ማንትራ አምስት
ታድ ኤጃቲ ታን ናይጃቲ
ታድ ዱሬ ታድ ቫ አንቲኬ
ታድ አንታር አስያ ሳርቫስያ
ታድ ኡ ሳርቫስያስያ ባህያታህ
ታት — ይህ ዓብዩ ጌታ፣ ኤጃቲ — ይራመዳል፣ ታት — እርሱም፣ ና — አይደለም፣ ኤጃቲ — ይራመዳል፣ ታት — እርሱ፣ ዱሬ — ሩቅ ነው፣ ታት — እርሱ፣ ኡ — ጭምር፣ አንቲኬ — በጣም ቅርብ ነው፣ ታት — እርሱ፣ አንታህ — በውስጥ ነው፣ አስያ — የዚህ፣ ሳርቫስያ — የሁሉም፣ ታት — እርሱ፣ ኡ — ጭምር፣ ሳርቫስያ — የሁሉም፣ አስያ — የዚህ፣ ባህያታህ — በውጪም ጭምር
ዓብዩ ጌታ የሚራመድ ቢሆንም በፈቃደ ኃይሉ የማይራመድም ሆኖ የሚገኝ ነው፡፡ በጣም በርቀት የሚገኝ ቢሆንም፣ በቅጽበት በቅርባችንም ሆኖ ሊገኝ የሚችል ነው፡፡ በሁሉም ነገር ውስጥ ገብቶ የሚገኝ ቢሆንም፣ ከሁሉም ነገርም ውጪ በመሆን የሚገኝ ዓብይ ጌታ ነው።
በዚህ ጥቅስ ውስጥ የተገለጸልን፣ አሰላስለን ለመረዳት የማንችለውን ኃይሉን እና ዓብዩ ጌታ ለማድረግ የሚችለውን መንፈሳዊ እንቅስቃሴው ነው፡፡ በዚህም ጥቅስ ውስጥ እንደቀረበው፣ በእነዚህ የተቃረኑ ኃያላት ዓብዩ ጌታ ምን ያህል ሊተመን የማይችል ኅይል እንዳለው ለመረዳት እንችላለን። “ይራመዳል እንዲሁም አይራመድም” በልምዳችን እንደምናየው አንድ ሰው ለመራመድ የሚችል ከሆነ፣ አይራመድም ማለት ቁም ነገር ያለው አነጋገር አይሆንም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ለዓብዩ ጌታ ስንጠቀምበት ግን፣ መራመድ ሳያስፈልገው መላ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ዓለምን ለመቆጣጠር፣ ምን ያህል ሊተመን የማይችል ኅይል እንዳለው ያስረዳናል፡፡ በዚህም በጠበበ አስተሳሰባችን፣ ይህንን ዓይነት የተቃረነ ሐሳብ በቀላሉ ልንረዳው አንችልም፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ስለ ዓብዩ ጌታ በአቅማችን መርምረን ልንደርስበት የቻልነው ዕውቀት ሁሉ፣ ያልተሟላ እና የተወሰነ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የዓብዩን ጌታ ሰብአዊነት የማይረዱት “ማያቫዲ” የሚባሉት ፈላስፎች የሚቀበሉት፤ የዓብዩ ጌታ ሰብአዊ ያልሆነ ኃይሉን ብቻ ሲሆን፣ እንደ ሰብአዊነቱ ደግሞ በመንፈሳዊ ዓለም ውስጥ የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ሳይቀበሉ በመከራከር ይኖራሉ፡፡ ቢሆንም ግን የብሀገቨድ ጊታ ተማሪዎች ደግሞ የዓብዩን ጌታ ደረጃ በትክክለኛ መንገድ በመረዳት፣ ወሰን የሌለውን ኅይል እንዳለው እየተቀበሉ፤ ሰብአዊ እና ሰብአዊ ያልሆነውን ኃይሉንም በትክክል ለይተው ያውቁታል፡፡ “ብሀገቨታ” ተብለው የሚታወቁት የዓብዩ ጌታ ትሑት አገልጋዮች፣ ዓብዩ ጌታ ኅይል ተመን ሳይኖረው “ዓብይ ጌታ” ለመባል እንደማይችል የተረዱ ናቸው፡፡
ገና ለገና ዓብዩ ጌታን እንደፈቃዳችን በቁሳዊ ዓይናችን ለማየት አልበቃንምና፣ ዓብዩ ጌታ በሰብአዊ ኃይሉ ሊኖር አይችልም ለማለት አንችልም፡፡ ሽሪ ኢሾፓኒሻድ ይህንን ዓይነት ሐሳብ በመቃረን፣ ዓብዩ ጌታ ከዚህ በጣም ሩቅ ሲሆን፣ በቅርባችን እንደሚገኝም ገልጾልናል፡፡ የዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ዓለም ከዚህ ከቁሳዊው ትዕይንተ ዓለም ባሻገር በጣም ርቆ የሚገኝ ነው፡፡ እኛም የመንፈሳዊ ዓለምን በአቅማችን ለመድረስ ይቅርና፣ ይህንን እኛ የምንገኝበትን ዓለማዊ ትዕይንተ ዓለም ለመለካት እንኳን ምንም ዓይነት አቅም የለንም፡፡ ይህ ቁሳዊው ትዕይንተ ዓለም ይህን ያህል ስፋት ያለው ከሆነ፣ ከዚያ ባሻገር ያለው የመንፈሳው ዓለም ምን ያህል ሊተመን እንደማይችል ለመገመት አያዳግትም፡፡ የዚህ የመንፈሳዊ ዓለምም ምን ያህል ርቀት እንዳለው በብሀገቨድ ጊታ ተገልጿል፡፡ (ብጊ 15፡6) ይሁን እንጂ ምንም እንኳን ዓብዩ ጌታ ከዚህ በጣም ርቆ የሚገኝ ቢሆንም፣ በፈለገው ጊዜ በቅጽበት እና ሴኮንድ እንኳን በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ከመንፈሳዊው ዓለም ወርዶ አጠገባችን መገኘት ይችላል፡፡ ይህም ፍጥነት ከንፋስ ሆነ ከሐሳባችን ፍጥነት በላይ ነው፡፡ መሮጥ ወይም መብረር ከፈለገም ማንም ሊደርስበት የማይችል ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህም ቀደም ሲል ባለው ጥቅስ ላይ ተጠቅሶልናል፡፡
ምንም እንኳን ዓብዩ ጌታ በገዛ ፈቃዱ ያለንበት ድረስ ቢመጣልንም እንኳን፣ ችላ ስንለው እንታያለን፡፡ ይህ ዓይነቱ በሞኝነት የተጠቃ ቸልተኝነት፣ በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ በዓብዩ ጌታ ራሱ ተወቅሷል፡፡ (9፡11) እንዲህም ብሎ ጠቅሶልናል፡፡ “በሞኝነት የተጠቁ ሰዎች ምድር በመጣሁ ጊዜ እኔንም እንደ ተራ ሰው ሟች አድርጎ በማየት፣ በንቀት ዓይን ሲመለከቱኝ ይታያሉ፡፡ “ዓብዩ ጌታ እንደ ተራ ሰው በሕልፈተ-ሕይወተ የሚጠቃ አይደለም፡፡ ወደ እኛ የሚመጣበትም ገላ፣ እንደ ተራ ሰው በቁሳዊ ንጥረ ነገሮች የተገነባ አይደለም፡፡ ዓብዩ ጌታ እንደ እኛ በቁሳዊ ገላው ወደ እዚህ ምድር ይመጣል ብለው የሚያምኑ ብዙ ምሁራን አሉ፡፡ እነዚህ ግን ሊተመን የማይቻል ኅይል እንዳለው የተረዱ አይደሉም፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ በሞኝነት የተጠቁ ሰዎች ዓብዩ ጌታን ከሰው እኩል ሲያነጻጽሩት ይገኛሉ፡፡
ዓብዩ ጌታ ልናስተውለው ከምንችለው በላይ ያለውን ልዑል ኅይል በመጠቀም፣ በማናቸውም መንገድ የምናቀርበውን ትሑት አገልግሎት ሲቀበል ይገኛል፡፡ ኃይሉንም እንዳሻው በመቀያየር ሊያሳየን ይችላል፡፡ እምነት የሚጎልባቸው ሰዎች እንደሚከራከሩትም ከሆነ፣ ዓብዩ ጌታ ወደምድር ሊመጣ አይችልም በማለት ይከራከራሉ። የሚመጣ ከሆነ ደግሞ እንደ ተራ ሰው ተወልዶ በቁሳዊ ገላ ብቻ ሊከሰት ይችላል ብለው ያምናሉ፡፡ ዓብዩ አምላክ ሊተመን የማይቻል ልዑል ኅይል እንዳለው በትክክል የተረዳን ከሆነ ግን፣ እንዲህ ዓይነት የክርክር ነጥቦች አንዳችም ፋይዳ እንደሌላቸው እንረዳለን፡፡ በሌላም ዘርፍ ስናየው ደግሞ፣ ዓብዩ ጌታ በቁሳዊ ገላ እንኳን የሚመጣ ቢሆን፣ ቁሳዊ ገላውን በቀላሉ ወደ መንፈሳዊ ገላ የመቀየር ኅይል አለው። የምናያቸው የቁሳዊ ሆነ የመንፈሳዊ ኅይል መነሻ፣ አንድ ዓብዩ ጌታ በመሆኑ፣ ይህ መነሻ እነዚህን ኅያል እንዳሻው ሊጠቀምባቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ዓብዩ ጌታ ”በአርቻ ቪግራሀ“ ምስሉ ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህም የአምላክ ምስል ከአፈር፣ ከድንጋይ ወይም ከእንጨት ለመሠራት የሚችል ነው፡፡ ምንም እንኳን እነዚህም የአምላክ ምስሎች በእንጨት ተፈልፍለው የተሠሩ ወይም ከድንጋይ እና ከሌላ ቁሳዊ ነገሮች የተሰሩ ቢሆኑም እንደ ተራ ጣዖት መታየት አይገባቸውም፡፡
በዚህ ጉድለት በተሞላበት ዓይን እና ዓለማዊ ኑሮ ውስጥ ሆነን፣ ዓብዩ ጌታን በቀጥታ ለማየት ኅይል የለንም፡፡ ቢሆንም ግን ዓብዩ ጌታን በቀጥታ ለማየት ለሚሹ ለትሑት አገልጋዮቹ፣ ዓብዩ ጌታ እንደሰው ቁሳዊ በመሰለ ገላው፣ በቀጥታ ሊከሰትላቸው እና የፍቅር አገልግሎታቸውን ሊቀበል ይችላል፡፡ ስለዚህ ምስሉን እንደ ጣዖት በመቁጠር፣ የዓብዩ ጌታን ምስል የሚያመልኩ ጀማሪ ወይም አዲስ አማኞች ናቸው ማለት አይገባንም፡፡ በቬዲክ ሥነጽሑፎች እንደተደነገገው፣ የሚያመልኩትም የዓብዩ ጌታን ምስል ነውና፡፡ ይህም ዓብዩ ጌታ በዚህ መንገድ በቀላሉ እንዲደርሱበት እና እንዲያመልኩት ይሁንታውን በፈቃዱ በመስጠቱ ነው፡፡ ይህንንም ሊረዳ የሚችለው ትሑት የዓብዩ ጌታ አገልጋዩ ብቻ ሲሆን፣ ከሃዲያን ግን ይህንን ሊረዱት አይችሉም።
በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ እንደተገለጸው (ብጊ 4፡11) ዓብዩ ጌታ እንዲህ በማለት ጠቅሶልናል። ዓብዩ ጌታ ለእያንዳንዱ ትሑት አገልጋይ ያለው አቀራረብ ምን ያህል እንደሆነ የሚወስነው የአገልጋዮቹ የፍቅር አቀራረብ ነው። ይህም ምን ያህል ልቦናቸውን እንደሰጡት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ዓብዩ ጌታ እንደፈቃዱ፣ በዓይናችን ወይም በልባችን ውስጥ ለመከሰት ወይም ላለመከሰት መብት አለው፡፡ ሆኖም፣ ልቦናቸውን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ የፍቅር አገልግሎት ለሚያቀርቡት ግን፣ በቀላሉ ሊከሰትላቸው ይችላል፡፡ በመሆኑም ሕሊናቸውን ለእርሱ ለሰጡ ሁሉ ከአጠገባቸው አይርቅም፡፡ በአንጻሩ፣ የፍቅር አንደበታቸውን ለእርሱ ላልሰጡ እና ለከሃዲያን ግን፣ በርቀት ሊተመን ከማይችል በላይ ርቆ ይገኛል፡፡ ፈጽሞ ሊደረሱበትም አይችሉም፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ መንገድ የቬዲክ ሥነጽሑፎች ሁለት ቃላትን በተደጋጋሚ ሲጠቅሱ እናያለን፡፡ እነዚህም “ሳጉና” ወይም ዓይነት እና “ኒርጉና” ዓይነት የሌለው ናቸው፡፡ እነዚህ በጣም አስፈላጊ ቃላት ናቸው፡፡ ሳጉና የሚለው ቃል የሚገልጸው ዓብዩ ጌታ የተወሰነ ዓይነት ባሕሪይን በፍቃዱ ይዞ ሲመጣ፣ የቁሳዊ ባሕሪ ይዞ በመምጣት፣ በተፈጥሮ ቁጥጥር ሥር ሆነ ማለት አይደለም፡፡ ለእርሱ በቁሳዊ እና በመንፈሳዊ ኅይል መሀከል ብዙ ልዩነት የለም፡፡ ምክንያቱም እርሱ የሁለቱም ኅይል መነሻ በመሆኑ ነው፡፡ የኅይል ሁሉ ምንጭ ሆኖ እያለ፣ እንደኛ በእነዚህ ኅይል ቁጥጥር ሥር ሊውል አይችልም። ይህ የቁሳዊ ትዕይንተ ዓለም የሚንቀሳቀሰው በእርሱ መሪነት ነው፡፡ በመሆኑም በእነዚህ ኅይል በቁጥጥራቸው ሥር ሳይሆን፣ ለፈለገው ዓላማ ሁሉ ሊያንቀሳቅሳቸው ይችላል። በዚህም ረገድ ሲታይ ዓብዩ ጌታ “ኒርጉና” ወይም “ዓይነት የሌለው” ተብሎ ሊታወቅ ይችላል፡፡ ይህ ሲባል ግን ምስል የሌለው ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም እርሱ በምስሉ ቀዳማዊ እንደመሆኑ፣ ምስሉም ለዘለዓለም ነባሪ ነው፡፡ ሰብአዊ ያልሆነው ክስተቱ ወይም “የብራህማን” ጮራ የሚባለውም፣ ከገላው የሚፈልቀው መንፈሳዊ ብርሃኑ ነው፡፡ ይህም ልክ ከፀሐይ ጌታ እንደሚመነጨው የፀሐይ ጮራ ይመሰላል፡፡
ፕራህላድ መሀራጅም በልጅነቱ ከሃዲ ከሆነው ከአባቱ ፊት ሲቀርብ፣ አባቱ እንዲህ ብሎ ጠይቆት ነበር፡፡ “አምላኬ አምላኬ የምትለው አምላክህ የት አለ፣ እስቲ አሳየኝ?” ፕራህላድም “ዓብዩ ጌታ በሁሉም ቦታ አለ ብሎ መለሰለት፡፡” ከሃዲ አባቱም “ይህ አምላኬ የምትለው ቤተመንግሥቱን በደገፈው ምሶሶ ውስጥ ይገኛል?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ልጁም “አዎን በምሶሶው ውስጥም በሁሉም ቦታ ይገኛል” ብሎ መለሰለት፡፡ በዚህም ጊዜ ከሃዲ አባቱ ከመቅጽበት ምሰሶውን በጎራዴው መትቶ ብትንትኑን አወጣው፡፡ በዚህም ጊዜ ዓብዩ ጌታ ከተሰበረው ምሶሶ ውስጥ “ንርሽማ ዴቭ” ተብሎ የሚታወቀውን ምስል ይዞ ብቅ አለበት፡፡ ይህ ምስል ከፊል ሰውን እና ከፊል አንበሳን የያዘ ነበር፡፡ ከዚያም ከከሃዲው አባቱም ጋር ትግል በመግጠም በመጨረሻም ሊገድለው በቃ፡፡ ከዚህም እንደምንረዳው ዓብዩ ጌታ በሁሉ ቦታ ይገኛል፡፡ ወሰን በሌለው ኃይሉም የተለያዩ ነገሮችን ማድረግ ይችላል፡፡ በዚህም ከቶም ሊተመን በማይቻል ኃይሉ በፈለገው ወቅት እና ቦታ ሁሉ፣ ትሑት አገልጋዩን ለማስደሰት መምጣት ይችላል፡፡ ጌታ “ነርሽምሀ” ከምሰሶው ውስጥ ፈልቅቆ የወጣው፣ በከሃዲው ንጉሥ ትእዛዝ ሳይሆን፣ በትሑት አገልጋዩ በፕራህላድ ምኞት ነው፡፡ ከሃዲ ሰው ዓብዩ ጌታ እንዲከሰትለት በመጠየቅ እንዲመጣ ሊያስገድደው አይችልም፡፡ ነገር ግን ዓብዩ ጌታ ትሑት አገልጋዩን ለማስደሰት፣ በማናቸውም ቦታ እና በማናቸው ጊዜ ቸርነቱን ሊያሳየው በመምጣት መከሰት ይችላል፡፡ በብሀገቨድ ጊታ በተመሳሳይ መንገድ እንደተገለጸውም (ብጊ 4፡8) ዓብዩ ጌታ ከሃዲያንን ለመደምሰስ እና፣ አማኝ አገልጋዮቹን ለመንከባከብ ወደ ምድር ይወርዳል፡፡ በእርግጥ እነዚህንም ከሃዲያን ለማጥፋት ዓብዩ ጌታ ብዙ ተወካዮቹን እና አገልጋዮቹን ወደ ምድር ይሰዳቸዋል፡፡ ቢሆንም ግን፣ ትሑት አገልጋዮቹን ለማስደሰት እርሱ ራሱ ወርዶ መምጣትም ደስታን ይሰጠዋል፡፡ ስለሆነም ወደዚህ ዓለም በፈቃዱ ወርዶ ይመጣል፡፡ ዋና ምክንያቱም ትሑት አገልጋዮቹን ለማስደሰት እንጂ ለሌላ ፍላጎት አይደለም፡፡
በብራህማ ሰሚታም እንደተገለጸው (ብሰ፡ 5፡35) ቀዳማዊው ጌታ “ጐቪንዳ” በከፊል ወገኑ በሁሉም ቦታ ውስጥ ገብቶ እና፣ በጠፈርም ውስጥ ተሰራጭቶ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በእያንዳንዳቸው አቶሞች ውስጥም ገብቶ ይገኛል፡፡ “ቪራት” በተባለው ቅርጹም በመላ ህዋ ውስጥ ሰፍኖ ይገኛል፡፡ “አንታርያሚ” በተባለው ቅርጹ ደግሞ፣ በሁሉም ነገር ውስጥ ገብቶ ይገኛል፡፡ አንታርያሚ ሆኖም ማናቸውንም ነገር ውስጥ የሚካሄደውን ነገር በሙሉ በመታዘብ ላይ ይገኛል፡፡ “ካርማ ፋላ” ተብሎ እንደሚታወቀውም እንደየሥራችን የሚገባንን ነገር ሁሉ ያቀርብልናል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ሕይወታችን ያደረግነውን ነገር ሁሉ እንረሳ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ዓብዩ ጌታ በውስጣችን ሠርጾ በመገኘት፣ ሁሉንም ነገር የሚታዘብ በመሆኑ የሥራችንን ውጤት ሁሉ እንደሚገባን አድርጎ ያቀርብልናል፡፡ በተፈጥሮ መቀበል የሚገባንንም ቅጣት ሁሉ በዚሁ አማካኝነት እናገኘዋለን፡፡
በእርግጥ መረዳት የሚኖርብን ነገር ቢኖር ዓብዩ ጌታ በሁሉም ነገር ውስጥ እና ከሁሉም ነገር ውጪ እንደሚገኝ ነው፡፡
ሁሉም ነገር የሚመነጨው በተለያዩት ኃይላቱ አማካኝነት ነው፡፡ የሙቀት እና የብርሃን ኅይል ከእሳቱ ተነጥለው እና በአንድነትም እንደሚገኙ ሁሉ፣ በዓብዩ ጌታ እና በተለያዩ ኃይላቱም መሀከል አንድነት አለ፡፡ ምንም እንኳን ይህ ውሕደት ቢኖርም፣ ዓብዩ ጌታ የራሱ የግሉ የሆነ ቅርጽን ወይም ምስልንም ይዞ ይገኛል፡፡ በዚህ በግል ምስሉ ወይም መንፈሳዊ ገላው ውስጥ እያለም በእያንዳንዶቹ አገልጋዮቹ ውስጥ የሚሰማቸውን ደስታ በማየት፣ እርሱም ይደሰታል፡፡