No edit permissions for Amharic

ማንትራ ስምንት

ሳ ፓርያጋክ ቹክራም አካያም አቭራናም
አስና ቪራም ሱድሀም አፓፓ ቪድሀም
ካቪር ማኒሲ ፓሪብሁህ ስቫያምብሁር
ያትሃታትሂያቶ ርትሀን ቭያዳድሃክ ቻስቫቲብህያህ ሳማብህያህ

ሳህ — ያ ሰው፣ ፓርያጋት — በእርግጥ ማወቅ አለበት፣ ሱክራም — ኅያል የሆነው፣ አካያም — ሥጋዊ ገላ የሌለው፣ አቭራናም — የማይደረስበት፣ አስናቪራም — ደምሥር የሌለው፣ ሱድሀም — ፀረ ጀርም፣ አፓፓ ቪድሀም — ለመከላከል የሚረዳ፣ ካቪህ — ዕውቅና ያለው፣ ማኒሲ — ፈላስፋ፣ ፓሪብሁህ — ከሁሉም በላይ የሆነ፣ ስቫያምብሁህ — በግሉ በቂ አቅም ያለው፣ ያትሀታትሂአታሀ — ይህን በመከተል፣ አርትሀን — የሚያስፈልጉ፣ ቭያዳድሀት — የሚሰጥ፣ ሳስቫቲብህያህ — ለማስታወስ ከሚያዳግት፣ ሳማብህያህ — ጊዜ

እንዲህም ዓይነቱ ሰው፣ ከሁሉም በላይ የላቀውን ዓብዩ ጌታን በትክክል ለመረዳት ብቁ ነው ማለት ነው፡፡ ዓብዩ ጌታ በሥጋዊ ገላ የማይወርድ፣ ሁሉንም ነገር ለማወቅ የማይሳነው፣ ሊደረስበት የማይችል፣ ያለ ደም ሥር ድጋፍ የሚኖር፣ ንጹሕ እና ሊበከል የማይችል፣ በራሱ ፍጹም የሆነ ፍልስፍና የሚጸና እና የሁሉንም ምኞት ለዘመናት ሲያሟላ የሚገኝ ነው፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥ የምናገኘው ገለጻ ላይ ፍጹም የሆነው የዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ እና ዘለዓለማዊ አካል እና ባሕሪ ተተንትኖ ቀርቦልናል፡፡ ዓብዩ ጌታ አካል የሌለው አይደለም፡፡ የእራሱ የሆነ መንፈሳዊ ቅርጽ እና አካል አለው፡፡ ይህም መንፈሳዊ አካል በተራው ቁሳዊ ዓለም ውስጥ እንደሚገኙት ዓይነት አካላት አይደለም፡፡ በዚህ ዓለም ውስጥ የሚገኙት የሕያው ፍጥረታት አካል ሁሉ፣ በግዑዝ ቁሳዊ ገላ የተሸፈኑ ናቸው፡፡ የሚንቀሳቀሱትም ልክ እንደ ቁሳዊ ማሽኖች ነው፡፡ የቁሳዊ ገላችን ሥነብልት ወይም የሠውነት አሰራር በሜካኒካል መንገድ የተገነቡ እና በደምሥር እና በሌላም የሰውነት አካላት የተሞሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን የዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ አካል በደምሥር እና በሌላ ቁሳዊ አካል የተገነባ አይደለም፡፡ በዚህ ጥቅስ እንደተጠቀሰው፣ በሥጋዊ አካል የተሸፈነ ገላ አይደለም፡፡ ይህም ማለት፣ በገላው እና በነፍሱ መሀል ምንም ልዩነት የለም፡፡ በተፈጥሮ አማካኝነትም እንደኛ ተገድዶ ከሥጋዊ ገላ ጋር የሚወለድ አይደለም፡፡ በቁሳዊ ዓለም ሕይወት ውስጥ እያለን፣ በነፍሳችን እና ሐሳባችንንም በሚጨምረው በቁሳዊ ገላችን መካከል ልዩነት አለ፡፡ ለዓብዩ ጌታ ግን በመንፈሳዊ አካሉ፣ በሐሳቡ እና በነፍሱ መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፡፡ መንፈሳዊ አካሉ ምሉእ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህም ማለት ሀሳቡ፣ ገላው እና ሁለመናው አንድ እና ምንም ልዩነት ያላቸው አይደሉም፡፡

በብራህማ ሰሚታ ውስጥም (ብሰ፡ 5፡1) ስለ ዓብዩ ጌታ እንደዚሁ የተመሳሰለ ገለጻ ቀርቦልናል። በዚህም በሚገኘው ጥቅስ ውስጥ፣ ዓብዩ ጌታ “ሳት ቺት አናንዳ” ተብሎ ተገልጿል። ይህም ማለት እርሱ መንፈሳዊ ኅይል ያለው እና ዘለዓለማዊ ቅርጽን የያዘ፣ ሙሉ ዕውቀት እና ሙሉ ደስታ ያለው ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ዓለም ውስጥ እንደሚያስፈልገን የተለየ ገላ ወይም ሐሳብ አያስፈልገውም፡፡ የቬዲክ መጻሕፍትም በግልጽ እንደሚያስተምሩን የዓብዩ ጌታ አካል ከእኛ ገላ ጋር ሲወዳደር ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ስለዚህም አንዳንድ ጊዜ አካል የሌለው ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የእኛን የመሰለ ሥጋዊ አካል የለውም ማለት ነው፡፡ በዚህም መንገድ በሐሳባችን ልንረዳው የማንችለው ዓይነት መንፈሳዊ አካል ይዞ ይገኛል። በብራህማ ሰሚታም (ብሰ፡ 5፡32) እንደተገለጸው፣ በእያንዳንዱ የገላው የስሜት ወገን፣ የፈለገውን ዓይነት ነገር ማድረግ ይችላል፡፡ ይህም ማለት ዓብዩ ጌታ በእጁ ሊራመድ ይችላል፡፡ በእግሩም የቀረበለትን መቀበል ይችላል፡፡ በእጆቹ እና በእግሮቹም ማየት ይችላል፡፡ በዓይኖቹም ወዘተ መብላት ይችላል፡፡ በሽሩቲ ማንትራዎች እንደተገለጸውም፣ ምንም እንኳን ዓብዩ ጌታ የእኛን የመሰለ ሥጋዊ እጅ እና እግር ባይኖረውም፣ ከእኛ የተለየ ዓይነት መንፈሳዊ እጅ እና እግር ግን አለው፡፡ በእነዚህም እጆቹ በፍቅር የምናቀርብለትን ሁሉ ይቀበላል፡፡ ከማናቸውም ፍጥረታት በላይም፣ በእግሮቹ መሮጥ ይችላል፡፡ ይህም ገለጻ በስምንተኛው ማንትራ ወይም ጥቅስ ውስጥ ለየት ባለ ቃል ተጠቅሷል፡፡ ይህም “ሱክራም” ወይም ምሉእ ኅይል ያለው ማለት ነው፡፡

ዓብዩ ጌታ፣ በቤተ መቅደስ ውስጥ ለስግደት እና ለአምልኮት የተቀመጠውን “የአርቻ ቪግራሀ” ምስልን ይዞ የሚቀርበው፣ እርሱን በትክክል ለተረዱት አቻርያዎች ወይም መምህራን እና አገልጋዮች ነው፡፡ ይህም የሚያስረዳን፣ በማንትራ ሰባት እንደተገለጸው፣ ዓብዩ ጌታ ራሱ ከዓብዩ ጌታ ምስል ጋር ምንም ልዩነት የለውም፡፡ የዓብዩ ጌታ ዋነኛው ምስል፣ የዓብዩ ጌታ የሽሪ ክርሽና ምስል ነው፡፡ ቢሆንም ሽሪ ክርሽና የተለያየ ቅርጾችን በመያዝ ተስፋፍቶ ይገኛል፡፡ እነዚህም እንደ ባላዴቭ፣ ራም፣ ንርሲምሀ እና ቫራሀ ወዘተ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ የተለያዩ የዓብዩ ጌታ ክስተቶች ሁሉ፣ ዓብዩ ጌታ ራሱ ናቸው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በቤተመቅደስ ውስጥም የምናያቸው የዓብዩ ጌታ “የአርቻ ቪግራሀ” ምስሎች ሁሉ፣ ከዓብዩ ጌታ ተነጥለው ሊታዩ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ከዓብዩ ጌታ ተስፋፍተው እና ለስግደት እርሱን ወክለው የቀረቡ በመሆናቸው ነው፡፡ እነዚህንም “የአርቻ ቪግራሀ” ምስሎችን በማምለክ፣ ዓብዩ ጌታን በቀጥታ ለማምለክ እና ለማገልገል ይቻላል፡፡ ዓብዩ ጌታ ምሉእ ኅይል የተሞላበት እንደመሆኑ፣ “ለአርቻ ቪግራሀ” ምስሎቹ እንኳን በፍቅር ከአገልጋዮቹ የሚቀርብለትን ነገር ሁሉ ተቀብሎ ይባርካል። “የአርቻ ቪግራሀው” ወይም ዓብዩ ጌታን የምናመልክበት ምስል የሚቀርብልን በአቻርያዎች፣ ወይም በመንፈሳዊ መምህራን እቅድ እና ፍላጎት ነው። ይህም “የአርቻ ቪግራሀ” ምስል ምሉእ ኅይል ያለው ዓብዩ ጌታን ወክሎ፣ ሆኖ እና ቀርቦ የሚገኝ ነው፡፡ በሞኝነት የተጠቁ እና የሽሪ ኡፓኒሻድ፣ የሽሩቲ ማንትራዎች መንፈሳዊ ዕውቀት የተሳናቸው ሰዎች ግን፣ ይህንን በአገልጋዮች የሚመለከውን “የአርቻ ቪግራሀ” ምስል ልክ እንደ ቁሳዊ አካል አድረገው ያዩታል፡፡ ይህ የአርቻ ቪግራሀ ምስል፣ በዓለማዊ ሕይወት በተበከለው ዓይናችን፣ በሞኝነታችን በካኒሽታ አዲካሪ መንፈሳችን ስናየው፣ ቁሳዊ ነገር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ቢሆንም ግን ያልተረዳነው ነገር ቢኖር፣ ዓብዩ ጌታ ምሉእ ኅያል እና ሁሉን ዐዋቂ በመሆኑ፣ ቁሳዊ ነገርን ወደ መንፈሳዊ እና መንፈሳዊ ነገርን ወደ ቁሳዊ ነገር እንደ ፍላጎቱ የመቀያየር ኅይል ያለው ነው፡፡

በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ (ብጊ 9፡11-12) ዓብዩ ጌታ እንደጠቀሰው፣ እርሱ ወደ ምድር በወረደ ቁጥር፣ በመንፈሳዊነት ደረጃ ብቁ ያልሆኑ ሰዎች እንደ ተራ ሰው አድርገው በንቀት ዓይን ይመለከቱታል፡፡ እነዚህ በመንፈሳዊ ንቃታቸው ያልዳበሩ ሰዎች፣ ዓብዩ ጌታ ምሉእ መንፈሳዊ ኅይል እንዳለው አይረዱም፡፡ በግምታዊ አንደበት ደግሞ፣ ዓብዩ ጌታን ለመረዳት ለሚሹ ሰዎች፣ ዓብዩ ጌታ ሙሉ ኃይሉን አይከስትላቸውም፡፡ ልቦናቸውን ለሰጡ ትሑት መንፈሳውያን ሰዎች ግን ዓብዩ ጌታ እንደ አቀራረባቸው ይከሰትላቸዋል፡፡ ወደ እዚህ ዓለም በውስን ሕይወት ውስጥ የገባነው ሕያው ፍጥረታት ሁሉ፣ ለዚህ ደረጃ የበቃነው ከዓብዩ ጌታ ጋር ያለንን ይህንን የመሰለውን ግንኙነት በመዘንጋታችን ነው።

በዚህ ማንትራ ወይም ጥቅስ እና በሌሎችም የቬዲክ ማንትራዎች በግልጽ እንደተጠቀሰው፣ ዓብዩ ጌታ ለሕያው ፍጥረታት የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ፣ ለዘመናት ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ አንድ ሕያው ፍጥረት አንዳንድ ነገሮችን ለማግኘት ፍላጎት ባደረበት ቁጥር፣ ዓብዩ ጌታ እንደብቁነቱ እና እንደሚገባው አድርጐ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ያቀርብለታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የበላይ የሕግ ዳኛ ለመሆን ከፈለገ፣ የሚያስፈልገውን ትምህርት መማር ብቻ ሳይሆን፣ የበላይ የሕግ ዳኝነቱን ማዕረግ የሚሰጠው ባለሥልጣን እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ዓይነት ማዕረግ ለማግኘት በትምህርቱ ብቁ ብቻ መሆን የሚበቃ አይደለም፡፡ በከፍተኛ ባለሥልጣን ማዕረጉ ከጊዜ በኋላ መሰጠት ይኖርበታል፡፡ በትምህርቱ መመረቅ ብቻ ሥልጣን ለመያዙ በቂ አይደለም፡፡ እንደዚህም ሁሉ ሕያው ፍጥረታት በመንፈሳቸው ብቁ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ የዓብዩ ጌታ ርኅራኄ እና በረከትም ያስፈልጋቸዋል፡፡

በመሠረቱ ብዙኃን ሕያው ፍጥረታት፣ ከዓብዩ ጌታ ምን መጠየቅ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ወይም ምን ዓይነት ደረጃ ላይ መሆን እንደሚገባቸው በትክክል የተረዱ አይደሉም፡፡ ቢሆንም ሕያው ፍጥረታት መሠረታዊ እና መንፈሳዊ ደረጃቸውን በትክክል ሲረዱ፣ ወደ መንፈሳዊ ዓለም በመግባት እና ከዓብዩ ጌታ ጋር በመሆን ትሑት አገልግሎታቸውን ለመቀጠል ይችላሉ፡፡ ያለመታደል ሆኖ ግን፣ ሕያው ፍጥረታት በቁሳዊ ዓለም ልቦና ምክንያት፣ በዓለማዊ የጋለ ፍላጎት ላይ ሲያተኩሩ ይገኛሉ፡፡ ይህም በብሀገቨድ ጊታ (ብጊ 2፡41) ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ በዚህም እንደተጠቀሰው ልቦናቸው እና አእምሮዋቸው የተከፋፈለ ነው፡፡ የመንፈሳዊ አእምሮ አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህም ዓብዩ ጌታን በፍቅር ማገልገል ነው። የቁሳዊ ዓለም ተራ አእምሮ እና ምኞት ግን፣ በብዙ የተከፋፈለ ነው፡፡ በሽሪማድ ብሀገቨታም (ሽብ 7፡5፡30-31) እንደተጠቀሰው፣ በዚህ ጊዚያዊ የቁሳዊ ዓለም ቁንጅና ልቦናው የተሳበ ሰው ሁሉ፣ የሕይወቱ ዋና ዓላማ ምን እንደሆነ የዘነጋ ነው፡፡ የሕይወታችን ዋና ዓላማ፣ ወደ ዓብዩ ጌታ የመንፈሳዊ ዓለም መመለስ ነው፡፡ ይህንንም በመዘንጋት፣ የሰው ልጅ በዚህ ዓለም ላይ፣ ደስታን ለማግኘት የተለያየ ጥረት እና እቅድ ሲያደርግ ይገኛል፡፡ ይህም የሚመሰለው፣ ልክ ታኝኮ የተተፋውን የሸንኮራ አገዳ እንደገና አንስቶ እንደማኘክ ማለት ነው፡፡ ቢሆንም ግን፣ ዓብዩ ጌታ በዚህ ዓለም ውስጥ እንድንቀጥል ጣልቃ ሳይገባ እንደፍላጐታችን ለመኖር መብቱን በቸርነቱ ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ በዚህ የሽሪ ኢሾፓኒሻድ ማንትራ ላይ እንደተጠቀሰው፣ ማንትራው ትክክለኛ የሆነ ቃልን በመጠቀም መልእክቱን ገልጾለታል፡፡ ይህም ቃል “ያትሀታትህያታ” የሚለው ነው፡፡ ይህም ማለት፣ ዓብዩ ጌታ ለሕያው ፍጥረታት ሁሉ እንደፍላጎታቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ያቀርብላቸዋል ማለት ነው፡፡ አንድ ሕያው ፍጥረት ወደ ሲኦል መሄድ ከፈለገ፣ ዓብዩ ጌታ ጣልቃ ሳይገባ መንገዱን ይከፍትለታል፡፡ ወይም ደግሞ ወደ መንፈሳዊው ዓለም ለመመለስ የሚፈልግ ከሆነ፣ ዓብዩ ጌታ መንገዱን በመክፈት ይመራዋል፡፡

በዚህ ጥቅስ ላይ እንደተጠቀሰው፣ ዓብዩ ጌታ “ፓሪብሁህ” ወይም ከሁሉም በላይ የሆነ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ከእርሱ ጋር እኩል ወይም የበላይ ሊሆን አይችልም፡፡ ሌሎች ሕያው ፍጥረታት ደግሞ፣ ዓብዩ ጌታን ለጥቅማቸው የሚለምኑ ናቸው፡፡ ዓብዩ አምላክም ሕያው ፍጥረታት የሚለምኑትን ነገር ሁሉ ያቀርብላቸዋል፡፡ እነዚህም ሕያው ፍጥረታት ከዓብዩ ጌታ ጋር በኃይላቸው እኩል ቢሆኑ ኖሮ፣ ወይም ምሉእ ኅይል እና ምሉእ ዕውቀት ያላቸው ቢሆን ኖሮ፣ ከዓብዩ ጌታ ለጥቅማቸው የሚለምኑት ነገር አይኖርም ነበር፡፡ ከዚህ ቁሳዊ ዓለምም ነጻ ለመውጣትም አይለምኑም ነበር፡፡ ትክክለኛው ነጻነት ማለት፣ ወደ መንፈሳዊው ዓለም መመለስ ማለት ነው፡፡ በዓብዩ ጌታ ዓብይ ሰብአዊነት የማያምኑ ሁሉ፣ ይህ ዓይነቱ ነጻነት ምን እንደሆነ በትክክል የተረዱ አይደሉም፡፡ በቁሳዊ ዓለም ውስጥ ስሜታቸውን ለማርካት በጉጉት ላይ ያሉ ሁሉ፣ በዚሁ ስቃይ በተሞላበት ዓለም ውስጥ ለዘለዓለም በመኖር ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም የመንፈሳዊ ደረጃቸውን በትክክል የተረዱ ሁሉ፣ ወደ መንፈሳዊው ዓለም ለመመለስ ይበቃሉ፡፡ ራሱን በራሱ የቻለ እና ከማንም ጠለላ የማያስፈልገው ዓብዩ ጌታ ብቻ ነው፡፡

ዓብዩ የመንግሥተ ሰማያቱ ጌታ ሽሪ ክርሽና፣ ወደ እዚህ ዓለም ከ5000 ዓመታት በፊት መጥቶ የነበረ ጊዜ እንደ ዓብይነቱ ሙሉ ኃይሉን ለመላ ዓለም አሳይቶ ነበረ፡፡ ይህንንም ያሳየው በተለያዩ ታሪካዊ ድርጊቶቹ ነው፡፡ በልጅነቱም ከፍተኛ ሰይጣናዊ ኅይል የነበራቸውን አጋንንት ሁሉ ለማጥፋት እና ለመግደል በቅቶ ነበር፡፡ እነዚህም እንደ አጋሱራ፣ ባካሱራ እና ሻካታሱራን የመሳሰሉት አጋንንት ናቸው፡፡ ልጅ ሆኖም እያለ፣ ይህንን ሁሉ ያደረገውም ምንም ዓይነት ጉልበትን ሳያባክን ነበር፡፡ የጐቨርድሀንን ተራራ በእጁ ወደላይ ሲያነሳው፣ ምንም ዓይነት የአካል ማጎልመሻ ልምድ አስፈልጎት አልነበረም፡፡ ከጐፒዎቹም ጋር እንዳሻው ደስታ በተሞላበት “የራሳ ዳንስ” ላይ ሲሰማራ ከኅብረተሰቡ ምንም ዓይነት የቁጥጥር ጫና አልነበረውም፡፡ ምንም እንኳን የጎፒዎቹ አቀራረብ፣ በትዳር ላይ እያሉ የፍቅር አቀራረብ ቢሆንም፣ ከሽሪ ክርሽና ጋር የነበራቸው ግንኙነታቸው፣ በሽሪ ቼታንያ መሀ ፕራብሁ የሚመለክ ነበር፡፡ ይህም ምንም እንኳን ሽሪ ቼታንያ መሀ ፕራብሁ የመነኩሴ ሥርዓትን እና መመሪያዎችን በጥብቅ የሚከታተል ቢሆንም እንኳን ማለት ነው፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ ሽሪ ኡፓኒሻድ እንደሚገልጸው ዓብዩ ጌታ “ሹድሀም” ወይም ፀረ ህዋሳት እና “አፓፓ ቪድሀም” ወይም ህዋሳትን እንደሚከላከል አድርጐ ገልጾታል፡፡ ፀረ ህዋሳት ተብሎ የተጠቀሰውም ንጹሕ ያልሆኑ ነገሮች እንኳን ከእርሱ ጋር ሲገናኙ ንጹሕ እንደሚሆኑ ለመግለጽ ነው፡፡ ህዋሳትን የሚከላከል የሚለው አባባል የቀረበውም፣ ዓብዩ ጌታ ያለውን ንጹሕ የማድረግ ኅይል ለመግለጽ ነው፡፡ በብሀገቨድ ጊታ እንደተገለጸው (ብጊ 9፡30–31) በመጀመሪያ ደረጃ ትሑት አገልጋይ “ሱ ዱራቻራ” ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ማለት በፀባዩ ሥርዓት የሌለው ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን ወደ ትክክለኛ መንፈሳዊ ፈለግ ከተመለሰ፣ እንደ ንጹሕ አገልጋይ መቆጠር ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም በትክክለኛ መንፈሳዊ ክልል ውስጥ መሰማራት ስለጀመረ ነው፡፡ ይህም ህዋሳትን እንደሚከላከለው የአምላክ ባሕሪ ምሳሌ እንደተሰጠው ነው፡፡ ዓብዩ ጌታ “አፓፓ ቪድሀም” ተብሎም ይታወቃል፡፡ ይህም ማለት ምንም ዓይነት ኃጢያት ሊያጠቃው አይችልም፡፡ ምንም እንኳን ኃጢያት በመሰለ ነገር ላይ የተሰማራ ቢመስለንም፣ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ንጹሕ እና ጥሩ ነው፡፡ በኅጢአትም ፈጽሞ ሊጠቃ አይችልም፡፡ ምክንያቱም እርሱ በሁሉም ደረጃ “ሱድሀም” ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ንጹሕ የሆነ ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜም ከፀሐይ ጋር ይመሰላል፡፡ ፀሐይ ርጥበትን ከቆሸሸ እና ከበሰበሰ ቦታ በማትነን፣ አካባቢው ንጹሕ እንዲሆን ታደርገዋለች። ሆኖም ግን ፀሐይ ሁልጊዜ ንጹሕ ሆና ትገኛለች፡፡ ፀሐይ ባላት ኅይል ብዙ የተበከሉ ስፍራዎችን ታፀዳለች፡፡ ታድያ ይህች አንድ ቁሳዊ ፀሐይ በመላ ዓለም ውስጥ ለማጽዳት ይህንን ያህል ኅይል ካላት፤ የዓብዩ ጌታ የማጽዳት ኃይሉ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ለመገመት አያዳግተንም፡፡

« Previous Next »