡ ብዙውን ጊዜ እንደነዚህ ዓይነት አገልጋዮች የቀረበላቸውን ትእዛዝ ብቻ የሚከተሉ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም እርስ በእርስ ሲተንኳኮሉ ይታያሉ፡፡ ይህም የአንዱ አገልግሎት ከሌላው እንደሚበልጥ በማመሳከር ነው፡፡ እነዚህ “ካኒስታ አዲካሪዎች” ተብለው የሚታወቁት፣ ዓለማዊ መንፈስ የተቀላቀለባቸው የዓብዩ ጌታ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ሆንም ግን የቁሳዊ ዓለምን በመሸጋገር፣ ወደ መንፈሳዊው ዓለም ለመሄድ የሚሹ ናቸው፡፡

ሁለተኛው መንፈሳዊ ደረጃ ላይ የደረሱት ደግሞ “ማድህያም አዲካሪ” በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ አገልጋዮች ደግሞ፣ በመላው ፍጥረታት ውስጥ በአራት የተከፈሉ ሕያው ፍጥረታት እንዳሉ በመገንዘብ ይመለከታሉ፡፡ 1) ዓብዩ ጌታ 2) የዓብዩ ጌታ አገልጋዮች 3) ገለልተኞች ወይም ስለ ዓብዩ ጌታ ምንም ግድ የማይሰጣቸው 4) ከሀድያን ወይም በዓብዩ ጌታ ምንም እምነት የሌላቸው እና ትሑት አገልጋዮችንም የሚጠሉ ናቸው፡፡ ይህ እንዲህ እያለ “ማድህያም አዲካሪ” ተብሎ የሚታወቀው አገልጋይ፣ እነዚህን በአራት የተከፈሉ ምድቦች በተለያየ መንገድ የሚቀርብ ነው፡፡ ይህም ማለት ዓብዩ ጌታን ሲሰግድለት እና ሲያመልከው ይታያል፡፡ ወደ ዓብዩ ጌታ ትሑት አገልጋዮች በፍቅር በመቅረብም ጓደኝነትን ይፈጥራል፡፡ ገለልተኞችንም በመቅረብ የዓብዩ ጌታ ፍቅር በልባቸው ውስጥ እንዲቀሰቀስ ጥረት ያደርጋል፡፡ የዓብዩን ቅዱስ ስም የሚያንቋሽሹ ከሃዲያኖችን ደግሞ ይርቃቸዋል፡፡

ከእነዚህ “ከማድህያም አዲካሪዎች” በላይ የሚገኘው ደግሞ “ኡተማ አዲካሪ” ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡ እርሱም ሁሉንም ነገር ከዓብዩ ጌታ ጋር በማነጻጸር የሚያይ እና፣ በመንፈሱም የላቀ ብቁ አገልጋይ ነው። “ኡተማ አዲካሪ” ከሃዲያንን እና አማንያንን ለያይቶ አያይም፡፡ ሁሉንም የሚያያቸው፣ የዓብዩ ጌታ ወገን እና ቅንጣቢ አካል እንደሆኑ አድርጎ ብቻ ነው፡፡ በጥልቅ መንፈሳዊ እውቅና ካለው ባሕታዊ እና፣ በመንገድ በሚያልፍ ውሻ መሀከል ምንም መሠረታዊ ልዩነት እንደሌለ አድርጎ የሚያይ ነው። ምክንያቱም ሁለቱም የዓብዩ ጌታ ወገን እና ቁራሽ አካል እንደሆኑ ስለሚያውቅ ነው፡፡ ይህም፣ ምንም እንኳን በተለያየ ሥጋዊ ገላ ውስጥ ተጠምደው ቢገኙም እንኳን ማለት ነው፡፡ “ኡተማ አዲካሪ” እንደሚረዳውም፣ እነዚህ ፍጥረታት ይህንን ዓየነት የተለያየ ቁሳዊ ገላ ሊያገኙ የቻሉት፤ በቀድሞ ዘመን ሕይወታቸው ከነበራቸው የልቦና ዓይነት እና ካደረጉት የእንቅስቃሴ ዓይነት አኳያ እንደሆነ በማየት ነው፡፡ የሚኖረው አመለካከትም፣ ብራህማናው (ካህኑ) ዓብዩ ጌታ የሰጠውን ኃላፊነት በትክክል የተወጣ እንደሆነ አድርጎ ሲሆን፤ ለውሻው ደግሞ በቀድሞው ሕይወቱ በዓብዩ ጌታ የተሰጠውን ነጻነት እና ኃላፊነት በአግባቡ ባለመጠቀሙ፣ በተፈጥሮ ቅንብር ሳቢያ የውሻ ቁሳዊ ገላ በመያዝ ለመወለድ እንደበቃ የተረዳ ሰው ነው፡፡ ባሕታዊው እና ውሻው የሚያደርጉት ነገር ላይም ሳያተኩር፣ ሁለቱም የዓብዩ ጌታ ልጆች በመሆናቸው ብቻ አድርጎ ይመለከታል።

“ኡተማ አዲካሪው” ለሁለቱም በጐ ለማድረግ የሚያስብ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱም በመንፈሳዊ ሕይወቱ የበለጸገ ሰው፣ ሕያው ፍጥረታት በተመደበላቸው ወይም ባላቸው የቁሳዊ ገላ ግራ አይጋባም፡፡ በሕሊናው የሚያስበው ግን፣ በገላቸው ውስጥ የምትገኘው መንፈሳዊ ኅይል ወይም ነፍስ በመኖሯ፣ እኩልነታቸውን ብቻ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለመላው ኅብረተሰብ የበጎ አድራጐትን ሥራ የሚሰሩ በመምሰል፣ ሰውን ሁሉ እንደ አንድ በማየት “ኡተማ አዲካሪን” ለማስመሰል ይጥራሉ፡፡ ቢሆንም ግን ህልውናቸው እና አቀራረባቸው በቁሳዊ ገላ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ትክክለኛ “ኡተማ አዲካሪ” ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ስለ ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት ጽንሰ ሐሳብ ለመማር የምንችለው፣ ከኡተማ አዲካሪ እንጂ፣ በልባችን ውስጥ ስለሚገኘው ዓብዩ ጌታ እና፣ ስለ ነፍስ መሠረታዊ ዕውቀት ከሌላቸው ሰዎች አይደለም፡፡

ስለዚህ ጉዳይ በዚህ በስድስተኛው ጥቅስ ላይ በደንብ ተገልጿል። ይህ የሚያመለክተን የመንፈሳዊነትን ደረጃ በትክክል ማየት እና መገንዘብ እንደሚያስፈልገን ነው፡፡ ትክክለኛውን ግንዛቤ ለመያዝም፣ የቀድሞ አቻርያ ወይም መምህራንን መከተል ይኖርብናል፡፡ እነዚህ መምህራን ትክክለኛ እና ሥልጣን ያላቸው መምህራን ናቸው፡፡ ከዚህ ሐሳብ ጋር ተያይዞ የሚገኘው የሳንስክሪት ቃል “አኑፓሽያቲ” ይባላል፡፡ “አኑ” ማለት መከተል ሲሆን “ፓሽያቲ” ማለት ደግሞ መገንዘብ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ”አኑፓሽያቲ“ ማለት፣ አንድ ሰው በውን ዓይኑ በሚያየው ነገር ብቻ ማመን ሳይሆን፣ የቀድሞ አቻርያዎችን ወይም መምህራን ትምህርት በመውሰድ፣ ዕውቀትን በተሞረኮዘ መንገድ ማየት እና፣ መገንዘብ ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ በቁሳዊው ዓለም በተበከለው ልቦናችን ምክንያት፣ በውን ዓይኖቻችን በማየት ብቻ ሁሉን ነገር በትክክል ለመረዳት አንችልም፡፡ ሥልጣን ካላቸው መምህራን ትምህርትን የማንቀስም ከሆነ፣ በውን ዓይኖቻችን በማየት ብቻ፣ መንፈሳዊ ዕውቀትን በትክክል መገንዘብ አንችልም፡፡ ታላቁ የዕውቀት ምንጭ፣ በዓብዩ ጌታ የቀረበልን የቬዲክ ዕውቀት ነው፡፡ የቬዲክ ዕውቀት የተላለፈልን ከጌታ ብራህማ ወደ ናራዳ፣ ከናራዳ ወደ ቭያስ፣ ከቭያስ ወደ በርካታ ደቀመዛሙርት በመተላለፍ ነው፡፡ በቀድሞ ጊዜ ይህንን የቬዲክ ዕውቀት መመዝገብ ወይም መጻፍ አያስፈልግም ነበር፡፡ ምክንያቱም በቀድሞ ጊዜ የነበሩት ሰዎች በጣም ዐዋቂዎች እና የማስታወስ ችሎታቸውም በጣም ከፍ ያለ ነበር፡፡ በማዳመጥ ብቻ የተሰጣቸውንም ትምህርት እና ትእዛዝ፣ በመላ ዕድሜያቸው ያስታውሱ ነበር፡፡ ይህንንም ትምህርት የሚያዳምጡት፣ ዕውቅና እና ሥልጣን ካላቸው የቬዲክ መንፈሳዊ መምህራን ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ በቬዲክ ሥነጽሑፎች ላይ በርካታ ገለጻዎች ተሰጥተዋል፡፡ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ገለጻዎች ግን ከዋነኛው ከሽሪላ ቭያሳዴቭ የዲቁና ሥርዓት ተከታትለው ከሚመጡ ሰዎች አይደለም። ሽሪላ ቭያሳዴቭ የቬዲክ ዕውቀትን ለመጀመሪያ ጊዜ የጻፈው ባሕታዊ ነው፡፡ የሽሪላ ቭያሳዴቭ የመጨረሻው እጅግ ታላቅ እና ልብ የሚማርከው መጽሐፍ፣ ሽሪማድ ብሀገቨታም የሚባለው የቬዳ ትምህርቶች ማጠቃለያ፣ ገለጻው ወይም ሐተታው ነው፡፡ ይህም ቬዳንታ ሱትራ በመባል ይታወቃል፡፡ ብሀገቨድ ጊታ የሚባለውም የተቀደሰ መጽሐፍ በዓብዩ ጌታ የተነገረ እና በሽሪላ ቭያሳዴቭ የተጻፈ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ በጣም አስፈላጊ የሆኑ የቬዲክ ዕውቀቶች ናቸው፡፡ የእነዚህን የብሀገቨድ ጊታ እና የሽሪማድ ብሀገቨታም መልእክቶች የሚቃረን ገለጻ ሁሉ መንፈሳዊ ሥልጣን እንደሌለው መገንዘብ ይገባናል፡፡ ኡፓኒሻድ፣ ቬዳንታ ሱትራ፣ ቬዳዎች፣ ብሀገቨድ ጊታ እና ሽሪማድ ብሀገቨታም የመሳሰሉትን የቬዲክ መጻሕፍቶች ሁሉ፣ በስምምነት ያሉ እና የተቀረነ መልእክትም የሌላቸው ናቸው፡፡ ከሽሪላ ቭያሳዴቭ ጀምሮ በዲቁና ሥርዓት ከመጡት እና በዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ ከሚያምኑት ተከታዮች በስተቀር፣ ማንም ሰው ስለቬዳዎች የተለየ ትርጉም መስጠት አይገባውም። በኢሾፓኒሻድም እንደተገለጸው የሽሪላ ቭያሳዴቭ ተከታዮች ሁሉ፣ ዓብዩ ጌታ በሚከስታቸው የተለያዩ መንፈሳዊ ኃይላት፣ ትክክለኛ ግንዛቤን የያዙ ናቸው።

በብሀገቨድ ጊታ እንደተገለጸው (ብጊ 18፡54) አንድ ሰው ከቁሳዊ ዓለም አንደበት ነጻ ሲሆን፣ (ብራህማ ብሁታ) “ኡተማ አዲካሪ” እና ትሑት አገልጋይ ለመሆን ይችላል፡፡ በዚህም ጊዜ መላ ሕያው ፍጥረታትን ሁሉ፣ እንደ ወንድሙ እና እንደ እህቱ ለማየት ይበቃል፡፡ ነገር ግን ይህም ዓይነቱ ሕሊና፣ ለምሳሌ በፖሎቲከኞች ላይ ሊታይ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ብዙኋኑ ያላቸው ምኞት ለግል ጥቅም እና ዓለማዊ ሥልጣንን ለመያዝ ነው፡፡ እንዲህም ዓይነቱ ሰው “ኡተማ አዲካሪ” ነኝ ብሎ የሚያስመስል ከሆነ፤ ዝና ወይም ቁሳዊ ሀብትን ለማግኘት ተመኝቶ ይሆናል እንጂ የውስጣዊ ነፍሱን ለማገልገል ተመኝቶስ አይደለም፡፡ ይህም ዓይነቱ አስመሳይ፣ ስለ ውስጣዊ ነፍሱ እና ስለ መንፈሳዊው ዓለም ዕውቀትን የያዘ ሆኖ አይገኝም፡፡ ኡተማ አዲካሪ ግን፣ በውስጡ ያለውን ነፍስ በትክክል የተረዳ እና መንፈሳዊ አገልግሎትን የሚያቀርብም ነው፡፡ ይህንንም ዓይነት አእምሮ በመያዙ የዓለማዊ አደረጃጀቶች ሁሉ በቅልጥፍና ይሟሉለታል።

« Previous Next »