ማንትራ አስራ ሦስት
አንያድ ኤቫሁህ ሳምብሀቫድ
አንያድ አሁር አሳምብሀቫት
ኢቲ ሱስሩማ ድሂራናም
ዬ ናስ ታድ ቪቻቻክሺሬ
አንያት — የተለየ፣ ኤቫ — በእርግጥ፣ አሁህ — እንደተገለጸው፣ ሳምብሀቫት — የሚንቀሳቀሱ ሁሉ መነሻ የሆነውን ዓብዩ ጌታን በማምለክ፣ አንያት — የተለየ፣ አሁህ — እንደተገለጸው፣ አሳምብሀቫት — ዓብይ ጌታ ያልሆነውን በማምለክ፣ ኢቲ — ስለዚህ፣ ሱስሩማ — እንደሰማሁት ከሆነ፣ ድሂራናም — በሐሳብ ሊረበሹ ከማይችሉት መንፈሳዊ ባለሥልጣናት፣ ዬ — ማን፣ ናህ — ለእኛ፣ ታት — ስለዚህ ርእስ፣ ቪቻቻክሺሬ — በጥሩ ሁኔታ ተገልጿል
በዚህ ጥቅስ ውስጥ እንደተገለጸው የፍጥረታት ሁሉ መነሻ የሆነውን ዓብዩ ጌታን በማምለክ ከፍተኛ ውጤት የሚገኝበት ሲሆን፣ ዓብይ ጌታ ያልሆነውን መልአክ በማምለክ ደግሞ፣ ሌላ የተለየ ዝቅተኛ ውጤት ይገኛል፡፡ ይህም ሁሉ መንፈሳቸው ሊረበሽ በማይችሉት መንፈሳዊ ባሕታውያን እና ባለሥልጣናት በግልጽ ተተንትኖ ቀርቧል፡፡
በዚህ ማንትራ ውስጥ እንደተገለጸው ሕሊናቸው በዓለማዊ ጉጉት ከማይረበሸው ከመንፈሳዊ ምሁራን እና መንፈሳዊ ባለሥልጣናት ምክርን መቀበል፣ በመጽሐፉ የተደገፈ ሐሳብ ነው። ከእንደነዚህ ዓይነት “አቻርያዎች” አንድ ሰው መንፈሳዊ ዕውቀቱን መቅሰም ይገባዋል። አለበለዚያ ግን ትክክለኛ መንፈሳዊ ዕውቀትን ለመቅሰም አይችልም። ዕውቅና እና መንፈሳዊ ሥልጣን ያለው አቻርያ፣ ከቀድሞው አቻርያዎች ልክ እንደ “ሽሩቲ ማንትራ” ያዳመጠውን እና የቀሰመውን ብቻ ሲያስተላልፍ ይገኛል። ከቬዲክ መጻሕፍት መመሪያዎች ውጪም ሲያስተምር አይገኝም። በብሀገቨድ ጊታ (ብጊ 9:25) እንደተገለጸው የቀድሞ አባቶቻቸውን ወይም “ፒትር” የሚያመልኩ ሁሉ፣ የቀድሞ አባቶቻቸው ወደሚገኙበት ፕላኔት ይጓዛሉ። በዚህ ዓለም ውስጥ በመቀመጥ ዓለማዊ ኑሮዋቸውን ለመቀጠል የሚመኙ ሁሉ፣ ወደ እዚሁ ዓለም በመደጋገም ይወለዳሉ። ዓብዩ ሽሪ ክርሽናን በትሑት መንፈስ ለማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ ደግሞ፣ ወደ መንፈሳዊ ዓለም በመመለስ፣ ከዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና ጋር ለመኖር ይበቃሉ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸውም የተለያዩ ኃይላትን በማምለክ የተለያየ ውጤት ወይም መድረሻን ለማግኘት ይቻላል። አብዩ ሽሪ ክርሽናን በትሑት መንፈስ በማገልገል ግን፣ ወደ ዘለዓለማዊው መንፈሳዊ ዓለም ለመመለስ እንችላለን። እንደዚሁም ሁሉ የፀሐይንም ሆነ የጨረቃን መላእክት በማምለክ፣ ወደ እነዚሁ ፕላኔቶች ለመጓዝ ይቻላል። ወደነዚህ ዓይነት የሞት እና መወለድ ስቃይ ወደተሞላበት ዓለማዊ ምድር ለመቆየት ከፈለግንም፣ ምኞታችን ሊሳካ ይችላል።
ነገር ግን፣ በማንኛቸውም መንፈሳዊ መመሪያዎች ውስጥ፣ በእንደዚህ ዓይነት ዓለማዊ ስግደት ወደ መንፈሳዊ ዓለም ለመጓዝ ይቻላል ተብሎ አልተጠቀሰም። እንደዚህ ዓይነቱ ንድፈ ሐሳብ ግን፣ በአስመሳይ መንፈሳውያን ሲሰበክ ይገኛል። እንደዚህ ዓይነቱ አስመሳይ መንፈሳውያን፣ ከማናቸውም ሥልጣን ካለው የቬዲክ የዲቁና ሥርዓት የመጡ አይደሉም። እራሳቸውን በራሳቸው የሰየሙ መንፈሳውያን ናቸው። ሥልጣን ያላቸው የቬዲክ መንፈሳውያን፣ ሁሉም ዓይነት እምነት ወደ አንድ መንፈሳዊ ግብ ያደርሳል ብለው አያስተምሩም። ሁሉም የፈለገውን እምነት በመከተል ወይም የፈለገውን መልአክ በማምለክ፣ ወደ ትክክለኛው የመንፈሳዊው ግብ ይደርሳል ብለውም አያስተምሩም። በቫይሽናቫ የዲቁና ሥርዓት ዕውቅና ያለው መንፈሳዊ አባት፣ ሁሉም የእምነት ሥርዓት ወደ ተመሳሳይ ግብ የሚያደርስ ነው ብሎ አያስተምርም። ማንም ሰው ቢሆን እንዳሻው የራሱ የሆነውን የመላእክት ስግደት ሥርዓት በመከተል፣ የመንፈሳዊ ሕይወቱን በትክክል ስኬታማ ለማድረግ አይችልም። ሁላችንም በቀላሉ እንደምንረዳው፣ አንድ ሰው ወደ ጉዞው መድረሻ ሊደርስ የሚችለው፣ ለመድረሻው የሚሆን ቲኬት ከገዛ ብቻ ነው። ወደ ካልካታ ለመሄድ የገዛነው ቲኬት፣ ወደ ቦምቤ ሊያደርሰን አይችልም። አስመሳይ መንፈሳዊ መምህራን ግን፣ ሁሉም መንፈሳዊ ሥርዓት ወደ ተመሳሳይ የመንፈሳዊ ግብ ያደርሳሉ ብለው ያስተምራሉ። በእንዲህ ዓይነቱ ተራ እና የተሳሳተ እምነት ትምህርት፣ በመንፈሳዊ ዕውቀት ያልዳበሩትን ስዎች እንዲከተሏቸው ያደርጓቸዋል። እነዚህ ተከታዮች ይህንን የተሳሳተ መንፈሳዊ ዕውቀት በመያዝ፣ ትዕቢት በተሞላበት መንፈስ ሲከተሉት ይታያሉ። ስለሆነም ይህን የመሰለው መመሪያ በቬዲክ ትምህርቶች የተደገፈ አይደለም። አንድ ሰው ትክክለኛ መንፈሳዊ ዕውቀትን ለማግኘት የቫይሽናቫ የዲቁና ሥርዓት ተከትሎ የመጣው የመንፈሳዊ አባትን መቅረብ ይገባዋል። ከእርሱም ትክክለኛ የቬዲክ መንፈሳዊ ዕውቀትን ለማግኘት ይችላል። ይህንን በተመለከተም ሽሪ ክርሽና ለአርጁና በብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ (ብጊ 4:2) እንዲህ በማለት ገልጾለታል።
ኤቫም ፓራምፓራ ፕራፕታም
ኢማም ራጃርሳዮ ቪዱህ
ሳ ካሌኔሀ ማሃታ
ዮጎ ናስታህ ፓራንታፓ
“ይህ ታላቁ ሳይንሳዊ ትምህርት ሲተላለፍ የቆየው፣ ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣው የመንፈሳዊ ዲቁና ሥርዓት ነው። መንፈሳዊ ነገሥታትም ትምህርቱን የቀሰሙት በዚሁ መንገድ ነው። ቢሆንም ከዘመናት በኋላ የዲቁናው ሥርዓት ተቋርጦ ስለነበረ፣ ይህ ትምህርት ወደ መጥፋቱ ደርሶ ነበረ።”
ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና በዚህ ምድር ላይ መጥቶ በነበረበት ጊዜ፣ በብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ተገልጸው የነበሩት “የብሀክቲ ዮጋ” ዋና ዋና መመሪያዎች፣ የተበረዘ ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር። ስለዚህም ሽሪ ክርሽና እነዚህን መመሪያዎች እንደገና በአርጁና በመጀመር በትክክለኛ መንገድ ለማቋቋም በቃ።
አርጁና የሽሪ ክርሽና ትሑት አገልጋይ እና የቅርብ ታማኝ ጓደኛውም ነበረ። ይህንንም ዕውቀት ጌታ ሽሪ ክርሽና ለአርጁና ገልጾለታል። (ብጊ 4:3) እንደተገለጸውም አርጁና የሽሪ ክርሽና ትሑት አገልጋይ እና የቅርብ ታማኝ ጓደኛ በመሆኑ፣ ይህንን የብሀገቨድ ጊታ መመሪያዎች በቀላሉ እና በትክክል ለመረዳት ቻለ። ይህም ማለት የብሀገቨድ ጊታን መልእክት በትክክል ለመረዳት የሚችሉት፣ የሽሪ ክርሽና ትሑት አገልጋይች ብቻ ናቸው። ወይም ደግሞ የአርጁናን የትሑት መንፈስ ፈለግ የሚከተሉ ሁሉ የብሀቨድ ጊታን መልእክት በትክክል ለመረዳት ይችላሉ።
በአሁኑ ዘመን የዚህን የብሀገቨድ ጊታን ታላቅ ውይይት እና መልእክት የሚተረጉሙ ብዙ ተርጓሚዎች አሉ። እነዚህ ብዙኃን ተርጓሚዎች ለሽሪ ክርሽናም ሆነ ለአርጁና መንፈሳዊ ማዕረግ ምንም ደንታ የሰጣቸው አይደሉም። በዚህም ምክንያት የብሀገቨድ ጊታን መልእክት እንዳሻቸው የራሳቸውን ትርጉም በመስጠት፣ መልእክቱንም በማዛባት፣ በጊታ ስም ሕትመታቸውን ለሕዝብ ሲያቀርቡ ይታያሉ። እነዚህም ዓለማዊ ተርጓሚዎች ስለ ሽሪ ክርሽና መንፈሳዊ ማዕረግም ሆነ ስለ መንግሥተ ሰማያቱ ምንም ዓይነት እምነት ያላቸው አይደሉም። ታድያ በዚህ ዓይነት መንፈስ እንዴት አድረገው የብሀገቨድ ጊታን ቅዱስ መንፈሳዊ ዕውቀት በትክክል ሊያቀርቡ ይችላሉ?
ሽሪ ክርሽና በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ እንደገለጸው፣ የተሳሳተ መንፈስ የያዙ ሁሉ፣ የዓለማዊ ቁሳዊ ሀብትን ለማግኘት ሲሉ፣ መላእክትን ሲያመልኩ ይታያሉ። (ብጊ 7:20 23) በመጨረሻም በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ሽሪ ክርሽና እንደገለጸው፣ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ስኬታማ ለማድረግ መላእክትን ለቁሳዊ ነገሮች ከማምለክ ይልቅ፣ ለዓብዩ ጌታ ብቻ ሙሉ ልቦናችንን መስጠት ይገባናል። (ብጊ 18:66፟) ለዓብዩ ጌታ የማይወላወል እምነት ሊኖራቸው የሚችሉ ሰዎች፣ ልቦናቸው ከኅጢአት ሁሉ የጸዳ በመሆኑ ነው። ሌሎች ግን በቁሳዊ ዓለም ውስጥ ስሜታቸውን በማርካት ጉጉት ውስጥ የተጠመዱ ናቸው። በተሳሳተ የመላእክት ስግደታቸውም ምክንያት ስኬታማ ከሚያደርጋቸው የመንፈሳዊ ፈለግ አፈንግጠው የወጡ ናቸው። ይህም ሁሉም የስግደት ሥርዓት፣ ወደ አንድ የመንፈሳዊው ዓላማ የሚያመራ ነው በሚል የትዕቢት መንፈስ የሚከናወን ነው።
በሚቀጥለው የሽሪ ኡፓኒሻድ ጥቅስ ውስጥ እንደተገለጸው፣ “ሳም ብሀቬት” የሚለው ቃል፣ ታላቅ ትርጉም የያዘ ነው። ይህም ማለት “ለዓብዩ ጌታ ብቻ መስገድ” ማለት ነው። “ሽሪ ክርሽና የመንግሥተ-ሰማያት ሁሉ ዓብዩ ጌታ ነው።” በመንፈሳዊው ዓለምም ሆነ በቁሳዊው ዓለም ውስጥ የሚገኙት ሁሉም ነገሮች የሚመነጩት፣ ከዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና ነው። በብሀገቨድ ጊታም ውስጥ፣ በሽሪ ክርሽና እንዲህ በማለት ተገልጿልናል። (ብጊ 10:8)
አሀም ሳርቫስያ ፕራብሃቮ
ማታህ ሳርቫም ፕራቫርታቴ
ኢቲ ማትቫ ብሃጃንቴ ማም
ቡድሀ ባሃቫ ሳማንቪታህ
“እኔ የመንፈሳዊው ዓለም እና የቁሳዊው ዓለም ሁሉ መነሻ ነኝ። ሁሉም ነገር የሚመነጨው ከእኔ ነው። ይህንን በትክክል የተገነዘቡ መንፈሳውያን አዋቂዎች፣ ለእኔ ትሑት አገልግሎትን በማቅረብ ላይ ተሰማርተው በሙሉ ልቦናቸው እየሰገዱልኝ ይገኛሉ።”
ይህም ስለ ዓብዩ ጌታ፣ በራሱ በዓብዩ ጌታ የተሰጠ መግለጫ ነው። ይህ “ሳርቫስያ ፕራ ብሀቫ” የሚለው ቃል የሚገልጽልን፣ ሽሪ ክርሽና የሁሉም ነገር ፈጣሪ እንደሆነ ነው። ይህም ማለት ጌታ ብራህማን፣ ጌታ ቪሽኑን እና ጌታ ሺቫንን ጨምሮ የፈጠረ ማለት ነው። እነዚህ ሦስቱ የመላው ቁሳዊው ዓለም መሠረታዊ አማልእክት ናቸው፡፡ ሦስቱም የተፈጠሩት በሽሪ ክርሽና በመሆኑ፣ ሽሪ ክርሽና የመላው ቁሳዊው ዓለም እና የመንፈሳዊው ዓለም ፈጣሪ እና ዓብዩ ጌታ ሆኖ ይገኛል። “በአትሀርቫ ቬዳ” ሥነጽሑፍ ውስጥም በተመሳሳይ እንደተጠቀሰው፣ (ጎፓላ ታፓኒ ኡፓኒሻድ - ጎታኡ፡ 1.24) “ጌታ ብራህማ ከመፈጠሩ በፊት፣ በቀዳማዊነት የነበረው፤ እንዲሁም ለጌታ ብራህማ የቬዲክ ዕውቀትን በጥልቀት የገለጸለት ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና ነው።” እንዲሁም በተመሳሳይ “በናራያን ኡፓኒሻድ” ውስጥ እንደተገለጸው “ዓብዩ ጌታ ናራያን በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ሕያው ፍጥረታት ለመፍጠር ሲወስን፣ በመጀመሪያ ደረጃ ጌታ ብራህማን ፈጠረ። ከዚያም ጌታ ናራያን መላ ፕራጃፓቲዎችን ሁሉ ፈጠረ። ከዚያም ኢንድራን ፈጠረ። ከዚያም ስምንቱን ቫሱዎች ፈጠረ። ከዚያም ጌታ ናራያን አስራ አንዱን ሩድራዎች ፈጠረ። ከዚያም አስራ ሁለቱን አዲትያዎች ፈጠረ።” ምንም እንኳን ጌታ ናራያን ለየት ብሎ የሚገኝ የዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና አካል ቢሆንም፣ ጌታ ናራያን እና ሽሪ ክርሽና አንድ ናቸው። ስለዚህም ናራያን ኡፓኒሻድ ማንትራ አራት ላይ ተገልጿል። “የዴቫኪ ወልድ ሽሪ ክርሽና ዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ ነው።” ጌታ ናራያን ዓብዩ የፍጥረታት ሁሉ ጌታ ስለ መሆኑ፣ በታላቁ መምህር በ“ሽሪፓድ ሻንካራ አቻርያ” ተገልጿል። ይህም ምንም እንኳን ሻንከራ አቻርያ ራሱ በቫይሽናቭ ወይም በጌታ ክርሽና ዓብይ ሰብአዊነት የማያምን ትምህርት ይሰጥ የነበረም ቢሆንም እንኳን ነው። የአትሀርቫ ቬዳ (ማሀ ኡፓኒሻድ) ሥነጽሑፍ ውስጥም እንዲህ ተብሎ ተገልጿል። “በመጀመሪያ ዓብዩ ጌታ ናራያን ብቻ ነበረ። በዚያን ጊዜ ብራህማ፣ ሺቫ፣ እሳት፣ ውሀ፣ ክዋክብት፣ ፀሐይ፣ ጨረቃ ሁሉ አልተፈጠሩም ነበር።” በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ዓብዩ ጌታ ብቻውን አይቆይም። ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደ ፍላጎቱ ቁሳዊ ዓለምን አጥፍቶ እንደገና መፍጠር ይጀምራል። “በሞክሻ ድሀርማ” መጽሐፍ ውስጥ ሽሪ ክርሽና ራሱ እንዲህ ብሎ ገልጾልናል። “ፕራጃፓቲዎችን እና ሩድራዎችን የፈጠርኳቸው እኔው ነኝ። ስለ እኔ ግን የተሟላ ዕውቀት የላቸውም። ምክንያቱም በቅዠት ላይ እንዲሰፍኑ በሚያደርጋቸው የእኔ ኅይል ስለተጋረዱ ነው።” “በቫራሀ ፑራን” መጽሐፍ ውስጥም እንዲህ ተብሎ ተጠቅሷል። “ናራያን ዓብዩ ጌታ ነው። ከእርሱም አራት ጭንቅላት ያለው ጌታ ብራህማ እና ሩድራ ከመንፈሳዊ ዕውቀት ጋር ተፈጠሩ።”
እንደዚህም በመሰለ መላ የቬዳ መጻሕፍት ጌታ ናራያን ወይም ሽሪ ክርሽና፣ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ ወይም መነሻ እንደሆነ የሚገልጹ ናቸው። በብራህማ ሰሚታ ጥቅስ (ብሰ፡ 5.1) ውስጥ ደግሞ፣ እንዲህ ተብሎ ተገልጿል። “ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና ወይም ጎቪንዳ፣ ለእያንዳንዱ ፍጥረት ደስታን የሚሰጥ እና፣ የተፈጥሮ ሁሉ መነሻ እና ፈጣሪ ነው።” በመንፈሳዊ ዕውቀት የገፉ ሰዎች ሁሉ የባሕታውያንን እና የቬዳ መጻህፍትን መረጃ በመከተል፣ ሽሪ ክርሽናን እንደ ዓብይነቱ በመቀበል ሲያመልኩት ይገኛሉ።እነዚህም መንፈሳውያን “ቡድሀ” ወይም በመንፈሳዊ ዕውቀት የላቁ ተብለው ይታወቃሉ። ምክንያቱም አንድ ዓብይ ጌታ ሽሪ ክርሽናን ብቻ ስለሚያመልኩ ነው።
ሽሪ ክርሽና የፍጥረታት ሁሉ መነሻ መሆኑን ለመረዳት እና ያለውን እምነት ለማጠንከር፣ አንድ ሰው፣ መንፈሳዊ ዕውቀቱን ተግባራዊ ካደረገ መንፈሳዊ መምህር፣ ወይም “አቻርያ” ትምህርቱን መቅሰም ይገባዋል። የዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና ፍቅር እና እምነት የሌለው ሰው ግን ይህንን ቀላል መልእክት ሊቀበለው አይችልም። እነዚህ በዓብዩ ጌታ እምነት የሌላቸው ሰዎች በብሀገቨድ ጊታ መጽሐፍ ውስጥ (ብጊ 9.11) “ሙድሀ” ወይም በሞኝነት የተጠቁ ተብለው ተገልጸዋል። እንደተገለጸውም እነዚህ “ሙድሀዎች” ዓብዩ ጌታን ሲያንቋሽሹ ይገኛሉ። ምክንያቱም ከመንፈሳዊ መምህሩ ወይም በእምነቱ ከማያወላውለው አቻርያ፣ ትምህርቱን ስላልቀሰሙ ነው። ለዓለማዊ ሕይወት የሚጓጓ እና፣ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ላይ የሚወላውል ሰው፣ “አቻርያ” ሊሆን አይችልም።
የብሀገቨድ ጊታን ዕውቀት ከዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና ከመቅሰሙ በፊት፣ አርጁና ዓለማዊ ጉጉት ስለነበረው በመወላወል ላይ ነበር። ይህም ለቤተሰቡ፣ ለኅብረተስቡ እና ለአገሩ ሰው ባለው ቅርበት ምክንያት ነበር። በዚህም ምክንያት አርጁና በጎ አድራጊ፣ ጠበኛ ያልሆነ እና በጉልበቱ የማይመካ ለመሆን ፈልጎ ነበር። ቢሆንም ግን፣ የብሀገቨድ ጊታን ዕውቀት ከዓብዩ ሽሪ ክርሽና ከቀሰመ በኋላ እና፣ “ቡድሀ” ለመሆን ሲበቃ፣ አቀራረቡን ቀይሮ የሽሪ ክርሽና ትሑት አገልጋይ ለመሆን በቃ። በዚያን ጊዜ የነበረውንም የኩሩክ ሼትራ ጦርነት ያደራጀው ሽሪ ክርሽና ራሱ ነበር። አርጁናም የሽሪ ክርሽናን ዕውቀት በትሑት መንፈስ በመቀበል፣ በጦርነቱ ላይ ከዘመዶቹ ጋር ሳይቀር በመዋጋት መሳተፍ ጀመረ። በዚህም መንፈሱ የሽሪ ክርሽና ንጹሕ እና ትሑት አገልጋዩ ለመሆን በቃ። ይህም ዓይነት መንፈስ ሊኖረን የሚችለው፣ ትክክለኛውን ዓብይ ጌታ ወይም ሽሪ ክርሽና ልክ በብሀገቨድ ጊታ እና በሽሪማድ ብሀገቨታም እንደተገለጸው ብቻ ስናመልክ ነው። በሽሪ ክርሽና መንፈሳዊ ዕውቀት ያልዳበሩ እና ራሳቸውን እንደ ሽሪ ክርሽና በማስመሰል የሚያስተምሩትን ሰዎች የምንከተል ከሆነ ግን፣ ይህ ንጹሕ እና ትሑት መንፈስ ሊያድርብን አይችልም።
በቬዳንታ ሱትራ እንደተገለጸው “ሳምብሁታ” ማለት፣ የትውልድ እና የሕይወት ጌታ እንዲሁም መላው የቁሳዊው ዓለም ከተደመሰሰ እንኳን በኋላ፣ ሊጠፋ የማይችል ማለት ነው። “ጃንማዲ አሽያ ያታሀ” በሽሪማድ ብሀገቨታም የቬዳንታ ሱትራ ገለጻ ውስጥ እንደተገለጸው የቁሳዊው ዓለም ፈጣሪ ዓብዩ ጌታ፣ ሕይወት እንደሌለው ግዑዝ ቁሳዊ ነገር ሳይሆን፣ ሙሉ በሙሉ ንቁ የሆነ ወይም “አብሂግያ” ነው። ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽናም በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ እንደገለጸልን (ብጊ 7:16) እርሱ የቀድሞውን ጊዜ፣ የአሁኑን እና የወደፊቱን ክስተት ሁሉ የሚያውቅ እና፣ እንደ ጌታ ሺቫ እና ጌታ ብራህማ የመሳሰሉት መላእክት ሁሉ፣ ሙሉ በሙሉ ማንነቱን በጥልቀት እንደማያውቁ ነው። ይህም እንዲህ እያለ፣ ከፊል የመንፈሳዊ ዕውቀት ያላቸው መንፈሳዊ መሪዎች እና፣ በዓለማዊ ስሜት የተመሰጡ ሰዎች፣ ፈጽሞ ኅያልነቱን ሊያውቁ አይችሉም። እንደነዚህ ዓይነቶቹ መንፈሳዊ መሪዎች፣ ኅብረተሰቡን በማታለል እና ራሳቸውን እንደ መላእክት እንዲቆጥሯቸው በማድረግ፣ ትክክለኛውን የዓብዩ ጌታን አምልኮት ሲያራክሱት ይገኛሉ። ተከታዮቻቸውን ሁሉ የአምልኮታቸው ዓላማ እነሱ እንደሆኑ በማድረግ እና ከተከታዮቻቸው ጋር በስምምነት ደረጃ ላይ በመሆን ሲንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ቢሆንም ግን ይህ እንደ ተረት የሚቆጠር የተሳሳተ ሥርዓት ነው። ምክንያቱም የሰው ልጅ እንደ ዓብዩ ጌታ ከቶም ፍጹም ሊሆን አይችልም። ይህንን የመሰለው በአንዳንድ አሳሳች መንፈሳዊ መሪዎች የሚሰጠው ትምህርት የሚመሰለው፣ ልክ ለአንድ ተክል፣ ውሀን ከሥሩ ይልቅ በቅጠሉ ላይ ማጠጣት እንደማለት ነው። ተክልን በተፈጥሮ ለማሳደግ በሥሩ ላይ ውሀ ማጠጣት ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነቶቹ መንፈሳዊ መሪዎች ግን፣ ያላቸው ፍላጎት ሥሩን ሳይሆን የተክሉን ቅጠል እንደማጠጣት ይመሰላሉ። ምንም እንኳን ቅጠሉን ማጠጣት ቢቀጥሉም ግን፣ ቀስ በቀስ መላ ተክሉ የተመጣጠነ ምግብ እና ውሀን በማጣት ምክንያት፣ መድረቅ ይጀምራል።
ሽሪ ኢሾፓኒሻድ የሚያስተምረን ግን፣ ውሀውን ወደ ሥሩ ዘንበል በማድረግ ማጠጣትን ነው። ይህም የተክሉ እድገት ሁሉ መነሻ ነው። ይህ ለመላ ኅብረተሰቡ የሚቀርበው የቁሳዊ እና የሥጋዊ አገልግሎት፣ ለነፍሳችን መሰጠት ከሚገባው አገልግሎት በሁለተኛ ደረጃ ላይ መታየት የሚገባው ነው። ይህች ነፍሳችን የምትታየው፣ ልክ እንደ ተክሉ ሥር ነው። “ካርማ” ተብሎ የሚታወቀውን የተፈጥሮ ሕግጋትንም በመከተል፣ ነፍሳችን በሞት እና በትውልድ በመፈራረቅ የተለያዩ ገላዎችን በማፍራት የምትገኝ ናት። ለምሳሌ የሰው ልጅን በየሆስፒታሉ እና የትምህርት ማዕከላትን እያገለገልን፣ ከቬዳ ትምህርቶች በተጻረረ መንገድ ከብቶችን እና ሌሎች እንስሳትን በየጊዜው መግደል፣ ለሕያው ነፍስ መንፈሳዊ እድገት እንቅፋት የምሆን ነው።
ይህንን በመሰለ መንገድ ሕያው ፍጥረታት ሁሉ፣ በተለያየ ቁሳዊ ገላ ውስጥ በመወለድ በቁሳዊ ዓለም ውስጥ ወሰን ለሌለው ጊዜ፣ በመሰቃየት ላይ ይገኛሉ። ይህም በመወለድ፣ በእርጅና፣ በሕመም እና በተደጋጋሚ ሞት ነው።ይህ የሰው ልጅ ትውልድ ግን፣ ከዚህ ዓይነቱ ውስብስብ ዓለማዊ ኑሮ እና ስቃይ ነጻ እንድንሆን ዕድሉን የሚሰጥ ገላ ነው። ይህም ትውልድ ከዓብዩ ጌታ ጋር የነበረንን ግንኙነት እንደገና ለመመሥረት እና ለማዳበር ዕድሉን የሚሰጠን ነው። ዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ፍልስፍናን ለማስተማር ወደዚህ ቁሳዊ ዓለም ከዘመን ዘመን ሲወርድ ቆይቷል። ይህም “ሳምብሁታ” ይባላል። ለሰው ልጅ ትክክለኛው በጎ አድራጎት ሊመሠረት የሚችለው፣ ዓብዩ ጌታን በፍቅር እና በመላው ኃይላችን ማገልገል እንደሚገባን ማስተማር ስንጀምር ነው። በኢሾፓኒሻድ መጽሐፍ ጥቅስ ውስጥ የምናገኘው መልእክትም ይህንኑ ነው።
ዓብዩ ጌታን በፍቅር ለማገልገል ቀላሉ ሥርዓትም፣ ቅዱስ ስሙን በመዘመር እና በረከቱን እና ሥራውንም ሁሉ በማስታወስ እና በማመስገን ነው። በግምት ላይ የተመሠረተ አስተሳሰብ ያላቸው ፈላስፎች ግን፣ የዓብዩ ጌታ ሥራዎች እና የሚያወርድልን በረከት ሁሉ፣ እንደ ሕልም የሚቆጠሩ ናቸው ብለው ያስተምራሉ። በዚህም ምክንያት ሰዎች ስለ ዓብዩ ጌታ ትምህርትን ከመቀበል ይርቃሉ። በምትኩ ግን የራሳቸውን አስመሳይ እና አሳሳች የሆነ ፍልስፍናቸውን እየፈጠሩ፣ ንጹሕ የሆነውን የኅብረተሰብ አተያይ በመቀየር ላይ ይገኛሉ። ስለ ዓብዩ ሽሪ ክርሽና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ከማዳመጥ ፋንታ፣ እነዚሁ አሳሳች መንፈሳዊ መሪዎች ከዓብዩ ጌታ ይልቅ ስለራሳቸው ዝና እንዲዘመር እና እንዲመሰገኑ ያደርጋሉ። በአሁኑ የዘመናዊ ጊዜ እንደዚህ ዓይነቶቹ አሳሳቾች ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል። ንጹሕ ለሆኑት የዓብዩ ጌታ አገልጋዮችም፣ እንደዚህ ዓይነት መንፈሳዊ መሪዎች፣ አስመሳዮች እና አሳሳች ነብያት፣ ትልቅ እንቅፋት እየሆኑ መጥተዋል። ይህም ሊሆን ይቻለው በሚያስፋፉት መንፈሳዊ ያልሆነ ፕሮፖጋንዳ ምክንያት ነው።
የኡፓኒሻድ መጻሕፍት ወደ ዓብዩ ጌታ እንድናተኩር በተዘዋዋሪ መንገድ ያስተምሩናል። የብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መጽሐፍ ደግሞ፣ የኡፓኒሻድ ትምህርቶች ማጠቃለያ በመሆኑ ስለ ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና በቀጥታ ያስተምረናል። ስለ ሽሪ ክርሽና ማንነት በቀጥታ ለመማር ሊረዱን የሚችሉት የብሀገቨድ ጊታ እና የሽሪማድ ብሀገቨታም መጻህፍት ናቸው። እነዚህን መጻሕፍት በጥሞና በመከታተል፣ በአሳሳች መምህራን የተበከለውን መንፈሳችንን ሁሉ ቀስ በቀስ ለማጽዳት እንችላለን። በሽሪማድ ብሀገቨታም (ሽብ 1:2:17) እንደተገለጸው “አንድ ሰው ስለ ዓብዩ ጌታ በማዳመጥ ብቻ፣ በዓብዩ ጌታ ላይ በቀላሉ ለማተኮር ይችላል። ዓብዩ ጌታ በልባችን ውስጥ እንደሚገኝም ሁሉ፣ ትሑት አገልግሎታችንን በማየት የሚያስፈልገንን መመሪያ ሁሉ ሊሰጠን ይችላል።” የብሀገቨድ ጊታም (ብጊ 10.10) ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን መልእክት በማካተት ገልጾታል። “ዳዳሚ ቡድሂ ዮጋም ታም ዬና ማም ኡፓያንቲቴ”
በልባችን ውስጥ የሚገኘው የዓብዩ ጌታ መንፈስ እና የሚሰጠን መመሪያ፣ የትሑት አገልጋዮችን፣ የቁሳዊ ዓለም የጋለ ፍላጎት እና፣ በድንቁርና ኑሮ ምክንያት የተበከለውን ሕሊና ሁሉ ሊያፀዳ ይችላል። ትሑት አገልጋይ ያልሆኑት ሁሉ፣ በቁሳዊ ኑሮ የጋለ ፍላጎት እና በድንቁርና የተጠቁ ናቸው፡፡ ለቁሳዊው ዓለም የጋለ ፍላጎት ያለው ሁሉ፣ ከዓለማዊ ጉጉቶች ለመራቅ በጣም ያዳግተዋል። በድንቁርና ሥር ያለ ሰው እሱ ራሱ ማን እንደሆነ እና፣ ዓብዩ ጌታ ማን መሆኑን ለይቶ ለማወቅ ይሳነዋል።ስለዚህ ምንም እንኳን አንድ ሰው መንፈሳዊ መሪ ነኝ ብሎ ራሱን ቢያስተዋውቅም፣ ለዓለማዊ ኑሮ የጋለ ፍላጎት ካለው እና በድንቁርና የተጠቃ ከሆነ፣ የራሱን ማንነት ለማወቅ በጣሙን ይቸገራል። ለዓብዩ ጌታ ትሑት አገልጋይ ግን፣ እነዚህ ዓለማዊ የጋሉ ፍላጎቶች እና ድንቁርናዎች፣ በዓብዩ ጌታ በረከት፣ ከንቃተ ሕሊናው ሙሉ በሙሉ የጸዱ ናቸው። በዚህም መንገድ ትሑት አገልጋዮች ሁሉ፣ በጥሩ መንፈሳዊ ደረጃ ላይ በመገኘት የንጹሕ ብራህማና (የቀሳውስት) ባሕርይን ይዘው ይገኛሉ። ማናቸውም ሰው ቢሆን የትሑት መንፈሳዊ አገልግሎትን ዕውቀት፣ በታወቁ መንፈሳዊ መምህራን ሥር ሆኖ እስከቀሰመ ድረስ “ብራህማና” ለመሆን ይችላል።
ኪራታ ሁናንድህራ ፑሊንዳ ፑልካሳ
አብሂራ ሱምብሀ ያቫናህ ክሀሳዳያህ
ዬ ንዬ ቻ ፓፓ ያድ አፓስራያስራያህ
ሱድህያንቲ ታስማይ ፕራብሀቪሽናቬ ናማሀ
“ማናቸውም ከዝቅተኛ ቤተስብ እንኳን የተወለደ ሰው ቢሆንም፣ በንጹሕ መንፈሳዊ እና በትሑት የዓብዩ ጌታ አገልጋይ ላይ በመሳተፍ፣ ንቃተ ሕሊናውን ሊያጸዳ ይችላል። ይህም የሚያሳየን ምን ያህል ዓብዩ ጌታ ለንጹሕ አገልጋዮቹ ኅይል ሊሰጣቸው እንደሚችል ነው።”
አንድ ሰው የብራህመና ባሕርይ እና ብቃት ሲኖረው፣ ለዓብዩ ጌታ ትሑት አገልግሎትን ለማቅረብ ደስተኛና ቅን ይሆናል። የዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ዕውቀት እና ሳይንስንም በቀላሉ ሊረዳው እና ሊገለጽለት ይችላል። አንድ ሰው ቀስ በቀስ ይህንን የመንፈሳዊ ዕውቀት በትክክል በመረዳት ከቁሳዊው ዓለም ጉጉት ለመራቅ ይችላል። በአንደበታችን ውስጥ የነበረው ጥርጣሬ ሁሉ በዓብዩ ጌታ በረከት ግልጽ ሊሆንልን ይችላል። በዚህም ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ሁሉ ነፍሱ ፃድቅ ናት ለማለት ይቻላል። ዓብዩ ጌታንም በእያንዳንዱ የሕይወቱ ደረጃ ላይ በቅርቡ የማየት ኅይል ይኖረዋል። በዚህም በኢሾፓኒሻድ ጥቅስ ውስጥ “ሳምብሀቫ” ተብሎ እንደተጠቀሰው ፍጹም አገልጋይ ልንሆን የምንችለው እንዲህ ዓይነት ንቃተ ሕሊና ሲኖረን ነው።