ማንትራ አስራ ስምንት
አግኔ ናያ ሱፓትሀ ራዬ አስማን
ቪሽቫኒ ዴቫ ቫዩናኒ ቪድቫን
ዩዮ ድሂ አስማጅ ጁሁራናም ኢኖ
ብሁዪስትሀም ቴ ናማ ኡክቲም ቪድሄማ
አግኔ — ልክ እንደ እሳት ኅያል የሆንከው ጌታዬ ሆይ፣ ናያ — በቸርነትህ ምራ፣ ሱፓትሀ — ወደ ትክክለኛው መንገድ፣ ራዬ — ወደ አንተ ለመድረስ፣ አስማን — እኛ፣ ቪሽቫኒ — ሁላንችም፣ ዴቫ — ጌታዬ ሆይ፣ ቫዩናኒ — የምናደርጋቸው፣ ቪድቫን — ዐዋቂው፣ ዩዩድሆኒ — እባክህ አስወግደው፣ አስማት — ከእኛ፣ ጁሁራናም — በመንገድ ላይ የሚገኙትን እንቅፋቶች ሁሉ፣ ኤናህ — ክፋቶችን ሁሉ፣ ብሁዪስትሀም — በቁጥር ሊተመኑ የማይችሉ፣ ቴ — ወደ አንተ፣ ናማሀ ኡክቲም — እጅ በመንሳት ምስጋና ማቅረብ፣ ቪድሄማ — አደርጋለሁ
ጌታዬ ሆይ ቅዱስ ኅይልህ እንደ እሳት የሆነ፣ ኦ የማይሳንህ እና ሁሉን በትዕግሥት የቻልክ አምላክ ሆይ፣ ወደ እግርህ ሥር፣ መሬት በመውደቅ እሰግድልሃለሁ፡፡ ጌታዬ ሆይ ወደ አንተ በቀጥታ ለመምጣት እንድችል እባክህ መንገዱን አሳየኝ፡፡ ከዚህ በፊት ያደረግሁትን እንደምታውቅ ሁሉ ከኃጢያቴ ሁሉ ነጻ አውጣኝ፡፡ ይህንንም ምህረት ካገኘሁ ወደ አንተ ለመምጣትም ምንም እንቅፋት ሊያጋጥመኝ አይችልም፡፡
ሙሉ ልቦናውን ለዓብዩ ጌታ በመስጠት እና ምህረቱን ለማግኘት ጸሎት በማድረግ አንድ ትሑት አገልጋይ ራስን በማወቅ ጥናቱ ስኬታማ ሊሆን ይችላል። ዓብዩ ጌታ አንዳንድ ጊዜ እንደ እሳት ይቆጠራል። ምክንያቱም ሙሉ ልቦና ለሰጡት ትሑት አገልጋዮቹ ሁሉ ኃጢያታቸውን አመድ አድርጎ ሊደመስስላቸው ስለሚችል ነው። ቀደም ብለው በተጠቀሱት ማንትራዎች እንደተገለጸውም ከሁሉም በላይ የሆነው የዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ ገጽታ፣ በመንግሥተ-ሰማያት ውስጥ የሚገኘው ዓብዩ ሰብአዊ ገጽታው ነው። ከዚህ መንፈሳዊ ገጽታው የሚመነጨው ሰብአዊ ያልሆነው እና “ብራህማ ጅዮቲ” ተብሎ የሚታወቀው የብርሃን ነጸብራቁ ግን፣ እንደ አስደናቂነቱ፣ ይህን የአብ ሰብአዊ ገጽታውን ለመገንዘብ እና ለማወቅ አዳጋች ያደርገዋል። ስሜቶቻችንን ለማስደሰት የምናደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ፣ “ካርማ ካንዳ” ተብሎ የሚታወቀው፣ ዝቅተኛው የዓለማዊ እንቅስቃሴ ነው። እነዚህ እንቅስቃሴዎች ከቬዳዎች መመሪያ መስመር ለቀው ሲሄዱ፣ “ቪካርማ” ተብሎ ወደሚታወቀው ደረጃ ይደረሳሉ። ይህ ደረጃ ስሜቶቹን ለማርካት ለሚጥረው ሰው ወደ ጭለማ የሚያመራ እና የሚበጅ አይደለም። ይህ “ቪካርማ” ተብሎ የሚታወቀው ስሜትን ለማስደሰት የሚደረገው እንቅስቃሴ፣ የተሳሳተ ዓለማዊ እና ፀረ መንፈሳዊ ሕሊና በያዙ ሰዎች የሚከናወን ነው። በዚህም ምክንያት እንደዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ፣ ራስን የማወቅ መንፈሳዊ ጥናትን ለማድረግ እንቅፋት ይሆንብናል።
ራስን የማወቅ መንፈሳዊ ጥናት ለማድረግ የሚቻለው፣ በሰው ልጅ ትውልድ ውስጥ ብቻ ነው። ሌሎች ሕያው ፍጥረታት፣ ራስን ለማወቅ በሚደረገው ጥናት ላይ ሊሳተፉ አይችሉም። በቁሳዊ ዓለም ውስጥ 8,400,000 የሚሆኑ የተለያዩ ሕያው ፍጥረታት ይገኛሉ።ከእነዚህ ሁሉ የተለያዩ ሕያው ፍጥረታት፣ የሰው ልጅ “የብራህመናዊ” ወይም የቀሳውስት መንፈሳዊ ባህል ላይ ለመሳተፍ ብቁ ዕድል ተሰጥቶታል። “የብራህመናዊ” ወይም የቀሳውስት ባህል የምንላቸው የሚከተለውን ሁሉ ያጠቃልላሉ። እውነተኝነት፣ ስሜቶችን መቆጣጠር፣ መታገስ፣ ቀለል ያለ ኑሮ መኖር፣ መንፈሳዊ ዕውቀትን መያዝ እና በዓብዩ ጌታ ሙሉ እምነትን መያዝን ያካትታል። አንድ ሰው ከፍ ባለ ቤተሰብ ተወላጅነት ብቻ፣ ኩራት እንዲሰማው አያስፈልግም። ቢሆንም ግን፣ ከፍ ካለ ቤተሰብ ውስጥ በመወለድ፣ አንድ ሰው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለመድረስ ዕድል ይኖረዋል። በተመሳሳይም አንድ ሰው፣ ከብራህማና ወይም ከመንፈሳዊ ቀሳውስት ቤት ውስጥ ከተወለደ፣ ጥሩ መንፈሳዊ ብራህመና ለመሆን ዕድል ያገኛል። ቢሆንም ግን፣ ይህ ተወላጅነት ብቻ በቂ አይደለም። አንድ ሰው ወደዚህ የብራህመና ደረጃ ላይ ለመድረስ፣ በግሉ ብዙ ጥረት ማድረግ ይገባዋል። በተወለደበት ቤተሰብ የሚኮራ ሰው ሆኖ፣ እያለና የብራህማና ልምምድ ኃላፊነቱን የማይወጣ ከሆነ፣ በኅብረተሰቡ የተናቀ ሰው ሊሆን ይችላል። ራስን የማወቅ ትምህርቱንም ከመከታተል ሊባክን ይችላል። በዚህም ምክንያት የሰው ልጅ ሆኖ፣ የተወለደበት ዓላማው እና ተልእኮው ሊደናቀፍ፣ በቀጣዩም ስኬታማ ላይሆን ይችላል።
በብሀገቨድ ጊታ ውስጥ እንደተጠቀሰው (ብጊ 6፡41-42) ዓብዩ ጌታ እንዲህ በማለት አስተምሮናል። “ዮጋ ብህራስታስ” ወይም ራስን የማወቅ መንፈሳዊ ጥናትን ከመቀጠል፣ የወደቁ ሰዎች ሁሉ መንፈሳዊ መንገዳቸውን ለማቃናት ዕድል እንዲኖራቸው በሚቀጥለው ትውልዳቸው፣ በብራህማና ቤተሰብ ወይም በሀብታም ቤተሰብ ውስጥ እንደገና ይወለዳሉ። ይህም አዲስ ትውልድ በመንፈሳዊ መንገድ ራስን የማወቅ ጥናታቸውን እንደገና ለመቀጠል ጥሩ ዕድል ይሰጣቸዋል። ይሁን እንጂ ይህንን በመሰለው ዕድል በአግባቡ የማይጠቀም ሰው፣ ዓብዩ ጌታ የሰጠውን ጥሩ የሰው ልጅ ትውልድ ዕድል አባከነው ማለት ነው።
የቬዲክ መመሪያዎችን እና የተደነገጉትን ደንቦችን የሚከተል ሰው ሁሉ፣ ስሜትን ለማርካት ከሚደረገው የረከሰ እንቅስቃሴ በመቆጠብ፣ ወደ መንፈሳዊ ዕውቀት እና ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል። ይህንን መንፈሳዊ ዕውቀት ለብዙ ትውልድ ካዳበረ በኋላ፣ አንድ ሰው በመጨረሻ ሙሉ ልቦናውን ለዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት፣ ሕይወቱን ስኬታማ ማድረግ ይችላል። ይህ በተደጋጋሚ እና በአጠቃላይ የሚታየው አካሄድ ነው። ቢሆንም ግን በዚህ ማንትራ ጥቅስ ውስጥ እንደተገለጸው፣ አንድ ሰው ከመጀመሪያውኑ ሙሉ ልቦናውን ለዓብዩ ጌታ ለመስጠት ከቻለ፣ የትሑት አገልግሎት ብልጽግና ደረጃዎችን ሁሉ፣ በቀላሉ በማለፍ፣ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ስኬታማ ሊሆን ይችላል። በብሀገቨድ ጊታ (ብጊ 18:66) ውስጥ እንደተገለጸው ሙሉ ልቦናቸውን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ለሰጡ ሁሉ፣ ዓብዩ ጌታ ሙሉ ኃላፊነቱን በመውሰድ ከኃጢያት ሁሉ ነጻ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። “በካርማ ካንዳ” ወይም ስሜትን ለማስደሰት በምናደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ፣ የተለያዩ የኃጢያት ዓይነቶችን ስንፈጽም እንገኛለን። “በግያና ካንዳ” ወይም መንፈሳዊ አገልግሎት በሌለበት የፍልስፍና ዕውቀት ግንባታ ብቻ በሚደረገው እንቅስቃሴ፣ የሚከናወነው ኃጢያት ያነሰ ሆኖ ይገኛል። ቢሆንም ግን በመንፈሳዊ ትሑት አገልግሎት ወይም “በብሀክቲ” ሥርዓት ላይ ሙሉ በሙሉ የተሰማሩ ሁሉ፣ በምንም ዓይነት የኃጢያት ወጥመድ ሊያዙ አይችሉም። ምክንያቱም የዓብዩ ጌታ ትሑት አገልጋይ የሆኑ ሁሉ፣ እንደ ዓብዩ ጌታ መልካሙን ባሕርይ የያዙ በመሆናቸው ነው። የብራህማና ወይም የቀሳውስት ዓይነት ሕይወት ለያዙ ደግሞ፣ ከዚያም በላይ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ስኬታማ የሆኑ ናቸው። የዓብዩ ጌታ ትሑት አገልጋይ የብራህመናነት ባሕርይ እና ብቃትን በቅጽበት ለማግኘት የሚችል ነው። መንፈሳዊ ሥርዓቶችንም ለማከናወን ብቁ የሆነ አገልጋይ ነው። ይህ ችሎታ ሊገኝ የሚችለው፣ ምንም እንኳን አንድ ሰው ከብራህማና ቤተሰብ ውስጥ ያልተወለደ ቢሆንም ነው። የዓብዩ ጌታ መንፈሳዊ አገልግሎት፣ በረከት የመስጠት ኃይሉም ይህንን የመሰለ ነው። በብራህማና ቤተሰብ የተወለደው ሰው፣ ዕድሉን በትክክል የሚጠቀምበት ካልሆነ፣ ሕይወቱ ከእንስሳ ያልተሻለ ሕይወት ሊሆን ይችላል። ከእንስሳ ያልተሻለ ወይም ውሻን ከሚመገብ ዝቅተኛ ቤተሰብ የተወለደው ሰው ደግሞ፣ በትሑት መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ በጥሞና የተሰማራ ከሆነ፣ ያለበት ደረጃው ከፍ ብሎ ብቁ ብራህማና ለመሆን የሚበቃበትን ዕድል ያገኛል።
በሙሉ ኅይል ድሎት የተዋበው ዓብዩ ጌታ፣ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ይገኛል። በዚህም ምክንያት ለእያንዳንዱ ትሑት አገልጋዮች ትክክለኛውን መንፈሳዊ መስመር እንዲይዙ አቅጣጫውን እያሳየ ሲመራቸው ይገኛል። እንዲህ ዓይነቶቹ መንፈሳዊ መመሪያዎች ሁልጊዜ ለትሑት አገልጋዮቹ የሚሰጡ ናቸው። ይህም ምንም እንኳን አልፎ አልፎ ትሑት አገልጋዮቹ የግል ስሜትን ለማስደሰት በሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ላይ ቢያዘነብሉም ነው። በመንፈሳዊ ትሑት አገልግሎት ላይ ላልተሰማሩት ሰዎች ግን ስሜታቸውን ለማስደሰት ለሚያደርጓቸው ጥረት ሁሉ ዓብዩ ጌታ መንገዱን ይከፍትላቸዋል። ይህም ግን በራሳቸው ኃላፊነት የሚያደርጉት እንቃሳቃሴ ሲሆን፣ ወደፊት ለችግር የሚያጋልጣቸውም ሆኖ ይገኛል። ትሑት አገልጋዩን ግን፣ ስሕተት ወደሞላበት እንቅስቃሴ እንዳያመራ ወይም ወደ ኃጢያት ውስጥ እንዳይገባ፣ ዓብዩ ጌታ አቅጣጫውን ያሳየዋል። ይህም በሽሪማድ ብሀገቨታም ውስጥ እንዲህ ተብሎ ተገልጾልናል። (ሽብ 11.5.42)
ስቫ ፓዳ ሙላም ብሀጃታህ ፕሪያስያ
ትያክታንያ ብሀቫስያ ሀሪህ ፓሬሳህ
ቪካርማ ያክ ቾትፓቲታም ካትሀንቺድ
ድሁኖቲ ሳርቫም ህርዲ ሳኒቪስታህ
“ሙሉ ልቦናቸውን ለሰጡ ለትሑት አገልጋዮቹ፣ ዓብዩ ጌታ በጣም ሩኅሩኅ ነው። ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ትሑት አገልጋዩ ስሜቶቹን ለማስደስት ወደ “ቪካርማ” እንቅስቃሴዎች እና ከቪዴክ መመሪዎች ውጪ ሕሊናውን ቢያሰማራም እንኳን፣ ዓብዩ ጌታ በልቡ ውስጥ ሆኖ ከእነዚህ ዓይነት ድርጊቶች እንዲርቅ ይመራዋል። ምክንያቱም እነዚህ ትሑት አገልጋዮች በዓብዩ ጌታ በጣም የሚወደዱ በመሆናቸው ነው።”
በዚህ በኢሾፓኒሻድ ማንትራ ወይም ጥቅስ ውስጥ እንደተገለጸው፣ ትሑት አገልጋዩ ለጥፋቱ ምሕረት እንዲደረግለት ለዓብዩ ግታ ጸሎቱን ሲያቀርብ ይታያል። በዓለም ላይ እንደሚታየው፣ አንዱ የሰው ልጅ ድክመት፣ ስሕተትን መሥራት ነው። በዚህ ዓለም ላይ የተወለዱ ሕያው ፍጥረታት ሁሉ፣ በስሕተት የሚጠቁ ናቸው። ከእነዚህም ዓይነቶች በድንገት ሳናስባቸው ከሚከሰቱት ስሕተቶች መራቅ የምንችለው፣ ለዓብዩ ጌታ በምንሰጠው ትሑት አገልግሎት ብቻ ነው። ምክንያቱም ይህንን ሥርዓት በመከተል ብቻ፣ ዓብዩ ጌታ ከእነዚህ ስሕተቶች እና ኃጢያት ሊሰውረን እና ሊያርቀን ስለሚችል ነው። ዓብዩ ጌታ ሙሉ ልቦናቸውን ለትሑት አገልግሎት ለሰጡ ሁሉ ሙሉ ኃላፊነቱን ይወስዳል። በዚህም ረገድ ልቦናችንን በመስጠት እና የእርሱን አቅጣጫ በመከተል ብቻ ሁሉም ዓይነት ችግሮች ሊፈቱልን ይችላሉ። እነዚህም አቅጣጫዎች ወደ ትሑት አገልጋዮቹ ዘንድ፣ በሁለት ዓይነት መንገድ ይቀርባሉ። አንደኛው መንገድ በመንፈሳዊ ሰዎች አማካኝነት፣ በቅዱስ መጻህፍት እና በመንፈሳዊ አባት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በራሱ በልባችን ውስጥ በሚገኘው በዓብዩ ጌታ አማካኝነት ነው። በአጠቃላይ ግን፣ ትሑት አገልጋዩ በቬዲክ ዕውቀት በጥልቅ የተማረ በመሆኑ ከብዙ ያልታሰቡ ስሕተቶች ለመቆጠብ ይችላል።
የቬዲክ ዕውቀት መንፈሳዊ እንደመሆኑ፣ በተለመደው የትምህርት ቤት ሥርዓት ልንቀስመው አንችልም። የቬዲክ ዕውቀት ማንትራዎችን መረዳት የምንችለው፣ የዓብዩ ጌታ እና የመንፈሳዊ አባታችን በረከት ሲኖር ብቻ ነው። “ያስያ ዴቬ ፓራ ብሃክቲር ያትሀ ዴቬ ታትሀ ጉሮ” አንድ አገልጋይ እውቅና ያለውን መንፈሳዊ አባቱን ጠለላ የያዘ ከሆነ፣ በቅጽበት የዓብዩ ጌታን በረከት ማግኘት ይችላል። በዚህን ጊዜ ዓብዩ ጌታ ለአገልጋዮቹ እንደ መንፈሳዊ አባት ሆኖ ይከሰታል። በዚህም መንገድ መንፈሳዊው አባት፣ የቬዲክ መመሪያዎች እና በልባችን ውስጥ የሚገኘው ዓብዩ ጌታ፣ ትሑት አገልጋዩን በሙሉ ኅይል ይመሩታል። ይህንን በመሰለ መንገድ ትሑት አገልጋዩ ተመልሶ ወደ ቁሳዊው ዓለማዊ ኑሮ እንደገና ሊወድቅ አይችልም። በሁሉም አቅጣጫ ትሑት አገልጋዩ ጠለላ ስለሚያገኝ ከጊዜ በኋላ ወደ ታላቁ የመንፈሳዊ ዓለም ለመመለስ ብቁ ይሆናል። እነዚህም ሥርዓቶች በዚህ ማንትራ እና በሽሪማድ ብሀገቨታም (ሽብ 1.2. 17-20) ውስጥ ተተንትነው ተገልጸዋል።
የዓብዩ ጌታን ምስጋና ማዳመጥ፣ መዘመር እና ማስተማር፣ ለመንፈሳዊ ሕይወት ብልጽግናችን የሚቀና ተግባር ነው። ዓብዩ ጌታ ሁሉም አገልጋዮቹ እንዲያዳምጡ እና እንዲያስተምሩ ይፈልጋል። ምክንያቱም ለሁሉም ሰዎች መንፈሳዊ ንቃት የሚያስብ በመሆኑ ነው። ስለ ዓብዩ ጌታ ምስጋና በማዳመጥ፣ በመዘመር እና በማስተማር ከሠራናቸው ብዙ ኃጢያቶች ሁሉ ነጻ ለመሆን እንችላለን። ለዓብዩ ጌታ የምናደረገው የትሑት እና የፍቅር አገልግሎታችንም የጸና ይሆናል። እዚህ ደረጃ ላይ የሚደርስ ትሑት አገልጋይ፣ ብራህማና የመሆን ብቁ ደረጃ ላይ ይደርሳል። በተፈጥሯችን የሚገኙት ዝቅተኛ፣ የድንቁርና እና ዓለማዊ የጋለ ፍላጎታችን ሁሉ ከኅሊናችን ውስጥ ፈጽሞ ይጠፋሉ። በሚሳተፍበትም የትሑት አገልግሎት፣ አገልጋዩ በመንፈሳዊ አንደበት የነቃ ይሆናል።
ወደ ዓብዩ ጌታም እንዴት እንደሚመለስ አቅጣጫው ሁሉ ግልጽ ይሆንለታል። የነበሩት ጥርጣሬዎች ሁሉ ይጠፋሉ። በመጨረሻም ንጹሕ መንፈሳዊ ልቦና ያለው ትሑት አገልጋይ ይሆናል።
ይህ የሽሪ ኡፓኒሻድ መጽሐፍ ይህንን በመሰለ መንገድ፣ አንድ ሰው እንዴት ወደ ዓብዩ ጌታ ሽሪ ክርሽና ለመቅረብ እንደሚችል የሚያስተምረን መጽሐፍ ነው።
በዚህም የብሀክቲቬዳንታ ፍሬ ነገር ገለጻዎች ይደመደማሉ።