No edit permissions for Amharic

ማንትራ አሥራ አንድ
 

ቪድያም ቻቪድያም ቻ ያስ
ታድ ቬዶ ብሀያም ሳሀ
አቪድያያ ምርትዩም ቲርትቫ
ቪድያያምርታም አስኑቴ

ቪድያም — ግልጽ የሆነ ዕውቀት፣ ቻ — እና፣ አቪድያም — ድንቁርና፣ ቻ — እና፣ ያህ — አንድ ሰው፣ ታት — እንዲህ፣ ቬዳ — የሚያውቅ፣ ኡብሀያም — ሁለቱንም፣ ሳሀ — በአንድ ጊዜ፣ አቪድያያ — በድንቁርና ባህል፣ ምትርዩም — ተደጋጋሚ ሞት፣ ቲርትቫ — በመሸጋገር፣ ቪድያያ — ዕውቀት በተሞላበት ባህል፣ አምርታም — ሞትን ያሸነፈ፣ አስኑቴ — የሚደሰት

ድንቁርና የተሞላበትን የዓለማዊ ሕይወትን እና የመንፈሳዊ ዕውቀትን ጎን ለጎን አመዛዝኖ በትክክል እና ለይቶ ለማወቅ የቻለ ሰው ብቻ፣ ከዚህ ከተደጋጋሚው የሞት እና የትውልድ ወጥመድ ለማምለጥ ይችላል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ፣ ሞት ወደማይገኝበት ዘለዓለማዊ መንፈሳዊ ሕይወትን በማግኘት ፍጹም በሆነ ደስታ ለዘለዓለም መታደል ይችላል።

ይህ ቁሳዊ ትዕይንተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ፣ እያንዳንዱ ሕያው ፍጥረት ዘለዓለማዊ ደስታ እና ሕይወትን ለማግኘት የሚጥር ሆኖ ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ የተፈጥሮ ሕግ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ማንም ሕያው ፍጥረት ቢሆን፣ ከሞት እንዳይተርፍ ተደርጐ ተደራጅቷል። ማንም ሕያው ፍጥረት ቢሆን፣ ለመሞት፣ ለማርጀት ወይም ለመታመም ፈቃደኛ አይደለም፡፡ የተፈጥሮ ሕግ ግን ከማርጀት፣ ከመታመም ወይም ከመሞት እንዳንድን ሆኖ ተደንግጓል፡፡ ምንም እንኳን የዘመኑ ሳይንስ የረቀቀ ቢሆንም፣ ከእነዚህ ሕግጋት ውጪ ሊንቀሳቀስ ወይም ለችግሩ መፍትሔ ሊያገኝ አይችልም፡፡ በተቃራኒው ግን፣ የዘመኑ ሳይንስ የሞትን ቅርበት ለማምጣት፣ የኒውክሊየር ቦምብን ለመሥራት የሚችል ሥልጣኔን የያዘ ነው፡፡ ነገር ግን የተፈጥሮ ሕግ በመሆኑ፣ የሰው ልጅን ከማርጀት፣ ከመታመም እና ከመሞት የሚያተርፍ መፍትሔ ሊፈጥር አይችልም፡፡

ከፑራና መጻሕፍት እንደምንማረው፣ በቁሳዊ ዓለም ዕውቀት በጣም የዳበረ “ሂራንያካሺፑ” የሚባል ንጉሥ ነበረ፡፡ ይህ ንጉሥ በነበረው የቁሳዊ ዓለም ዕውቀት እና ዓለማዊ ሀብት ተመክቶ፣ ሞትን ለማሸነፍ የሚጣጣር ንጉሥ ነበር፡፡ ያደርገው በነበረውም ጥልቅ የሐሳብ ትኩረት ወይም ሜዲቴሽን፣ ከፍተኛ የቬዲክ ምስጢራዊ ኅይልን ለማግኘት በመብቃቱ፣ በተለያዩ ፕላኔቶች ውስጥ የሚገኙትን ፍጥረታት ሁሉ ለመረበሽ በቅቶ ነበረ፡፡ በዚህ ከፍተኛ ኃይሉም ትዕይንተ ዓለምን ያቀነባበረውን ጌታ ብራህማ፣ ወደ እርሱ እንዲመጣ ለማድረግ ቻለ፡፡ ጌታ ብራህማንም እንዲቀርብለት ካደረገ በኋላ፣ “አማራ” እንዲሆን ወይም ሞትን ለማሸነፍ እንዲችል ኅይል እንዲሰጠው ጠየቀው፡፡ ምንም እንኳን ጌታ ብራህማም ትዕይንተ ዓለምን ለመቆጣጠር በአምላክ ሥልጣን የተሰጠው ቢሆንም፣ እርሱ ራሱ ሟች በመሆኑ ሞትን ለማሸነፍ ኅይል ሊሰጠው እንደማይችል ገለጸለት፡፡ በብሀገቨድ ጊታም እንደተገለጸው (ብጊ 8፡17) ምንም እንኳን ጌታ ብራህማ ረጅም ዕድሜ ለመኖር የሚችል ቢሆንም፣ እንደ ሁሉም ፍጥረታት ከሞት ሊተርፍ የሚችል ፍጡር አይደለም።

“ሂራንያ” ማለት ወርቅ ማለት ነው፡፡ “ካሺፑ” ማለት ደግሞ ለስላሳ አልጋ ማለት ነው። ይህ “ሂራንያካሺፑ” የተባለው ንጉሥ የነበረው ፍላጐት ሁሉ፣ በሁለት ነገሮች ላይ የተመሠረተ ነበር። ይህም ኩሉም በላይ ሀብት የመያዝ እና ከሴት ልጆች ጋር ለመደሰት ነበር፡፡ ሞትን በማሸነፍ፣ እነዚህ ሁለቱን ዓላማዎች፣ ለዘለዓለም ሊደሰትባቸው ፍላጎት ነበረው፡፡ ነገር ግን ጌታ ብራህማም ሞትን ለማሸነፍ ኅይል ሊሰጠው ባለመቻሉ፣ በተለያየ መንገድ ከሞት ለመራቅ የሚችለበትን መንገድ ሁሉ፣ ከጌታ ብራህማ በምርቃት ለማግኘት ሞከረ፡፡ ጌታ ብራህማ ከሞት ሊያድነው እንደማይችል ስለተረዳም፣ ሂራንያካሺፑ ከመሞት እንዲተርፍ ከጌታ ብራህማ የተለያዩ ኃይሎችን ለማግኘት መጠየቅ ጀመረ፡፡ በመጀመሪያም በሰው ልጅ፣ በእንስሳ፣ በመላእክት ወይም ከ8,400,000 ዓይነቶቹ ፍጥረታት መሀል በማናቸውም ዓይነት ፍጥረት እንዳይገደል ኅይል ማግኘትን ጠየቀ፡፡ ከዚያም በመሬት ላይ፣ በአየር ውስጥ፣ በውሀ ውስጥ፣ ወይም በማናቸውም መሣሪያ እንዳይሞት ኃይሉን ለማግኘት ጠየቀ፡፡ ይህ ሞኝ ንጉሥ ይህንንም ሁሉ ኅይል ለማግኘት ጌታ ብራህማን በመጠየቅ ከመሞት ለማምለጥ ዋስትና የሚያገኝ መስሎት ነበር፡፡ የጠየቀውን ኅይል ሁሉ ጌታ ብራህማ ሰጠው። በመጨረሻው ግን ምንም እንኳን ጌታ ብራህማ እነዚህን ኅይል ሁሉ ሊሰጠው ቢበቃም ዞሮ ዞሮ “ነረሲምሀ” ተብሎ በሚታወቀው የዓብዩ ጌታ አካል ተገደለ፡፡ ይህም “ነረሲምሀ” ተብሎ የሚታወቀው የዓብዩ ጌታ አካል፣ በከፊል የሰውን እና በከፊል የአንበሳ አካልን የያዘ ነበረ፡፡ ሂራንያካሺፑን ለመግደል ምንም ዓይነት መሣርያ አልተጠቀመም፡፡ ምክንያቱም የገደለው ጥፍሩን ብቻ በመጠቀም ነው፡፡ የተገደለውም መሬት ላይ፣ አየር ውስጥ ወይም በውሀ ውስጥ ሳይሆን፣ በዓብዩ ጌታ “በነረሲምሀ” ጉልበት ላይ ተጋድሞ ነበር፡፡

ይህም አገዳደል በዓብዩ ጌታ የተከናወነው ሂራንያካሺፑ እራሱን ከሞት ለማዳን ሊገምተው ከሚችለው በላይ በተቀነባበረ መንገድ ነበር፡፡ ከዚህ ለመማር የምንችለው ነገር ቢኖር፣ ምንም እንኳን ሂራንያካሺፑ በትዕይንተ ዓለም ከሚገኙት ዓለማውያን ሁሉ የላቀ ደረጃ የነበረው ቢሆንም እንኳን፣ በግል እቅዱ ሞትን ለማሸነፍ አቅም አልነበረውም። ታድያ በአሁኑ ዘመን በሚገኙት ትናንሽ ሂራንያካሺፑዎች፣ ሞትን ለማሸነፍ ምን ዓይነት ውጤት ሊገኝ ይችላል? ሞትንም ለማሸነፍ የሚያደርጉት ጥረቶች ሁሉ በተደጋጋሚ በመክሸፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

ሽሪ ኢሾፓኒሻድ እንደሚያስተምረንም፣ የዓለማዊ ኑሮ ትግልን ለማሸነፍ፣ በዓለማዊ ዕውቀት ብቻ ያተኮረ ትግል ማድረግ አይገባንም፡፡ እርግጥ ሁሉም ፍጥረታት ለመኖር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ የተፈጥሮ ሕግ ኅይል ያለው በመሆኑ፣ ማናቸውም ፍጡር ቢሆን፣ ከእነዚህ ሕግጋት ውጪ ለማምለጥ አይችልም፡፡ ቢሆንም ግን፣ የሰው ልጅ፣ የዘለዓለማዊ ሕይወትን ለማግኘት ወደ መንግሥተ-ሰማያት ለመሄድ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡

ወደ ዓብዩ ጌታ መንግሥተ-ሰማያት ለመሄድ የሚያስተምረን ሥርዓት፣ ከዓለማዊው ዕውቀት ውጪ የተለየ የዕውቀት ዘርፍ ነው፡፡ ይህንንም መማር የሚገባን በመንፈስ ሊገለጹ ከሚችሉት ከቬዲክ ሥነጽሑፎች ነው፡፡ እነዚህም ኡፓኒሻድ፣ ቬዳንታ ሱትራ፣ ብሀገቨድ ጊታ እና ሽሪማድ ብሀገቨታምን የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡ በሕይወታችን ደስተኛ ለመሆንም ሆነ፣ ከሞት በኋላም ዘለዓለማዊ ደስተኛ ሕይወትን ለማግኘት የምንሻ ከሆነ፣ እነዚህን የቬዲክ መጻሕፍት በማጥናት መንፈሳዊ ዕውቀትን ማዳበር ይኖርብናል፡፡ ይህች በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ውስን በሆነ ኑሮ ውስጥ የምትገኝ ነፍስ፣ ከዓብዩ ጌታ ጋር ያላትን ዘለዓለማዊ ግንኙነት ዘንግታለች፡፡ በስሕተትም ይህንን የተወለደችበትን ጊዜያዊ ቦታ ልክ ከሁሉም በላይ እንደሆነ መኖሪያ በማድረግ፣ ተቀብላው ትገኛለች፡፡ ዓብዩ ጌታም በቸርነቱ፣ ከዚህ በላይ ስለ መኖር የተጠቀሱትን መንፈሳዊ መጻሕፍት፣ በህንድ አገር እና፣ በሌሎች አገሮች የሚገኙ ሃይማኖታዊ መጻሕፍትን በተለያየ መንገድ አቅርቦልናል፡፡ ከነዚህ መንፈሳዊ መጻሕፍት የምንማረው በዚህ በቁሳዊው ዓለም ውስጥ የሚገኘው ቤታችን፣ ዘለዓለማዊው ቤታችን እንዳልሆነ ነው፡፡ ሕያው ፍጥረታት ሁሉ መንፈሳዊ አካል ያላቸው እንደመሆናቸው፣ ሊደሰቱ የሚችሉት ወደ መንፈሳዊ ቤታቸው ሲመለሱ ብቻ ነው፡፡

ዓብዩ ጌታም የመንግሥተ ሰማያት ትሑት አገልጋዮቹን ወደዚህ ዓለም በመላክ፣ እንዴት ወደ መንፈሳዊው ዓለም ለመመለስ እንደምንችል መልእክቱ እንዲተላለፍ እየረዳን ይገኛል፡፡ አልፎ አልፎም ዓብዩ ጌታ እራሱ ወደዚህ ምድር ላይ በመውረድ ሊያስተምረን ይመጣል፡፡ እያንዳንዳቸው ሕያው ፍጥረታት፣ የዓብዩ ጌታ ልጆች ወይም ከፊል ወገኑ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ከእኛም በላይ ዓብዩ ጌታ በዚህ ምድር ላይ የሚገኘውን የእኛን ስቃይ በማየት ቅር ሲያሰኘው ይገኛል። በዚህ ዓለም ውስጥ የሚገኘውም ስቃይ፣ ይህ ዓለም ለነፍስ የሚያመች እንዳልሆነ የሚያስተምረን ሆኖ የቀረበ ነው፡፡ በመንፈሱ የላቀ ዐዋቂ ሰውም፣ ከእነዚህ ማስታወሻዎች በመማር፣ የመንፈሳዊ ዕውቀታቸውን በማዳበር ላይ ይሰማራሉ፡፡ የሰው ልጅ ሕይወት ይህንን መንፈሳዊ ዕውቀት ለማዳበር፣ ከፍተኛውን ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ ይህንን ዕድል የማይጠቀም የሰው ዘር፣ “ናራድሀማ” ወይም ከሰው በታች እንደሆነ በቬዲክ መጻሕፍት ተጠቅሷል፡፡

ድንቁርና የተሞላበት ዕውቀት ወይም ስሜቶቻችን ለማርካት የዓለማዊ ዕውቀትን ብቻ ማዳበር፣ ተደጋጋሚ ትውልድ እና ሞትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ሕያው ነፍስ መንፈሳዊ በመሆኗ፣ ትውልድም ሆነ ሞት የላትም፡፡ ትውልድ እና ሞትን የሚቀበለው ግን፣ የነፍስ ሽፋን የሆነው ቁሳዊው እና ሥጋዊው ገላችን ነው፡፡ ሞት የሚመሰለው ልብሳችንን እንደማውለቅ ሲሆን፣ ትውልድ ደግሞ የሚመሰለው ልብሳችንን እንደመልበስ ማለት ነው፡፡ በሞኝነት የተጠቁ እና በአቪድያ፣ ወይም ድንቁርና በተሞላበት ባህል ውስጥ የተመሰጡ ሰዎች ሁሉ፣ ይህ ክፋት የተሞላበት ዓለማዊ ሥርዓት ወደ ፊት በመግፋቱ፣ ምንም ቅር አይላቸውም፡፡ በዚህ በቁሳዊ ዓለም ቁንጅና እና ቅዠትም ተመስጠው፣ በዚህ በተደጋጋሚው የዓለም ስቃይ ሲጠቁ ይታያሉ፡፡ ከተፈጥሮም ሕግ ፈጽሞ ሲማሩ አይታዩም፡፡

ስለዚህ ቪድያ ወይም ዕውቀት የተሞላበት መንፈሳዊ ባህል፣ ለሰው ልጆች ሁሉ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ገደብ የሌለው የዚህ የቁሳዊ ገላችን ዓለማዊ እና ስሜታዊ ደስታ፣ የሰው ልጅን ወደ ድንቁርና እና ተደጋጋሚ ትውልድ እና ሞት ሊያመራው ይችላል፡፡ እያንዳንዱ ሕያው ፍጥረት ያለ መንፈሳዊ ስሜቶች የተፈጠረ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሕያው ፍጥረት ንጹሕ የመንፈሳዊ ስሜቶችን ይዞ የሚገኝ ቢሆንም፣ በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ በመፈጠሩ፣ ስሜቶቹ ሁሉ በቁሳዊ ገላ እና በዓለማዊ ሕሊና የተሸፈኑ ናቸው፡፡ ዓለማዊ የሆኑት ስሜቶቻችን ከመንፈሳዊው እና ከመሠረታዊው የተፈጥሮ ስሜቶቻችን ጋር ሲነጻጸሩ፣ ልክ እንደተገላበጠ የመስታዋት ምስል ይመሰላሉ፡፡ በዚህ ሕመም በተሞላበት የተገላበጠ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ሕያው ፍጥረታትም ተመስጠው፣ በተለያዩ ዓለማዊ የደስታ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሰማርተው ይገኛሉ። ትክክለኛው የስሜት ደስታ ሊገኝ የሚችለው ግን፣ የቁሳዊው ዓለም ደስታ ጉጉታችን ወይም ሕመማችን ሲወገድ ብቻ ነው፡፡ ንጹሕ የሆነው መንፈሳዊ ገላ ሲኖረን፣ ወይም የተበከልንበት የቁሳዊ ዓለም መንፈስ ሲወገድ፣ ስሜቶቻችንን በትክክለኛው መንገድ ለማስደሰት እንችላለን፡፡ አንድ በበሽታ ላይ የወደቀ ሰው፣ በትክክል ስሜቶቹን ሊደሰትባቸው የሚችለው፣ ከነበረው በሽታ ሲፈወስ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የሕይወታችንም ዓላማ መሆን ያለበት፣ ይህንን የተገላቢጦሽ የሆነውን የስሜትን ደስታ ለማርካት ሳይሆን፣ እራሳችንን ከዚህ ዓለማዊ በሽታ በማዳን ነው፡፡ ይህንን ዓለማዊ ደስታ ለመጨመር የምናደርገው ትግል ሁሉ፣ የዕውቀት ምልክት ሳይሆን፣ የአቪድያ ወይም የድንቁርና ምልክት ነው፡፡ አንድ ሰው ጥሩ ጤና ለማግኘትም፣ ትኩሳቱን ከ40.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ወደ 41.6 ዲግሪ ከፍ ማድረግ አይገባውም። ነገር ግን ትኩሳቱን ወደ ትክክለኛው 37 ዲግሪ ለመመለስ መጣር አለበት፡፡ የሕይወታችን ዓላማም እንደዚሁ መሆን አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው የቁሳዊው ዓለም እንቅስቃሴ ግን፣ ዓላማው ሁሉ ይህንኑ የዓለማዊ ስሜቶቻችንን ትኩሳት ከፍ ለማድረግ ሲሆን፣ ይህም ትኩሳት የአቶሚክ ቦንብን እሰከመሥራት ድረስ ከፍ ብሎ ወደ 41.6 ዲግሪ ደርሷል፡፡ በዚህም ወቅት ግር ያላቸው ፖሎቲከኞች ሁሉ ዓለም በቅርቡ ወደ ሲኦል ልትሄድ ትችላለች በማለት ሲጨነቁ ይታያሉ፡፡ በቁሳዊ ዓለም ሥልጣኔም መገስገስ ይህንን የመሰለ ውጤት ሊያመጣ ይችላል፡፡ ይህም የሚመነጨው በሕይወታችን በጣም አስፈላጊ የሆነውን መንፈሳዊ ባህል ባለማዳበራችን ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በተቃረነ መንገድ መንፈሳዊ ዕውቀትን እና ባህልን ማዳበር ይገባናል፡፡ ከዚህ ክፉ ከሆነውም ቁሳዊው ዓለም ተደጋጋሚ ሞት ልንተርፍ የምንችለው፣ ይህንን ፈለግ በመከተል ብቻ ነው፡፡

ይህም ማለት ግን፣ ሁሉም የቁሳዊ ገላችን እንክብካቤ ይቁም ማለት አይደለም፡፡ ይህንንም ለማቆም የሚቻል ነገር አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከትኩሳት በሽታችን ለመዳን ብለን፣ ትኩሳታችንን ፈጽሞ ለማጥፋት ብቻ መጣር አይጠበቅብንም፡፡ የሚጠበቅብን የተሳሳተውን ነገር ማስተካከል ብቻ ነው፡፡ መንፈሳዊ ዕውቀት እና ባህላችንን ለማዳበር፣ ገላችንን እና ሐሳባችንን በአግባቡ መጠቀም እና በእንክብካቤ መያዝ ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም ገላችን እና ሐሳባችን ይህንን ስኬት ለማግኘት በጣም የሚያስፈልጉን በመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ የመንፈሳዊ ዓላማችንን ግብ ለማድረስ፣ ቁሳዊ ገላችንን እና ሐሳባችንን በአግባቡ መንከባከብ የግድ ያስፈልገናል፡፡ ይህም የሚመሰለው ልክ ትኩሳታችን ወደ ትክክለኛው 37.0 ዲግሪ እንደማድረስ ማለት ነው፡፡ ለዘመናት በህንድ አገር የኖሩት ባሕታውያን እና መንፈሳውያን ሁሉ፣ ይህንኑ የመንፈሳዊ እና የቁሳዊ ዓለም ዕውቀታቸውን በማመዛዘን ይዘውት ይታዩ ነበር፡፡ ይህንን የሰው ልጅ ሕይወታቸውን፣ ለተሳሳተ እና በሽታ ለተሞላበት ዓለማዊ ስሜትንም ለማርካት ሲጠቀሙበት አይታዩም ነበር፡፡

የሰው ልጅ ኅብረተሰብ ለሰሜታዊ ደስታው ያለው የተሳሳተ ጉጉት መገደብ እንደሚገባው፣ በቬዳዎች ትምህር ውስጥ ነፍስን ነጻ ለማውጣት በተደነገጉት መመሪያዎች ውስጥ ተገልጿል፡፡ በዚህ መመሪያ ውስጥ፤ ሃይማኖትን፣ ልማትን፣ ስሜታዊ ደስታን እና የነፍስ ነጻነትን፣ እንዴት አድርገን አመዛዝነን እንደምንመራ ተገልጿል፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ለሃይማኖት እና ለነፍስ ነጻነት ምንም ግድ የሚሰጣቸው ሆኖ አይታይም፡፡ ዓላማቸው ሁሉ አንድ ይመስላል፡፡ ይህም ስሜታዊ ደስታ የሚያገኙበትን መንገድ ከፍ ለማድረግ ነው፡፡ ይህንንም ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ትኩረታቸው ሁሉ ወደ ልማት ብቻ ሆኖ ይገኛል፡፡ በተሳሳተ ግንዛቤ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችም ሃይማኖት ለሀብት ልማት የሚረዳ ስለሆነ፣ መጥፋት አይኖርበትም ብለው ያምናሉ፡፡ ይህ የሀብት ልማት የተፈለገው፣ ስሜታዊ ደስታቸውን ከፍ ለማድረግ ነው፡፡ ይህንን በመሰለ መንገድ ከሞት በኋላም ወደ ገነት ለመሄድም ሆነ ስሜታዊ ደስታን ከፍ ለማድረግ፣ የሚረዱ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ይህ የሃይማኖት ንጹሕ ዓላማ አይደለም፡፡ የሃይማኖት ዓላማ በመንፈሳዊ መንገድ ራስን የማወቅን ጥናትን ከፍ በማድረግ፣ ወደ ዓብዩ ጌታ ወደ መንፈሳዊው ዓለም መመለስ ነው፡፡ የሀብት ልማትም የሚያስፈልገው፣ ቁሳዊ አካላችንን በጥሩ እና ጤና በተሞላበት መንገድ ለዚህ ዓላማ ብቻ ለመያዝ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህንን ዓላማ ለማሳካት የሰው ልጅ ጤንነት የተሞላበት ኑሮ መኖር ይገባዋል። “ቪድያ” ወይም መንፈሳዊ ዕውቀትንም ለመረዳት እንዲመቸው፣ መንፈሱ የረካ እና ጭንቅላቱ በሰላም የተመሰጠ መሆን ያስፈልገዋል፡፡ ይህንን የመንፈሳዊ ዕውቀት መረዳት፣ ለሰው ልጅ ሕይወት ዋነኛው ዓላማ ነው፡፡ ይህ የሰው ልጅ ሕይወት፣ እንደ አህያ በመሥራት “ለአቪዲያ” ወይም ለድንቁርና እና ለስሜታዊ ደስታ መባከን የለበትም፡፡

“የቪድያ” ወይም የመንፈሳዊው ዕውቀት ሥርዓት “ሽሪማድ ብሀገቨታም” ተብሎ በተሰየመው መጽሐፍ ውስጥ በዝርዝር ተገልጿል፡፡ ይህም መጽሀፍ የሰው ልጅ ፍጹም እውነት የሆነውን መንፈሳዊ ዕውቀት እንዲኖረው የሚመራ ነው፡፡ ይህም ፍጹም እውነት የሆነው መንፈሳዊ ዕውቀት በሦስት ተከፍሎ ይገኛል፡፡ እነዚህም “ብራህማን”፣ “ፓራማትማ” እና “ብሀገቫን” ወይም ዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታን የማወቅ ዕውቀት ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ፍጹም እውነት የሆነው የመንፈሳዊ ንቃት ሊገኝ የሚችለው፣ መንፈሳዊ ዕውቀት ካለው መንፈሳዊ መምህር እና ከዓለማዊ ነገሮች ሁሉ ከራቀው ብቁ መንፈሳዊ ሰው ነው፡፡ እርሱንም ለመቅረብ ብቁ ለመሆን የምንችለው፤ በማንትራ አስር የፍሬ ነገሮች ገለጻ ውስጥ የተጠቀሱትን አሥራ ስምንት የብሀገቨድ ጊታ መመሪያዎችን በመከተል ነው፡፡ የእነዚህ አሥራ ስምንት መመሪያዎች ዋና ዓላማ፣ በፍቅር የተመሰጠ አገልግሎትን ለዓብዩ ጌታ ለማቅረብ ብቁ እንድንሆን ነው፡፡ ስለዚህ በእያንዳንዱ የኅብረተሰብ አካል ውስጥ የምንገኝ ሁሉ፣ እነዚህን የመሰሉ መመሪያዎች በመከተል በፍቅር ተመስጠን ለዓብዩ ጌታ አገልግሎት የማቅረብን ስልት መማር ይገባናል፡፡

የቪድያ ወይም የዕውቀት ሁሉ መድረሻ መንገድ፣ በክቡር ሩፓ ጎስዋሚ ብሀክቲ ራሳ አምርታ ተብሎ በተሰየመው መጽሐፍ ውስጥ በተረጋገጠ ሁኔታ ተገልጿል፡፡ ይህም ገለጻ “ኔክታር ኦፍ ድቮሽን” ተብሎ በሰየምነው መጽሐፍ ውስጥ ቀርቧል፡፡ ቪድያ ወይም ዕውቀት የተሞላበት ባህልም፣ በሽሪማድ ብሀገቨታም ውስጥ (ሽብ 1-2-14) እንደሚከተለው ተገልጿል።

ታስማድ ኤኬና ማናሳ
ብሀገቫን ሳትቫታም ፓቲህ
ሽሮታቭያ ኪሪቲታቭያስቻ
ድህዬያህ ፑጅያስ ቻ ኒትያዳ

“ስለዚህ በአንድ ትኩረት ብቻ ሳይወላውል አንድ ሰው ዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያትን ጌታ ማወደስ፣ ማስታወስ፣ መስገድ እና ስለእርሱም ሁሌ ማዳመጥ ይኖርበታል፡፡ ዓብዩ ጌታ የሁሉም ትሑት አገልጋዮቹ ጠለላ ነው፡፡”

በሚቀጥሉትም ገጾች እና በዚህ በኢሾፓኒሻድ መጽሐፍ ውስጥም እንደተገለጸው፣ የሃይማኖት እንቅስቃሴዎች፣ የሀብት ልማት እና ስሜቶቻችንን ለማርካት የምናደርገው ጥረት ሁሉ፣ ዓብዩ ጌታን ለማስደሰት ካልሆነ፣ እንቅስቃሴያችን ሁሉ በድንቁርና የተመከነ እንደሆነ ተገልጿል።

« Previous Next »