No edit permissions for Amharic

2

የመዘመር እና ክርሽናን የማወቅ መንገድ

ሀሬ ክርሽና ሀሬ ክርሽና ክርሽና ክርሽና ሀሬ ሀሬ ሀሬ ራማ ሀሬ ራማ ራማ ራማ ሀሬ ሀሬ፡፡ ይህ የቅዱስ ስም አቧራ የሸፈነው መስተዋት የመስለውን ዓለማዊ አንደበትና ሀሳባችንን ሊያፀዳልን የሚችል ማህሌት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዚህ የሀሳባችን መስታወት ላይ የዓለማዊ የምኞት አቧራ ተከማችቶ ይገኛል፡፡ ይህም በኒውዮርክ ውስጥ በቁጥር ሁለት መንገድ ላይ በተጓዙ ወቅት በብዛት ተከማችቶ እንደምናየው አቧራ ሊመሰል ይችላል፡፡ እኛም እንደዚሁ በዚህ ዓለም ላይ እየተጓጓዝን አዕምሮዋችንን እና ሀሳባችንን በብዙ የቁሳዊ ዓለም ባህርዮች በመሙላት ንጹህ የነበረውን የሀሳባችንን መስታወት በዚህ ዓለማዊ አቧራ ሞልተነው እንገኛለን፡፡ በዚህም ምክንያት ይህችን ዓለም በትክክለኛ እና በንጹህ አመለካከት ለማየት ሲያዳግተን እንገኛለን፡፡ ቢሆንም ግን ይህንን የቅዱስ ስም ማህሌት በመዘመር (የሀሬ ክርሽና መሀ ማንትራ) ይህን የተከማቸውን የዓለማዊ አንደበት አቧራ ልናፀዳው እንችላለን፡፡ ይህም ስርዓት የእራሳችንን ትክክለኛ ማንነት ለመገንዘብም እንድንችል የሚረዳን ነው፡፡ እንዲህ ብለንም ለመረዳት እንችላለን “እኔ ማለት እኮ በገላዬ ውስጥ የምገኝ ነፍስ እንጂ ቁሳዊው ገላዬ አይደለሁም፡፡ ይህን የማውቅበት መንገድም በገላዬ ውስጥ ከነፍሴ የመነጨ ሙሉ ንቃት በመኖሩ ነው፡፡” እንዲህም በመገንዘብ ውስጣዊ የሆነ ንጹህ ደስታችንን ለመመስረት እንችላለን፡፡ ይህንንም የሀሬ ክርሽና የቅዱስ ስም ማህሌት በተደጋጋሚ በመዘመር የዓለማዊ ጭንቀት እና ስቃዮቻችን ሁሉ ለማጥፋት እንችላለን፡፡ በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ብዙ የመከራ እና የስቃይ እሳቶች እየነደዱ ነው፡፡ መላው የምድር ህዝብም ይህንን እሳት ለማጥፋት በመሯሯጥ ላይ ይገኛል፡፡ ቢሆንም ግን የአንድ ሰው ሕይወቱ በንጹህ የመንፈሳዊ ንቃት ላይ የተመሰረተ ካልሆነ እነዚህ በዓለም ላይ ያሉት የጭንቀት እና የመከራ እሳቶች ሊጠፉ አይችሉም፡፡

ዓብዩ ሽሪ ክርሽና ወደ እዚህ ምድር ላይ የመጣበት ዋናው ዓላማ ይህንን የቁሳዊው ዓለምን የመከራ ስቃይ ለማጥፋት እና ድሀርማ ወይም የመንፈሳዊ አገልግሎት የመስጠት ስርዓትን ለማቋቋም ነው፡፡

ዳ ያዳ ሂ ድሀርማስያ
ግላኒር ብሀቨቲ ብሀረታ
አብህዩታናም አድሃርማስያ
ታዳትማናም ስርጃሚ አሀም

ፓሪትራናያ ሳድሁናም
ቪናሻያ ቻ ዱስክርታም
ድሀርማ ሳምስትሀ ፓናርትሀያ
ሳምብሀቫሚ ዩጌ ዩጌ

“የሀይማኖት እምነት እና ልምድ በወደቀ ጊዜ እና ከሀዲነት የተሞላበት ህብረተሰብ በተፈጠረ ቁጥር ኦ የብሀረት የልጅ ልጅ ሆይ፤ በዚያን ጊዜ እኔ ራሴ ወደ ምድር እወርዳለሁ፡፡ የምመጣበትም ምክንያት አማኝ መንፈሳውያንን ለመጠለል፣ ከሀድያንን ለማጥፋት እና የሀይማኖታዊ ስርዓቶችን እንደገና ለመመስረት (ድሀርማ) ከዘመን ዘመን እኔ ራሴ ወደ እዚህ ዓለም እመጣለሁ፡፡” (ብጊ፡ 4.7-8)

በዚህም ጥቅስ ላይ “ድሀርማ” የተባለው ቃል ተጠቅሷል። ይህም ቃል ወደ እንግሊዘኛ በተለያየ ትርጉም ተተርጉሞ እናገኘዋለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ “እምነት” ወይም “ሀይማኖት” ተብሎ ተተርጉሞ እናገኘዋለን፡፡ ነገርግን ከቬዲክ ስነጽሁፎች አንፃር ስናየው “ድሀርማ” ማለት እምነት ማለት አይደለም፡፡ እምነት ሊቀያየር ይችላል፡ ነገርግን “ድሀርማ” ሊቀየር የማይችል ነው፡፡ የውሀ ፈሳሽነት ሊቀየር የማይችል ነው፡፡ የውሀነት ባህሪውም ወደ በረዶነት ቢቀየር ውሀ መሆኑ ቀረ ማለት ነው፡፡
ውሀ እና የፈሳሽነት ባህርይ ሊነጣጠሉ አይችሉም፡፡ በረዶ ሲሆን ግን የውሀ መሰረታዊ ባህርዩን ቀይሮ ወደ ሌላ ደረጃ ተቀየረ ማለት ነው፡፡ የእኛም ድሀርማ ወይም መሰረታዊ ደረጃችን የዓብዩ የመላእክት ጌታ ቅንጣፊ አካል እና ወገን እንደመሆናችን ሁሉ የእኛ ድሀርማ ዓብዩ አምላክን ማገልገል ብቻ ነው፡፡ መንፈሳችንንም እርሱን ለማገልገል መግራት ይገባናል፡፡

ይህ ንጹህ ዓብዩ አምላክን የምናገለግልበት መንፈሳዊ አንደበታችን በዓለማዊ ኑሮ ውስጥ ገብቶ በስህተት ሌሎችን በማገልገል ተሰማርቶ ይገኛል፡፡ ማገልገል በመሰረታዊ ፍጥረታችን ውስጥ ያለ እና የማይለየን ነው፡፡ ሁላችንም አገልጋዮች እንጂ የበላይ ጌታ አይደለንም፡፡ እያንዳንዱ ሰው ሌላውን ሲያገለግል እናያለን፡፡ ምንም እንኳን የአገሩ ፕሬዝዳንት የሀገሪቱ መሪ ሆኖ ቢገኝም መንግስትን እና ህብረተሰቡን ለማገልገል የቆመ ነው፡፡ አገልግሎቱንም መስጠት ሲያበቃ ከስልጣን ይወርዳል፡፡ አንድ ሰው “እኔ የሁሉም የበላይ ጌታ ነኝ” ብሎ ማሰብ “ማያ” ወይም ስህተታዊ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዓይነቱ የቁሳዊ ዓለም አንደበት የተፈጥሮ መንፈሳዊ አገልግሎታችንን ዘንግተን እና ዓለማዊ ማዕረጋችንን ይዘን ዓብዩ አምላክን የማገልገል ባህርያችንን አዳክመን እንገኛለን፡፡ ከእነዚህም ዓለማዊ ማዕረጎች እና እራሳችንን እንደ ጌታ አድረገን ከማሰቡ ነፃ ስንሆን አቧራው እንደተወለወለ መስታወት ንፁህ አንደበት ይዘን እንገኛለን፡፡ የፍጥረታችንም መሰረታዊ ዓላማ ሽሪ ክርሽናን ለማገልገል ብቻ መሆኑንም በቀላሉ እንረዳለን፡፡

አንድ ሰው ሊገነዘበው የሚገባው ነገር ቢኖር በዚህ ዓለም ላይ የምንሰጠው አገልግሎት እና በመንፈሳዊ ኑሮ የምንሰጠው አገልግሎት የተለያዩ መሆናቸውን ነው፡፡ እንዲህም ልናስብ እንችል ይሆናል፡፡ “ከዚህ ዓለም ነፃ ከወጣን በኋላ እንደገና አገልጋዮች ሆነን እንፈጠር ይሆን?” ይህም ዓይነት አስተሳሰብ ሊኖረን የሚችለው በዚህ ዓለም ላይ አገልጋይ መሆን ደስታን የሚሰጥ ባለመሆኑ ነው፡፡ በመንፈሳዊ ዓለም ግን እንደዚህ ዓይነት ስሜት አይኖርም፡፡ በመንፈሳዊ ዓለም ላይ በአገልጋዩ እና በጌታ ብዙ የማእረግ ልዩነት የለም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ግልጽ የሆነ የማዕረግ ልዩነት አለ፡፡ ፍጹም በሆነው የመንፈሳዊው ዓለም ግን እንደዚህ ዓይነት ግልፅ የሆነ ልዩነት የለም፡፡ ለምሳሌ ከብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መጽሀፍ እንደምንረዳው ክርሽና የአርጁና የሰረገላው ነጂ ለመሆን መርጦ እናየዋለን፡፡ በመሰረታዊ ደረጃው ግን አርጁና የሽሪ ክርሽና አገልጋይ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ በጠባዩ እና በፍቃዱ ግን አንዳንድ ጊዜ ዓብዩ ጌታ የአገልጋዮቹ አገልጋይ ሆኖ ይታያል፡፡ ይህም የበታች ሊያደርገው አይችልም፡፡ (ቼቻ፡ ማድህያ 13 80)ስለዚህም አንዳንድ ጊዜ ይህን የዓለማዊ አስተሳሰባችንን ከመንፈሳዊ መሰረታዊ ትርጉሞች ጋር ቀላቅለን ከማየት መቆጠብ ይኖርብናል፡፡ በዓለማዊ መንገድ የምናያቸውም ነገሮች ሁሉ ከመንፈሳዊው ዓለም የተገላቢጦሽ ናቸው፡፡

ይህም “ድሀርማ” ወይም አምላክን የማገልገሉ መንፈስ በዓለማዊ አስተሳሰብ ተበክሎ በተገኘ ቁጥር ዓብዩ ጌታ እራሱ ወደ እዚህ ዓለም ይመጣል ወይም ትሁት አገልጋዮቹን ወደዚህ ዓለም ለማስተማር ይልካል፡፡ ለምሳሌ ጌታ እየሱስ ክርስቶስ “የዓብዩ ፈጣሪ አምላክ ልጅ” እንደሆነ ገልጾልናል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በዓብዩ የመላእክት ጌታ የምድር ተወካይ ሆኖ ማስተማሩንም እንረዳለን፡፡ በሌላ ምሳሌ ነብዩ መሀመድ የዓብዩ ጌታ “አላህ” አገልጋይ መሆኑን ገልጾልናል፡፡ በምድር ላይ የመንፈሳዊ ደረጃችን በተቃወሰ ቁጥር ዓብዩ ጌታ ከግዜ ግዜ እራሱ ይመጣል ወይንም ደግሞ ተወካዮቹን በመላክ የመንፈሳዊ ትምህርታችንን እንድንማር ያመቻችልናል፡፡

ስለዚህም “ድሀርማ” አንድ የተፈጠረ የሀይምኖት እምነት ነው ብለን መሳሳት አይኖርብንም፡፡ በትክክለኛ መንገድ ስናየው “ድሀርማ” በፍፁም ከነፍሳት ተነጥሎ ሊኖር የሚችል ነገር አይደለም፡፡ ልክ ጣፋጭነት ከስኳር እንደማይለይ ሁሉ፤ ጨውነትም ከጨው እንደማይለይ ሁሉ፤ ጥንርካሬም ከድንጋይ እንደማይለይ ሁሉ፤ ዓብዩ አምላክን የማገልገል የነፍስ ባህርይ (ድሀርማ)ከነፍስ ተነጥሎ ሊኖር የሚችል አይደለም፡፡ በምንም ደረጃ ነፍሳችን ከዚህ ባህርይ ተለይታ ልትኖር አትችልም፡፡ የነፍሳት ድሀርማ ዓብዩ ጌታን ማገልገል ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ እያንዳንዳንችን ይህ የማገልገል ባህርይ እንደአለን በቀላሉ ለማየት እንችላለን፡፡ ይህም ወይ እራሳችንን ወይም ሌሎችን በማገለገል ነው፡፡ የብሀገቨድ ጊታ የቅዱስ መጽሀፍም የሚያስተምረን እንዴት ክርሽናን ለማገልገል እንደምንችል፤ እንዴት ከዚህ ዓለማዊ አገልግሎት እንደምንላቀቅ፤ እንዴት የክርሽናን ንቃትን እንደምናዳብር እና እንዴት ከዚህ ከቁሳዊ አካላችን አስተሳሰብ እንደምንርቅ ነው፡፡

ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው “ፓሪትራናያ ሳድሁናም” (ብጊ፡ 4.8) ከሚለው ጥቅስ “ሳድሁ” የሚለው ቃል ሲተረጐም፤ ባህታዊ ወይም መንፈሳዊ ሰው ማለት ነው፡፡ ባህታዊ ሰው ማለት በጣም ትእግስት ያለው፣ ለሁሉም ሩህሩህ የሆነ፣ ለሁሉም ጓደኛ እና ለማንም ጠላት ያልሆነ እንዲሁም በማናቸውም ጊዜ ሰላምተኛ የሆነ ሰው ማለት ነው፡፡ አንድ መንፈሳዊ ሰው 26 ዓይነት ባህርዮች እንደአሉት በቬዲክ ስነጽሁፎች ተገልጿል፡፡ በብሀገቨድ ጊታም ሽሪ ክርሽና ስለነዚህ ብህርዮች ግምገማ ሲሰጥ እናያለን፡፡

አፒ ቼት ሱዱራቻሮ
ብሀጃቴ ማም አናንያ ብሀክ
ሳዱር ኤቫ ሳ ማንታቭያህ
ሳምያግ ቭያቫሲቶ ሂሳሀ

“አንድ ሰው ምንም እንኳን በጣም የሚያስኮንን ኃጥያት ፈጽሞ ቢሆንም በልቦናው ዓብዩ ጌታን የማገልገል ባህርይ ካለው መንፈሳዊ ተብሎ ሊታይ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በትክክለኛ አንደበት እና ስርዓት ላይ ስለሚገኝ ነው፡፡” (ብጊ፡ 9.30)

በተራ የዓለማዊ ዓይን ስናየው የአንድ ሰው ጥሩ ግብረ ገባዊ አንደበት ለሌላው ጥሩ ሆኖ ላይታየው ይችላል፡፡ የአንድ ሰው ጥሩ ግብረ ገባዊ ያለሆነ መጥፎ አንደበት ለሌላው ጥሩ መስሎ ሊታየው ይችል ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በሂንዱ ባህል ወይን ጠጅ መጠጣት ግብረ ገባዊ ጥሩ ምግባር ሆኖ አይታይም፡፡ ነገር ግን በምእራባውያን አገሮች ይህ ወይን ጠጅ መጠጣት በባህሉ ውስጥ የተለመደ እና ተቀባይነት ያለው ነገር ነው፡፡ ስለዚህ የግብረ ገብ ባህሪ ጊዜ ቦታ አካባቢው እና የህብረተሰቡ አስተሳሰብ ሊወስነው ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን በእያንዳንዱ ህብረተሰብ ይህ የጥሩ ወይም የመጥፎ የግብረገብ ባህሪ ሁሌ ይገኛል፡፡ በዚህም ጥቅስ ዓብዩ ሽሪ ክርሽና የሚገልፀው ምንም እንኳን አንድ ሰው ከዚህ ቀደም በመጥፎ ግብረ ገብ ባህርይ ተሰማርቶ ቢገኝም አንደበቱን ለውጦ ለክርሽና ንቃት ከበቃ የቀድሞ ባህሪው ላይ ትኩረት ሊሰጥ አይገባም፡፡ ይህ ሰው ከምንም ዓይነት ዓለማዊ ህይወት እንኳን ቢመጣም አንደበቱን ወደ ክርሽና ንቃት ከመለሰ ቀስ በቀስ ልቦናው እየፀዳ በመሄዱ መጥፎ የነበረው ባህሪው ሁሉ እየጠፋ ቀስ በቀስም ወደ መንፈሳዊ ወይም ባህታዊነት ለመድረስ ይችላል፡፡

ለምሳሌ እንዲሆን አንድ ወደ ቅዱስ የሆነ ከተማ የሄደ የሌባን ታሪክ እንመልከት፡፡ ይህ ሌባ ወደ እዚህ ቅዱስ ከተማ ለመሄድ ጉዞ ላይ እያለ እርሱ እና ሌሎች ተጓዥ ምእመናን በአንድ ሆቴል ለማደር ወሰኑ፡፡የመስረቅ ጠባይም ያለው ይኀው ሌባ ምሽት ላይ የሌሎቹን ምእምናን ቦርሳዎች እየከፈተ እንዴት ለመስረቅ እንደሚችል ዝግጅት ማድረግ ጀመረ፡፡ ነገር ግን በሀሳቡ “እኔ ለመንፈሳዊ ዓላማ መጥቼ እንዴት ወደ መስረቅ እሰማራለሁ” ብሎ ማሰብ ጀመረ፡፡ “ማድረግ አይገባኝም” ብሎም ወሰነ፡፡ ነገር ግን በዚህ በመስረቅ ልማዱ እጁን ከመስረቅ ለመሰብሰብ አቃተው፡፡ ስለዚህ አንዱን ቦርሳ አንስቶ ወደ ሌላ ሰው ወገን አስቀመጠው፡፡ ሌላውንም ቦርሳ እንዲሁ አንስቶ ወደ ሌላ ወገን አስቀመጠው፡፡ ነገር ግን የመስረቅ ጥፋት ውስጥ ለመግባት ስሜቱ ስለተሸበረ ምንም ነገር ለመስረቅ አልቻለም፡፡ ጥዋትም ሲነጋ እና መንገደኞቹ ተነስተው ቦርሳቸውን ሲፈልጉ ያስቀመጡትን ለማግኘት አልቻሉም፡፡ በዚህም ምክንያት ብጥብጥ ተነሳ እና ወደ መጨረሻም ሁሉም ቦርሳቸውን ለማግኘት በቁ። ቦርሳቸውን ካገኙም በኋላ ሌባው ተነሳ እና ሁኔታውን መግለፅ ጀመረ፡፡ “ክቡራን ሆይ እኔ ያለኝ ሙያ የሌብነት ሙያ ብቻ ነው፡፡ ሌሊት የመስረቅም ከፍተኛ ልምድ ስላለኝ ከሁላችሁም ቦርሳ ለመስረቅ አስቤ ነበር፡፡ ነገር ግን የመጣሁበት ዓላማ ወደ ቅዱስ ስፍራ ለመሄድ በመሆኑ መስረቅ አይገባኝም ብዬ ወስንሁ፡፡ በዚህም ባለኝ ልምድ ምክንያት ቦርሳችሁን በማንሳት የተዘበራረቀ ቦታ ለማስቀመጥ ተገድጃለሁ፡፡ ስለዚህም ይቅርታችሁን በትህትና እጠይቃለሁ፡፡” ይህም የሚያሳየን የመጥፎ ልማድ በቀላሉ እንደማይለቀን ነው፡፡ ለመስረቅ ምንም ዓላማ አልነበረውም ነገር ግን ልምዱ ስለአለበት እጁን ለማሳረፍ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ክርሽና እንዲህ ይለናል፡፡ “አንድ ሰው ከመጥፎ ልማዱ ለመወገድ ውሳኔ ካደረገ እና በክርሽና ንቃቱ መዳበር ከጀመረ እንደ ሳድሁ ወይም እንደ መንፈሳዊ ሆኖ ይቆጠራል፡፡ ይህም ምንም እንኳን በቀድሞ ልማዱ ወይም በድንገት ወደ ስህተቱ ቢመለስም ነው፡፡ በሚቀጥለውም ጥቅስ ክርሽና እንዲህ ብሎ ገልጾልናል፡፡

ሺፕራም ብሀቨቲ ድሃርማትማ
ሻሽቫክ ቻንቲም ኒጋቻቲ
ኮንቴያ ፕራቲጃኒሂ
ናሜ ብሀክታ ፕራናሽያቲ

“እርሱም በቶሎ ትክክለኛ ይሆንና የዘለቀ ሰላምን ያገኛል፡፡ ኦ የኩንቲ ልጅ ሆይ የእኔ አገልጋይ የሆነ በፍጹም ሊወድቅ እና ሊጠፋ እንደማይችል ለህዝብ በይፋ ተናገር፡፡” (ብጊ፡ 9.31)

በዚህ ጥቅስ ላይ በሽሪ ክርሽና እንደተጠቀሰው ሁሉ አንድ ሰው የክርሽናን ንቃት ለማዳበር ውሳኔ ሲያደርግ በአጭር ጊዜ ውስጥ መንፈሳዊ ሰው ለመሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የኤሌክትሪክ ማራገቢያውን የመብራት ሀይል ሊያጠፋው ይችላል፡፡ ምንም እንኳን የመብራት ሀይሉ ቢጠፋም ግን ማራገቢያው ለጥቂት ጊዜ መሽከርከሩን አያቆምም፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ከመሽከርከር መቆሙ የተረጋገጠ ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ አንድ ጊዜ ልቦናችንን ወደ ዓብዩ ሽሪ ክርሽና እና የሎተስ እፅዋት ወደ መሰለው እግሩ ከመለስን የዓለማዊ አዝማሚያችን ሁሉ እየቀነሰ ይመጣል፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ ዓለማዊ ባህርዮች ለጥቂት ጊዜ ቢቀጥሉም ከጊዜ በኋላ ግን እንደሚጠፉ ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህም የምንረዳው አንድ ሰው የሽሪ ክርሽናን ንቃት መከታተል ሲጀምር ጥሩ ሰው ለመሆን በተለየ መንገድ ጥረት ማድረግ አያስፈልገውም፡፡ ጥሩ የሚባሉ ባህሪዮች ሁሉ ወዲያውኑ ይመሰረታሉና ነው፡፡ በሽሪማድ ብሀገቨታም ቅዱስ መጽሀፍም እንደተጠቀሰው አንድ የክርሽና ንቃተ ባህርይ ያለው ሰው ጥሩ የሚባሉት ባህርያት ሁሉ የሚከሰቱበት ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው የዓብዩ የመላእክት ጌታ መንፈስ የራቀው ሆኖ ምንም እንኳን ጥሩ የሚባሉ ነገሮች ቢያደርግም እነዚህ ድርጊቶች ጥሩነቱን ለማጎልበት ሀይል አይኖራቸውም፡፡ ምክንያቱን እነዚህ የተወሰኑ ባህሪያት ብቻ ከሌላ ከማያስደስቱ ዓላማዊ ነገሮች ሁሉ ሊቆጥቡት ስለማይችሉ ነው፡፡ አንድ ሰው የሽሪ ክርሽናን ንቃት ለማዳበር ካልበቃ በዚህ ቁሳዊ አለም ውስጥ ጥፋቶችን እንደሚያደርግ የተረጋገጠ ነው፡፡

ጃንማ ካርማ ቻሜ ድቭያም
ኤቫም ዮቬቲ ታትቫታሀ
ትያክትቫ ዴሀም ፑናር ጃንማ
ናይቲ ማም ኢቲ ሶርጁና

“በዚህ ዓለም ላይ የእኔን መንፈሳዊ አመጣጥ እና ስራዎቼን ሁሉ በትክክሉ የሚረዳ ሰው ይህን ቁሳዊ ገላውን በሞት ሲለይ ወደ እዚህ ቁሳዊ ዓለም እንደገና ለመወለድ አይመጣም፡፡ ኦ አርጁና ሆይ የሚሄደውም ወደ እኔ የዘለዓለማዊው መንግስተ ሰማያት ነው፡፡” (ብጊ 4.9 )

ሽሪ ክርሽና ወደ እዚህ ቁሳዊ ዓለም የሚመጣበትም ምክንያት በዚሁ ምዕራፍ በትንተና ተገልጿል፡፡ ለተወሰነ ዓላማም ወደ እዚህ ዓለም ሲመጣ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ይኖራሉ፡፡ በእርግጥ ዓብዩ ጌታ ወደ ምድር እንደ ሰው ሆኖ ሊመጣ አይችልም ብለው የሚያምኑ አንዳንድ ፈላስፋዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እንዲህም ይላሉ “ለምን ዓብዩ ጌታ ወደ እዚህ ወደ ቆሻሻ ዓለም ይመጣል?” ነገር ግን በብሀገቨድ ጊታ ጥቅሶች በግልፅ የተፃፈውን አንብበን ልንረዳ እንችላለን፡፡ ይህን ለመረዳትም የብሀገቨድ ጊታን ትምህርት እንደ ቅዱስ መፅሀፍነቱ እንደተገለፀው መቀበል ይገባናል፡፡ አለበለዛ ማንበቡ ብቻ ጥቅም አይኖረውም፡፡ በብሀገቨድ ጊታ ሽሪ ክርሽና እንደገለፀው በዚህ ምድር ላይ ሽሪ ክርሽና እንደ ሰው ሆኖ በመምጣት ዓላማውን ለሟሟላት እንቅስቃሴዎችን እንደሚያደርግ ገልፆልናል፡፡ ለምሳሌ ለአርጁና የሰረገላ ነጂ ለመሆን መርጦ በኩሩክሼትራ የጦር ሜዳ ላይ ብዙ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል፡፡ በጦርነትም ጊዜ አንድ ሰው ወይም ህብረተሰቡ ወደ አንድ ሰው ወይም ወደ አንድ ህብረተሰብ የማድላት አዝማሚያውን ሊያሳይ ይችላል፡፡ ዓብዩ ጌታ ክርሽናም በኩሩክሼትራ ጦርነት ጊዜ ወደ አርጁና ወገን እንደሚያደላ አንደበቱን ግልፅ አድርጎ ነበር፡፡ ሽሪ ክርሽና በተፈጥሮው በነፍሳቶች መሀከል የሚያዳላ አይደለም፡፡ ነገር ግን በውጪ ስናየው በጦርነቱ ላይ አዳልቶ የቀረበ ይመስለናል፡፡ ይህም የሽሪ ክርሽና የማዳላት አዝማሚያ እንደ ተራ ሆኖ መታየት አይገባውም፡፡

በዚህም ጥቅስ ላይ ሽሪ ክርሽና እንደገለፀው እርሱ ወደዚህ ዓለም የመጣበት ምክንያት ለመንፈሳዊ ተግባር ነበር፡፡ ይህ ዲቭያም የተባለው ቃል መንፈሳዊ ማለት ነው፡፡ በምድር ላይ የነበሩት የሽሪ ክርሽና እንቅስቃሴዎች ሁሉ ተራ እንቅስቃሴዎች አልነበሩም፡፡ በህንድ አገር ውስጥ በነሐሴ ወር ውስጥ ምንም የዘር ልዩነት ሳይኖር መላ ህብረተሰቡ የክርሽናን ልደት ያከብራሉ፡፡ ይህም ልክ በምእራባውያን አገር እንደምናየው የገና በዓል ሆኖ ሊመሰል ይችላል፡፡ የክርሽና የልደት ቀን “ጃንማስተሚ” ተብሎ ይታወቃል፡፡ በዚህም ጥቅስ ላይ ክርሽና “ጃንማ” የሚለውን ቃል ሲጠቀምበት እናያለን፡፡ ይህም ማለቱ “የእኔ ልደት” ማለቱ ነው፡፡ ልደትም ስለነበረ እንቅስቃሴዎችም ነበሩ፡፡ የክርሽና ልደት እና እንቅስቃሴዎች ሁሉ መንፈሳዊ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ልደቱ እና እንቅስቃሴዎቹ ሁሉ እንደ ተራ ሆነው ሊታዩ አይገባቸውም፡፡ አንድ ሰው የሽሪ ክርሽና እንቅስቃሴዎች እንዴት መንፈሳዊ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ “ሽሪ ክርሽና እንደ ሰው ተወልዷል፣ ከአርጁና ጋርም በጦርነት ተሰማርቷል፣ ቫሱዴቭ የሚባል አባት እና ዴቫኪ የተባለች እናት አለችው፡፡ ታድያ መንፈሳዊነቱ ምን ላይ ነው?” ብሎ አንድ ሰው ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ክርሽና ደግሞ በብሀገቨድ ጊታ “ኤቫም ዮ ቬቲ ታትቫታሀ” ብሎ ተናግሯል፡፡ ይህም የትውልዱን እና የሚያደርገውን እንቅስቃሴዎች ሁሉ ከተራ እንቅስቃሴዎች ለይተን በእውነቱ ማወቅ ይገባናል፡፡ አንድ ሰው ይህንን ትውልዱን እና እንቅስቃሴውን በእውነቱ ለመረዳት ብቁ ከሆነ ውጤቱ ምን እንደሆነ በብሀገቨድ ጊታ ተገልጿል፡፡ “ትታክትቫ ዴሀም ፑናር ጃንማ ናዪቲ ማም ኢቲ ሶ አርጁና” (ብጊ፡ 4.9) ይህም ሰው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ ወደ እዚህ የመከራ ቁሳዊ ዓለም ተመልሶ ለትውልድ አይመጣም፡፡ የሚሄደውም በቀጥታ ወደ ሽሪ ክርሽና ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ነፍሱ ከዚህ ቁሳዊ ዓለም ኑሮ ነፃ ወጣች ማለት ነው፡፡ የሚሄደውም ወደ ዘለዓለማዊው ወደ መንፈሳዊ ዓለም ሲሆን የመንፈሳዊ ተፈጥሮውንም በመያዝ የደስታ፣ የሙሉ እውቀትና የዘለዓለማዊውን ኑሮ ይጀምራል፡፡ ይህንን ሁሉ ለማግኘት የሚቻለው የክርሽናን ትውልድ እና እንቅስቃሴዎች መንፈሳዊ እንደመሆናቸው በእውነቱ በመገንዘብ ነው፡፡

በተፈጥሮ እንደሚታየው አንድ ሰው በሞት ገላውን ለቅቆ ሲሄድ ሌላ ገላ በመያዝ እንደገና መወለዱ የማይቀር ነው፡፡ የሁሉም ነፍሳት ሕይወት ሲቀጥል የምናየው ገላቸውን ከአንድ ዓይነት ገላ ወደ ሌላው ዓይነት ገላ በመቀያየር ነው፡፡ ይህም የነፍስ ከዚህ ዓለም ኮብልሎ መሄድ እና እንደገና መወለድ ማለት ነው፡፡ ይህንንም ትውልድ የሚወስነው በዓለም ላይ የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ የያዝነውን ቁሳዊ ገላ እንደ ራሳችን አድረገን ስንቆጥረው እንገኛለን፡፡ ነገር ግን ይህ ገላችን የሚመሰለው እንደ ልብሳችን ነው፡፡ ከቬዲክ ስነፅሁፎች እንደምንማረው የራሳችን የሆነ ዘለዓለማዊ ገላ አለን፡፡ ይህም ገላ መንፈሳዊ ገላችን ነው፡፡ ይህ ቁሳዊ ገላ ከዘለዓለማዊው መንፈሳዊ ገላችን ጋር ሲወዳደር በሀሰት እውነትን እንደሚያስመስል የስንዴ ሽፋን ገለባ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህም ገላችን ሲያረጅ እና ሲጐሳቆል ወይም በአደጋ ምክንያት ከጥቅም ውጪ ሁኖ ሲገኝ ልክ እንደ ቆሸሸ ወይም እንደ ተበላሸ ክዳናችን ወደ ጐን አስቀምጠነው ሌላ አዲስ ገላ ለመያዝ እንበቃለን፡፡

ቫሳምሲ ጂርናኒ ያትሀ ቪሀያ
ናቫኒ ግርህናቲ ናሮ ፓራኒ
ታትሀ ሻሪራኒ ቪሀያ ጂርናኒ
አንያኒ ሳምያቲ ናቫኒ ዴሂ

“አንድ ሰው ያረጀውን ክዳን አውልቆ አዲስ ክዳን እንደሚለብስ ሁሉ ነፍሳችንም ያረጀውን እና ከጥቅም ውጪ የሆነውን ቁሳዊ ገላችንን እርግፍ አድርጋ ትታ አዲስ ገላ ለመያዝ ትበቃለች፡፡” (ብጊ፡ 2.22)

በመጀመሪያም በፅንስ ጊዜ ገላችን ከአተር ፍሬ ያነሰ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዚህም በላይ በማደግ ሕፃን ልጅ ለመሆን ይበቃል፡፡ ከዚያም ትንሽ ልጅ፣ ወጣት ልጅ፣ አዋቂ ሰው እና ያረጀ ሰው በመሆን ሲተላለፍ ቆይቶ ገላው ከጥቅም ውጪ ሲሆን ደግሞ ነፍስ ገላዋን ቀይራ ሌላ ገላ በመያዝ እንደገና ትወለዳለች፡፡ በዚህም መንገድ ገላ ሁልጊዜ ይቀያየራል ማለት ነው፡፡ ሞት ማለት ደግሞ የመጨረሻው ደረጃ እና የገላ መቀየር ማለት ነው፡፡

ዴሂኖ ስሚን ያትሀ ዴሄ
ኮማራም ዮቫናም ጃራ
ታትሀ ዴሀንታራ ፕራፕቲር
ድሂራስ ታትራ ና ሙህያቲ

“በዚህ በቁሳዊ ገላችን ውስጥ የምትገኘው ነፍሳችን ከልጅነት ወደ ወጣትነት እና ወደ እርጅና ስትተላለፍ እንደምተገኝ ሁሉ ይህችው ነፍስ በሞት ጊዜ ወደ አዲስ ገላ ለመተላለፍ ትበቃለች፡፡ የእርሱን ማንነትም በእውነት የተረዳ ሰው በዚህ የሞት ለውጥ ፈጽሞ አይደናገርም ወይም አይረበሽም፡፡” (ብጊ፡ 2.13)

ምንም እንኳን ይህ ቁሳዊ ገላችን ሁልጊዜ በመቀያየር ላይ ቢገኝም በውስጥ የምትገኘው ነፍሳችን ፈጽሞ አትቀያየርም፡፡
ልጅ ወደ አዋቂነት እድገት ቢያሳይም በቁሳዊው አካል ገላ ውስጥ የምትገኘው ነፍስ ግን ምንም ሳትቀየር ትገኛለች፡፡ አዋቂነትም ደረጃ ላይ ስንደርስ በልጅነት የነበረችን ነፍስ ለቅቃ ሂዳለች ማለት አይደለም፡፡ የሜዲካል ሳይንስ እንደሚያስረዳን የቁሳዊ አካላችን በየጊዜው በመቀያየር ላይ እንደሚገኝ አረጋግጧል፡፡ በዚህም የገላ መለዋወጥ ነፍሳት ግር እንደማይላቸው ሁሉ ነፍስ ገላን ለቅቃ የሞት ደረጃ ላይ ስትደርስም በመንፈሳዊ እውቀት የዳበረ ሰው ሊደናገር አይችልም፡፡ የዚህን ለውጥ በእውነቱ ለመረዳት ያልቻለ ሰው ግን በሞት ጊዜ በጣም ጥልቅ ሀዘን ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ በቁሳዊ ዓለም ውስጥ በመኖር ላይ እያለን ገላችንን ሁልጊዜ በመቀያየር ላይ እንገኛለን፡፡ ዋናው በሽታችንም ይህ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህም ማለት ሁልጊዜ የሰው ልጅ ቁሳዊ ገላ ይኖረናል ማለት አይደለም፡፡ ወደ እንስሳ ገላ ወይም ወደ መላእክት ገላም ለመቀየር እንችል ይሆናል፡፡ ይህንን የሚወስነው ግን በምድር ላይ የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ በፓድማ ፑራናም ይህ በትንተና ተገልጿል፡፡ ሽሪ ክርሽና ቃል እንደገባውም አንድ ሰው የክርሽናን መወለድ እና እንቅስቃሴዎችን በእውነቱ የተረዳ ከሆነ ከዚህ ከተደጋጋሚ ትውልድ እና ሞት ነፃ ይወጣል፡፡

ይህንንስ የክርሽናን ትውልድ እና እንቅስቃሴ እንዴት በእውነቱ መረዳት እንችላለን? ይህም በብሀገቨድ ጊታ በአስራ ስምንተኛው ምዕራፍ ተገልጿል፡፡

ብሀክትያማም አብሂጃናቲ
ያቫን ያሽ ቻስሚ ታትቫታሀ
ታቶ ማም ታትቫቶ ግያትቫ
ቪሻቴ ታድ አናንታራም

“ዓብዩ የመንግስተ ሰማያትን ጌታ ለመረዳት የምንችለው በሙሉ ትሁት ልቦና በምናቀርበው አገልግሎት ነው፡፡ በዚህም ትሁት ልቦና በተመሰጠ አገልግሎት አንድ ሰው ወደ ዓብዩ አምላክ ቤተ መንግስት ሊገባ ይችላል፡፡” (ብጊ፡ 18.55)

በዚህም ጥቅስ ውስጥ፡ “ታትቫ” ወይም “በእውነት” ተብሎ የሚተረጐመው ቃል ተጨምሮ እናየዋለን፡፡ አንድ ሰው በእውነትም የክርሽናን ሳይንስ ሊረዳ የሚችለው ትሁት አገልጋይ በመሆን ነው፡፡ አንድ ሰው ትሁት አገልጋይ ካልሆነ እና የክርሽናን ንቃት ለማዳበር ጥረት የማያደርግ ከሆነ ክርሽናን በእውነቱ ለመረዳት ያዳግተዋል፡፡ በአራተኛው ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ በሚገኙትም ጥቅሶች ላይ ክርሽና ለአርጁና እንዲህ ብሎ ይነግረዋል፡፡ (ብጊ፡ 4.3) “ይህንን የጥንት የዮጋ ሳይንስ የማስተምርህ አንተ ትሁት አገልጋዬ እና ጓደኛዬ በመሆንህ ነው፡፡” አንድ ሰው እንደ ሥነፅሁፍ ባለሞያ ብሀገቨድ ጊታን አንብቦ ለመረዳት ቢሞክር የብሀገቨድ ጊታ ሳይንስ ሚስጥር ሆኖ ያገኘዋል፡፡ ብሀገቨድ ጊታ ከመጽሀፍ ቤት ተገዝቶ እና እንደ ምሁርነት ተነቦ ሊረዱት የሚችሉት መፅሀፍ አይደለም፡፡ አርጁና ትልቅ ምሁር፣ ቬዳንቲስት፣ ፈላስፋ፣ ብራህማና ወይም መነኩሴ አልነበረም፡፡ አርጁና ባለትዳር እና ተዋጊ ወታደር ነበር፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ደረጃ ላይ ቢገኝም ክርሽና እርሱን መርጦ ብሀገቨድ ጊታን የመሰለ ትምህርት በማስተማር ለዚህ እውቀት እና የድቁና ስርአት የመጀመሪያው ባለስልጣን እንዲሆን አደረገው፡፡ ለምን? “ምክንያቱም አንተ የእኔ ትሁት አገልጋይ እና ትሁት ጓደኛዬ በመሆንህ ነው” ብሀገቨድ ጊታንም ለመረዳት እና ሽሪ ክርሽናን በእውነት ለመረዳት የሚያበቃን ስልት ይኅው ብቻ ነው፡፡ ይህም የክርሽናን ንቃት በማዳበር ይመሰረታል፡፡

የክርሽና ንቃትስ ምንድን ነው? ይህም በህልውናችን መስታወት ውስጥ የሚገኘውን ዓለማዊ አቧራ የክርሽናን ቅዱስ ስም በመዘመር ማፅዳት ማለት ነው፡፡ “ሀሬ ክርሽና ሀሬ ክርሽና ክርሽና ክርሽና ሀሬ ሀሬ ሀሬ ራማ ሀሬ ራማ ራማ ራማ ሀሬ ሀሬ” ይህንንም ማንትራ ወይም ቅዱስ ስም በመዘመር እና ብሀገቨድ ጊታን አንብቦ በመረዳት የክርሽና ንቃታችንን ለማዳበር እንችላለን፡፡ ኢሽቫራ ሳርቫ ብሁታናም (ብጊ፡ 18 61)ክርሽና በልባችን ውስጥ ሁልጊዜ አለ፡፡ ነፍሳችን እና የዓብዩ ጌታ ነፍስ እንደ ዛፍ በሚታየው ገላችን ውስጥ ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ ነፍስ ወይም “ጂቫ” በዚህ ዛፍ ውስጥ የሚገኘውን ፍራፍሬ ስተበላ ትገኛለች፡፡ የዓብዩ ጌታ ነፍስ ደግሞ “ፓራማትማ” የነፍስን እንቅስቃሴ በመታዘብ ላይ ይገኛል፡፡ ነፍስም የክርሽናን ንቃት በማዳበር እና የትሁት ልቦናዊ መንፈሳዊ አገልግሎትም መስጠት ስትጀምር በልባችን ውስጥ የሚገኘው ዓብዩ አምላክ በሀሳባችን ውስጥ የሚገኘውን ዓለማዊ አቧራ እና ቆሻሻ ሊያፀዳልን ይችላል፡፡ ክርሽና ለሁሉ መንፈሳውያን ጓደኛ ነው፡፡ የክርሽናን ንቃትም ለማዳበር የምናደረገው ጥረት መንፈሳዊ ነው፡፡ “ሽራቨናም ኪርታናም” (ሽብ፡ 7.5.23)በመዘመር እና በማዳመጥ አንድ ሰው የክርሽናን ሳይንስ ለመረዳት እና ክርሽናን በእውነት ለማወቅ ይችላል፡፡ ክርሽናንም በእውነቱ ተረድቶ አንድ ሰው ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ ወደ መንፈሳዊው ወደ ክርሽና ቤተ መንግስት ለመጓዝ ይችላል፡፡ ይህም የመንፈሳዊው ዓለም በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ተገልጿል፡፡

ናታድ ብሀሳያቴ ሱርዮ
ና ሻሻንኮ ና ፓቫካሀ
ያድ ጋትቫ ና ኒቫርታንቴ
ታድ ድሀማ ፓራማም ማማ

”ይህም የእኔ መኖርያ በፀሀይ በጨረቃ ወይም በኤሌክትሪክ ብርሀን ቦግ ብሎ የሚገኝ አይደለም፡፡ ወደ እዚህም መኖርያዬ የሚደርስ ሁሉ ተመልሶ ወደ እዚህ የመከራ ቁሳዊ ዓለም ፈፅሞ አይመጣም፡፡” (ብጊ፡ 15.6)

ከጨለማው ዓለም ወጥተን ወደ ዘለዓላማዊው እና ቦግ ብሎ ወደሚገኘው መንፈሳዊ ዓለም እንድንመለስ ነው፡፡ ይህም የጨለማ ቃል ሁለት ዓይነት ትርጉም ይዞ ይገኛል፡፡ ብርሀን የጐደለበት ብቻ ማለት ሳይሆንም ድንቁርና የሚል ትርጉምም ይዞ ይገኛል፡፡

ዓብዩ አምላክ የተለያዩ ሀይሎችን ይዞ ይገኛል፡፡ ወደዚህም ቁሳዊ ዓለም የመምጣት ግዳጅ የለውም፡፡ በቬዳም ውስጥ እንደተገለፀው ዓብዩ ጌታ የስራ ግዳጅ የለውም፡፡ በብሀገቨድ ጊታም ሽሪ ክርሽና እንዲህ ብሎ ገልጾልናል፡፡

ናሜ ፓርታስትሂ ካርታቭያም
ትሪሹ ሎኬሹ ኪንችና
ናናቫፕታም አቫፕታቭያም
ቫርታ ኤቫ ቻ ካርማኒ

“ኦ የፓርትሀ ልጅ ሆይ በእነዚህ በሶስቱ ዓይነት የፕላኔቶች ዓለም ውስጥ ለእኔ ምንም ዓይነት የተመደበ ስራ የለም፡፡ ወይም እኔ የሚያስፈልገኝ ነገር ወይም ለማግኘት የምፈልገው ነገር የለም፡፡ ቢሆንም ግን በዚህ ዓለም ላይ እየመጣሁ በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡” (ብጊ፡ 3.22)

ስለዚህ ሽሪ ክርሽና ወደእዚህ ዓለም የመምጣት እና እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ ይገባዋል ብለን ማሰብ አይገባንም፡፡ ማንም ሰው ከሽሪ ክርሽና ጋር እኩል ወይም የላቀ ሊሆን አይችልም፡፡ ሽሪ ክርሽና በተፈጥሮው ሙሉ የሆነ እውቀት አለው፡፡ እውቀትንም ለማግኘት እንደእኛ ጥረት ማድረግ አያስፈልገውም፡፡ በማናቸውም ጊዜ ሙሉ እውቀት ይዞ የሚገኝ ነው፡፡ ብሀገቨድ ጊታንም ለአርጁና ለማስተማር በቅቷል፡፡ ቢሆንም ግን ክርሽና ከማንም መምህር ብሀገቨድ ጊታን አልተማረም፡፡ የዚህንም የክርሽናን ፍጥረት በእውነቱ እና በትክክል የተረዳ ሰው እዚህ ዓለም ወደሚገኘው የመወለድ እና የመሞት ፔዳል ውስጥ ተመልሶ አይመጣም፡፡ በዓለማዊ እና ሀሰታዊ አስተሳሰብ ውስጥ ሆነን በዚህ ዓለም ላይ የተለያዩ የሚመቹ ነገሮችን ለመፍጠር በመሞከር ሕይወታችንን እናባክናለን፡፡ ነገር ግን ይህ የሰው ልጅ ሕይወት ዓላማ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ሕይወት ዓላማ የክርሽናን ሳይንስ ለመረዳት መቻልን ነው፡፡

በዚህ ቁሳዊ ዓለም የሚገኙት ምኞታችን የሚከተሉትን ለሟሟላት ነው፡፡ የመመገብ ችግራችንን ለመወጣት፣ የወሲብ እርካታ፣ የመተኛትን ምኞት፣ እራሳችንን የመከላከል እና የስሜታዊ ደስታችንን ለማርካት መጣር ነው፡፡ እነዚህ ስሜቶች ደግሞ በእንስሶች እና በሰው ልጆች ሁሉ የሚገኙ ናቸው፡፡ እንስሶችም እነዚህን ፍላጎቶቻቸውን ለማርካት ሲሯሯጡ ይታያሉ፡፡ እኛም ታድያ እንደ እንስሶቹ በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ብቻ ከተሰማራን ከእንስሶች ልዩ የሚያደርገን ምን ሆኖ ይገኛል? የሰው ልጅ ከእንስሳ ልዩ የሚያደርገው መንፈሳዊ እና የክርሽናን ንቃት ለማዳበር አቅም እና ችሎታው ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ተሰማርቶ የማይገኝ ከሆነ ግን እንቅስቃሴዎቹ ሁሉ ከእንስሳዎቹ የተሻሉ አይሆኑም፡፡ የሰው ልጅ የኑሮ ድክመት ትኩረቱን ሁሉ ወደተፈጥሮ ዓለማዊ ግዳጆቹ ብቻ ማተኮሩ ነው፡፡ መንፈሳዊ ነፍስ እንደመሆናችንም ያለን የኑሮ ግዳጅ ከዚህ ከተወሳሰበ መወለድ እና መሞት እራሳችንን ነፃ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም ሰው ሆኖ የመፈጠር እድላችንን ማባከን አይገባንም፡፡ ሽሪ ክርሽና እራሱ ወደዚህ ምድር ላይ መጥቶ ይህንን ብሀገቨድ ጊታን በማስተማር የአብዩን ጌታን ንቃት እንዴት እንደምናዳብር መንገዱን አሳይቶናል፡፡ ይህም የቁሳዊ ዓለም የተፈጠረልን ይህንኑን ትምህርት ለማዳበር እንድንጠቀምበት ነው፡፡ ይህንንም የሰው ልጅ ፍጥረት ዕድል አግኘተን የክርሽናን ንቃት ለማዳበር የማንጠቀምበት ከሆነ ይህንን የማይገኝ ዕድል አባከነው ማለት ነው፡፡ የመንፈሳዊ ንቃታችንንም የማዳበር ስርዓቱ በጣም ቀላል ነው፡፡ “ሽራቫናም ኪርታናም” (ሽብ፡5 23)መስማት እና መዘመር፡፡ በጥሞና ከማዳመጥ እና ከመዘመር ሌላ የተለየ ስራ መስራትም አያስፈልግም፡፡ በዚህም ስርአት ሙሉ የክሽና ንቃት ሊገኝ ይችላል፡፡ ክርሽናም በልባችን ውስጥ ተቀምጦ ሰለሚገኝ በቀላሉ ሊረዳን ይችላል፡፡ ከእኛም የሚጠበቀው ይህንን ሙከራ ማድረግ እና የተቻለውን ያህል ጊዜ ማቅረብ ብቻ ነው፡፡ ምን ዓይነት እርምጃ እየተራመድን እንደሆነ የሚያስረዳን ሰው የግድ ሊኖረን አያስፈልግም፡፡ እኛው እራሳችን የመንፈሳዊ እርምጃ ማድረጋችንን ለማወቅ እንችላለን፡፡ ልክ እንደ ተራበ ሰው ሙሉ ምግብ መብላቱን በመርካት እንደሚታወቀውም ሁሉ ነው፡፡

በመሰረቱ ይህ የክርሽና ንቃት ወይም እራስን የማወቅ ጥናት ስርአት በጣም አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ክርሽና ለአርጁና ብሀገቨድ ጊታን አስተማረው፡፡ እኛም ልክ እንደ አርጁና ብሀገቨድ ጊታን ለመረዳት ብንበቃ ፍጹም ወደ ሆነው ደረጃ ለመድረስ ምንም አያዳግተንም፡፡ ነገር ግን ብሀገቨድ ጊታን በራሳችን ተራ አስተሳሰብ ዓይተነው መልእክቱን ለመተርጎም ብንሞክር መላው መልእክት የተበላሸ እና ልንረዳው የማንችል ይሆንብናል፡፡

ከዚህም በፊት እንደተገለፀው ይህ የሀሬ ክርሽናን ቅዱስ ስም የመዘመር ስርዓት የተበከለውን የአንደበት መስታወት ሊያፀዳ ይችላል፡፡ የክርሽና ንቃትን ለማዳበር ከዚህ ውጪ የሚያስፈልግ ነገርም የለም፡፡ ምክንያቱም የክርሽና ንቃት በውስጣችን ተሸፍኖ ስለሚገኝ ነው፡፡ ይህም ንቃት ነፍስ በተፈጥሮ ያላት ነው፡፡ የሚያስፈልገውም ይህንን የተሸፈነ ንቃት በክርሽና የንቃት ስርአት መቀስቀስ ብቻ ነው፡፡ የክርሽና ንቃት ስርአት ዘለዓለማዊ እና ፍጹም እውነትን የያዘ ነው፡፡ በድርጅቶችም ውስጥ የተፈለሰፈ እምነት ወይም ስርዓት አይደለም፡፡ ይህም ንቃት በሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን በእንስሶችም ውስጥ ሁሉ የሚገኝ ነው፡፡ ጌታ ቼታንያ በደቡብ ህንድ ጫካ ውስጥ በተዘዋወረም ጊዜ የሀሬ ክርሽናን ቅዱስ ስም ላገኛቸው አውሬዎች ሁሉ በመዘመር ላይ ይገኝ ነበር፡፡ ነብሮች፣ ዝሆኖችም እና አጋዘኖችም ሁሉ በዚህ ቅዱስ ስም ተመስጠው ይገኙ ነበር፡፡ በእርግጥም ይህንን ለማድረግ እንደ ጌታ ቼታንያ ንጹህ ልብ እና ንፁህ ዝማሬ ያስፈልጋል፡፡ እኛም ይህንን ቅዱስ ስም በመዘመር ስንቀጥል አንደበታችን ንፁህ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተረጋገጠ ይሆናል፡፡

« Previous Next »