ማንትራ አራት
አኔጃድ ኤካም ማናሶ ጃቪዮ
ናይናድ ዴቫ አፕኑቫን ፑርቫም አርሳት
ታድ ድሀቫቶ ንያን አትዬቲ ቲስትሀት
ታስሚን አፖ ማታሪስቫ ዳድሀቲ
አኔጃት — የጸና፣ ኤካም — አንድ፣ ማናሳህ — ከሐሳብ በላይ፣ ጃቪያህ — ፍጥነት ያለው፣ ና — አይደለም፣ ኤናት — ዓብዩ ጌታ፣ ዴቫህ — እንደ “ኢንድራ” የመሳሰሉ መላእክት፣ አፕኑቫን — ሊቀርቡት ይችላሉ፣ ፑርቫም — ከፊት ለፊት፣ አርሳት — በአስቸኳይ መንቀሳቀስ፣ ታት — እርሱ፣ ድሀቫታህ — የሚሮጡት ሁሉ፣ አንያም — ሌሎች፣ አትዬቲ — የሚሸጋገር፣ ቲስትሀት — በአንድ ቦታ መጽናት፣ ታስሚን — በእርሱ፣ አፓህ — ዝናብ፣ ማታሪስቫ — ንፋስን እና ዝናብን የሚቆጣጠሩ መላእክት፣ ዳድሀቲ — ማቅረብ
ዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ፣ ምንም እንኳን በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ በሚገኘው መኖሪያው ሁሌ የሚገኝ ቢሆንም ከሐሳብ የበለጠ ፍጥነት ያለው እና ማናቸውም ዓይነት ቅልጥፍና ሊወዳደሩ የማይችሉት ነው፡፡ ከፍተኛ ኅይል ያላቸው መላእክት ፈጽሞ ሊወዳደሩት አይችሉም። በመንግሥተ-ሰማያት ውስጥ በአንድ ቦታ ላይ ተቀምጦም፤ መላ ተፈጥሮን እንደ አየር እና ዝናብ የመሳሰሉትን ሁሉ ሲቆጣጠር ይገኛል፡፡ በመሆኑም ከማናቸውም ዓይነት ቅልጥፍና፣ የበላይ ሆኖ ይገኛል።
ግምታዊ በሆነ መንገድ በመመራመር፣ ማናቸውም ታላላቅ ሊቃውንት እና ፈላስፎች ፍጹም የሆነውን ዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ ለመረዳት አይችሉም፡፡ ዓብዩ ጌታ በትክክል ሊታወቅ የሚችለው፣ በቸርነቱ ለትሑት አገልጋዮቹ ለመገለጽ ፈቃደኛ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በብራህማ ሰሚታ (ብሰ፡ 5፡34) ውስጥ እንዲህ ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ “ምንም እንኳን አንድ የጌታ አገልጋይ ያልሆነ ፈላስፋ በህዋ ውስጥ እንደ ንፋስ በፈጠነ ጉዞ ለመቶ ሚሊዮን ዓመታት ቢጓዝም እንኳን፣ ዓብዩ ጌታን ሊደርስበት አይችልም፡፡ እንዲያውም ወሰን እንደሌለው እና በጣም ሩቅ ሆኖ እንደሚገኝ ለመረዳት ይበቃል፡፡” የብራህማ ሰሚታ ሥነጽሑፍ በተጨማሪ እንደሚገልጸውም (ብሰ፡ 5፡37) ፍጹም የሆነው ዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ በመንፈሳዊ ዓለም ውስጥ የግሉ የሆነ መንፈሳዊ መኖሪያ አለው፡፡ ይህም መንፈሳዊ መኖሪያ “ጎሎካ” ይባላል፡፡ በዚህም መኖሪያ ውስጥ ታሪካዊ ሕይወትን ከትሑት አገልጋዮቹ ጋር በፍቅር በማሳለፍ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም መኖሪያ ውስጥ ተቀምጦም እያለ ምንም በማይሳነው ኃይሉ በፈጠረው ዓለም ውስጥም ሁሉ ተሰራጭቶ ይገኛል፡፡ በቪሽኑ ፑራና መጻሕፍት ውስጥ ዓብዩ ጌታ ከእሳት እንደሚመነጨው ሙቀት እና ብርሃን ተመስሎ ተገልጿል፡፡ ምንም እንኳን እሳት በአንድ ወገን የሚገኝ ቢሆንም፣ ሙቀቱ እና ብርሃኑ ግን፣ ሰፋ ባለ ቦታ ሁሉ ተሰራጭቶ ይገኛል፡፡ እንደዚህም ሁሉ ዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ ምንም እንኳን በመንፈሳዊ ዓለም መኖሪያው ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም፣ ተጨማሪ ኃይሉን በፈጠራቸው ስፍራዎች ሁሉ አሰራጭቶ ይገኛል፡፡
ምንም እንኳን እነዚህ የተለያዩ ስፍራዎች በቁጥር ሊተመኑ የማይችሉ ቢሆኑም፣ በሦስት ዋና ዋና ከፊሎች ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ እነዚህም የውስጣዊ ኅይል፣ ማዕከላዊ ኅይል እና የውጪ ኅይል ናቸው፡፡ ከእነዚህም ከእያንዳንዱ ክፍፍሎች ሥር በመቶ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንኡስ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ ቁሳዊ ዓለማትን ለማስተዳደር ኅይል የተሰጣቸው እና የሚቆጣጠሩት መላእክት በማዕከላዊው ኅይል ውስጥ የተመደቡ ናቸው፡፡ እነዚህም መላእክት፣ አየርን፣ ብርሃንን፣ ዝናብን ወዘተ የሚቆጣጠሩ ናቸው፡፡ የዓብዩ ጌታ የማዕከላዊ ኃይላት የሰው ልጆችን እና ሕያው ፍጥረታትን ሁሉ ይጨምራል፡፡ ነገር ግን ግዑዝ የሆኑት የቁሳዊው ፍጥረታት በሙሉ፣ የዓብዩ ጌታ የውጪ ወይም ዝቅተኛ ተብለው የሚታወቁት ኃይላት ናቸው፡፡ ዓብዩ ጌታ የሚኖርበት በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ የሚገኘው መኖሪያው ደግሞ፣ ከዓብዩ ጌታ የውስጣዊ ወይም ከፍተኛ ተብሎ ከሚታወቀው ኃይሉ የመነጨ ነው፡፡
በዚህ ዓይነት መንገድም የዓብዩ ጌታ ኃይላት በየቦታው ተሰራጭተው ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳን ዓብዩ ጌታ እና ሀያላቱ ተለያይተው የማይታዩ ቢሆኑም አንዳንድ ሰዎች እነዚህ ተሰራጭተው የሚገኙት ኃይላት ዓብዩ ጌታ ራሱ ነው የሚል ስሕተት ውስጥ እንዳይገቡ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ወይም ደግሞ ዓብዩ ጌታ ሰብአዊነት ሳይኖረው እንደ ኅይል ተበታትኖ የሚኖር እና ሰብአዊነቱን ያጣ ነው የሚል ስሕተት ውስጥም ከመግባት መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ዓብዩ ጌታ ምን እንደሆነ በራሳቸው ግምገማ እና በተወሰነ የመረዳት ችሎታቸው በማሰላሰል፣ ስለ ዓብዩ ጌታ ማንነት ለመወሰን ይበቃሉ፡፡ ቢሆንም ግን፣ ዓብዩ ጌታን በዚህ በተወሰነው የአስተሳሰብ ችሎታችን ለመረዳት የምንችለው ጌታ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ሽሪ ኡፓኒሻድ ዓብዩ ጌታን በራሳችን ጥረት እና በተወሰነው አቅማችን ፈጽሞ ልንረዳው እንደማንችል ገልጾልናል፡፡
በብሀገቨድ ጊታ (ብጊ፡ 10፡2) ውስጥ በዓብዩ ጌታ እንደተገለጸው፣ ታላላቅ “ርሺስ” (ባሕታውያን) እና “ሱራዎች” (መላእክት) ቢሆኑ እንኳን፣ በትክክል ሊረዱት አይችሉም፡፡ እነርሱ ይቅሩና “አሱራዎች” ወይም መለኮታዊ ባሕሪ የሌላቸው እንዴት አድርገው ሊረዱት ይችላሉ? ይህም አራተኛው የኢሾፓኒሻድ ጥቅስ እንደሚገልጽልን፣ ፍጹም እውነት የሆነው ጌታ ዓብዩ የመንግሥተ-ሰማያት ጌታ ነው፡፡ እርሱም በመሆኑ፣ እንዲህ ዓይነቱ የዓብዩ ጌታ መለኮታዊ የግለሰብነት ባሕሪው ገለጻ ተደጋግሞ በኢሾፓኒሻድ መጽሐፍ ቀርቦልናል።
ምንም እንኳን የዓብዩ ጌታ ማዕከላዊ ኃይላት የዓብዩ ጌታ ዓይነት ባሕሪ ቢኖራቸውም፣ የሚሠሩበት ስፍራ እና አቅም የተወሰነ በመሆኑ፣ ዓብዩ ጌታን ለመረዳት የተወሰነ ኅይል ብቻ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህም ማዕከላዊ ኃይላት (ነፍስ) የዓብዩ ጌታ የከፊል እና ቁራሽ ወገን ስለሆኑ፣ ሁለንተናው ከተሟላው ዓብይ ጌታ ጋር ፈጽሞ ሊወዳደሩ ወይም እኩል ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ውስን በመሆናቸውም እንደ ዓብዩ ጌታ ፍጹም የተሟላ ዕውቀት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ በቁሳዊው ዓለም ኅይል እና ተጽዕኖ ምክንያት፣ በሞኝነት እና በድንቁርና የተጠቁ ሕያው ፍጥረታት ሁሉ ስለ ዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ማዕረግ በመጠራጠር እና በመመራመር ላይ ይገኛሉ። ሽሪ ኡፓኒሻድ እንደሚያስጠነቅቀንም፣ ዓብዩ ጌታን በምርምር እና በግምታዊ መንገድ ለመረዳት ፈጽሞ የማይቻል እና ጊዜን የሚያባክን ጥረት ነው፡፡ ስለ ዓብዩ ጌታም መንፈሳዊነት መረዳት የሚገባን፣ ከዓብዩ ጌታ ከራሱ ነው፡፡ እርሱም የቬዳዎች ሁሉ ዕውቀት መነሻ ነው፡፡ ስለ ራሱ መንፈሳዊነት የሚያውቅ እና ፍጹም የሆነ ዕውቀትን አሟልቶ የያዘው ዓብዩ ጌታ ብቻ ነው፡፡
ሙሉ ከሆነው የዓብዩ ጌታ ኅይል ተነጥላ በከፊል የምትገኘው የዓብዩ ጌታ ኅይል (ነፍስ)፤ በጌታ ትእዛዝ ሥር በመተዳደር ልታደርገው የምትችለው ኅይል አላት፡፡ የጌታ ከፊል እና ወገን የሆነችው ነፍስ፣ በዓብዩ ጌታ ሥር በመተዳደር ማድረግ የሚገባትን ነገር ሁሉ የዘነጋች ከሆነች፣ በማያ ወይም በሐሰታዊ ራእይ ውስጥ ተጠመደች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሽሪ ኡፓኒሻድ እንዳስጠነቀቀን፣ በዓብዩ ጌታ ቁጥጥር ሥር በመሆን፣ የሚጠበቅብንን ወይም የተወሰነልንን ነገር ብቻ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ይህም ማለት ሕያው ፍጥረታት የራሳቸው የሆነ መብት ወይም ሐሳብ የማመንጨት ችሎታ የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ሕያው ፍጥረታት የዓብዩ ጌታ ከፊል እና ወገን እንደመሆናቸው፣ ከዓብዩ ጌታ የመነጨውን ሐሳብ መከተል ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንድ ሰው ሐሳብ የማመንጨት ችሎታውን አእምሮውን በመጠቀም እና፣ ዓብዩ ጌታ የሁሉም ነገር ባለቤት መሆኑን በመረዳት በተፈጥሮ ያለውን ንጹሕ መንፈሳዊ ንቃት ሊያነቃቃ ይችላል። ይህም ንጹሕ የመንፈሳዊ ንቃት “በማያ” (የዓብዩ ጌታ የውጪ ኅይል) ተሸፍኖ ስለነበረ ወይም በሐሰታዊ ራእይ ውስጥ ሰርጎ ስለነበረ፣ ጠፍቶበት የነበረው ንቃት ነው፡፡
ሁሉም ዓይነት ኅይል፣ ሊገኝ የሚችለው ከዓብዩ ጌታ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ያገኘነውን እያንዳንዱን ኅይል፣ ዓብዩ ጌታን ለማስደሰት ብቻ መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ዓብዩ ጌታ ለመገለፅ የሚችለው የትሑት አገልግሎት ስብዕና ላለው ሰው ብቻ ነው፡፡ ፍጹም የሆነ ዕውቀት ማለት የዓብዩ ጌታን ባሕርይ ማወቅ፣ ኃይላቱን ለይቶ ማወቅ፣ እነዚህ ኃይላትም በፈቃዱ እንዴት እንደሚሠሩ ማወቅ ነው፡፡ ይህንንም የመሳሰሉ ትምህርቶች በዓብዩ ጌታ በራሱ በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ ተገልጾልናል፡፡ ይህ ብሀገቨድ ጊታ ከኡፓኒሻድ መጻሕፍት ጋር ሲወዳደር፣ የነጠረ መንፈሳዊ ዕውቀትን የያዘ ነው፡፡