ሽሪ ኡፓኒሻድ
-
መቅድመ ማንትራ: ዓብዩ ጌታ ፍጹም እንከን የሌለው እና በሁሉም ረገድ ሁለንተናው የተሟላ ሆኖ የሚገኝ ነው፡፡ ፍጹም የተሟላ እና ፍጹም እንከን የሌለው በመሆኑም፣ በዚህ ቁሳዊ ዓለም ላይ በእርሱ የተፈጠሩ ሁሉ፣ ከእርሱ የሚመነጩ ፍጥረታት እንደመሆናቸው፣ ሁለንተናቸው የተሟላ ሆነው የተቀነባበሩ እና እንከን የለሽ ሆነው የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ፍጹም ሙሉእ ከሆነው ከዓብዩ ጌታ የተፈጠሩ ሁሉ፣ በሁሉም ረገድ የተሟሉ ሆነው ተፈጥረዋል። ዓብዩ ጌታ ፍጹም የተሟላ አካል የያዘ በመሆኑም፣ ምንም እንኳን ብዙ የተሟሉ አካላት ከእርሱ የሚፈጠሩ ቢሆኑም፣ እርሱ ለዘለዓለም ሳይጎድል፣ ሁለንተናው የተሟላ ሆኖ ይኖራል፡፡” (ሽሪ ኡፓኒሻድ መቅድመ ማንትራ)
ማንትራ አንድ: በዚህ ቁሳዊ ጠፈር ውስጥ የሚገኙ የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ፍጥረታት ሁሉ የዓብዩ ጌታ ሀብት የሆኑ እና በእርሱ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው ቢሆን በዚህ ዓለም ውስጥ የሚገኙትን ፍጥረታት ሁሉ የዓብዩ ጌታ ሀብት እንደመሆናቸው በመገንዘብ፣ የሚያስፈልገውን ብቻ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ እነዚህም ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሁሉ፣ በተፈጥሮ ለእያንዳንዱ ፍጥረታት የተመደቡ ናቸው። ከዚህ ድርሻ በላይ የተረፈውን ሀብት የማን እንደሆነ በመገንዘብ፣ ከሚገባን በላይ ለመውሰድ ጥረት ማድረግ አይገባንም።፡
ማንትራ ሁለት: ይህንንም ዓይነት ሕይወት በመከተል፣ አንድ ሰው ለብዙ መቶ ዓመታት ለመኖር መሻት ይችላል፡፡ ከተወሰነለት ድርሻው በላይ ሳይወስድ በመሥራትም፣ ከተፈጥሮ የካርማ ወይም የተፈጥሮ ሕግ የመጣስ መተሳሰር ነጻ ሊሆን ይችላል፡፡ ከካርማ ነጻ ለመሆን፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ከዚህ ዓይነቱ ጥንቃቄ ውጪ ሌላ ምንም አማራጭ አይኖርም፡፡
ማንትራ ሦስት: ይህንን ብርቅ የሆነውን የመንፈሳዊ አገልግሎት የመስጠት ዕድላቸውን የሚያባክኑ እና የከሀዲያን መንፈስ ያላቸው ሰዎች ሁሉ፤ ልክ እንደ ነፍስ አጥፊዎች የሚቆጠሩ ሲሆን፤ ከሞትም በኋላ እምነት ወደሚጎድልባቸው ዓለማዊ ፕላኔቶች ያመራሉ፡፡ እነዚህም ፕላኔቶች የመንፈሳዊነት ድንቁርና፣ ጨለማነት እና ስቃይ የተሞላባቸው ናቸው፡፡
ማንትራ አራት: ዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ፣ ምንም እንኳን በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ በሚገኘው መኖሪያው ሁሌ የሚገኝ ቢሆንም ከሐሳብ የበለጠ ፍጥነት ያለው እና ማናቸውም ዓይነት ቅልጥፍና ሊወዳደሩ የማይችሉት ነው፡፡ ከፍተኛ ኅይል ያላቸው መላእክት ፈጽሞ ሊወዳደሩት አይችሉም። በመንግሥተ-ሰማያት ውስጥ በአንድ ቦታ ላይ ተቀምጦም፤ መላ ተፈጥሮን እንደ አየር እና ዝናብ የመሳሰሉትን ሁሉ ሲቆጣጠር ይገኛል፡፡ በመሆኑም ከማናቸውም ዓይነት ቅልጥፍና፣ የበላይ ሆኖ ይገኛል።
ማንትራ አምስት: ዓብዩ ጌታ የሚራመድ ቢሆንም በፈቃደ ኃይሉ የማይራመድም ሆኖ የሚገኝ ነው፡፡ በጣም በርቀት የሚገኝ ቢሆንም፣ በቅጽበት በቅርባችንም ሆኖ ሊገኝ የሚችል ነው፡፡ በሁሉም ነገር ውስጥ ገብቶ የሚገኝ ቢሆንም፣ ከሁሉም ነገርም ውጪ በመሆን የሚገኝ ዓብይ ጌታ ነው።
ማንትራ ስድስት: በዓለም ላይ የሚገኙትን ነገሮች በሙሉ ከዓብዩ ጌታ ጋር አዛምዶ የሚያይ፤ በምድር የሚገኙት ፍጥረታት በሙሉ የዓብዩ ጌታ ከፊል እና ቁራሽ መሆናቸውን የተገነዘበ፤ ዓብዩ ጌታም በሁሉም ነገር ውስጥ የሚገኝ እንደሆነ የተረዳ ሁሉ፣ ምንም ነገርን ወይም ማናቸውንም ፍጥረታት ሊጠላ አይችልም፡፡
ማንትራ ሰባት: ሕያው ፍጥረታት ሁሉ የዓብዩ ጌታ ከፊል ቅንጣቢ ሆነው፣ ከዓብዩ ጌታ ጋርም በዓይነታቸው የተመሳሰሉ መሆናቸውን በትክክል የተረዳ ሰው፣ በእውነቱ ዕውቀት ያለው ሰው ነው፡፡ ይህንንስ ዕውቀት ይዞ ምን ዓይነት ጭንቀት ወይም ሐሰታዊ ራእይ ላይ ሊወድቅ ይችላል?
ማንትራ ስምንት: እንዲህም ዓይነቱ ሰው፣ ከሁሉም በላይ የላቀውን ዓብዩ ጌታን በትክክል ለመረዳት ብቁ ነው ማለት ነው፡፡ ዓብዩ ጌታ በሥጋዊ ገላ የማይወርድ፣ ሁሉንም ነገር ለማወቅ የማይሳነው፣ ሊደረስበት የማይችል፣ ያለ ደም ሥር ድጋፍ የሚኖር፣ ንጹሕ እና ሊበከል የማይችል፣ በራሱ ፍጹም የሆነ ፍልስፍና የሚጸና እና የሁሉንም ምኞት ለዘመናት ሲያሟላ የሚገኝ ነው፡፡
ማንትራ ዘጠኝ: ድንቁርና በተሞላበት ዓለማዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚሰማሩ ሁሉ፣ ጉዞዋቸው ጭለማ ወደተሞላበት የድንቁርና ኑሮ፣ ወይም ክልል የሚያመራ ነው፡፡ ከእነርሱም በላይ በሚገኝ የድንቁርና ሥራ ላይ የተሰማሩት ሰዎች ደግሞ፣ ሳያውቁ እናውቃለን በሚል መንፈስ በድንቁርና ውስጥ በገፋ መንገድ የሰመጡ ሰዎች ናቸው፡፡
ማንትራ አስር: ጠቢብ የሆኑት ምሁራን እንደገለጹትም፣ ዕውቀት ከተሞላበት ባህል የላቀ ውጤት ሲገኝ፣ ድንቁርና ከተሞላበት ባህል ደግሞ የተለየ ኅብረተስቡን የሚያቆለቁል ውጤት ይገኛል፡፡
ማንትራ አሥራ አንድ
: ድንቁርና የተሞላበትን የዓለማዊ ሕይወትን እና የመንፈሳዊ ዕውቀትን ጎን ለጎን አመዛዝኖ በትክክል እና ለይቶ ለማወቅ የቻለ ሰው ብቻ፣ ከዚህ ከተደጋጋሚው የሞት እና የትውልድ ወጥመድ ለማምለጥ ይችላል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ፣ ሞት ወደማይገኝበት ዘለዓለማዊ መንፈሳዊ ሕይወትን በማግኘት ፍጹም በሆነ ደስታ ለዘለዓለም መታደል ይችላል።
ማንትራ አስራ ሁለት: ከዓብዩ ጌታ በስተቀር መላእክትን ልክ እንደ ዓብዩ ጌታ በመቁጠር የሚያመልኩ ሁሉ ወደ ጨለማው እና ድንቁርና ወደተሞላበት ፈለግ ያመራሉ፡፡ በዓብዩ ጌታ ዓብይ ሰብአዊነት የማያምኑት እና ሰብአዊ ያልሆነውን የዓብዩ አምላክ ኅይልን የሚያመልኩትም ሁሉ፣ ወደእዚሁ ስፍራ ያመራሉ።
ማንትራ አስራ ሦስት: በዚህ ጥቅስ ውስጥ እንደተገለጸው የፍጥረታት ሁሉ መነሻ የሆነውን ዓብዩ ጌታን በማምለክ ከፍተኛ ውጤት የሚገኝበት ሲሆን፣ ዓብይ ጌታ ያልሆነውን መልአክ በማምለክ ደግሞ፣ ሌላ የተለየ ዝቅተኛ ውጤት ይገኛል፡፡ ይህም ሁሉ መንፈሳቸው ሊረበሽ በማይችሉት መንፈሳዊ ባሕታውያን እና ባለሥልጣናት በግልጽ ተተንትኖ ቀርቧል፡፡
ማንትራ አስራ አራት: ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽናን፣ ቅዱስ ስሙን፣ አቋሙን፣ ባሕርዩን እና ታሪኩን እንዲሁም ይህንን የፈጠረውን ጊዜያዊ ቁሳዊ ዓለም፣ መላእክትን፣ ሰዎችን፣ እንስሳትን ሁሉ በትክክል ለይተን መረዳት ይገባናል፡፡ አንድ ሰው እነዚህን ሁሉ በትክክል የሚረዳ ከሆነ፤ ሞትን እና ይህንን ቁሳዊ ጠፈር በቀላሉ ለመሸጋገር ሲችል፤ ወደ ዘለዓለማዊው መንፈሳዊ መንግሥተ-ሰማያትም በመመለስ፣ ዘለዓለማዊ ሕይወትን፣ ደስታን እና ዕውቀትን ለማግኘት ይችላል፡፡
ማንትራ አስራ አምስት: ኦ ጌታዬ ሆይ፤ ሕያው ፍጥረታትን ሁሉ በፍቅር የምትንከባከብ፤ መንፈሳዊ ገላህ የፀሐይ ጮራን የመሰለ መንፈሳዊ ብርሃንን ስለሚያንጸባርቅ፣ ቅዱስ ፊትህን ለማየት አዳጋች ሆኗል። በመሆኑም፣ እባክህን ይህንን የመንፈሳዊ ብርሃን ጮራህን ገለል አድርገህ፣ ቅዱስ ፊትህን ለማየት እንዲችሉ፣ ለትሑት እና ለንጹሕ አገልጋዮችህ መንፈሳዊ ኃይሉን ስጣቸው፡፡
ማንትራ አስራ ስድስት: ኦ ጌታዬ ሆይ፤ አንተ ቀዳማዊው የፍልስፍና ሁሉ ምንጭ ነህ። መላ ጠፈርን የምንትንከባከብ፣ የተፈጥሮ መመሪያዎች ሁሉ የበላይ ተቆጣጣሪ፣ የትሑት አገልጋዮችህ ሁሉ መድረሻ፣ ለሰው ልጆች ዘር ሁሉ በጐ የምትመኝ፣ ደስታ የተሞላበት አቅዋምህን በትክክል እንድመለከተው፣ እባክህ ይህንን መንፈሳዊ ጮራህን ገለል አድርግልኝ። እኔ ትሑት የፀሐይ ጌታ እንደመሆኔ፣ አንተ ደግሞ የዘለዓለማዊው መንፈሳዊው ዓለም እና የመላው ቁሳዊ ዓለም ዓብይ ጌታ ነህ፡፡
ማንትራ አስራ ሰባት: ይህም ጊዜያዊ እና ሥጋዊ ገላ በመቃጠል አመድ ይሁን፡፡ ይህም የሕይወት እስትንፋሴ ወጥቶ ከመላው አየር ጋር ይዋሐድ፡፡ ጌታዬ ሆይ የምጠይቅህ ነገር ቢኖር ግን፣ አንተ የበላዩ ተጠቃሚ እንደመሆንህ፣ ለአንተ ያበረከትኩትን መስዋእት ሁሉ በመቀበል፣ ይህንን በደካማነቴ በፍቅር ያደረግሁልህን ነገር ሁሉ እንድታስታውስልኝ በማክበር እጠይቅሃለሁ፡፡
ማንትራ አስራ ስምንት: ጌታዬ ሆይ ቅዱስ ኅይልህ እንደ እሳት የሆነ፣ ኦ የማይሳንህ እና ሁሉን በትዕግሥት የቻልክ አምላክ ሆይ፣ ወደ እግርህ ሥር፣ መሬት በመውደቅ እሰግድልሃለሁ፡፡ ጌታዬ ሆይ ወደ አንተ በቀጥታ ለመምጣት እንድችል እባክህ መንገዱን አሳየኝ፡፡ ከዚህ በፊት ያደረግሁትን እንደምታውቅ ሁሉ ከኃጢያቴ ሁሉ ነጻ አውጣኝ፡፡ ይህንንም ምህረት ካገኘሁ ወደ አንተ ለመምጣትም ምንም እንቅፋት ሊያጋጥመኝ አይችልም፡፡