መግቢያ
“የቬዳዎች ትምህርት”
[በክቡር አ. ቻ. ብሀክቲቬዳንታ ስዋሚ ፕራብሁፓድ በኮንዌይ አዳራሽ በለንደን ከተማ እንግሊዝ አገር ውስጥ እኤአ በኦክቶበር 6 በ1969 ዓ.ም. የተሰጠ ትምህርት]
ክቡራት እና ክቡራን በዛሬው ዕለት የምንሰጠው የትምህርት ርዕስ ስለ ቬዳዎች ይሆናል፡፡ ቬዳዎች ምንድን ናቸው? በሳንስክሪት ቋንቋ ቬዳ የሚለው የግስ ቃል በተለያዩ ፍቺዎች ሊገለፅ የሚችል ቃል ነው፡፡ ፍሬነገሩ ግን አንድ ነው፡፡ በመሰረቱ ቬዳ ማለት እውቀት ማለት ነው፡፡ ማናቸውም ዓይነት የምንቀስመው እውቀት ሁሉ ቬዳ ተብሎ ሊሰየም ይችላል፡፡ ምክንያቱም የሁሉም ዓይነት እውቀት መሰረት ወይንም መነሻው የቬዳ እውቀት በመሆኑ ነው። ቢሆንም ግን በዚህ በቁሳዊ ዓለም ውስጥ በመኖር ላይ እያለን የምንቀስመው አንዳንድ ዓለማዊ እውቀት ትክክለኛ እና ጥራት የሚጎድለው ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡ ይህም ዓይነቱ እውቀት ፍፁም ባለመሆኑ ስህተትን ለማድረግ እና ወደ ጉድለት የተሞላበት እውቀት ሊያጋልጠን ይችላል፡፡ በዚህ ዓለም ውስጥ በዚህ ትውልድ ውስን በሆነው ሕይወታችን ላይ ያለች ነፍስ እና ሌላ በሕይወቷ ነፃ በሆነችው ነፍስ መሀከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ልዩነታቸውም በዚህ ዓለም ውስጥ የተፈጠረችው እና በውስን ኑሮ የተጠመደችው የሰው ልጅ ነፍስ በአራት ዓይነት ጉድለቶች የምትጠቃ ናት፡፡ የመጀመሪያው ጉድለት የሰው ልጅ ነፍስ ስህተትን በማድረግ የምትጠቃ ፍጡር ናት፡፡ ለምሳሌ በሕንድ አገር ውስጥ ይኖር የነበረው ማህተመ ጋንዲ እንደ ታላቅ ሰው በጣም የገነነ ነበረ፡፡ ቢሆንም ግን ልክ እንደ ሌላው ሰው ለተለያዩ ስህተቶች የተጋለጠ ነበረ፡፡ ለምሳሌ በሕይወቱ መጨረሻ ላይ ረዳቱ እንዲህ ብሎ አስጠንቅቆት ነበረ፡፡ “ወደ ኒው ደልሂ ለስብሰባ ዛሬ ባትሄድ ይሻላል፡፡ ምክንያቱም ከጐደኞቼ እንደሰማሁት ከሆነ አንተ ወደ ስብሰባ በምትሄድበት ወቅት ለሕይወትህ አስጊ ጊዜ በመሆኑ ነው፡፡” እርሱ ግን ይህንን ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ለመሄድም በፀና መንገድ ስለወሰነ ወደ ስብሰባው መሄዱ ለመገደል አበቃው፡፡ ስለዚህ እንደ ማህተመ ጋንዲ፣ ፕሬዚደንት ኬኔዲ የመሳሰሉት ሌሎች ብዙዎች ታላላቅ ሰዎችም ሁሉ ታላላቅ እና ታዋቂ ይሁኑ እንጂ ስህተቶችን ለማድረግ የተጋለጡ ነበሩ፡፡ ስህተት ማድረግ ለሰው ልጅ በተፈጥሮው የሚገኝ ባህርዩ ነው፡፡ ይህም ለስህተት መጋለጥ በዚህ ቁሳዊ ዓለም ውስጥ ለተፈጠረችው እና በውስን ኑሮ ለተጠመረችው ነፍስ አንዱ ድክመቷ ነው፡፡
ሌላው ጉድለት ደግሞ በሀሰታዊ ራእይ መጠመድ ነው፡፡ የሀሰት ራእይ ማለትም ያልሆነውን ነገር “የሆነ ነው” ብሎ ማሰብ ወይም መቀበል ማለት ነው፡፡ ይህም በሳንስክሪት ቋንቋ “ማያ” ይባላል፡፡ ማያ ማለት “ያልሆነ” ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ሁሉም ሰው ቁሳዊ ገላውን እንደ ራሱ አድርጐ ተቀብሎት ይገኛል፡፡ ለምሳሌ አንተ ማን ነህ ተብለን ብንጠየቅ “እኔ ሚስተር ጆን ነኝ፣ እኔ ሀብታም ሰው ነኝ፣ እኔ እንዲህ ነኝ፡፡” በማለት እንመልሳለን፡፡ እነዚህ መልሶች ሁሉ ግን ከቁሳዊ ገላችን ማንነት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ቢሆንም ግን እኛ ወይንም ነፍስ ቁሳዊ ገላ አይደለንም፡፡ ቁሳዊው ወይም ሥጋዊ ገላችን ነን ማለት ደግሞ የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡
ሶስተኛው የውስን ነፍስ ወይንም የሰው ልጅ ጉድለት ደግሞ የማታለል ባህሪ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ሌላውን ሰው የማታለል አዝማምያ አለው፡፡ አንድ ሰው ምንም እንኳን በአንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሞኝ ሰው ቢሆንም እንኳን ራሱን ልክ እንደ አዋቂ አድርጐ የማቅረብ ባህርይ አለው፡፡ ይህም ዓይነት ሰው ምንም እንኳን በሀሰታዊ አመለካከት የተጠመደ እና ለስህተት የተጋለጠ መሆኑ ቢታወቅም እንዲህ በማለት ላይ ይገኛል፡፡ “ይህ እኮ እንደዚህ ነው፡፡ ይህ እንደዚህ መሆን አለበት፡፡” በዚህም ዓይነት አቀራረብ ምንም እንኳን እርግጠኛ ቢመስልም የሚገኝበትን መንፈሳዊ ደረጃ እንኳን የማያውቅ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ሙያው እና እውቀቱም እንከን የተሞላበት ቢሆንም እንኳን ራሱን ልክ እንደ አዋቂ ሰው በማቅረብ የፍልስፍና መፃህፍቶችን ሲፅፍ ይገኛል፡፡ አንዱ የሰው ልጅ ድክመትም ይህ ነው። ይህም ደግሞ የማታለል ባህርይ ይባላል፡፡
አራተኛው ጉድለት ደግሞ ለሰው ልጅ እውቀትን ሊሰጡት የሚችሉት የስሜት አካላት ሁሉ ፍፁም እውነት የሆነ መረጃ ሊሰጡት የማችሉ በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ዓይኖቻችን በሚሰጡን የማየት ሀይል በጣም ኩራት የሚሰማን ልንሆን እንችላለን፡፡ አንዳንድ ግዜም ሰዎች ሲከራከሩን ይታያሉ፡፡ “አምላክን ልታሳየኝ ትችላለህ?” ይሁን እንጂ ለመሆኑ አምላክን ለማየት የሚችል ዓይን አለን ብለን እናምናለን? አምላክን ለማየት የሚችል ዓይን ከሌለንም ፈፅሞ ልናየው አንችልም፡፡ ያለንበትም ክፍል በድንገት ጨለማ ቢሆን ዓይኖች እያሉን የገዛ እጃችንን እንኳን ለማየት አንችልም። ታድያ ምን ዓይነት የማየት ሀይል አለን እና ነው አምላክን በእርቃነ ዓይናችን ለማየት የምንደፍረው? ስለዚህ እነዚህ ጉድለት የተሞላባቸው ስሜቶቻችን በመተማመን ፍፁም የሆነውን መንፈሳዊ እውቀት ለመረዳት አዳጋች መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። በዚህ በውስን ቁሳዊ ሕይወታችን ውስጥ እነዚህ ሁሉ ጉድለቶች እያሉን ፍፁም ትክክል የሆነ መንፈሳዊ እውቀትንም ለመስጠትም አንችልም፡፡ ምክንያቱም ፍፁም እንከን የለሽ ሰዎች ባለመሆናችን ነው፡፡ ስለዚህም ከዓብዩ ጌታ የመነጩትን የቬዳን እውቀቶች ልክ እንደቀረቡት በመቀበል መረዳት ይጠበቅብናል፡፡
”ቬዳዎች ከሕንድ አገር ስለመነጩ የሂንዱዎች እውቀት ናቸው፡፡“ ብለን እናስብ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ “ሂንዱ” የሚለው ቃል ለህንድ አገር እንግዳ ነው፡፡ በቬዳዎች ውስጥም ይህ ቃል ፈፅሞ አይገኝም። የቬዲክ ተከታዮችም ሂንዱ ተብለው ሊሰየሙ አይገባቸውም፡፡ ትክክለኛው ስያሜ ግን “ቫርና አሽራማ” ነው፡፡ የ”ቫርና አሽራማ” ቃል የሚወክለው የቬዳ ተከታዮችን ነው፡፡ ይህም የሰው ልጅ በስምንት ዓይነት ክፍፍል እንደሚመራ የሚቀበሉ ናቸው፡፡ አራት ዓይነት ማህበረ ሰቦች እና አራት ዓይነት የመንፈሳዊ ሕብረተሰቦች ይገኛሉ፡፡ ይህም ቫርና አሽራማ ይባላል፡፡ ይህም በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ (4፡13) እነዚህም ክፍፍሎች በዓብዪ ጌታ እንደመፈጠራቸው በሰው ልጅ ሕብረተሰብ ውስጥ ሁሉ ይታያሉ፡፡
አራቱ ማህበረ ሰቦች ብራህማና፣ ሻትርያ፣ ቫይሽያ እና ሱድራ ተብለው ይታወቃሉ፡፡ “ብራህማና” የሚባሉት በተለይ መንፈሳዊ እውቀት የተሞላባቸው የሕብረተሰቡ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህም “ብራህማን” ወይንም መንፈስ ምን እንደሆነ በትክክል የተረዱ ናቸው፡፡ “ሻትርያ” የሚባሉት ደግሞ የአስተዳደር ክፍል ውስጥ የተሰማሩ ናቸው፡፡ እነዚህም ከብራህማናዎች ቀጥሎ አዋቂ ተብለው የሚታወቁት የሕብረተሰቡ አካላት ናቸው፡፡ ከዚያም “ቫይሽያ” ተብለው የሚታወቁት የንግድ እና የእርሻ የሕብረተሰብ አካላት ናቸው፡፡ በአራተኛ ደረጃም “ሱድራ” የሚባሉት የቀን ሰራተኞችን ያጠቃልላል፡፡ እነዚህም አራቱ ክፍፍሎች በሰው ልጅ ሕብረተሰብ ውስጥ የሚታዩ ናቸው፡፡ ይህም በቬዲክ እውቀት የቀረበ የሕብረተሰብ ክፍፍል እንደመሆኑ እንደቀረበልን እንቀበለዋለን፡፡ የቬዲክ እውቀት እና መመሪያ ፍፁም የሆነ እውቀት እንደመሆኑ በቅፅበት ልንቀበለው የሚገባ እውቀት ነው፡፡ ይህ የቬዲክ እውቀት ከዓብዩ አምላክ የመነጨ እንደመሆኑም ምንም ዓይነት ጉድለት የማይታይበት ነው፡፡ የግል ትርጉም ሳናካትትበት ልክ እንደቀረበልን ልንቀበለው የሚገባ እውቀት ነው፡፡ ለምሳሌ በሕንድ አገር ውስጥ የላም እበት ልክ እንደ ንፁህ ነገር የሚወሰድ ነው፡፡ ቢሆንም ግን የላም እበት ልክ እንደ ሌላው የእንስሳ ፍግ ነው፡፡ በቬዲክ መፃህፍት ውስጥ እንደተገለፀውም አንድ ሰው ምንም ዓይነት የእንስ ፍግ ወይንም ዓይነ ምድርን የነካ ከሆነ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ከማቅረቡ በፊት ገላውን መታጠብ እንዳለበት ነው፡፡ በሌላው የቬዲክ እውቀት ወገን ደግሞ የላም እበት ልክ እንደ ንፁህ ነገር ተደርጎ ተጠቅሷል፡፡ እንዲያውም ንፁህ ባልሆነ አካባቢ ላይ የላም እበት ቢለቀለቅ ንፁህ ያልሆው ቦታ ንፁህ ለመሆን እንደሚበቃ ተጠቅሷል፡፡ ተራ በሆነ አመለካከት ስናየው ግን ይህ የተቃረነ አስተሳሰብ ይመስለናል፡፡ ቢሆንም ግን የተቃረነ አመለካከት ይመስላል እንጂ በቬዳዎች ስለተገለፀ ስህተት ሆኖ አይገኝም፡፡ በካልካታ ከተማ ውስጥ አንድ ታዋቂ ሳይንቲስት እና ዶክተር የላም እበት ላይ ምርምር አድርጐ ነበር፡፡ የምርምሩም ውጤት እንዳሳየውም የላም እበት የፀረ ህዋሳት ንጥረ ነገር እንዳለው ተደርሶበት ነበር፡፡
በሕንድ አገር ውስጥ አንድ ሰው “ይህን ማድረግ አለብህ፡፡” ብሎ ከተናገረ ሌላው ደግሞ “ምን ማለትህ ነው? ያለ ክርክር ይህንን ትእዛዝህን መቀበል ያለብኝ ይህ ትእዛዝ በቬዲክ የተደነገገ በመሆኑ ነው?” ብሎ ይመልሳል፡፡ የቬዲክ መመሪያዎች ሌላ የሰው ልጅ ትርጉም ወይንም ማብራሪ አያስፈልጋቸውም፡፡ እነዚህንም የቬዲክ እውቀቶች በጥሞና ተከታትለን የምንማር ከሆነ ትክክለኛ መሆናቸውን ለመረዳት እንበቃለን፡፡
ቬዳዎች የሰው ልጅ በግል ጥረቱ እውቀቱን አቀነባብሮ የመዘገባቸው አይደሉም፡፡ የቬዲክ እውቀቶች የመጡት ከመንፈሳዊው ዓለም ነው፡፡ ይህም ማለት ከዓብዩ ጌታ ከሽሪ ክርሽና ነው፡፡ የቬዳዎች ሌላኛው ስም “ሽሩቲ” ተብሎ ይታወቃል፡፡ ”ሽሩቲ“ ማለትም በማዳመጥ የተገኘ እውቀት ማለት ነው፡፡ በምርምር እና በሙከራ የተገኘ ትምህርትም አይደለም፡፡ “ሽሩቲ” ማለትም ልክ እናታችንን በጥሞና እንደማዳመጥ ይመሰላል፡፡ ከልጅነት ጀምሮ ከእናታችን ብዙ እውቀትን ስንወስድ እንገኛለን፡፡ ለምሳሌ አባታችን ማን እንደሆነ ለማወቅ ከፈለግን ከማን ትክክል መልስ ለማግኘት እንችላለን? ለዚህም መልስ ለመስጠት እናታችን ባለስልጣን ናት፡፡ እናታችን በቀና መንፈስ ይህ አባታችሁ ነው ካለች መልእክቱን በቀጥታ መቀበል ይኖርብናል፡፡ አባታችን ስለመሆኑም የተለየ ምርምር ማድረግ አያስፈልገንም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ከልምዳችን ውጪ የሆነውን ነገር ለማወቅ ሲያስፈልገን፤ ወይንም በሙከራ እና በምርምር ለማወቅ የሚያዳግተንን ነገር ለመረዳት ስንሻ፤ ወይንም ስሜቶቻችን ሊገልፁልን ከሚችሉት በላይ ለማወቅ ከፈለግን፣ የቬዳዎችን እውቀት መቀበል እና መረዳት ያስፈልገናል፡፡ እነዚህ እውቀቶችም ምንም ዓይነት ምርምር አያስፈልጋቸውም፡፡ ምክንያቱም ለረጅም ዘመናት ስኬታማ ስለመሆናቸው በሙከራ እና በልምድ የታወቁ ናቸው፡፡ እውነታቸውም የተረጋገጠ ነው፡፡ ይህም ልክ እናት ስትሰጠው እንደቆየችው እውቀት ይመሰላል፡፡ እናታችን በጥሩ አንደበት ያለሀሰት የምትሰጠንን በሙከራ እና በልምድ የቀሰመወችውን እውቀት እንደ ተረጋገጠ እውነት ብንቀበል ይረዳናል፡፡ ሌላው መንገድ አድካሚ ሊሆን ይችላል፡፡
ቬዳዎች እንደ እናት ይቆጠራሉ፡፡ ጌታ ብራህማ ደግሞ እንደ አያት ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም የቬዲክ እውቀት ለመጀመሪያ ግዜ የተሰጠው በጌታ ብራህማ በመሆኑ ነው፡፡ መላው ቁሳዊ ጠፈር ከመፈጠሩ በፊት በመጀመሪያ ደረጃ የተፈጠረው ፍጡር ጌታ ብራህማ ነበር፡፡ ይህንንም የቬዲክ እውቀት ከዓብዩ ጌታ ከቀሰመ በኋላ ለናራዳ እና ለሌሎች ደቀመዝሙሮቹ እንዲሁም ለልጆቹ አስተላለፈ፡፡ እነርሱም በድርሻቸው ለሌሎች ደቀመዝሙሮች እና ለልጅ ልጆቻቸው ይህንኑ እውቀት አስተላለፉ፡፡ በዚህም መንገድ የቬዲክ እውቀት የድቁና ስርዓቱን ተከትሎ ለዘመናት ለመተላለፍ በቃ፡፡ በብሀገቨድ ጊታ ቅዱስ መፅሀፍ ውስጥም የቬዲክ እውቀት ይህንን ስርዓት በመከተል ለዘመናት ትምህርቱ እንደተላለፈ ተገልጿል፡፡ የቬዳንም እውቀት ለመፈተን ሙከራ ብናደረግም፣ ውጤቱ የተለየ ሊሆን የማይችል እና ከተሰጠውም ድምደማ ውጪ ሊሆን የማይችል ነው፡፡ ግዜያችንን ላለማባከን ግን የቬዲክ እውቀትን እንዳለ መቀበል ይኖርብናል፡፡ አባታችን ማን እንደሆነ ለማወቅ ከፈለግን እና እናታቻችንን እንደ ታማኝ ባለ ስልጣን የምናያት ከሆነ የምትነግረንን ሁሉ ያለ ምንም ክርክር መቀበል ይበጀናል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ሶስት ዓይነት መረጃ የማግኘት ፈለጎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በሳንስክሪት ቋንቋ “ፕራትያክሻ፣ አኑማና እና ሻብዳ” ተብለው ይታወቃሉ፡፡ “ፕራትያክሻ” ማለት በቀጥታ የሚታይ ወይንም የሚገኝ መረጃ ማለት ነው፡፡ በቀጥታ የሚታይ ወይንም የሚገኝ መረጃ ሁልግዜ አስተማማኝ እና ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በስሜቶቻችን አማካኝነት የሚገኝ መረጃ በመሆኑ እና ዓለማዊ ስሜቶቻችንም ፍጹም የሆነ እውቀት ሊሰጡን ስለማይችሉ ነው፡፡ ለምሳሌ ፀሀይን በቀን በቀን እናያታለን፡፡ የምትታየንም ልክ እንደ ትንሽ ክብ ሰሀን ሆና ነው፡፡ በእውነቱ ግን ፀሀይ ከብዙ የተለያዩ ፕላኔቶች በላይ በጣም ትልቅ የሆነች ናት፡፡ ስለዚህ በቀጥታ ዓይተን የተረዳነው አስተሳሰብ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል አይደለም፡፡ የሚገባውን እውቀት ለመቅሰምም መፃህቶችን ማንበብ ያስፈልገናል፡፡ በዚህም መንገድ ስለ ፀሀይ ለመረዳት እና ትክክለኛ እውቀቱን ለማግኘት እንችላለን፡፡ ስለዚህ ስሜቶቻችንን ተመክተን በቀጥታ የምናገኛቸው እውቀቶች ሁሉ ትክክለኛ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ የሚቀጥለውም መረጃ የማግኘት ፈለግ “አኑማና” የሚባል ሲሆን ይህም በምርምር ተጠንቶ አንድ የተወሰነ ንድፈ ሀሳብ ላይ የደረስንበት እውቀት ሊሆን ይችላል፡፡ “እንዲህ ሊሆን ይችላል፡፡” የሚል ያልተረጋገጠ መረጃም ወይንም ፅንሰ ሀሳብ ሊኖረን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የዳርዊን ፅንሰ ሀሳብ እንደሚያሳየን “ይህ እንዲህ ሊሆን ይችላል፡፡” የሚል አቀራረብ አለው፡፡ ይህ ሳይንስ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ዓይነቱ ፅንሰ ሀሳብ የተመራማሪውን አስተያየት የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ይህም ፍፁም የሆነ እውነትን ይዞ ላይገኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን እውቀትን ስልጣን ካላቸው ሰዎች የምንወስድ ከሆነ ትክክለኛ መረጃ ልናገኝ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ብዙውን ግዜ የራድዮ ጣብያ መልእክቶችን አምነን ስንቀበል እንገኛለን፡፡ ብዙውን ግዜ ሳንጠራጠር ወይንም መረጃውን ለማረጋገጥ ሙከራ ሳናደርግ በቀጥታ እንቀበለዋለን፡፡ ይህም የሚያሳየን መልእክቱ የመጣው ስልጣን ያለው ከሚመስል ምንጭ እና፤ ለሰፊው ሕዝብ እንደ እውነታ ተመስሎ በመቅረቡ አምነን እንቀበለዋለን፡፡
የቬዲክ እውቀት “ሻብዳ ፕራማና” ይባላል፡፡ ሌላው ስሙ ደግሞ “ሽሩቲ” ነው፡፡ ሽሩቲ ማለት በማዳመጥ መተላለፍ የሚገባው እውቀት ማለት ነው፡፡ ቬዳዎችም እንደሚያስተምሩን መንፈሳዊ እውቀትን ለመረዳት የምንችለው ስልጣን ካላቸው መንፈሳውያን ስንቀበለው እና መልእክቱንም በጥሞና በማዳመጥ ስንከታተለው ነው፡፡ የመንፈሳዊው እውቀት ከዚህ የቁሳዊው ጠፈር ባሻገር የሚመጣ ነው፡፡ በዚህ ቁሳዊው ዓለም ውስጥ የሚገኘው እውቀት ዓለማዊ ሲሆን ከዚህ ቁሳዊ ጠፈር ባሻገር የሚገኘው እውቀት ደግሞ መንፈሳዊ እውቀት ነው፡፡ ይህንንም ፍፁም እውቀት ለማግኘት ወደ መንፈሳዊው ዓለም ተሻግሮ ለመሄድ ይቅርና ወደ ቁሳዊ ዓለማት ጠፈር መጨረሻ እንኳን ለመድረስ አንችልም፡፡ ስለዚህ የተሟላ ፍፁም እውቀትን በዝውውር ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡
የመንፈሳዊ ሰማይ ከዚህ ቁሳዊ ዓለም ባሻገር ይገኛል፡፡ ይህም መንፈሳዊ ዓለም በተደጋጋሚ ከሚከሰተው እና አንዳንድ ግዜ ከማይከሰተው የቁሳዊው ዓለም ፍጥረት የተለየ ዓለም ነው፡፡ ታድያ ስለዚህ ስለ መንፈሳዊው ዓለም ሕያውዎቹ እና ፕላኔቶቹ እንዲሁም ዘለዓለማዊ ስለሆኑት የመላ መንፈሳዊ ዓለማት መረጃ ከየት ልናገኝ እንችላለን? ይህም ዓይነት እውቀት ሁሉ በቬዳዎች ውስጥ ተተንኖ ቀርቦልናል፡፡ ቢሆንም ግን እንዴት አድረገን ተመራምረን ልናረጋግጠው እንችላለን? ይህም የማይቻል ነገር ነው፡፡ ስለማይቻልም የቬዳን እውቀት ልክ በዓብዩ ጌታ እንደቀረበው በመቀበል ስለዚህ መንፈሳዊ ዓለም ለመረዳት እንችላለን፡፡ ይህም የቬዲክ እውቀት ይባላል፡፡ በክርሽና ንቃተ ማህበራችንም የምንቀበለው እውቀት ሁሉ ከፍተኛ ስልጣን ካለው ከቬዳዎች የመነጨ ነው፡፡ ይህም እውቀት የመነጨው መንፈሳዊ ስልጣን ካለው ዓብዩ ጌታ እና ፈጣሪ ሽሪ ክርሽና ነው፡፡ ሽሪ ክርሽና ከሁሉም የሰው ልጅ ክፍፍሎች በላይ የሆነ ዓብዩ ባለ ስልጣን ነው፡፡ በዚህ ምርድ ላይ ሁለት ዓይነት መንፈሳውያን ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያው መንፈሳውያን “ማያቫዲ” ተብለው የሚታወቁት እና ዓብዩ ጌታ የሰብአዊ ባህርይ የለውም ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ እነዚህም ሳንካራ አቻርያ በተባለው የቀድሞ መምህር ትምህርቶች የሚመሩ እና “ቬዳንቲስት” ተብለው የሚታወቁት ናቸው፡፡ ሌሎቹ መንፈሳውያን ደግሞ “ቫይሽናቫዎች” ተብለው ይታወቃሉ፡፡ እነዚህም እንደ “ራማኑጃ አቻርያ፣ ማድሀቫ አቻርያ፣ ቪሽኑ ስዋሚ” የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡ እነዚህ ሁለቱም፣ የሳንከራ ሳምፕራዳያ (የድቁና ስርዓት) እና የቫይሽናቭ ሳምፕራዳያ፤ ሽሪ ክርሽና ዓብዩ የመንግስተ ሰማያት ጌታ እንደመሆኑ በማረጋጥ የተቀበሉ ናቸው፡፡ ሳንከራ አቻርያ በዓብዩ ጌታ ሰብአዊነት የማያምን እና ዓብዩ ጌታ ሰብአዊ አካል እንደሌለው የሚሰብክ ነበረ፡፡ ሲያስተምር የነበረውም ዓብዩ ጌታ የሰብዓዊነት ባህርይ የሌለው ዓብይ መንፈስ ነው በማለት ነው፡፡ ቢሆንም ግን ለይምሰል ነበር እንጂ በውስጡ የዓብዩ ጌታን መፈሳዊ ሰብአዊነት የሚያምን ነበረ፡፡ በብሀገቨድ ጊታ ላይ በሰጠውም ገለፃ ላይ እንዲህ ብሎ ፅፎ ነበረ፡፡ “ናራያን ወይም ዓብዩ የመንግስተ ሰማያት ጌታ የሚገኘው ከቁሳዊው ሕዋ ባሻገር ነው፡፡“ ከዚያም በኋላ እንዲህ ብሎ ደምድሞ ነበረ፡፡ ”ይህም ዓብዩ የመንግስተ ሰማያት ጌታ ናራያን ወይንም ሽሪ ክርሽና ነው፡፡ ሽሪ ክርሽና ወደ እዚህ ምድር የቫሱዴቭ እና የዴቫኪ ልጅ ሆኖ መጥቶ ነበረ፡፡” በእዚህም ጥቅስ እንደምናየው በተለይ የሽሪ ክርሽናን እናት እና አባት ስም በግልጽ ጠቅሶ ነበረ፡፡ እንደዚህም ሁሉ ሁለቱም ዓይነት መንፈሳውያን ሽሪ ክርሽናን እንደ ዓብዩ የመንግስተ ሰማያት ጌታነቱ ተቀብለውት እናያለን፡፡ በክርሽና ንቃተ ማህበራችን ውስጥ የመንፈሳዊ እውቀታችን መነሻ ብሀገቨድ ጊታ ነው፡፡ ይህም ትምህርት የመጣው በቀጥታ ከሽሪ ክርሽና ነው፡፡ ብሀገቨድ ጊታንም “እንደተዘመረው” ብለን አትመነዋል፡፡ ምክንያቱም የክርሽናን መልእክት የምንቀበለው ልክ በሽሪ ክርሽና እንደተነገረው ወይንም እንደተዘመረው ሳንቀይር ነው፡፡ ሽሪ ክርሽና የተናገረውን መልእክት ሁሉ ልክ እንዳለ ባለመቀየር እንቀበለዋለን፡፡ ይህም የክርሽና ንቃት ይባላል፡፡ በቀጥታ መቀበላችንም ጊዜያችንን እንዳናባክን አድርጐናል፡፡ እውቀትን ከሚታመን እና ስልጣን ካለው ምንጭ የምንወስድ ከሆነ ግዜያችንን ሳናባክን መረጃውን በቀጥታ በመውሰድ በእውቀታችን ለመዳበር እንችላለን፡፡ በዚህ ዓለም ላይ እውቀትን ለማግኘት ስንሻ ሁለት ዓይነት ፈለጎችን እናገኛለን፡፡ እነዚህም በምርምር የተደረሰባቸው እና ከበላይ ባለስልጣን የምንወስዳቸው እውቀቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የሰው ልጅ እንደሚሞት ሁላችንም የምንቀበለው ነገር ነው፡፡ አባታችን የሰው ልጅ ሟች ነው ይለናል፡፡ እናታችን የሰው ልጅ ሟች ነው ትለናለች፡፡ ሁሉም ሰው የሰው ልጅ ሟች ነው ይለናል፡፡ ሆኖም ግን እያንዳንዱ ሰው መሞት ወይንም አለመሞቱን ለማረጋገጥ ሙከራ ሲያደርግ አይታይም፡፡ የሰው ልጅ ሟች እንደሆነ ግን ያለምንም ጥርጥር ተቀብለነው እንገኛለን፡፡ ሰው ሟች መሆን አለመሆኑን ምርምር ለማድረግ ከፈለግን ግን እያንዳንዱን ሰው መመርመር ሊያስፈልገን ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ሊሞት የማይችል ሰው ሊኖር ይችል ይሆናል እስካሁንም አላየነውም ብለን ልናስብ ስለምንችል ነው፡፡ ይህም ዓይነቱ ምርምር መጨረሻ ሊኖረው የማይችል ነው፡፡ በሳንስክሪት ቋንቋ ይህ ዓይነቱ ስርዓት “አሮድሀ” ወይንም በምርምር ሊገኝ የማይችል እውቀት ይባላል፡፡ ስለዚህ ፍጹም እውቀትን በግላችን ምርምር ለመረዳት ጉድለት የተሞላባቸውን ስሜቶቻችንን በመጠቀም የምናገኛቸው እውቀቶች ሁሉ ወደ ትክክል ድምደማ ላይመሩን ይችላሉ፡፡ ፍፁም የሆነውን መንፈሳዊ እውቀትን በዚህ ዓይነት መንገድ ለማግኘት አንችልም፡፡
በብራህማ ሰሚታ መዝሙር ውስጥ እንዲህ አይነት ጥቅስ ይገኛል፡፡ “እንደ ሀሳባችን ፍጥነት በሚመጥቅ አይሮፕላን ላይ ተጓዙ፡፡” በምድራችን ላይ የሚገኙት ፈጣን አይሮፕላኖች ከ2000 ማይል በላይ በሰዓት ውስጥ ሊበሩ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ፍጥነት ጋር በማመሳከር የሚገኘው የሀሳባችን ፍጥነትስ ምን ያህል ነው? በቤታችን ውስጥ ተቀምጠን ሀሳባችን ወደ ሕንድ አገር በቅፅበት ልናበረው እንችላለን፡፡ ይህም ከ10,000 ማይል በላይ ርቀት ሊኖረው የሚችል ይሆናል፡፡ ከዚያም ተመልሶ ሀሳባችን ወደ ቤት በቅፅበት ለመመለስ ይችላል፡፡ ሀሳባችን በቅጽበት እዚያ ደርሶ ለመመለስ ችሏል። ይህንንም ስንመለከት የሀሳባችን ፍጥነት ሊደረስበት የማይችል እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህም በቬዲክ መፃህፍት እንደተገለፀው “በዚህ ዓይነቱ ፍጥነት ለሚሊዮን ዓመታት እንኳን የምንጓዝ ቢሆን የመንፈሳዊውን ዓለም ወሰን ልንደርስበት አንችልም፡፡” ይህንንም መንፈሳዊ ዓለም በዚህ ዓይነቱ ጉዞዋችን ልንደርስበት ወይም ልንረዳው የሚያዳግት ነው፡፡ ስለዚህ የቬዲክ መመሪያዎች እንደሚገልፁልን ይህንን እውቀት ለማግኘት ታማኝ የሆነውን መንፈሳዊ መምህር መቅረብ ይኖርብናል፡፡ ይህም መምህር “ጉሩ” ይባላል፡፡ በዚህም ገለፃ ላይ “በግዴታ” የሚለው ቃል ተጠቅሷል፡፡ ይህስ መንፈሳዊ መምህር ማሟላት የሚገባው ነገር ምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ የቬዲክ እውቀትን በትክክል የድቁና ስርዓትን ተከትሎ ከመጣ መምህር የተቀበለ መሆን አለበት፡፡ በተግባርም በብራህማን ወይንም በመንፈሳዊ አገልግሎት የተሰማራ መሆን ይገባዋል። እነዚህ ሁለት ባህርዮች እንዲኖረው ያስፈልገዋል፡፡ አለበለዛ ግን ታማኝ መንፈሳዊ መምህር ሊሆን አይችልም፡፡
የዚህ የክርሽና ንቃተ ማህበር እንቅስቃሴያችን በቬዲክ መመሪያዎች ስልጣን ስር የሚተዳደር ነው፡፡ በብሀገቨድ ጊታም ሽሪ ክርሽና እንዲህ ብሎ ገልፆልናል፡፡ “የቬዲክ እውቀት ዓላማ ሽሪ ክርሽናን በትክክል ለመረዳት ነው፡፡” በብራህማ ሰሚታም እንዲህ ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ “ሽሪ ክርሽና መጠን የሌለው የተለያዩ ቅርፆች አሉት፡፡ ቢሆንም ግን ሁሉም የተለያዩ ቅርጾች ይሁኑ እንጂ አንድ ናቸው፡፡” የዓብዩ ጌታ አካል እንደኛ ወዳቂ አካል ወይንም ሥጋዊ የሰውነት አቋም የያዘ አይደለም፡፡ የዓብዩ ጌታ አካል ወይንም የሰውነት አቋም ፈራሽ አይደለም፡፡ የእኔ የሰውነት አካል መነሻ ያለው ነው፡፡ የእርሱ የሰውነት አቋም ግን መነሻ ወይንም መጀመሪያ የለውም፡፡ “አናንታ” ወይንም ዘላለማዊ ተብሎም ይታወቃል፡፡ ወሰን የሌለውም የተለያዩ የሰውነት ቅርፆች እና አካላት አሉት፡፡ የእኔ ሥጋዊ ገላ እዚህ በስራ ቦታዬ የተቀመጠ ከሆነ በቤቴ ውስጥ ሊገኝ አይችልም፡፡ አንተም እዚህ ተቀምጠህ የምትገኝ ከሆነ በቤትህ ውስጥ ልትኖር አትችልም፡፡ ቢሆንም ግን ሽሪ ክርሽና በሁሉም ቦታ በአንድ ግዜ መገኘት የሚችል ነው፡፡ በጐሎካ ቭርንዳቫን መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ተቀምጦ በሁሉም ቦታ በአንድ ግዜ ውስጥ መገኘት ይችላል፡፡ በሁሉም ቦታ ተስፋፍቶ ለመገኘት የሚችል ዓብይ ሀይል ያለው ፈጣሪ ነው፡፡ የሁሉም ዋነኛ እና ከሁሉም በፊት የነበረ እና ቀዳማዊ ይሁን እንጂ የሽሪ ክርሽናን ምስል በስእል ላይ ስታዩት ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ሀያ ዓመት የሚመስል የወጣትነት መልክ ያለው ነው፡፡ እርጅና የተሞላበት የክርሽናን ስእል ልታገኙ አትችሉም፡፡ ለምሳሌ ሽሪ ክርሽና እንደ ሰረገላ ነጂ ተመስሎ የተሳለውን የብሀገቨድ ጊታን መፅሀፍ ሽፋን አይታችሁት ይሆናል፡፡ በዚያን ግዜም ሽሪ ክርሽና ከ100 ዓመት ያነሰ እድሜ አልነበረውም፡፡ በምድር ላይ ወርዶ በነበረበት ወቅት የልጅ ልጆችም በዚያን ግዜ የነበረው ነው፡፡ ቢሆንም ግን በዚያን ግዜ የነበረው መንፈሳዊ ገላ ወጣትን የሚመስል ነበር፡፡ ሽሪ ክርሽና ወይንም ዓብዩ ጌታ እርጅና እደደ ሰው ልጅ ሊያጠቃው የሚችል አይደለም፡፡ ይህም ዓብይ ሀይሉ ነው፡፡ የቬዲክ ስነፅሁፎችንም በግል በማጥናት ስለ ሽሪ ክርሽና ለመመራመር ወይንም ለመረዳት ብትሞክሩ ግራ ልትጋቡ ወይም ልትደናገሩ ትችሉ ይሆናል፡፡ ለመረዳት ብትችሉ እንኳን በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከትሁት አገልጋዩ ወይንም ከመንፈሳዊ መምህር ይህንኑ ትምህርት በመቀበል በቀላሉ ልትረዱት ትችላላችሁ፡፡ መምህሩም ወይንም የሽሪ ክርሽና ትሁት አገልጋይ ሽሪ ክርሽናን በቀላሉ እንድትረዱት ሊረዳችሁ ይችላል፡፡ “ሽሪ ክርሽና ይህን የመሰለ እና የዚህ ዓይነት ሀይል ያለው ነው፡፡” በማለት በቀላሉ ለማስረዳት ይችላል፡፡ የሽሪ ክርሽናም ትሁት አገልጋይ የማስረዳት አቅም ይህንን ይመስላል፡፡
በቀድሞ ግዜ አንድ የቬዳ እውቀት ብቻ ነበረ፡፡ የቬዳ እውቀትንም ለማንበብ አስፈላጊነት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በቀድሞ ግዜ ሰዎች በጣም አዋቂ ስለነበሩ እና የማስታወስ ችሎታቸውም በጣም ከፍ ያለ ስለነበረ አንድ ግዜ ቬዳን ከመንፈሳዊው መምህር ካዳመጡ የመረዳት እና በእድሜያቸው ሁሉ የማስታወስ ችሎታ ነበራቸው፡፡ የቬዳንም ፍሬ ነገር እና ገለፃውንም በትክክል የመረዳት ችሎታ ነበራቸው፡፡ ነገር ግን ከ5,000 ዓመታት በፊት ሽሪላ ቭያሳዴቭ የቬዳን እውቀት በሙሉ በመፅሀፍ ላይ አሰፈራቸው፡፡ ይህንንም ለማድረግ የተገደደው ለዚህ ካሊ ዩጋ ተብሎ ለተሰየመው ዘመን ደካማ ሕብረተሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዘመን ውስጥ የሚወለዱ ሰዎች ሁሉ እድሜያቸው በጣም ያጠረ፣ የማስታወስ ችሎታቸውም በጣም የወደቀ እና አእምሮዋቸውም ያልዳበረ ሰዎች እንደሚሆኑ በትንቢት ስለሚያውቅ ነበር፡፡ ስለዚህም እንዲህ በማለት ገልፆ ነበር፡፡ ”ይህንን የቬዲክ እውቀት ለወደፊት ትምህርት እንዲሆን በመፅሀፍ ላይ ማስፈር ይገባኛል፡፡“ ከዚያም የቬዲክ እውቀትን በአራት ከፋፈላቸው፡፡ እነዚህም ርግ ቬዳ፣ ሳማ ቬዳ፣ አትሀርቫ ቬዳ እና ያጁር ቬዳ ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ከዚያም እነዚህን የቬዳ ርእሶች ለተለያዩት ተከታዮቹ እና ደቀ መዛሙርቶቹ እንዲያስተምሩ አከፋፈላቸው፡፡ ከዚያም በቬዲክ እውቀት አእምሮዋቸው ደከም ላለው የሕብረተሰብ አካሎች ማሰብ ጀመረ፡፡ እነዚህም “ስትሪ፣ ሱድራ እና ድቪጃ ባንድሁ” ተብለው ይታወቃሉ፡፡ እነዚህም ”ስትሪ“ ወይንም የሴቶች ሕብረተሰብን፣ ”ሱድራ“ ወይንም የቀን ሰራተኞችን እና ”ድቪጃ ባንድሁ“ ተብለው የሚታወቁትን የብራህማና ወይንም የቀሳውስት ልጆችን ያጠቃልል ነበር፡፡ ድቪጃ ባንድሁ የሚባሉት ”ብራህማና“ ከሚባሉት የተከበሩ ቀሳውስቶች ቤት የተወለዱ ቢሆኑም በቀሳውስት ደረጃ ተምረው እና ሰልጥነው ማእረግ የያዙ አልነበሩም፡፡ አንድ ሰው በብራህመና ወይንም በቄስ ቤት ተወልዶ በቀሳውስት እውቀት እና ልምድ ያላደገ ከሆነ ”ድዊጃ ባንድሁ“ ተብሎ ይታወቃል፡፡ እንደዚህ ለመሳሰሉት የሕብረተሰብ አካሎችም ሽሪላ ቭያሳዴቭ ”መሀ ብሀራት (መብ)“ እና ”18 ፑራናዎች (ፑራ)“ የተባሉትን የቬዲክ መፃህፍት አዘጋጅቶ አቀረበ፡፡ መሀ ብሀራት ስለ ሕንድ አገር የቀድሞ ታሪክ የሚገልፅ ነው፡፡ እነዚህም መፃህፍቶች የቬዲክ ስነፅሁፍ አካል ናቸው፡፡ ”ፑራናዎች፣ መሀ ብሀራት፣ አራቱ ቬዳዎች፣ ኡፓኒሻድ“ የሚባሉት ሁሉ የቬዳ ስነፅሁፍ አካል ናቸው፡፡ ከዚያም ሽሪላ ቭያሳዴቭ ለታላላቅ መምህራን እና ለፈላስፋዎች የሚሆን የቬዲክ እውቀት ማጠቃለያን ”ቬዳንታ ሱትራ“ በሚባለው ስነፅሁፍ ውስጥ አዘጋጅቶ አቀረበ፡፡ ይህም የቬዳዎች ሁሉ የማጠቃለያ ስነፅሁፍ ነው፡፡
ሽሪላ ቭያሳዴቭ ይህንን የቬዳንታ ሱትራ ሊመዘግብ የበቃው ከመምህሩ ወይም “ከጉሩ መሀራጁ” ከናራዳ ሙኒ የተሰጠውን ትእዛዝ በመቀበል ነው፡፡ ቢሆንም ግን ይህንንም ከፃፈ በኋላ በአፃፃፉ ልቡ ሊረካበት የሚደርስ ደረጃ ላይ አልደረሰም ነበረ፡፡ ይህም በሽሪማድ ብሀገቨታም መፅሀፍ ውስጥ የተገለፀ ረጅም ታሪክን የያዘ ነው፡፡ ቬዳ ቭያስ ምንም እንኳን ፑራናዎችን፣ ኡፓኒሻድ እና ቬዳንታ ሱትራን ፅፎ ቢያቀርብም ልብን የሚያረካ ደረጃ ላይ አልደረሰም ነበር፡፡ ይህንን ድክመት አይቶ መምህሩ ናራዳ ሙኒ እንዲህ ብሎ አዘዘው፡፡ ”ቬዳንታ ሱትራ የሚባለውን የቬዳዎች ማጠቃለያ ተንትነህ አቅርበሀል፡፡“ ቬዳንታ ማለት ከሁሉም በላይ የሆነ እውቀት ማለት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የሆነው እውቀት ደግሞ ስለ ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና የሚገልፅ እውቀት ነው፡፡ ሽሪ ክርሽናም እንደገለፀልን የቬዳዎች እውቀት ዓላማ እርሱን በትክክል እንዲረዱት መሆን አለበት፡፡ ”ቬዳይስ ቻ ሳርቬር አሀም ኤቫ ቬድያህ“ ከዚያም ቀጥሎ ሽሪ ክርሽና እንዲህ ብሏል፡፡ ”ቬዳንታ ክርድ ቬዳ ቪድ ኤቫ ቻሀም“ ይህም ማለት “ቬዳዎችን ሁሉ አቀነባብሬ ያቀረብኩ እኔ ነኝ፡፡ የቬዳዎችንም እውቀት እና ዓላማም በግልፅ የማውቀው እኔው ነኝ፡፡” ስለዚህ የቬዲክ እውቀቶች ሁሉ ዓላማ ሽሪ ክርሽናን ለማወቅ ነው፡፡ ስለዚህም ድምደማ በሁሉ የቬዳንታ ፍልስፍና ውስጥ በተለያዩ የቫይሽናቫ ገለፃዎች ውስጥ ተጠቅሰው እናገኛቸዋለን፡፡ የእኛም የጐድያ ቫይሽናቫዎች የቀድሞ መምህራን በቬዳንታ ፍልስፍና ውስጥ ያቀረቡት ገለፃ አለ፡፡ ይህም በባላዴቭ ቪድያብሁሸና የተፃፈ እና “ጐቪንዳ ብሀስያ” ተብሎ የተሰየመው ገለፃ ነው፡፡ እንደዚህም ሁሉ ራመኑጃ አቻርያ የራሱን ገለፃ አቅርቧል፡፡ ማድሀቫ አቻርያም ገለፃ አቅርቧል፡፡ የቀረበልንም ገለጻ “ሳንከራ አቻርያ” የፃፈው ገለፃ ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ የቀረቡ የቬዳንታ ገለፃዎች ይገኛሉ፡፡ ቫይሽናቫዎችም ቀደም ብለው የቬዳንታን ገለፃ ስላላቀረቡ በቀድሞ ግዜ ብዙ ሰዎች የሻንከራ አቻርያ ገለፃ ብቻ የቀረበ ይመስላቸው ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ሽሪላ ቭያሳዴቭ የቬዳንታን ገለፃ በትክክል አቅርቦት ነበር፡፡ ይህም የሽሪማድ ብሀገቨታም ይባላል፡፡ የሽሪማድ ብሀገቨታምም እንዲህ በሚል ቃል የቬዳንታን ሱትራን ገለፃ ጀምሮት ነበር፡፡ “ጃንማዲ አስያ ያትሀ” ይህም “ጃንማዲ አስያ ያትሀ” ብሎ የሚጀምረው ጥቅስ በሽሪማድ ብሀገቨታም ውስጥ በትንተና ተገልጿል፡፡ የቬዳንታ ሱትራ ገለፃ የሚያተኩረው “ብራህማን” ወይንም “ፍፁም መንፈሳዊ እውነት” ምን እንደሆነ ነው፡፡ “ይህም ፍፁም መንፈሳዊ እውነት የሚባለው ሁሉም ነገር የሚመነጭበት መነሻ ነው፡፡” የሽሪማድ ብሀገቨታም ገለፃ የቪዲክ እውቀት የማጠቃለያው ዝርዝር ነው፡፡ ሁሉም ነገር ከፍፁም እውነት ከሆነው የሚመነጭ ከሆነ፤ የዚህስ ፍፁም እውነት ባህርይ ምንድን ነው? ይህም በሽሪማድ ብሀገቨታም ውስጥ በትንተና ተገልጿል፡፡ ይህም ፍፁም መንፈሳዊ እውነት ንቁ እና ለመንፈሳዊነት ብቁ ሊያደርገን የሚችል መሆን አለበት፡፡ ከዚህም መንፈሳዊ እውቀት ፍፁም የሆነ የእውቀት ብርሀን የሚመነጭ መሆን አለበት፡፡ “ስቫ ራት” በዚህም ቁሳዊ ዓለም ውስጥ የእኛ እውቀት ሊዳብር የሚችለው ከመንፈሳዊ መምህራኖቻችን ትምህርትን በመቅሰም ነው፡፡ በፍፁም መንፈሳዊ እውነታ ለተዋበው ዓብዩ ጌታ ግን ይህ የእውቀት ብርሀን ከራሱ የሚመነጭ ሆኖ የሚገኝ ነው፡፡ ቬዳንታ ሱትራ የቬዲክ እውቀት ሁሉ ማጠቃለያ ነው፡፡ ይህም ቬዳንታ ሱትራ ሽሪማድ ብሀገቨታም በተባለው መፅሀፍ ውስጥ በፀሀፊው ተተንትኖ ቀርቧል፡፡ ስለዚህ በመጨረሻ ልንጠይቅ የምንሻው ነገር ቢኖር የቬዲክ እውቀትን ለማጥናት ፍላጎት ያላቸው ሁሉ የቬዲክ እውቀትን ዝርዝር ማጠቃለያ ሽሪማድ ብሀገቨታምን እና ብሀገቨድ ጊታን በማንበብ ለመረዳት እንዲበቁ በትህትና እናሳስባለን፡፡